>
6:59 am - Wednesday December 7, 2022

"ጭብጦዬን ከቀማኝ ወዲህ አባይን አላምነውም!!!" (መስከረም አበራ)

“ጭብጦዬን ከቀማኝ ወዲህ አባይን አላምነውም!!!”
መስከረም አበራ
ተፈናቃዮች በመሬታቸው ቤት ሲሰራ ከህንፃው እጣ ፋንታ ይኑራቸው በሚል ቁጥራቸው ላልተገለፀ የኦሮሞ አርሶ አደሮች እና የአርሶ አደር ልጆች Yኮንዶሚንየም ቤት እሰጣለሁ ብሏል ታከለ ኡማ፡፡ይህ ነገር ብዙ ጥያቄ ያስነሳል፡፡አንደኛ አርሶ አደሮቹ ከመሬታቸው ሲፈናቀሉ ምንም አይነት ካሳ አልተከፈላቸው ነበር? ይህ በምን ተረጋገጠ? ካሳ ከተከፈላቸው በካሳው ላይ ቤት መደረባቸው ደግ ቢሆንም ተመሳሳዩ በጉራፈርዳ መሬቱ ምንም ለማይሰራበት “እንዲሁ ሰዎቹ ሃገሩን ምዕራብ ጎጃም ስላስመሰሉ” ተብለው የተፈናቀሉት ሰዎች ካሳቸውን ለማግኘት ከወደ አማራ ክልል የመጣ ንጉስ እስኪነግስ መጠበቅ ሊኖርባቸው ነው? ከጉጂ ጌዲኦ የሚፈናቀሉትስ ከኮቸሬ የሆነ ንጉስ ኢትዮጵያ ዉስጥ ካልነገሰ እምባቸው ሲፈስ መኖሩ ነው? ከአዲስ አበባ ለልማት ተነሱ ሰዎችስ ካሳቸው ምንድን ነው?
ንጉስ የወለደ ብሄር ከዚህም በላይ ይገባዋል ከተባለ ደግሞ ሁንና ይህ ኮንዶሚንየም የተሰራበት ቦታ የስንት አርሶ አደር መሬት  እንደነበረ በቁጥር ወስኖ ለህዝብ ማሳወቅ ይሄን ያህል ከባድ ነገር ነበር? ወይስ ቁጥር መጥቀሱ በሰፊ እጅ ከመዛቅ ያግዳል ተብሎ ነው? አርሶ አደሩ እና የአርሶ አደሩ ልጆች የቤት ባለቤት ይሆናሉ ማለት እንዴት ነው?ለአባት ለብቻ ለልጅ ለብቻ ቤት ይታደላል ማለት ነው ? አንድ አርሶ አደር ስንት ልጅ ቢኖረው ስንት ቤት ለባለመሬት ደርሶ ቀሪው አስራ አራት አመት ሙሉ ተስፋ ለሰነቀው ህዝብ ሊሆን ነው? እንዲህ ክፍት የተተወ አሰራር የአሻጥር መግቢያ በር እንጅ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
እጣ እንዳይወጣ ሲሉ የሰርግ ቤት ወጥ ማማሰያ የመሰለ ዱላ ይዘው የወጡ ጎረምሶች በራሳቸው ተነሳሽነት ወጥተው የገቡ ናቸው ወይስ ብዙ ለመውሰድ ሲባል ግርግር እንዲፈጥሩ ከእጣ አውጭዎቹ ጋር በጥቅሻ የሚሰሩ የዘመድልጆች ናቸው? እጣ እንዳይወጣ ብለው ከወጡ ምን ፈልገው ወጥተው ምን አግኝተው ገቡ? የጎረምሶቹ ግርግር “እጣም መውጣቱን የሚቃወም ፅንፈኛ ነበረ እኛ መሃለኞቹ እንሻላለን” አይነት የነገስታት ቁማር ነች ይሆን? “ጭብጦየን ከቀማኝ ወዲህ አባይን አላምነውም” ይላል የአባይ ማዶ ሰው እምነቱን መሸኘቱን ሲገልፅ::
Filed in: Amharic