>

ሕግ እና ዱላ!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ሕግ እና ዱላ!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
የሕግ እና የዱላ ነገር እየተምታቱብን ይመስላል። ለነገሩ ከሕግ ይልቅ ቅርበቱም ሆነ እውቂያው ያለን ከዱላው ጋር ስለሆነ ለሕግ ተገዥ እና በሕግ ገዢ ከመሆን ይልቅ ለዱላ ብንሰግድ እና በዱላ ብናሰግድ ነው የሚቀናን። በግፉ አገዛዝ ውስጥ ተወልደን፣ በግፍ ሥርዓት ውስጥ አድገን እና ጎልምሰን፤ የትላንት ግፈኛ የዛሬ ግፉእን፣ ትላንት ግፉአ ዛሬ ግፈኛ እየሆን እዚህ ደርሰናል። የሕግ የበላይነት በአግባቡ በተረጋገጠበት እና ሕዝብ የሥልጣን ባላቤት በሆነበት አገር ዱላ እና ጡንቻ ቦታ የላቸውም። ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት በሆነበት ዓለም ሁሉም ሰው እኩል ሰብአዊ ክብሩ ተረጋግጦና መብቱ ተከብሮ፤ እሱም ሕግ እና የሌሎች ሰዎችን መብት እና ክብር ጠብቆና አክብሮ ይኖራል።
ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ሦስት መሰረታዊ ነገሮች ሊኖሩ ይገባል። የመጀመሪያ ፍትሐዊ የሆነ የሕግ ማእቀፍ ነው። በሁሉም እረገድ የዜጎችን መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች የሚያረጋግጥና ጥበቃ የሚያደርግ፣ ፍትሐዊነትን የተላበሰ፣ መድሎን ያስወገደ እና ሁሉንም ሰው በእኩል የሚያይ ሕግ ያስፈልጋል። ሁለተኛው መሰረታዊ ነገር ለሕግ ተገዢ የሆነ ሕግ አስከባሪ አካል መኖር ነው። ሕግ አክባሪ የመንግስት አስተዳደር፣ በሕግ ብቻ የሚመራ የፍትህ ተቋም እና ጥሩ ሕግ የሚያወጣ እና መፈጸሙን የሚያረጋግጥ ሕግ አውጪ ያስፈልጋል። ሌላው እና ዋናው አካል ሕግ አክባሪ የሆነ እና በስነ ምግባር የታነጸ መልካም ዜጋ ያስፈልጋል። ከሦስቱ አንዱ ሲጎድል ወይም ከሕግ መስመር ስሲያፈነግጥ ዱላ ይነግሳል።
ትላንት በለገጣፎ የሺዎች ቤት ሲፈርስ እና ይህን የግፍ አድራጎት ስንቃወም ድርጊቱን ሕግ የማስከበር ሥራ ነው ብለው ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከሩ የነበሩ የቄሮ መሪዎች የአዲስ አበባ መስተዳድር በሕግ አግባብ ተመዝግበው እና ለረዥም ጊዜ ገንዘባቸውን ሲያጠራቅሙ ለነበሩ ሰዎች የኮንደሚኒየም ቤቶችን በአደባባይ ሲያስረክብ ሂደቱን ለማወክ እና መንግስትን ለማስፈራራት በጃዋር ጥሪ አቅርቅቢነት ዛሬ የታየው የዱላ ወጀብ የሕግ አምላክ ወዴት አለ ያስብላል።
ከትውልድ ቅያቸው በግፍ ለተነሱ እና የእርሻ መሬታቸውን ለተነጠቁ በአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚኖሩ አርሶ አደሮች እና ለቤተሰቦቻቸው የኑሮ ዋስትና ሊሰጥ ይገባል፣ ከተሰሩትም ቤቶች ላይ ቅድሚያ ሊያገኙ ይገባል የሚለው ጥያቄ እኔም የምደግፈው እና አግባብነትም ያለው ነው። ይህን ለመንግስት ለማሳሰብ እና ጥያቄውም ምላሽ እንዲያገኝ ጥያቄውን በአግባቡ ማቅረብ ተገቢም ነው። የመብትን ጥያቄ በዱላ እና በጉልበት ለማስጠበቅ ዛቻ መሰንዘር፣ የመንግስት ተቋማትን እና ሹማምንቱን ማዋከብ እና ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ ማድረግ፣ እንዲሁም ሌሎች ዜጎች ስጋት እንዲገባቸው እና እንዲሸማቀቁ ማድረግ ግን ፍጹም ሕገ ወጥ እና ሥርዓት አልበኝነት ነው።
ከእርሻ መሬታቸው እና ከቀያቸው በግፍ የተባረሩ የኦሮሞ ገበሬዎች ጥያቄ በአግባቡ ምላሽ እንዲያገኝ እኔም ለመንግስት ጥሪዮን አቀርባለሁ። በዚያ ግን አላበቃም፤ በየ ሚዲያው እየወጣ መንግስትን እና ሕዝብን እያስፈራራ ቄሮን ለሌላ አመጽ እና ሕገ ወጥ ተግባር እያነሳሳ ያለውን ጃዋርንም ሆነ ሌሎች የኦሮሞ ፖለቲከኞች አደብ እንዲገዙ ማድረግ የመንግስት ሃላፊነት ነው። ከቡራዩ እልቂት ልንማር ይገባል።
Filed in: Amharic