>
10:46 am - Sunday May 22, 2022

"የሽግግር መንግስት/ምክር ቤት አስፈላጊነትን በተመለከተ!!! (ያሬድ ጥበቡ)

“የሽግግር መንግስት/ምክርቤት አስፈላጊነትን በተመለከተ!!!
ያሬድ ጥበቡ
መግቢያ
ራሴን የማህበራዊ ሚዲያ ፊታውራሪ አድርጌ የሾምኩ ቢሆንም እንደ ብዙ የመስኩ ሰዎች ወድጄ የተቀበልኩትን ሃላፊነት በደንታቢስነት ልጠቀምበት ፈልጌ አላውቅም። ከዚህ በታች የማሰፍረውንም የሽግግር ምክርቤት ሃሳብ ተጨንቄበት፣ በአቅሜ አስቤበት፣ አልቅሼበት ነው።
– ለስንት ሰማይ የታጨች ንስረ ኢትዮጵያ ክንፏ ተሰብሮ ስትወድቅ እያየሁ ዝምታ  የተሻለው መንገድ ነው ብዬ ማሰብ አልቻልኩም።
– የኦቦ ለማ የዲሞግራፊ (የህዝብ ስብጥር ቀመር) ደባ ልቤን ሰብሮታል፣
– የአዲሱ አረጋ ጥጋብ አቁስሎኛል፣
– የዶክተር አቢይ የአዲስ አበባ ወሰን ኮሚቴ አመሠራረት ተስፋ አስቆርጦኛል። ዝም ልል ፣ እሾህን በእሾህ ነውም አልመረጥኩም። ሃገሬን ካንዣበበባት የዘረኝነት ደባ ልታደጋት ቆረጥኩ። ዋጋ እንዳለውና ሊያስከፍለኝ እንደሚችል እገምታለሁ ። በወርሃ መስከረም ሃገሬን ከብዙ ዓመታት በኋላ ሳይ አልቅሻለሁ።
 በመለየቴ ይሰማኝ የነበረው ጉዳት የበለጠ የተሰማኝ ሄጄ በዓይኔ ያጣሁትን ሳይ ነው። ሃገሬ ትመቻለች። የግል ጣጣዬን ጨርሼ ልኖርባትም እፈልጋለሁ። በአመት አንዴ ለእረፍት ሲሄዱ የሚቋደሱትን የሃገራችንን ፀጋ ላለማጣት መንግስትን ላለመንቀፍ የሚጠነቀቁ ወዳጆቼና ጓደኞቼ ጥቂት አይደሉም። የትዬለሌ ናቸው። ያ የነሱ  ስሜት አይፈታተነኝም ማለት አይደለም። በሰላም ሃገሬ መኖር ብችል ወይም እንደልቤ ገብቼ ብወጣ ደስ ይለኛል። ለዚህ የሚከፈለው ግን ነፃነት ከሆነ፣ ዋጋው በጣም ከባድ መስሎ ተሰምቶኛል። ስለሆነም መናገርን መርጫለሁ።
የሽግግሩ ችግሮች፣
ቲም ለማ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ወደ ዴሞክራሲያዊ ተስፋ ከማሸጋገር ይልቅ ራሱን የኦሮሞ የበላይነት ማስፈኛ ማእከል ወደመሆን ስላዘቀጠ፣ በምትኩ  ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ምክትላቸውን የሚረዳ የሽግግር ምክርቤት እንዲመሠረት ጥሪ ማድረግ መጀመራችን ይታወቃል። ሆኖም ይህ የሽግግር ምክርቤት ከየትና እንዴት እንደሚመሠረት ሃሳብ መለዋወጥ አልጀመርንም።
ባለፉት 11 ወራት የሃገሪቷን አንድነት ጠብቆ ካቆዩትና የለውጡን ሂደት ካስቀጠሉት ተቋማት መሃል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈትቤት ዋነኛው ነው። ይህም ሲባል ሥልጣኑ ብቻውን ሳይሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብእናና ተወዳጅነት ራሱ ለውጡን ከተቀናቃኝ ሃይሎች  እየጠበቀ እንዲቀጥል ረድቷል ። ሆኖም ዶክተር አቢይ በሚመሩት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራር ውስጥ የሚካሄደው ጠባብ ብሄርተኛ ስሌትና በአዲስ አበባ ባለቤትነት ዙሪያ ፓርቲያቸው የወሰደው የወራሪ አቋም፣ በለውጡ ዙሪያ የተሰባሰበውን ተስፈኛ ህዝብ እጅግ ያስደነገጠ ሆኗል ።
በእኔ አስተያየት፣ ራሱን ላከሰመ የኢህአዴግ አመራር የሃገሪቱ እጣ የሚተውበት ምንም ምክንያት የለም። ኢህዘዴግ፣ በተሰጠው እድል ባለፉት 11 ወራት ራሱን ከመጠላለፍ አውጥቶ ሃገራዊ አመራር ለመስጠት ባለመቻሉ ከዚህ ነጥብ በኋላ መዘናጋት ኢትዮጵያችንን መበደል ይሆናል ብዬ እፈራለሁ።
የሽግግር ምክርቤት አስፈላጊነት፣
በብርሃን ፍጥነት እያሽቆለቆለ የመጣውን  የጠቅላይ ሚኒስትሩን ተቀባይነት ለመታደግና፣ ሃገራችንን ከቀውስ ለመከላከል ከሽግግር መንግስት የተሻለ መሳሪያ ዛሬ በእጃችን የለም ። የሽግግር መንግስቱ፣ የሽግግር ምክርቤት በማቋቋም መጀመር ይችላል። የሽግግር ምክርቤቱም ከተደራጁ ተቋማት በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ሊሆን ይገባል። ህዝቡ በነፃነት በየአካባቢው ካሉት ተቋማቱ የተሻለ ሃገራዊ ርእይ አላቸው የሚላቸውን ወኪሎች መላክ ይችላል። ለምሳሌ ከባንኮች ሠራተኞች ፣ ከአየር መንገድ ፣ ከመብራት ሃይል፣ ከቴሌ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከክልል ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከአቃቂ ሠራተኞች፣ ከሰበታ ሠራተኞች፣ ከኤፈርት ሠራተኞች፣ ከድሬዳዋ ሠራተኞች፣ ከመንግስት ሠራተኞች፣ ከአዲስአበባ ነዋሪዎች ከየወረዳው፣ ከክልል ከተሞች ነዋሪዎች፣ ከአራቱ ወታደራዊ እዞች፣ ከኢትዮጵያ መምህራን፣ ከኢትዮጵያ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ከነጋዴዎች ምክርቤቶች፣ ከቀድሞ የፖለቲካ እስረኞች ፣ ከጋዜጠኞች ማህበር፣ ከ10 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ካላቸው የዳያስፖራ ከተሞች፣ ከተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ ከክልል ምክርቤቶች ተወካዮች፣ ከሃገርአቀፍ የሴቶችና የወጣቶች ማህበራት ተወካዮች፣ እና ከሌሎችም የተደራጁ ተቋማት የተላኩ የህዝብ ወኪሎች የሚመሠርቱት የሽግግር ምክርቤት አሁን ሃገራችን ከገባችበት የፖለቲካ ቅርቃር እንድትወጣ ይረዳት ይመስለኛል። በወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው የምርጫ ቦርድ እነዚህ ምርጫዎች ተገቢውን ውክልና ያገኙ መሆናቸውን ማረጋገጥና በቀናት ውስጥ መጠናቀቃቸውን መከታተል ሚና ሊጫወት ይችላል።
የሽግግር ምክርቤቱ ከራሱም ውስጥ ሆነ ከውጪው የፖለቲካ አመራር ብቃቱ፣ ብስለቱና ተቀባይነቱ አላቸው የሚላቸውን ከ9 እስከ 15 ዜጎች ያሉበትን የጠቅላይ ሚኒስትሩንና ምክትላቸውን የሚያማክርና በሥራቸው የሚያግዝ እንደ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ወይም የፖለቲካ ኮሚቴ ሆኖ የሚሠራ ከፍተኛ አካል ሊመሠርት ይችላል። ይህ የሽግግር ምክርቤት ሽግግሩን የሚረዱ ህጎች የማውጣት መብት ስላለው፣ በኢህአዴግ ካድሬዎች የተሞላው የተወካዮች ምክርቤት የተሰኘው አካል ቦታውን ለሽግግር ምክርቤቱ እንዲለቅ ማድረግ ይቻላል።
የሽግግር ምክርቤቱ ቢበዛ የሦስት ዓመታት እድሜ ያለው ሆኖ፣ ፓርላማን ተክቶ ሙሉ የህግ አውጪ ሥራዎችን የሚሠራ ሳይሆን፣ ሽግግሩን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ብቻ የሚያተኩርና ሃገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ተስፋ የሚያሸጋግሩ ጉዳዮች ላይ ብቻ ራሱን አቅቦ እንዲሰራ ማድረግ ይቻላል። ሊሠራ ከሚችላቸውም አንኳር ሥራዎች መሃል፣
1ኛ) የብሄራዊ እርቅ ማካሄድና የሃገሪቱን ቀልብ መሰብሰብና፣ ባለፉት 27 ዓመታት ሃገሪቱ ያለፈችበትን የወዳጅ/ጠላት ክፍፍል ምእራፍ መዝጋት፣
2ኛ) የብሄራዊ (ሃገራዊ) ህዝብ ቆጠራን ከአድልኦ በፀዳ መልክ መምራትና የምርጫ ወረዳዎችን የማመጣጠን ሥራ መሥራት፣
3ኛ) የህዝብ መብቶችን ለመጉዳት የወጡ ህግጋትን መሻር፣
4ኛ) ሃገሪቱን ለህገመንግስታዊ መሻሻል ማዘጋጀት፣ ሰፊ ህገመንግስታዊ ክርክሮች እንዲደረጉ በማመቻቸት፣ ህገመንግስታዊ ማሻሻያ ጉባኤ እንዲጠራና የተሻሻለው ህገመንግስት እንዲፀድቅ ማመቻቸት፣
5ኛ) በተሻሻለው ህገመንግስት መሠረትም ሃገርአቀፍ ምርጫዎች ፍትሃዊና ርቱእ በሆነ መንገድ መካሄዳቸውን በማረጋገጥ ለተመረጡት ህዝባዊ መማክርት ሸንጎ አስረክቦ የሽግግር ምክርቤቱን ማፍረስ ተግባራቱ ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ቢያስፈልግ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራር ሊሰጡ የሚችሉበት የሽግግር ምክርቤቱ ፕሬዚደንት ሆነው ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መቀጠል ከፈለጉም የሚኒስትሮች ምክርቤቱን የሚመራ የቴክኖክራት ሥልጣን ይዘው መቀጠል ይችሉ ይመስለኛል። በግሌ ለ11 ወራት ከታዘብኩት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን የያዙትን ጠቅላይ ሚኒስትርነት ይዘው በመቀጠል የሚኒስቴሮች ምክርቤትን ሲመሩ፣ የፖለቲካ አመራሩን ለምክርቤቱ ፕሬዚዳንት ማስተላለፍ የተሻለው አማራጭ ይመስለኛል።
አሁን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት በማገልገል ላይ ያሉት አቶ ደመቀ መኮንን ፕሬዚዳንት ሆነው ምክርቤቱን ሲመሩ፣ ከህወሓት አንድ ሰው (ለምሳሌ ዶ/ር አርከበ ወይም ወይዘሪት ሞንጆሪኖ ሊሆኑ ይችላሉ) የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ሊሞሉ ይችሉ ይመስለኛል ። በዚህ መልክ ብንሄድበት ሃገራችንን የተሻለ ተስፋ ማስጨበጥ እንችላለን ብዬ አስባለሁ።
እንግዲህ ይህ የአንድ ሰው ሃሳብ ነው፣ እስቲ ሃሳቡ ላይ ጨምሩበትና እናጎልምሰው ፣ ምን ይመስላችኋል?”
Filed in: Amharic