>
5:13 pm - Thursday April 19, 6198

ይሸሽበት ይጠጋበት ያጣ ትውልድ !!! (ውብሸት ሙላት)

ይሸሽበት ይጠጋበት ያጣ ትውልድ !!!
ውብሸት ሙላት
የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ተቋማት እምነት የሚጣልባቸዉ፣ ተስፋ የሚደረግባቸዉ፣ የክፉ ቀን መጠለያና መጠጊያ የመሆን ቁመና የላቸዉም፡፡ ዜጎች ግጭትና መከራ ቢመጣብን ያድኑናል፣ያስጥሉናል ይተደጉናል የሚሏቸዉ ባጡ ጊዜ የጭንቅ ቀን ያወጣናል የሚሉትን መፍትሔ መፈለጋቸዉ አይቀሬ ነዉ፡፡
በኢትዮጵያ ፓርላማዉ ወይም የፌደሬሽን ምክር ቤት እንኳን ለዜጎች ዋስተና ሊሆን ይቀርና ራሳቸዉም በአስፈጻሚዉ ችሮታ የሚኖሩ ናቸዉ፡፡
ፍርድ ቤትና ሚዲያዎችም እንኳን ሌዘጎች መከታ በመሆን ከጭንቅ ሊያወጡ ይቀርና መንግሥት ቢያነጥስ እልም የሚሉ ለጭላንጭል ያልበቁ ናቸዉ፡፡ ሚዲያዉ ቢፈልግ እንኳን መንግሥትን ተገዳድሮ ሊዘልቅ ይቀርና ራሱንን በመንግሥት ከመጥፋት መታደግ አይችለም፡፡
መከላከያ፣ፖሊስና ድኅንነቱም በብሔር የተከፋፈሉ፣ ወይም አብሮ እንደፖለቲካ ሥርዓቱ የታመሙ ናቸዉ፡፡ ለኢትዮጵያዊያን ለአንድነታቸዉ (ማንንም ከማን ሳይለዩ) የሚቆሙበት አቅም የላቸዉም፡፡ ይህ አቅማቸዉ ተቦርቡሯል፡፡ ዜጎችም እነዚህ ተቋማት ዉስጥ የሚገኙ ኃይሎች እርስ በራሰቸዉም እንዳይጨካከኑ ለፈጣሪያቸዉ ከመጸለይ ያለፈ የጭንቅ ቀን ታዳጊያችን ናቸዉ፡፡ ብሔርን ወይም ሌላ አሰላለፍን መሠረት ያደረገ ብጥብጥ ቢነሳ ቢያንስ እነዚህ ተቋማት አሉን የሚባሉ አይደሉም፡፡
ማን ቀረ ተስፋ የሚጣልበት የፖለቲካ ፓርቲ አለን የሃይማኖት ተቋማት (ምናልባት ትንሽ ትንሽ) ማሰባሰቢ ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል፡፡
ዜጎች ብሔራቸዉ ምንም ይሁን ምን፣ ጭንቀት ዉስጥ ሳይገቡ ግጭትና ቀዉስ ቢከሰት ግጭትና ቀዉሱን ተቆጣጥሮ የሚታደጋቸዉ መንግሥታዊ ተቋም ከሌለ፣ አማራጭ መፈለጋቸዉ አይቀሬ ነዉ፡፡
ምናልባት በጣም ሊተማመኑበት የሚሉት ቤተሰብን ነዉ፡፡ ዘመድን ነዉ፡፡ ጭንቅ ሲመጣ ጥሎ የማይጥል፣ የችግር ደራሽ መሆኑ አይቀሬ ነዉ፡፡ ግን ቤተሰብ ከፍ ላለ ግጭትና ቀዉስ በቂ መጠጊያ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ዉስጥ አሁን ላይ ዜጎች እምነታቸዉን የሚሳድሩት (ተስፋ የሚደርጉት) ብሔራቸዉን ብቻ እየሆነ ነዉ፡፡ አማራ ከየክልሉ ሲፈናቀል አዲስ አበባ አይመጣም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ምንም ያደርግልኛል፣ከችግሬ ይተደገኛል የሚል እምነት ስለሌለዉ፡፡ ጌዲዮ ከጉጂ ዞን ሲፈናቀል ወደ ጌዲዮ ዞን መጣ እንጂ ወደ ሐዋሳ እንኳን አልመጣም፡፡ አሮሞዎች ከሶማሊያ ሲፈናቀሉ ወደ ኦሮሚያ ነዉ የመጡት፡፡
ስለሆነም፣ አሁን ላይ ወደድንም ጠላን ቢያቅረንም ቢመረንም የመንግሥት ተቋማትን የሚያምን ወይም ተስፋ የሚደርግ አናገኝም፡፡ በተግባርም እየታየ ያለዉ ይሄዉ ነዉ፡፡
“መንግሥቴ እረኛዬ ነዉ፣ እረኛዬ ነዉ ፡፡  መጠጊያዬም ነዉ፡፡  መጥፎዉንና ክፉዉን አልፈራም መንግሥት አለልኝና” የሚል ዜጋ በሌለበት (ተቋማቱ ስለሌሉ) ተቋማቱም እንዲህ ዓይነት አቅምና ችሎታ አጥተዉ ባሉበት ወቅት   የአጣናና ሽመል ፖለቲካ ብቅ ሲል መጠጊያ የሚሆነዉ ብሔር ብቻ ነዉ፡፡ መራር ሐቅ ነዉ! ከእንደገና አመኔታ የሚጣልባቸዉ ተቋማትን ለመገንባትም ቢያንስ መቆሚያና መጠጊያ አስፈላጊ ሆኗል! የሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲሆን የሚጠበቀዉ የአዲስ አበባ መስተዳድር እንኳን አዲስ አበቤዎችን ጥግ እያስፈለገ መሆኑ ግልጽ ማሳያ ነዉ፡፡
(እነዚህን አቅም ያላቸዉ ለኢትዮጵያዉያን በጅምላዉ መመኪያና መጠጊያ የሚሆኑ ተቋማት መፍጠር የዘወትር ተግባር መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡)
Filed in: Amharic