>

አብይን የወደድኩት መንግሥታቸውን ጠልቼ ነው! (ደረጀ ደስታ)

አብይን የወደድኩት መንግሥታቸውን ጠልቼ ነው!
ደረጀ ደስታ
ፍሬ ነገሩ – 
…ግን ደግሞ ፣ “መንግሥት” የተባለ ተቋም ራሱ መደገፍ ያለበት ነገር ነው እንዴ? “መንግሥት” ከካድሬዎቹና ከሠራተኞቹ ውጭ በተቀረው ህዝብ እሚደገፍበት አገር በዓለም ላይ ይኖር ይሆን? በዚህ በዚህ ጉዳይ “የመንግሥትን አቋም እደግፋለሁ” ማለት ይቻል ይሆናል። መንግሥት በደፈናው የነካ የዳበሰውን ሁሉ እደግፋለሁ ብሎ አብዶና ሰግዶ እሚናገር ህዝብ ያለበት አገር የት ነው? እውነት ነው መንግሥት ሲበርድህ አንስተህ እምትለብሰው ወይም ሞቆኛል ብለህ ሲወብቅህ ወዲያ አውልቀህ ጥለህ እንደምታሽቀንጥረው ጃኬትም አይደለም። ተቋም ነው። ስታቆመውም ሆነ ስትንደው በሂደት ነው። ምክንያቱም እምታለብሰውና እምትገፈው ነገር ሰው ሳይሆን አገር ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በሌላው አገር፣ ያውም መንግሥታቸውን በዴሞክራሲያዊ መንገድ መርጠናል በሚሉበት አገር ሁሉ ሳይቀር፣ መንግሥትን በጥያቄና በተቃውሞ ማዋከብ የተለመደ ነው። እንደ ወስላታ ተቋም በተጠያቂነት ሳይንገረገብ ውሎ እሚያድር መንግሥት የለም። የመረጡት ሳይቀሩ “የመረጥንህ ለዚህ አይደለም!” ማለት የሚጀምሩት ገና በመረጡት ማግስት ነው። በህዝብ የተመረጡት የመንግሥት መሪዎች ሳይቀሩ፣ የራሳቸውን መንግሥት ሳይቀር ሲያወግዙና ሲከሱ ማየትም የተለመደ ነው።
 ዝርዝሩ ጽሁፍ
“እንዲህ ነው ወይ መውደድ እኔ ምን አውቄ…” ብሏል ዘፋኙ ። መሪ ወዶ መንግሥት መጥላት ይገርማል። የጠ/ሚ አብይ መንግሥት ግን ማነው? ወይስ መንግሥት የላቸውም? መቸም ጠ/ምኒስትሩን ብንጠይቃቸው፣ “የኢህአዴግ ሊቀመንበር መሆኔ፣ በጠ/ ሚኒስትርነትም የመረጠኝ ኢህአዴግ መሆኑ እየታወቀ ምን እሚሉት ጥያቄ ነው? ” ብለው የኢህአዴግን መንግሥትነት ሊመልሱልን ይችላሉ።  በለውጡ አንጀታቸውን ቅቤ ያጠጡ ሰዎች ደግሞ፣ ኢህአዴግ “መሞቱ”ን አምነው እስከማሳመን ርቀዋል። ኢህአዴግ ግን አንዴ እየደመቀ አንዴ እየለማ ግድየላችሁም አለሁ ብሎ ድምጹን እያሰማ ነው። ዶ/ር አብይም በሰሞኑ መግለጫቸው ድርጅቱ በህይወት መኖሩን ነግረውናል። ለነገሩ ቀድሞውንም ቢሆን ኢህአዴግ ሞቷል ብለውን አያውቁም። “በረከት” የሌለው ኢህአዴግ ምኑን በህይወት ኖረው? ብለው እሚሞግቱት እነበረከት ሰምዖን ካልሆኑ፣ ኢህአዴግ ተዳክሞም ይሁን ፈርጥሞ በአዲስ ማኔጅመንት ብቅ ብሏል።
ነገሩ ያልጣመው “እነ አብይን ብወድም ኢህአዴግን አልፈቅድም” እያለ ነው ። ቢሆንም ለነ አብይና ለእነለማ ስል ወይም አብይ ቀስ በቀስ ኢህዴግን እየለወጡ መንግሥታቸውን እኔ በተቀበልኩት መንግሥት ቀይረውልኝ…ከማልፈልገው መንግሥት ወደ ምፈልገው ሥርዓትና መንግሥት አሸጋግረውኝ… እያለ… ያኔ መንግሥትንም እደግፋለሁ እሚል ባለተስፋም ሞልቷል።
ግን ደግሞ ፣ “መንግሥት” የተባለ ተቋም ራሱ መደገፍ ያለበት ነገር ነው እንዴ? “መንግሥት” ከካድሬዎቹና ከሠራተኞቹ ውጭ በተቀረው ህዝብ እሚደገፍበት አገር በዓለም ላይ ይኖር ይሆን? በዚህ በዚህ ጉዳይ “የመንግሥትን አቋም እደግፋለሁ” ማለት ይቻል ይሆናል። መንግሥት በደፈናው የነካ የዳበሰውን ሁሉ እደግፋለሁ ብሎ አብዶና ሰግዶ እሚናገር ህዝብ ያለበት አገር የት ነው? እውነት ነው መንግሥት ሲበርድህ አንስተህ እምትለብሰው ወይም ሞቆኛል ብለህ ሲወብቅህ ወዲያ አውልቀህ ጥለህ እንደምታሽቀንጥረው ጃኬትም አይደለም። ተቋም ነው። ስታቆመውም ሆነ ስትንደው በሂደት ነው። ምክንያቱም እምታለብሰውና እምትገፈው ነገር ሰው ሳይሆን አገር ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በሌላው አገር፣ ያውም መንግሥታቸውን በዴሞክራሲያዊ መንገድ መርጠናል በሚሉበት አገር ሁሉ ሳይቀር፣ መንግሥትን በጥያቄና በተቃውሞ ማዋከብ የተለመደ ነው። እንደ ወስላታ ተቋም በተጠያቂነት ሳይንገረገብ ውሎ እሚያድር መንግሥት የለም። የመረጡት ሳይቀሩ “የመረጥንህ ለዚህ አይደለም!” ማለት የሚጀምሩት ገና በመረጡት ማግስት ነው። እንደ አሜሪካ ባሉ አገራት፣ በህዝብ የተመረጡት የመንግሥት መሪዎች ሳይቀሩ፣ የራሳቸውን መንግሥት ሳይቀር ሲያወግዙና ሲከሱ ማየት የተለመደ ነው።
ፕሬዘደንቶች እንኳ የገዛ መንግስታቸውን ይቃወማሉ። የኮንግረስ አባላት ለመንግሥት አይተኙም። ዋሽንግተኖችንም ሁል ጊዜ ዋሽንግተኖችን (መንግስታቸውን) እንደተቃወሙ ነው። እኔን ብትመርጡ ዋሽንግተንን እቀይራለሁ ማለት የተለመደ ነው። “እኔን ብትመርጡ ዋሽንግተን ሄጄ፣ ለኋይት ሓውስ ሰግጄ፣ እጅ እነሳለሁ!” እሚል የፖለቲካ ሰው ግን ተሰምቶ አይታወቅም።  ስለዚህ ይህ ማለት መንግሥትን እየተቃወሙ አገር መምራት ይቻላል ማለት ይሆን? ወይስ መንግሥትን እየተቃወሙ መንግሥት መሆን ወይም ተቃዋሚ መንግሥት መስሎ መታየት ዘመናዊው ፖለቲካ ይሆን? ወይስ ጮሌነት? ይህ ዘመናዊ ፖለቲካ እሚያምርበት ግን የመንግሥት ሥልጣን ክፍፍልና የኃይል ሚዛንን ሲጠበቅ ነው። መንግሥታት እንደሥላሴ “አንድም ሶስትም” ሆነው የህግ አውጭ ፣ህግ አስፈጻሚና ህግ ተርጓሚ ተቋማት ተለያይተው በነጻነት የቆሙበት ሥርዓት አላቸው። አንዱ ተቋም (መንግሥት) ሌላውን ተቋም (መንግሥት) ሊቆጣጣረው ዘንድ ሥራው ነውና አስፈጻሚው እየወቀሰ ያሳጣዋል፣ ህግ አውጪው እየጠራ ያፋጥጠዋል፣ ህግ ተርጓሚው ህገመንግስቱን ጥሰሃል ብሎ ይዳኘዋል። እንኳን በተለያዩ የመንግሥት አውታርና ቅርንጫፎች ቀርቶ በአንድ የመንግሥት ዘርፍም ሆነ ቢሮክራሲው ውስጥ ያሉት ሳይቀሩ ሚኒስትሮቻቸውን እየተቃወሙ ይሄ ጉዳይ የመንግሥትን እንጂ የህዝብን ጥቅም እሚያስጠብቅ አይደለም እያሉ ሲከሱ ይታያሉ። መንግሥት ማንም እንደፈለገ መጨፈር በማይችልበት ተጠያቂነትና ኃላፊነት ተዋቅሯል። መንግሥት ህዝብን ከፋፍሎ መግዛት ስለሚፈልግ አይታመንም። እዚህ ግን እሱም ራሱ ለህዝብ ሥልጣን ሲባል ተከፋፍሎና ተዳክሞ የተዋቀረበት ህገመንግሥታዊ ሥርዓት አለ። ያ ባለበት ሁኔታ መንግሥት ሆኖ መንግሥትን መቃወም ያስኬድ ይሆናል።
ተቋማት ተለይተው፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ተመስርተው፣ የህግ የበላይነት ተክብሮ ሥልጣን ተመጥኖ ፣ተቆጥሮና ተዘርዝሮ ባልተከፋፈለበት ሁኔታ፣ አንድ መንግሥት፣ አንድ ፓርቲ፣ አንድ መሪ ብቻ ያለገደብ ከዋኘበት፣ ውሎ አድሮ ውጤቱ ጥሩ አይሆንም። ያለው ምርጫ አስተዳደርና መንግሥቱን ከመቃወም ፣ ወይም ህዝብን ለሥልጣን እሚያበቃ ሥርዓትን በፍጥነት እንዲመጣ ከመጎትጎት ውጭ፣ “መሪዎቹ ተስማምተውኛል ሥርዓትና ድርጅታቸው ግን አይምጣብኝ” እያሉ መደገፉ የአስተዋይ ሰው ምርጫ አይመስልም። ኢህአዴግ ወይም ህገመንግስታዊ መንግሥቴን አትንኩብኝ ጠ/ሚ አብይን ግን አንሱልኝ ማለትም ይሉኝታ ማጣት ነው።
የግለሰቦችም ሆነ የድርጅቶች ራዕይ መጥፎ ነገር አይደለም። የገዛ ራዕይን የአገር ራዕይ አድርጎ መነሳትም ወንጀል አይሆንም፡፡ እጅግ አስፈላጊና አገር እሚያሳድግ ቀና ነገር ነው። ግን ራዕዩ እሚፈጸምበት መንገድ ስህተት ሊሆን ይችላል። ወይም ከሌላ ራዕይ ጋር ተወዳደሮ አሸንፎ መመረጥ ይኖርበታል። ሀሳብህ ቀና ነው ከአንተ የተሻለ ሌላ ሀሳብ ግን ሊኖር ይችላል ማለት ሥልጡንነት ነው። ለአገርም ቢሆን እጅግ አስፈላጊ ሥርዓት ነው። እሱን ዓይነት ሥርዓት መደገፍ ይገባል። አንድ ለናቱ መንግሥትን በደፈናው ትደግፋለህ ወይስ ትነቅፋለህ? መባሉ ግን ደስ አይልም። መሪዎች እንደሁኔታው ይወደዳሉ። በቃ እሱ የነካው ሁሉ ይስማማኛል ማለት ይቻል ይሆናል። ምክንያቱም መሪዎች ሲናገሩ ተስፋ ይሰጣሉ፣ ምኞት ያጠግባሉ የመንግሥታቸው መንግሥተ ሰማያት መቅረቧን ይሰብካሉ። የዚያኑ ያክልም ውለው አድረው ወደ ገሀነመ እሳት መጣል መኖሩንም ማስጠንቀቅ ይጀምራሉ። ያኔ ሰውነታቸው ቀርቶ ራሳቸውም መንግሥት መሆን ይጀምራሉ።
መንግሥት ደግሞ እሚያዘው ሠራተኛም ሆነ ካድሬ አለው። መንግሥት ጠመንጃ አለው፣ ገንዘብ አለው፣ ሥልጣን አለው። ሚዲያ፣ ተከታይና አልፎ ተርፎም አትንኩብኝ ባይ መንጋ አለው። ይህ መንጋ እዚያም እዚያም እየተንጋጋ አገርን በሆያሆዬ ከማጫናነቅ፣ሲቆጣም ነፍስን እንደልብስ ከማውለቅ ወደኋላ አይልም። ጋዜጠኞች፣ ዳኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ተንታኞች፣ በአጠቃላይ ሚዛን እንጠብቃለን ባይ ወገኖች የመንግሥት ሰለባ ከመሆናቸው በፊት መንግስታቱ የዚህን መንጋ ቡራኬ ማገኝታቸው የተለመደ ነው። መንጋው ከማህበር እሚነጥል፣ ስቀልልኝ ቀይ ሽብርን አፋፋምልኝ፣ ለፍርድም ሆነ ለእርድ አቅርብልኝ እያለ እሚማጸን፣ ቂመኛና አድመኛ ነው፡፡ መንግሥትም እንደ አክቲቪስቱ ቃሉን በጥሬው አምኖ እሚንጋጋለትን ሁሉ በጣም ይፈልገዋል። አንደኛው የሥልጣኑ መሠረትም ይህ ነው።
መንግሥትነት ተቋም ብቻ አይደለም ባህርይም ነው። መንግሥት የፖለቲካ ድርጅትና አክቲቪስቶች አንድ ናቸው ማለት ባይቻልም ሥልጣን አያመሳስላቸውም ማለት አይደለም። ሁሉም በየተከታዮቻቸው ላይ ያልተገደበ ሥልጣን አላቸው። ሥልጣን ቁንጣን ሲሆን ያጠግባል። ያ እንዳይሆን ሥልጣናቸው፣ መንግሥት ሲሆን በህዝብ፣ የፖለቲካ ድርጅት ሲሆኑ ደግሞ በአባሎቻቸው፣ አክቲቪስትም ሲሆኑ በተከተያዮቻቸው ተመጥኖና ተገድቦ ካልተሰጣቸው አደገኞች ናቸው። “የቤት አመል ገበያ ይወጣል” እንደሚባለው የድርጅት አመል የአገር ይሆናል። ድርጅቱና ደጋፊው ቆንጥጦ ያላሳደገው መሪ አገር የመምራት ሥልጣን ሲያገኝ አገር በሙሉ ድርጅት ይመስለዋል። ደጋፊዎቹን ሳይሆን ነቃፊዎቹን ሳይቀር ጨምሮና ደምሮ እንዲያስተዳድር የተመረጠ አይመስለውም። ደጋፊዎቹና መንጋዎቹም እነሱ ስለደገፉት ብቻ አገር እንዲደግፈው ከማስገደድ አይመለሱም። ዴሞክራሲ ደግሞ እንደሱ አይሠራም። ዴሞክራሲ ጥቂቱ ብዙሃኑን ፣ብዙሃኑ ጥቂቱን ረግጦ እሚገዛበት ሥርዓት ሳይሆን የበዛውና ያነሰው ሳይለይ፣ ሁሉም እኩል እሚተዳደርበት ሥርዓት ማለት ነው። እንኳን ምርጫ ሳይኖር ምርጫም ቢኖር አገር በድምጽ ብልጫና እርግጫ ብቻ አትተዳደርም። አገር እምታድረው ሁሉንም ተረድቶ በብልሃት በእኩልነትና በህግ ማሳደር እሚችል ሥርዓት ሲኖር ነው። ወይንም ያን ሥርዓት ለመገንባት የቆረጠ መንግሥት ሲመጣ የተስፋው ቃል ይፈጸማል። በእኔና በናንተ መካከል ይቅር እንጂ ያ መንግሥት ግን በፍጹም ኢህአዴግ ሊሆን አይችልም። ታዲያ ማነው?
ማንም ይሁን ማን፣ መንግሥት ያው መንግሥት ነው። ካልተቆጣጠሩት ቀሳፊ፣ ቀጣፊና ዘራፊ ነው። ህዝብን ከፋፍሎ መግዛት ታሪኩ ነው። ህዝብም በአንጻሩ መንግሥትን በተቋም ከፋፍሎና አዳክሞ እሚያዋቅርበት ህገመንግስትና ዴሞክራሲያ ሥርዓት ቢያቆም ይበጀዋል። ኢህአዴግ እንኳ በመከፋፈሉ የተገኘችውን ቀዳዳ ማስታወስ ነው። ስለዚህ ወዳጄ ሆይ! ደጋፊ ነቃፊ ተነጣፊ.. ነኝ ከማለትህ በፊት መንግሥት ምንድነው? ፍላጎቱና ሥልጣኑስ እስከምን ይሄዳል? ድጋፍና ተቃውሞስ ሲባል ምንድነው? ዴሞክራሲስ..? እያልክ ቆም ብለህ ማሰብ ያሻህ ቀን ከእያንዳንዷ ቃል ሳይቀር መላፋት ያምርሃል። ቃል ስትጨምቅ ሀሳብ ታንጠፈጥፋለህ። እምነት ታጠራለህ፣ አቋም ታስረግጣለህ። ከአቋምህ ጋር ግን አትቆርብም። እንደየሁኔታው ታስታርቀዋለህ። ተከራክሮ እሚረታህ አስተምሮህ እሚፈታህ ሲገኝ ከታሰርክበት ስህተት ወጥተህ ወደቀናውና ትክክለኛው ታቀናለህ። ጊዜ አንስቶ ጊዜ ከሚጥለው ሀሳብና መንግሥት ጋር ወድቀህ ሳትነሳ ዘመን በማይሽረው ነጻነትህ ጸንተህ፣ ሐቅህን ትይዝና ጊዜውን በሀሳብህ ትሞግተዋለህ እንጂ ተያይዘህም አታልፍም። ስለሆነም ጠመንጃህን ትተህ ሀሳብህን አቀባብለው። መፍትሄ አጉርሰህ ችግርህ ላይ ተኩስ፡፡ ህዝብ ሆኖ ያነጣጠረ ዒላማውን አይስትም፡፡ መንግሥትም የሱ ትሆናለች! አንተ የመንግሥት ከምትሆን መንግሥት ያንተ ቢሆን አይሻልህም?
(አብይ ወደ ሥልጣን የመጡ ሰሞን የተጻፈች ጽሑፍ ናት ትንሽ ተቀባብታለች)
Filed in: Amharic