>

ሞት ፣ ጊዜ ፣ ከበደ ሚካኤል፣ ጠቢቡ ሰሎሞን እና አብይ !  (ደረጀ ደስታ) 


ሞት ፣ ጊዜ ፣ ከበደ ሚካኤል፣ ጠቢቡ ሰሎሞን እና አብይ !
 ደረጀ ደስታ 
ሞት ወዳጅ ቤተሰቤን ጎብኝቶ አከታትሎ ሲነጣጥቀን ከረመ። አንድ ሰሞን አንድ ሠፈር ይውላል እሚባለውን አመንኩ። አሁንም ከአጠገቤ አልራቀም። አብራክና ክፋዩ የሞተበት ሰው ስለሞተበት ሰው ብቻ ያዝናል። ሟችንም በሀዘን የተሰበረውንም ሰው ደርበው ሲያውቁ ደግሞ ሀዘኑ ድርብ ይሆናል። ብርቱ ሀዘን የሰበረው ሰው ምን ሊሰማው እንደሚችል ተጠግቶ ማሰቡ ግን ለሟች ከማዘን የከፋ ሀዘን ይመስለኛል። ግን ለምን?
ከትካዜው አመልጥ ዘንድ ሞትን አሰላሰልኩት። ሌላ ቦታ አንድ ሚሊዮን ህዝብ እንኳ ቢያልቅ ለሀዘንህ መጽናኛ፣ ማስተዛዛኛና ማመዛዘኛ አይሆንህም። ሞት የግል ነው። ቁጥር ሳይሆን ዓይነት ነው። ሎጂክ ሳይሆን ስሜት ነው። በመርከብ ካለቀው ከአውሮፕላን የወደቀው በልጦ ያስለቅስሃል። የሶሪያ ህጻናት እያሉ ለአሜሪካ ጎረምሶች ለምን አለቅስክ አይባልም። ባንግላዴሽ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ቢያልቅ አዲስ አበባው ከሚሞተው አስር ሰው ሞት በልጦ አያስለቅስህም። ለቡራዩ እና ለጌድኦ ሀዘንህ እኩል ላይሆን ይችላል። ያንተ ብሔር ሞት የኩነኔ፣ የጠላትህ ብሔር ግን የአረመኔ ሊሆን ይችላል። ስትሞት መስዋዕትነት ስትገድል ጀግንነት ነው። እንዲሁ እንዳልክ፣ አታውቅ ይመስል በሞት ሰበር ዜና ተገርመህ እንዳዘንክ አንተም ቤት ከተፍ ይላል። ተዘጋጅተህ አትጠብቀውም።
ሞትኮ ወዳጅህን ለምን አታድርም፣ ባይሆን ትንሽ ተወጫውተህ አትሄድም፣ ምን አስቸኮለህ እምትለው ሽኝት አይደለም። እምትወድው ሰው ሳይነግር ሳይሰናበትህ እብስ ይላል። ሕጻንህ ሲቀጭ ፣ “ለምን ትንሽ አታድግም?” እምትልበት እድል የለህም። ጎልማሳህንም፣ “ሰዓቱ ገና አይደለ እንዴ ምን አጣደፈህ?” አትለውም።  አዛውንትህን – “አሁንማ ተጫወት እንጂ አንድያህን ትሄዳለህ!” ብለህ ትንሽ እንኳ አታግደረድረውም። እድሉ የለም። ሞት ማለት ፍቅረኛ ወዳጅህንም ሆነ የኑሮ አጋርህን- “ብቻዬን ጥለኸኝ- ጥለሽኝ!” ብለህ እማትወቅስበት ጸጸት ነው። ሞት ወረፋ ይዘህ እምትጠብቀበት፣ ማን ከማን እንደሚቀድም እማታውቅበት፣ ሌላው ሳያውቅ ባንድ ወገን የተያዘ ቀጠሮ ነው።
ሞት የቀረ ብቻ ሳይሆን የሌለ እያስመሰለ፣ ታውቆ እያታለለ፣ በዘላለማዊነት አጃጅሎ ከቅጽበት ህይወት በቅጽበት እሚቀማ ክፉ ነገር ነው። ከጫካኔው ብዛት፣ ደግነቱን ለማሳየት ፣ ህመም፣ ጣርና ስቃይን አብዝቶ ሲያበቃ፣ ገላጋይና አዳኝ መስሎ ይገድልና ሟችን “ተገላገለ!” ያሰኛል። አረፈም ይባላል። እሚጠላውንም ያህል ተወዶ እሚናፈቅበትም ጊዜ ያለው ለማስመሰል፣ እሱ እንኳ የተቀደሰ ሆኖ፣ “ምናለ በወሰደከኝ!” እያስባለ ያስመኛል። እሚገርመው ደግሞ ሞት ሰው አልገድልም ያለ ይመስል፣ ሰው ሰውን ይገድላል። አዳሜም ምሬሃለሁ የተባለ ይመስል፣ ወይም ሞት ድንገት የቀረ እንደሁ የት እገባለሁ ብሎ የሰጋ ይመስል፣ ወደ ሞቱ ይጣደፋል።
ህይወት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አይደለችም፣ “ከሞት በኋላ ዘለማለማዊ ህይወት አለ” ብሎ ያመነም ሆነ ያለመነውም ሁሉ ግን ፣ መክብብ በመጽሐፉ “እግዚአብሔር የሰው ልጅ ሁሉን ነገር መርምሮ እንዳያውቅ ዘላለማዊነትን በልቡ ሰጠው” እንዳለው፣ የሰው ልጅ አኗኗሩና አነጋገሩ ሞትን ድል እንደነሳ ሆኖ፣ ለአምልኮ ዘማሪ ፣ ለመግደል ፎካሪ መስሏል። በአብይም ዘመን ሞት በዛና፣ ገዳይ እየመራ ለሟች እየሠራ ያለ መሰለና፣ ነገር ተምታቶ መፍትሔው ግራ ገብቶ፣ ሞትን ድል መንሳት በሞት ሆነና ሌላ ምርጫ ጠፍቶ፣ ሞትን ገድሎ እሚያቆም ገዳይ መሪ ተናፈቀ። አብይ አልገድል ቢል የመግደል “አቅም” የሌለው መሪ እየተባለ ይገመገም ጀመር። ሞትን ለማቆም ገዳዮችን መግደል እማይችል መሪ ፣ የነገር ሂደቱ የሞት ዑደቱ አልገባ ካለው፣ ከመግደል ቢድን ከሞሞት ግን አያመልጥ ይሆናል። መግደል መሸነፍ ከሆነ መሞትም ማሸነፍ አይሆንም። ሁለቱም ቤት ሞት አለ።
ግን ደግሞ ማን ያውቃል! ምናልባት ህይወት ማለት፣ ሞት እስኪሸነፍ፣ ጨዋታውን እየመሩ መቆየት ሊሆን ይችላል። ግን ለምን ያህል ጊዜ ይሆን? ክርስቶስ ሞትን ድል ነስቶ መምጫው ግን አይታወቅም። ሁሉ በሱ ነውና ለአብይም ጊዜ ስጡት ሞትን ያለሞት፣ ደምን ያለደም ሊያቆመው ይችላልና ይላሉ ሌለኞቹ። ምክንያቱም “ለሁሉም ጊዜ አለው” ብሏል ንጉሥ ሰሎሞን። ችግሩ አብይ ጊዜ አገኙም አላገኙም፣ ገደሉም ሞቱም የጠለቅንባቸው ነገሮች በቀላሉ አይፈቱም ብሎ ላሰበ ሰው ግን፣ ጥያቄውን ወደ ደራሲና ባለቅኔ ከበደ ሚካኤል ይወስደዋል። ችግሩ አልቀር ካለው ከሞት እንጂ፣ ከተገዳዳዮች ብቻም ላይሆን ይችላል ብሎም ያስባል።  ጠቢቡን ሰሎሞንን ያህል በአንዲት ፈንጂ ጥያቄ የሞገቱት የአገሬ ጠያቂ ። የጠቢቡና ንጉሥ ሰሎሞንን ዝነኛ አባባል እንዲህ ሞግተዋታል-
ለሁሉም ጊዜ አለው ብሏል ሰሎሞን
እጠይቀው ነበር በተገናኘን
ሞት የሚሞትበት ጊዜው መች ይሆን?!
Filed in: Amharic