>

ጥሬ ልኮ ጥሬ መቀበል!!! (ኤፍሬም እንዳለ)

ጥሬ ልኮ ጥሬ መቀበል!!!
ኤፍሬም እንዳለ
ሰውየው አሞሌ ጨው ሲስርቅ እጅ ከፍንጅ ይያዛል፡፡ ምን ቅጣት እንደሚገባው ህዝቡ ይመክርና በአለንጋ እንዲገረፍ ይወሰናል፡፡ አደባባይ አውጥተው እህል ውሀ በማያሰኝ አለንጋ ሰንበር በሰንበር ካደረጉት በኋላ ቆም ያደርጉና ጥያቄ ያቀርቡለታል፡፡ “አሁንስ፣ ሁለተኛ እንዲህ አይነት ድርጊት ይለምድሀል?” ይሉታል፡፡ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው… “ዝም ብላችሁ አለንጋችሁን አትጨርሱ፣ የጨው ገበያን እንደሆነ መቼም አልተውም!” አለና አረፈው!!!
የዚች አገር ትልቁ ችግር “የጨው ገበያን መቼም አልተውም፣” አይነት ቡድኖችና ግለሰቦች መብዛታቸው ነው፡፡
የ“እኛና እነሱ” ፖለቲካ ብሶበታል፡፡ ብሶበታል ብቻ ሰይሆን መመሪያ የሆነ ይመስላል፡፡ ‘እኛ’… እኛ ነን፣ ‘እነሱ’ ደግሞ ጠላቶች ናቸው፡፡ የፖለቲካችን ዋናው መፈክር “ጠላት አታሳጣኝ… የሚለው ብሂል  ይመስላል፡፡
በዛኛው ወገን ጠላት መኖር አለበት፣ ከሌለም መፈጠር አለበት፡፡ 
ቀስቱን ከደረታችን ጋር ለማገናኘት ያደፈጠ፣ ግንባራችንን የኢላማ መለማመጃ ለማድረግ ያነጣጠረ ጠላት መኖር አለበት፡፡ ከሌለ ፖለቲከኛነታችን፣ አክቲቪስትነታችን… ሙሉ አይሆንም፡፡ በዛኛው ወገን ያለው የእኔ የሚለው አማራጭ ያለው ሳይሆን በቃ ጠላት ነው…አራት ነጥብ እንዲሉ ፖለቲከኞች፡፡ ጠላት ከሌለ ማን ይወገዝ! ማን “መጣባችሁ!”ይባል! ማን “ውስጥሀ ተሰግስገው ከዓላማህ ሊያሰናክሉሀ የሚሞክሩ…ይባል!
“የጨው ገበያን መቼም አልተውም፣” አገር እያመሰ ነው፡፡ 
አዎ… በኢትዮጵያ ፖለቲካ በአብዛኛው ተፈላጊዎቹ ‘ተቃዋሚ‘… ወይም ‘ፖለቲካል ኮሬክትነስ’ ነው ተብሎ በሚገመት አጠራር… ‘ተፎካካሪ ፓርቲዎች’ አይደሉም ጠላቶች እንጂ፡፡ ይህ ዙፋን ላይ የመቀመጥና ያለመቀመጥ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለእኛ መኖር አስፈላጊነት ማመሳከሪያዎች የሚሆኑት የእኛን ሀሳብ የሚሞግቱ አማራጭ ሀሳቦች ሳይሆኑ እኛን ለማጣጣል የሚያሴሩ የፖለቲካ ቡድኖች ናቸው፡፡
ለብዙዎቻችን በጨቅላነት ዘመን “ጭራቅ መጣብህ!” “ዋ ጅቡን እንዳልጠራብህ!” እየተባለ ያደግንበት ህብረተሰብ ነው፡፡ በዛ ጮርቃ እድሜያችን እኛ ያላየናቸው ግን አድፍጠው እንደሚጠብቁን የሚነገሩን የጭራቅና የጅብ ጠላቶች ነበሩ፡፡
በአዋቂነታችን ደግሞ የምናያቸውም፣ የማናያቸውም “ነብር አየኝ በል፣” ስንባል እንጂ በድርጊት ያልተረጋገጡልን ጠላቶች አሉን… እንደ ልጅነት ዘመናችን ጭራቅና ጅብ፡፡
ፖለቲካችን በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ የመሰባሰብ ጉዳይ ሳይሆን የአሳዳጅ፣ የተሳዳጅ ከመሆን ሊወጣ አለመቻሉ ያሳዝናል፡፡ የሚታዩ ግልጽ ምልክቶች ባይኖሩም የዛኛውን ጠላትነት ለማመሳከር “የሚለውን አትስማ፣ ሆዱ እባብ ነው!” አይነት ነገር ማለት ይበቃል፡፡
የእኛ ስኬት፣ የእሱ ሰቆቃ የሚሆንባቸው ጠላቶች በዛኛው ወገን ከሌሉ ምኑን ፖለቲከኛ ሆንነው! ምኑን አክቲቪስት ሆንነው! የሀገር ውስጥም ሆነ የፈረንጅ ሀገሩ እውቀት ከዚህ አይነት ቅድመ ኖህ ጭፍንነት ካልገላገለን አንደኛውን ለፊርማ አውራ ጣታችንን እያቀረብን መኖሩ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ለአገር እድገትና ለህዝብ ብልጽግና፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለሰብአዊ መብቶች ሳይሸራረፉ መከበር ያልዋለ እውቀት መጣ፣ ቀረ ምን ለውጥ ያመጣል!
ለብዙ ችግሮቻችን ከዋናዎቹ ምክንያቶች ገዘፈው በሁለት ሺህ አስራዎቹ ዘመን ሙሉ ልብስ ስር የአስራ ዘጠኝ ሀምሳዎቹን ጎዶሎ ፖለቲካ ተሸክመን ስለምንዞር መሆን አለበት፡፡ በዘመናቸው ትክክል ተብለው የሚታሰቡ ፖለቲካ እሳቤዎች ከሰው ልጅ ጉዞና ከዘመን ግስጋሴ ጋር የሚለወጡ መሆናቸውን ለመቀበል የሚያስችል የአእምሮ ብቃት ላይ መድረስ የቸገረን በዝተናል…በዚህ የተነሳ አገርም መከራዋን እየበላች ነው፡፡
በነገራችን ላይ ቆዳና ሌጦ ጥሬውን እንልክና ጃኬት፣ ቦርሳ ምናምን ሆኖ አልቆ ይመጣል፣ በሌላ አነጋገር ጥሬውን ልከነው በስሎ ይመጣል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰው ጥሬውን እንልክና ፖለቲከኛ፣ አክቲቪስት ምናምን የሚል ታርጋ ለጥፎ ይመጣል…በጥሬነቱ ! አይደለም መብሰል፣ ለብ ለብ ደረጃ እንኳን ያልደረሱ ሀሳቦች ስንሰማ ጥሬ ልከን ጥሬ እንደተመለሰልን እናውቃለን፡፡
“የኬኩ ትልቀኛው ክፍል የእኔ ነው” አይነት ቀስ ብሎ “እንደውም ሙሉ ኬኩ የእኔ ነው!” ወደሚል የሚመራ አስተሳሳብ ችግር ያለበት ነው… በሌለ ፉርኖ ስለ ኬክ መተራመስ!
“የጨው ገበያን መቼም አልተውም፣” አገር እያመሰ ነው፡፡ 
አንድ እያቆጠቆጠ ያለ ነገር አለ… በተለይ ቡድኖች ወይ ግለሰቦች ሀሳቦች ወይም ድርጊቶች ላይ ተቃውሞዎች ሲሰሙ ስረ መሰረቱን ይዞ ከመነጋገር ይልቅ “ለውጡን ለማደናቀፍ…” የምትለዋ ሀረግ እየተደጋገመች ነው፡፡ ምቾት በማይሰጥ ሁኔታ እየተደጋገመች ነው፡፡
በነገራችን ላይ ህዝባችን የዘር፣ የሀይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከት ሳይል ከመሀል አገር እስከ ዓለም ጫፍ ለድጋፍ “ሆ” ብሎ የወጣው፣ በእልልታ ሰማያ ሰማያቱን የሞላው፣ ብሎም ለውጡን የ“እኔ ነው…” ብሎ የተቀበለው የተስፋ ዜማ ስለሰማ ነው፣ የፍቅር  ዜማ ስለሰማ ነው፤ የመቻቻልና የወንድማማችነት ዜማ ስለሰማ ነው፣ ሁሉም እኩል ተጠቃሚ የሆነባትን የበለጸገች ኢትዮጵያን የመገንባት ዜማ ስለሰማ ነው፣ በአገሪቱ የትኛውም ስፍራ መኖር እንደሚችልና ማንም ሊያፈናቅለው እንደማይችል የሚረጋግጥለት ጣፋጭ ዜማ ሰለሰማ ነው፡፡
እና አሁን ቢያጉረመርም ምን ይገርማል! ግራ ተጋብቶ “ምን እየተካሄደ ነው?” ብሎ ቢጠይቅ “ድሮስ ለምን ምን አይጥማትም፣” ሊባል ነው! ምን ባጠፋ!…፡፡
የተስፋው ዜማ ከቅኝት እየወጣበት እኮ ነው፣ የፍቅር ዜማው ወደጥላቻ ቀረርቶ እየተለወጠበት ነው እኮ፣ የመቻቻልና የወንድማማችነት ዜማ የደመኛ ጠላትነት “በለው በለውና አሳጣው መድረሻ…” ፉከራ እየሆነበት እኮ ነው፣ ሁሉም እኩል ተጠቃሚ የሆነባት ኢትዮጵያን የመገንባት ዓላማ ‘ሳይንስ ፊክሽን’ እንዲመስለው እየተደረገ ነው እኮ…
እርግጥ ነው የተጀመረውን ለውጥ ወደራሳቸው የግልና የቡድን ጥቅም ለመለወጥ የሚሞክሩና ካልተሳካ ደግሞ አገር በአፍ ጢሟ ብትድፋ ግድ የማይሰጣቸው አሉ፡፡
 እንደውም ይህ እውን እንዲሆን ሚናቸውን ለመወጣት ዝግጁ የሆኑ አሉ… “መቼም ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት…” ተብሎ እንደሚታለፍ ነገር ቀላል አይደለም፡፡ ግን ደግሞ ‘የሀቅ’ ተቃውሞዎችን እና ‘የማነቅ’ ተቃውሞዎችን መለየቱ ደግ ነው፡፡
“የጨው ገበያን መቼም አልተውም፣” አገር እያመሰ ነው፡፡ 
“ሁሉንም ሰው ማመን መጥፎ ነው፣ ማንንም ሰው አለማመንም በተመሳሳይ መጥፎ ነው፡” ይላል አንዱ ፈላስፋ፡፡ የተያዘው ነገሮችን በእውነት ሚዛን ላይ ማስቀመጥ ሳይሆን የምንፈልገውን እያመንን የማንፈልገውን የምናጣጥልበት ነው፡፡ እውነት ታግታለችና…አጋቻቾቹም ሁላችንም ነንና!
የእውነትን መንገድ ተሳስቼ
ተቀጣሁ በውሸት ተመርቼ
እውነት ማሪኝ እላለሁ
ይቅርታ እለምናለሁ
እንደተባለው እውነትን “ማሪኝ…” የምንልበት ጊዜ ቢቀርብልን በወደድን፡፡
ሰውየው ውቃው የሚባል ዘመቻ ይሄዳል፡፡ እዛም እያለ ዘመቻው ላይ የነበረ ወንድሙን ሞት ያረዱታል፡፡ “ሬሳውን ካላየሁ አላምንም፣” ብሎ ወድቆበታል ወደተባለው ስፍራ ጉዞ ይጀምራል፡፡ መንገድ ላይ ግን የማይወዳቸው አማቹን ሬሳ ወድቆ ያያል፡፡
ይሄኔ ከዳር ዳር ፈገግ ብሎ ምን ቢል ጥሩ ነው…“ውቃው…እዚህ ላይስ ጥሩ አደረግሽ” አለ አሉ…ሰውየውን አይውዳቸውም ነበር፡፡ በወንድሙ ሞት ከማዘን ይልቅ “አልውዳቸውም” በሚላቸው ሰው ሞት ተደሰተ፡፡ ፖለቲካችንም እንዲሁ ነው…የምንረካው በእኛ ስኬት ሳይሆን በዛኛው ውድቀት ነው፡፡ ነገራችን “እሰይ ከፍ፣ ከፍ አልኩ” ሳይሆን፣ “እሰይ ተፈጠፈጡልኝ!” ነው፡፡
ይኸው ሰዎች እንደገና እየተፈናቀሉ፣ ከምሬትና እንባ አልፈው የ“እባካችሁ ድረሱልን!” ጥሪ አስከማሰማት ደርሰዋል፡፡ በገዛ አገራቸው፣ በእግዜሩ ምድር!
“ከእንግዲህ አትፈናቀሉም…”  ሲባል እልል ብለን ይኸው የትናንትና እና የትናንት ወዲያው ሳይለቀን አዲስ የማፈናቀል ዙር! እንደገና ሀዘን፣ እንደገና ለቅሶ፣ እንደገና አቅመ ቢስነት! እንደገና ጋሻ መከታ ማጣት! ይህ ነገር ነገ፣ ከነገ ወዲያ “ሀይ” ባይ በሌለበት ላለመቀጠሉ ምንም ማረጋገጫ የለንም፡፡ ነገን በስጋት ብናይም አይፈረድብንም፡፡
 “የጨው ገበያን መቼም አልተውም፣” አገር እያመሰ ነው፡፡
Filed in: Amharic