>

የጎሳ ፌደራሊዝም (በቃሉ አጥናፉ ታዬ (ዶ/ር))

የጎሳ ፌደራሊዝም


በቃሉ አጥናፉ ታዬ(ዶ/ር)

ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ

 

ብዝሃነትን ለማስተናገድ እና ስልጣንን ወደ ታችኛው የመንግስት መዋቅር ለማከፋፈል የፌደራል ስርዓት ተመራጭ እንደሆነ እንዳንድ ፀሃፍት ቢያተቱም፤ በተቃራኒው ደግሞ የፌደራል ስርዓት በተፈጥሮዎ ግጭትን እንደሚጋብዝ እና ተመራጭ እንዳልሆነ የሚያትቱም ተመራማሪዎች አሉ(አለማንተ, 2003).

ብዝሃነትን ከማስተናገድ አንፃር እንዳንድ የአፍሪካ አገራት (ኮንጎ, ከ1960-1965፣ ማሊ, 1959፣ ኬንያ, 1963-1965፣ ዩጋንዳ, 1962-1966፣ ካሜሮን, 1961-1972) ከነጻነት በኃላ የፌደራል ስርዓት መርጠው መተግበር ቢጀምሩም አስከፊነቱን ተረድተው የፌደራል መዋቅርን ትተውታል(ኢርከ, 2014)፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሶስት የአፍሪካ አገራት(ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያ፣ እና ኢትዬጲያ) በፌደራል ስርዓት የሚተዳደሩ አገራት ቢሆኑም የጎሳ የፌደራል ስርዓት የምትተገብረው አገር በዓለም ላይ ኢትዬጲያ ብቻ ናት፡፡

ምንም እንኳን የፌደራል ስርዓት በዘርፉ ተመራማሪዎች ዘንድ አወዛጋቢ ቢሆንም የጎሳ የፌደራል ስርዓት ግን ግጭትን እንደሚፈጥር እና አገርን እንደሚበትን ከአወዛጋቢነት ባለፈ የተረጋገጠ ሃቅ ነው፡፡ የጎሳ ፌደራሊዝም እንደ ዩጎዝላቪያ፣ የድሮዋን ሩሲያ(USSR)፣ ችኮዝላቫኪያን በመበታተን የሚታወቅ ስርዓት ሲሆን በእኛ አገርም እንዲተገበር የተፈለገበት ዋናው ምክንያት አገሪቱን ለመበታተን ታስቦ ነው፡፡ እኛ እና እነሱ፣ ነባርና መጤ፣ አፈናቃይና ተፈናቃይ በሚል የጎሳ ፖለቲካ ትርክት ውስጥ እንድንገባ ያደረገን የጎሳ ፌደራሊዝም ነው፡፡ አገርን በቋንቋ ከፋፍሎ ወጣቱ ለአገሩ ሳይሆን ለብሄሩ ብቻ ታማኝ እንዲሆን ያደረገው የጎሳ ፌደራሊዝም ነው፡፡ ጥርጣሬን፣ አለመተማመንን፣ ለጎሪጥ መተያየትን ያመጣው የጎሳ ፌደራሊዝም ነው፡፡ አገርን ብቻ ሳይሆን ቤተሰብን (ባልና ሚስትን፣ አባትን ከልጁ፣ ልጆችን ከወላጆች) እንዲለያዩ ያደረገው የጎሳ ፌደራሊዝም ነው፡፡

የኢትዬጲያ የጎሳ ፌደራሊዝም መስራቾች እና አቀንቃኞች አገሪቱን ለመበታትን የተጠቀሙበት ስልት እንደሆነ እየታወቀ፤ ይህን የጎሳ ፌደራሊዝም ማፍረስ ሲገባን በዶ/ር አብይ አስተዳደርም የብሄር ፖለቲካው፣ አድሎዓዊነት፣ ጎጠኝነቱ፣ መታየቱ እጅጉን ልብን ይሰብራል፡፡ ህወሃት የተጠቀመበትን የከፋፍለህ ግዛው የጎሳ ፖለቲካ እንዴት እንደነፃነት ምልክት አድርገን እንጠቀምበታልን? ሰብዓዊነትን ተላብስን፣ ኢትዬጲያዊነት ተጫምትን መቆም ሲገባን እንዴት ለጎሳ አባላቶቻችን ያደረግንላቸውን ነገር እንደ ታላቅ ጀብድ በሚዲያ እንተርካልን? ኢትዬጲያዊነት ሱስ ነው ብሎ የተረከ መሪ እንዴት ብሄርተኝነትን ያራምዳል? ልብ ይስጠን!!!

Filed in: Amharic