>

ታላቋ ድምጻዊት "አድዋን" እንዴትና ለምን ዘፈነችው?  (የኑስ ሙሐመድ)

ታላቋ ድምጻዊት “አድዋን” እንዴትና ለምን ዘፈነችው? 
የኑስ ሙሐመድ
አድዋ ኢትዮጵያኖች ናቸዉ፡፡ ለእኔ፣ ለወገኖቻቸዉ የሞቱት የታረዱት … ብዙ ነገር የሆነዉ። እና ከዚያ ምክንያት ተነስቼ ነዉ። የሰዉ ሃገር ሄደን አልነካንም መጡብን እንጂ እና ይሄ የጀግንነት ታሪክ አይደለም የሰዉ ልጅ ታሪክ እንጂ ! ” አዎ አድዋ የሰው ልጅ ሁሉ ታሪክ ነው፡፡ ጂጂ ከሁላችን ቀድማ ነበረ!!!
—-
ከእለታት አንድ ቀን…ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ አድዋ ለተሰኘው ፊልማቸው ማጀቢያ ሙዚቃ ይሆን ዘንድ ማነው ለዚህ የተከበረ የጥቁር ሕዝብ የነጻነት ተጋድሎ ፊልም ሙዚቃና ግጥም የሚጽፍልኝ ሲሉ በመላ አሜሪካን ማስታወቂያ አስነገሩ፡፡ ሐበሻ የተባለ ወይዛዝርቱና ኮበሌው ሁሉ ይህን ውድድር አሸንፎ ለአድዋ ጥሩ ማጀቢያ ሙዚቃ ለመስራት ይሯሯጥ ጀመር፡፡
በመጨረሻም አይደርስ የለምና የውድድሩ ቀን ደረሰ፡፡ ፕሮፌሰሩ ሊወዳደሩ የመጡ ከያንያንን ደርድረው ተራ በተራ ስቱዲዮ ውስጥ እያስገቡ መፈተን ጀመሩ፡፡ ሁሉም እየገባ ከመስታውቱ ባሻገር ላሉት ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ የጻፈውን ግጥምና ዜማ እያንጎራጎረ ወጣ፡፡ በርካታ የሙዚቃ ሰዎች ስራቸውን እያቀረቡ ቢወጡም ፕሮፌሰሩ ግን አንዱም ሥራ ስላልማረካቸው ካቀረቀሩበት እንኳን ቀና ብለው ተወዳዳሪዎችን አልተመለከቱም ነበር፡፡ ….ሁሉም ሥራቸውን አቅርበው ከጨረሱ በኋላ በስተመጨረሻ አንዲት ጉደኛ ወጣት ቀረች፡፡
ፕሮፌሰሩ እስካሁን ያሰቡትን ዐይነት ጎበዝ ባለቅኔ ድምጻዊ አላገኙምና ትቸው ልሂድ ወይስ የቀረችዋን ልጅ አድምጨ ልጨርስ እያሉ ማመንታት በጀመሩበት ስዓት…አንዲት ባገር ፍቅር ወኔ የተወሰወሰች ድምጸ መረዋ ወጣት ከተፍ አለች…ማር ወለላዋ፣ አፈ እርጎዋ፣ ዐይነ ሽልምልሟ፣ አዕምሮ ብሩኋ…ጂጂ
ምልሰት….
አሜሪካ ካሊፎርኒያ፤ ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት ድምጻዊት እጅጋየሁ ሽባባው ገና ልጅ እግር ነበረች፡፡ “ጽሐይ” የተሰኘውን የመጀመሪያ አልበሟን ለቅቃ ወደ ሙዚቃው ዓለም ብትቀላቀልም ገና ብዙም አልታወቀችበትም፡፡ የፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማን “የፊልም ስኮሪንግ” ማስታወቂያ እንደሰማች ቤቷ ውስጥ ቁጭ ብላ ማሰብና መብሰልሰል ጀመረች…
በበጎ አድራጎት ሥራዋ በድፍን ኢትዮጵያ እየተወደደች የመጣችው ታላቅ እህቷ ፍሬዓለም ሽባባው ሁለተኛ ልጇን ልትወልድ ወደ አሜሪካ በማቅናት ከእህቷ ከእጅጋየሁ ቤት አረፍ ብላ ነበር፡፡ “ፍርዬ” አለች ጂጂ በድንገት ወደ እህቷ ፈገግ ብላ እያየች፡፡ “ለዓድዋ ፊልም ማጀቢያ ሙዚቃ የሚሆን ዘፈን ስሩና ያሸነፈው ፊልሙን ያጅባል ተብሏል ይሄን እድልማ መሞከር አለብኝ” አለችና ወደ ታላቅ እህቷ ቀና አለች፡፡
ፍሬም የታናሽ ታናሿ የጂጂ ንቃተ ህሊናና ተሰጥኦ ከልጅነቷ ጀምሮ ሁሌም ይደንቃት ስለነበር “ወይ አጅሪት በያ እስኪ ጻፊውና ታሰሚናለሻ…” አለቻት፡፡ ጂጂም ወረቀትና ብዕሯን አፈፍ አደረገች…ወረቀቱ ላይ ቶሎ ቶሎ አትጽፍም በአዕምሮዋ ግን ቃላትን ታነበንባለች ትሰካካለች፡፡ ከተፈጥሮዋ ሁሉ እሚገርመው እንዲህ ከሰው መሀል ሆና እየተጨዋወተች በአጭር ጊዜ ውስጥ ግጥምና ዜማዎቿን መፍጠሯና ማንጎራጎሯ መሆኑን የሚያውቋት ሁሉ ይመሰክሩላታል፡፡ ጅምር እንዳደረገች አፍታም ሳትቆይ ጨረስኩ አለችና ወደ እህቷ ፊቷን አዞረች፡፡
ትንፋሿን ሰብሰብ አድርጋ…
“የሰው ልጅ ክብር ሰው መሆን ክቡር…” እንደማቋረጥ አለችና ወደ እህቷ ቀና ብላ “ደስ ይላል ፍርዬ…? ቆይ ቆይ አንዴ ስሚኝ ልጨርሰው…” ጂጂ ማዜሟን ቀጠለች…”ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን ሰውን ሲያከብር…” በየመሀሉ ጂጂ ትስቃለች ትቀልዳለችም፡፡ ስትቅበጠበጥ፣ ስትስቅ፣ ስታስብ አንዳንዴ ገና ለአካለመጠን ያልደረሰች ኮረዳ ስትመስል አንዳንዴ ደግሞ ያለጊዜዋ ሀሳቧ የገዘፈ ቁምነገረኛ ወጣት ትሆናለች፡፡
ስሜቶቿ ፊቷ ላይ በጉልህ እየተነበቡ በአስር ደቂቃ ውስጥ የጻፈችውን ግጥም ከነፍሬ ፊት ቁጭ ብላ ታንጎራጉርላቸው ጀመር…
አድዋ
የሰው ልጅ ክብር
ሰው መሆን ክቡር
ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን 
ሱውን ሊያከብር
በደግነት በፍቅር በክብር ተጠርቶ
በክብር ይሄዳል ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ
የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነጻነት
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ካጥንት
ቤቱ ውስጥ የነበረው ሁሉ በግጥሟና በእንጉርጉሮዋ ተደሰቱ፡፡ ጂጂ ግን ፈራች ማሸነፉ ቀርቶባት ጥሩ ተወዳዳሪም የምትሆን አልመስላት አለ፡፡ እውነት ለመናገር ይሄን የመሰለ ዓለምን ያነጋገረ የሰውን ልጅ ክብርነት አጉልቶ የሚያሳይ የአድዋ ድል ሙዚቃ በአስር ደቂቃዎች ውስጥ ተጠናቀቀ ቢባል ማን ያምን ይሆን? አብዛኛዎቹ የጂጂ ግጥምና ዜማዎች በዚሁ አጭር ጊዜ ተፈጥረው የተሰደሩ ናቸው ቢባል በስፍራው የነበረ ቢሆን እንጂ ሌላው ከቶ እንዴት ሊቀበል ይችላል? “ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ” አይደል የሚሉት አበው፡፡
ያ ከብዙ ድምጻውያን ጋር የምትወዳደርበት ቀን ደረሰና ስትፈራ ስትቸር ወደ ቃለመጠይቁና ወደ  መፈተኛው ቦታ አመራች፡፡ እሷና ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ለመጀመሪያ ጊዜ ገጽ በገጽ ተገናኙ፡፡ እጅጋየሁ ሽባባው ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማን ከዛ በፊት አለማወቋ እንዲሁም ልትወዳደር የቀረበችበት ግጥምና ዜማ የታላቁ የጥቁር ሕዝብ ድል የሆነው “አድዋ” በመሆኑ ፊቷ ላይ ፍርሃትና ትህትና ጎልቶ ይነበብባት ነበር፡፡
ፕሮፌሰሩ ብዕር በያዙበት እጃቸው ጉንጫቸውን ተደግፈው ካቀረቀሩበት አልተነሱም፡፡ ጂጂ የአድዋ ጀግኖቿን በአዕይነ ህሊናዋ እየሳለችና ከውስጥ በሚፈልቀው ወኔዋ አለቅጥ እየጋለች በዛ ጥዕም ልሳኗ በቤቱ ውስጥ ያለውን ሰው ሁሉ ይዛው ወደ እናት ሐገር ኢትዮጵያ፤ አድዋ ትወነጨፍ ጀመር….በመንታ ዐይኖቹ ስቅስቅ ብሎ የሚያለቅስ እንጂ እንደሰው ተቀምጦ የሚያዳምጥ አንድም ነፍስ በስፍራው አልነበረም…
ጂጂ የዘፈኑን የመጨረሻ ስንኞች ቋጭታ መጨረሷን ለማሳወቅ ወደ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ዘወር አለችና ዐይኗን ወደ መሬቱ መለስ አደረገች፡፡
ፕሮፌሰሩ ሲያነባ የቆየውን ዐይናቸውን ጠረግ አደረጉና ካቀረቀሩበት ቀና ብለው ጂጂን ከእግር ጥፍሯ እስከ ራስ ጸጉሯ ተመለከቷት፡፡ (ይሄኔ ይበልጥ ፈራሁዋቸው ትላለች ጂጂ) ዐይናቸውን አሸት አሸት እያደረጉ “ነይስኪ ወደኔ” አሏት ጂጂም ትንፍሽ ሳትል ካጠገባቸው ተቀመጠች፡፡
“ለመሆኑ ስምሽ ማን ይባላል?” አሏት “እጅጋየሁ ሽባባው እባላለሁ” አለች ፍርሃትና ትህትና ግምባሮቿ ላይ እየተነበቡ፡፡ ለወትሮው ሳቂታና ቸር የሆነችው ጂጂ እንዲህ የግምባሩ መስመር የዘመናት ታሪክን በተሸከመ እውቅ ምሁር ፊት ስትቆም ምን እንደሚሰማት መገመት ቀላል ነው፡፡
“የት ነው ምትኖሪው? ሥራስሽ ምንድን ነው?” በማለት አከታትለው ጠየቋት፡፡ ጂጂም “ካሊፎርኒያ ነው ምኖረው ብዙም አልቆየሁም ዘፈን እጫወታለሁ ጽሐይ የተሰኘ አልበምም በቅርቡ ለቅቄያለሁ” ስትል መለሰች፡፡
“አልበም?” አለ ፕሮፌሰሩ በመደነቅ ዐይነት “አዎ አልበም” ስትል አረጋገጠችለት፡፡
“ሳይሽ ገና ትንሽ ልጅ ነሽ ይሄ ሁሉ ነገር ካንቺ እንደወጣ ማመን አቃተኝ ራስሽ ነሽ የደረሽው?” ሲል በአግራሞት ተመለከታት “አዎ እኔው ነኝ ግጥምና ዜማ እሞካክር ስለነበር ወሬውን እንደሰማሁ ቤት ውስጥ ቁጭ ብዬ የጻፍኩት” ስትል እንዴት እንደሰራቸው አጫወተችው፡፡
ፕሬፌሰር ኃይሌ ገሪማ በሕይወታቸው እንዲህ ዐይነት ኢትዮጵያዊት ልጅ ገጥማቸው አታውቅም፡፡ ትኩር አርገው ይመለከቷትና በሀሳብ ርቀው ይጓዛሉ፡፡ ከግጥሙ ጥንካሬ የዜማው ማማር ከዜማው ውበት የአንደበቷ መጣፈጥ! እኒህ ፕሮፌሰር ምን ብለው አስተያየት ይስጡ? ምኑን ከምን ያድርጉት!? ብቻ በትዕግሥት ጠብቀው…በስተመጨረሻ የመጣችውን የቀይዳማ ጉብል ድምጽ በመስማታቸው አንድም ትዕግስታቸውን ሁለትም ፈጣሪያቸውን ከልብ አመሰገኑ፡፡
“በይ እናቴ ከእኔም ግምት በላይ ሆነሽ ሰርተሽዋል የአድዋ ድልን ከኛ በላይ የተረዳሽው አንቺው ነሽ በቃ መርጨሻለሁ ነገውኑ ተመልሰሽ ነይ፡፡” እያሉ ስራዋን እንደወደዱላትና የፊልሙ ማጀቢያ ሙዚቃ ለማድረግ እንደወሰኑ አበሰሯት፡፡ መሬት መሬቱን እያየች እሺ እያለች ከመመለስ ውጭ ምንም የማትለው ጂጂ ውስጧን በሙሉ ሀሴት ተሰማው፡፡
ጂጂ ከፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ እንደተለየች ቁና ቁና እየተነፈሰች ወደ እህቷ ወደፍሬ  ነበር ያቀናችው፡፡ ፍሬ ሰምኑንን የታናሿ ታናሽ የሆነችው የጂጂ እንግዳ ከሆነች ሰነባበተች፡፡ ቤት እንደደረሰች
“ውይ ውይ ውይ ፍርዬ ነይ ጉድሽን ስሚ” ስትል እቅፍ ረድርጋ ስማት ሶፋው ላይ አረፍ አለች፡፡
ፍሬዓለም ሽባባውም “እሺ እህቴ ተሳክቶልሻል ማለት ነው” እያለች የምስራች ለመስማት ተዘጋጀች፡፡ “በያ ንገሪኝ…”
ጂጂ ሴሮጥ ቆይቶ ቁጭ እንዳለ ህጻን እያለከለከችና እንደመሳቅ እያለች የገጠማትን ትተርክላት ጀመር…
“ፍርዬ ብታይ…ትልቅ ሰውየ ነው ጺሙ ሙልት ያለ፡፡ ልክ ዘፍኜ እንደጨረስኩ ከእግር እስከራሴ አየኝ፡፡ አቤት እንዴት እንደፈራሁት ብታይ…ከዛ እንባውን ጠረግ ጠረግ አደረገና ነይስኪ ካጠገቤ ቁጭ በይ አለኛ (ትወና በሚመስል አነጋገር)…የበለጠ እየፈራሁ ቁጭ አልኩና የሚለኝን ለመስማት ነፍሴ እስክትወጣ ድረስ ጓጓሁ፡፡ ከዛ ‘ለመሆኑ ስምሽ ማን ይባላል?’ ሲል ስሜንም ስራየንም ጠየቀኝ፡፡ አልበም አለኝ ስለውማ በጣም ተደነቀ፡፡
“እሺ እህቴ” ትላለች ፍሬ እንደሁልጊዜው ሁሉ ታናሿን በስስት እያየች፡፡
“…’እጅጋየሁ ጎበዝ ልጅ በጣም ነው ውስጤን የነካሽኝ፡፡ በዕውነቱ ማመን አቃተኝ’ እያለ ምስጋና በምስጋና አያደርገኝም መሠለሽ?…ከዛ በቃ ያንቺን ነው የወደድኩት በቃ ፊልሜን እንዲያጅብልኝ ወስኛለሁ ብሎ ሸኘኝ”..ብላ በእፎይታ ተነፈሰች..
ከዚህም በሁዋላ ይህ ሙዚቃ ተሰራና ለታሰበው የአድዋ ፊልሙ ማጀቢያ ሆነ፡፡ አገር ተንጫጫ፡፡ እራሳቸው ፕሮፌሰሩን ጨምሮ ሥራውን ያዩ ሁሉ ሙዚቃውን አግዝፈው መመልከት ጀመሩ፡፡ ለፊልም ማጀቢያነት የተሰራው ሙዚቃ ራሱን ችሎ ሊያደምጠው የሚፈልግ የጥበብ አዳኝ እልፍ አዕላፍ ሆነ…
ጂጂ ከዘፈኗ እኩል አንደበቷ ይጣፍጣል፡፡ ደግነቷ ያስደስታል፡፡ በኪሷ ብር ይዛ ከወጣች ስትመለስ አይደለም ብሯ ልብሷንም አስረክባ ነው ምትመጣው፡፡ ወደ ከተማ ተዟዙራ ስትመለስ ጂጂዬ ጋብዢን እንጂ ብሎ ቤተሰብ ቀለድ ሲያደርግ…”እሺ ግን ይሄው ኪሴ” ብላ ባዶዋን ኪስ ግልብጥ አድርጋ ታሳያለች ጂጂ ዘንድ ሰው እየተራበ ለነገ የሚባል ነገር ቀልድ ነው፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መጥታ በነበረበት ወቅት ከአንድ ሆቴል ስትወጣ አንድ የሆቴሉ ጥበቃ..”ጂጂዬ የሻሂ በይኝ እንጂ” ብሎ ጠየቃት…ቦርሳዋ ውስጥ አምስት ሺህ ጥሬ ብር ነበር…”ውይ ወንድሜ ኧረ እንካ ያዝ”ብላ ለሷ አምስትም ሳታስቀር ሁሉንም አስታቅፋው ሄዳለች፡፡ መስጠቷ አይደለም የሚገርመው “አሁን ይቺ ብር ምን አላት ሕይወቱን አትቀይርለት ወይ የተሻለ ሥራ አታሰራው” ብላ አዝና መሄዷ እንጂ፡፡ አጅሪት እንዲ ነች እንኳን እንዲ ዝነኛ ሆና ምንም ባይኖራት እንኳ እማዬ ብር አበድሪኝ ብላ ለለመናት ሁሉ መስጠት ልማዷ ነው
ሙዚቃው ከአጽናፍ አጽናፍ መወደዱን ተከትሎ “ምን ይሻላል?” የሚለው የሁሉም ጥያቄ ነበር፡፡ ፊልሙ ወዲህ ሙዚቃው ወዲያ ማዶ ጂጂ ሰማይ ላይ፡፡ ኃይሌ ገሪማ ራሳቸው ሳይቀር “እኔ ያሰራሁት ለፊልሜ ማጀቢያነት ነበር ዘፈኑ ግን ከጠበቅነው በላይ ሆኖ እኛን አስረሳን” ሲሉ ቀለድ ቢጤ ተናገሩ፡፡
“እህሳ..ይሄ ነገር ለምን ራሱን ችሎ ታትሞ ዘፈኑ ለሕዝቡ አይለቀቅም?” የሚሉ ድምጾች እዚህም እዚያም በረከቱ፡፡ ይሄ ለጂጂ እጅግ ቀላሉና አመቺው ወቅትም ነበር፡፡ “አድዋን” አሁን እንደምንሰማው አድርጋ በከፍተኛ ወኔና ብስለት ተጫወተችው፡፡ በሲዲም ታትሞ በየሙዚቃ ቤቱ ለአድናቂዎቿ ቀረበ፡፡
እጅጋየሁ ሽባባው ከዛሬ 20 ዓመት በፊት የአድዋን ሐቅ፤ የአድዋን የሰብዓዊነት ተጋድሎ፤ በዘፈኖቿ ቁልጭ አድርጋ ለዓለም አሳየች፡፡ ከሷ በፊት የሷን ያክል ድሉን ተረድቶ አድዋን የተጫወተ የኪነጥበብ ሰው አልነበረም፡፡ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ይሄን ዘፈን የሚበልጥ ኪነጥበባዊ ሥራ የለም ሲሉም የሚመሰክሩ አሉ፡፡
ጂጂ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ላይ ቀርባ አድዋን በዚ መልኩ የተጫወትሽበት ምክንያት ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ቀርቦላት ነበር፡፡ ምላሿ…
“አድዋ ኢትዮጵያኖች ናቸዉ፡፡ ለእኔ፣ ለወገኖቻቸዉ የሞቱት የታረዱት … ብዙ ነገር የሆነዉ። እና ከዚያ ምክንያት ተነስቼ ነዉ። የሰዉ ሃገር ሄደን አልነካንም መጡብን እንጂ እና ይሄ የጀግንነት ታሪክ አይደለም የሰዉ ልጅ ታሪክ እንጂ ! ” አዎ አድዋ የሰው ልጅ ሁሉ ታሪክ ነው፡፡ ጂጂ ከሁላችን ቀድማ ነበረ፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ዓይነት የፊልም ጠቢባን፣ እንደ ዶክተር ፈቃደ አዘዘ ዐይነት የስነቃል ምሁራን፣ እንደ ቴዎድሮስ ገብሬ ዐይነት የሥነጽሑፍ ልሂቃን እንደ ጂጂ ዐይነት በሳልና ባለቅኔ ከያኔ ባለበት ዘመን በመኖራቸው እድላቸውን አመስግነው ተናገሩ፡፡…አድዋን፣ አባይናን መሠል ዘፈኖቿን እያነሳሱ በየመድረኩ ጥናታዊ ጽሑፎቻቸውን አቀረቡ፡፡ በአፍሪካ፣ በአሜሪካና በአውሮፓ የጂጂ ዝና ጣሪያ የነካ ሆነ፡፡
ድምጻዊት እጅጋየሁ ሽባባው ለአድዋ ፊልም ከሰራችው በተጨማሪ “ኢንዱራንስ” ለተሰኘውና ትኩረቱን በአትሌት ኃይለ ገብረስላሴ ሕይወት ላይ ባጠነጠነው ዘጋቢ ፊልም “እናት ተራራ” የተሰኘ ማጀቢያ ሙዚቃ ሰርታለች፡፡ ከነዚህ ሁለት ዘፈኖች ባሻገር ሌሎች ሥራዎቿም ከአልበሟ እየተዘገኑ የተለያዩ ፊልሞችንና ዘጋቢ ፊልሞችን እንዲያጅቡ ተደርገዋል፡፡ ጂጂ በሙሉ አልበም ደረጃ ሰባት ያክል አልበሞችን አሳትማለች፡፡
ጎበዝ እኔ አንተ እናንተስ ላገራችን ምን አድርገን ይሆን?…ይቺ ከሁሉ ቀድማ የራሷን ፊደል ለቀረጸች ሐገር፣ ይቺ የረሷን ሥርዓተ መንግሥት ዘርግታ ለኖረች ሐገር፣ ለዚች ስደተኞችን በመቀበል ከዓለማችን ሕዝቦች ቀዳሚ ለሆነች ሐገር፣ ለዚች በስልጡን እጆቿ አክሱምን ላሊበላንና ንጎንደርን ላቆመች ሐገር፣ በዓለም አደባባይ ከሰው እንበልጣለን ያሉ ቅኝ ገዢዎችን ከማንም አትበልጡም ከማንም አታንሱም ብላ እብሪታቸውን ድባቅ በመምታት የዓለምን ጥቁሮች ነጻ ላወጣች ሐገር…እኔ አንተ እናንተስ የት ላይ ነን? አሁን ምን እያደረግን ነው?
…ጂጂ እናቷ ቻግኒ ውስጥ በስምሽኮ ሰፈር ተሰይሞልሻል ጂጂዬ አለቻት ጂጂም በጣም በመገረም “እንዴ እማዬ እኔ ላገሬ ምን አድርጌ ነው እንዲህ የሚያደርጉት? ምን ሰርቼ ነው ለመደነቅ የበቃሁት” ስትል ነበር በመተናነስ የመለሰችው! ከሷ የጥበብና የአስተውሎት ልብ አብዝቶ ያድለን! ረዥም እድሜና ክብር ለእጅጋየሁ ሽባባውና ለቤተሰቦቿ፡፡
******
(አስተያዬታችሁን ብታደርሱኝ ደስ ይለኛል፡፡ ለቀጣይ ስራ ስንቅ ነውና፡፡ በተረፈ ጂጂየን፣ ፍሬዓም ሽባባውንና ቤተሰቦቿን ከልቤ አመሰግናለሁ፡፡ ከኪነጥበባዊው አቀራረቡ በስተቀር…የጊዜውን ሁነት እንደወረደ ለማስፈር ሞክሬያለሁ፡፡ በድጋሚ እንኳን ለተከበረው የጥቁር ሕዝብ 123ኛ የድል በዓል አደረሳችሁ፡፡ ደና ሁኑ!)
Filed in: Amharic