>
11:45 am - Wednesday November 30, 2022

የአዲስ አበባ ሥጋት! (በፍቃዱ ዘሃይሉ)

የአዲስ አበባ ሥጋት!
 በፍቃዱ ዘሃይሉ
ያደግኩበት ሰፈር ለአረንጓዴ ልማት ከሚፈርሱት የአዲስ አበባ መንደሮች አንዱ ነው። የሰፈሬን ሰዎች በዚህ ወቅት ከዚህ በላይ የሚያሳስባቸው ነገር የለም። «የት ነው የምንሔደው?»፣ «ተመጣጣኝ ካሳ ይሰጠን ይሆን?»፣ ብዙዎቹ ግቢያቸው ውስጥ የሚከራዩ ቤቶችን ሠርተው በኪራዩ ሥለሚተዳደሩ «የገቢ ምንጫችን ይደርቅ ይሆን?» የሚል ሥጋትም አላቸው።
         ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ለልማት የፈረሱ መንደር ነዋሪዎች ጠንካራ ማኅበራዊ ግንኙነታቸው (ዕድር፣ ዕቁብ እና ወዘተ.) ፈርሶ የተለያየ ቦታ መበተናቸው ዋነኛ ብሶታቸው ነበር። ከዚህም በላይ ከመሐል ከተማ ተወስደው ገና መንገድ፣ ውሃ እና የኤሌክትሪክ አቅርቦትን የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች ያልተሟሉበት አካባቢ እንዲሰፍሩ ተደርገዋል። ስለሆነም የሰፈሬ ሰዎች ሥጋት ውስጥ መግባታቸው አያስገርምም።
     አዲስ አበባ ዓመታዊ የሕዝብ ብዛት ዕድገቷ በወሊድ ከሚወሰነው በላይ ከገጠር ወደ ከተማ በሚደረግ ፍልሰት እንደሚበየን ጥናቶች ያሳያሉ። ከተማዋ ነዋሪዎችን ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚውንም የምትስብበት መግነጢስ አላት።
    በአጭሩ የኢትዮጵያ የፖለቲካም ይሁን የኢኮኖሚ ማዕከል ናት። ይሁን እንጂ የመኖሪያ ቤት እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ነዋሪዎቹን እያንገላታቸው ነው። የቀድሞ የቤቶች ልማት ኀላፊ በአንድ ወቅት የመኖሪያ ቤት እጥረቱ ጉዳይ በዕድሜያቸው ተፈትቶ እንደማያዩ ተናግረው ነበር። ቀደምት መንደሮች በልማት ምክንያት መነሳታቸውና ወደ ዳርቻ መገፋታቸው እንዲሁም ከፍተኛ የአገር ውስጥ ፍልሰት አስተናጋጅ በመሆኗ የሕዝብ ቁጥሯ በፍጥነት ማደጉ አዲስ አበባን እንድትለጠጥ አስገድዷታል።
     የአዲስ አበባ መለጠጥ ለከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ መንሥኤ ሆኗል። ምንም እንኳን ሌሎች የታመቁ የፖለቲካ ጥያቄዎች ቢኖሩም፥ በ2008 የተፋፋመው እና ኦሮሚያ ክልልን ያዳረሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ “አዲስ አበባ እንድትስፋፋ ይፈቅዳል” የተባለው አዲስ አበባን እና በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖችን የሚያስተሳስረው ‘ማስተር ፕላን’ መተዋወቅን ተከትሎ ነው።  ተቃውሞዎቹ ተፅዕኖ ፈጥረው የፖለቲካ ለውጥ አምጥተዋል ከተባሉም በኋላም ዉዝግቡ አልቆሙም።
     የኦሮሞ ብሔርተኛ ፖለቲከኞች አዲስ አበባ (በነርሱ አጠራር ፊንፊኔ) የኦሮሚያ ክልል ታሪካዊ ርስት በመሆኗ አስተዳደሯም ቢሆን በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ አስተዳደሮች ሥር መሆን አለበት የሚል መከራከሪያ አላቸው። ከዚህ ውጪ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 49/5 ላይ የተቀመጠው “ልዩ ጥቅም” ምንጭም ይኸው ታሪካዊ ባለቤትነት ነው የሚሉ እና ራሱ ሕገ መንግሥቱ እንደሚለው “አስተሳሳሪ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች” ብቻ ናቸው የሚሉ የማያቋርጡ ክርክሮች አሉ።
      በነዚህ ክርክሮች ውስጥ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተሳትፎ እጅግ በጣም ትንሽ መሆኑ ነዋሪዎቹን ያልተወከሉ የከተማቸው ባይተዋሮች እንደሆኑ ዓይነት ስሜት እንዲሰማቸው አድርጓል።
አዲስ አበባ የለውጡን መሪዎች አኩርፋለች?
ራሳቸውን ዘውግ-ዘለል (post-ethnic) አድርገው የሚመለከቱት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሹመት በከፍተኛ ተስፋ ነበር የተቀበሉት።
      በሕዝባዊ አመፆቹ ዓመታት ወቅት ከፍተኛ ድብታ ውስጥ ገብታ የነበረችው ከተማ መነቃቃት ውስጥ የገባቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ነው። ይሁንና አዲስ አበባ ከዚያ በፊት የነበሩትን ተቃውሞዎች አልተቀላቀለችም። ይህም የሆነበት ምክንያት በአንድ በኩል ተቃውሞው በከተማዋ መሥፋፋት ላይ የተመሠረተ ከመሆኑም ባሻገር፣ ስልቶቹም ወደ ከተማዋ የሚያስገቡ፣ ወይም ከከተማዋ የሚያስወጡ መንገዶችን በመዝጋት ኢኮኖሚዋን በማናጋት ላይ የተመሠረተ ስለነበር ይመስላል።
    ስለዚህ ተቃውሞዎቹን አስቁሞ መረጋጋት እንደሚያመጣ ተስፋ የተጣለበትን የፖለቲካ ለውጥ አዲስ አበባ በይሁንታ መቀበሏ የሚያስገርም አልነበረም። ይሁን እንጂ ይህ ወዳጅነታቸው ለረዢም ጊዜ በመተማመን አልቀጠለም፤ በጥርጣሬ ወጀብ እየተመታ አሁን መኮራረፍ ደረጃ ደርሰዋል ማለት ይቻላል።
   የመጀመሪያው ጥርጣሬ የተጫረው የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ታከለ ሲሾሙ ነው። ታከለ ዑማ እንደ ተሾሙ “የምክር ቤቱ አባል ሳይሆኑ በሕግ ማስተካከያ ለምን ተሾሙ?” የሚለው የመጀመሪያው የጥርጣሬ መንሥኤ ሆኖ ነበር። ከዚያም በቡራዩ የደረሰው ጥቃት እና መፈናቀል በአዲስ አበባ ተቃውሞ የቀሰቀሰ ሲሆን፥ ከለውጡ በኋላ ሰዎች በመንግሥት የፀጥታ ኀይል የተገደሉበት አጋጣሚ ስለነበር “ለአዲስ አበባ ሰው ተቆርቋሪ የለውም” የሚል ቅሬታ አስከትሎ ነበር። ይባስ ብሎ እስካሁንም ድረስ በቂ ማብራሪያ ያልተሰጠበት አፈሳ በከተማዋ መደረጉ እና የታፈሱትም “የብሬይንወሺንግ” ሥልጠና በወታደራዊ ካምፖች እንዲወስዱ ከሕግ አግባብ ውጪ መገደዳቸው ብዙዎችን ቂም እንዲቋጥሩ አድርጓል።
      ይህ በእንዲህ እንዳለ የከተማዋ ነዋሪዎች የቤት ባለቤት ትሆናላችሁ ተብለው የቆጠቡለት የኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም ዕጣ መውጣት ተከትሎ በኦሮሞ ብሔርተኛ ፖለቲከኞች ከፍተኛ ተቃውሞ መደረጉ ለነዋሪዎቹ አስደንጋጭ ነበር። የዕጣው ባለ ዕድሎች ሥም ዝርዝር ኅትመትም በአዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት መታተም ከጀመረ በኋላ እንዲቋረጥ ተደርጓል። እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት ኦዴፓ የዕጣውን መውጣት በመቃወም መግለጫ ማውጣታቸው እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የኦሮሚያ ፕሬዚደንት “የከተሞችን ዴሞግራፊ ስለመቀየር” ያወሩበት ቪዲዮ መዘዋወሩ በከተማዋ ነዋሪዎች እና በለውጡ መሪዎች መካከል መቃቃርን አስከትሎ አሁን ለደረሱበት ኩርፊያ ሊባል የሚችል ደረጃ ዳርጓቸዋል።
ምን ይሻላል?
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያሉ ችግሮች ሕጋዊ፣ ፖለቲካዊ እና ታሪካዊ መሠረቶች ያሏቸው ናቸው። ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ ለመፍታት አስቸጋሪ የሚሆኑት አመራሮቹ በነዋሪዎች ዘንድ ሕዝባዊ ቅቡልነት ስለማይኖራቸው ነው። የአዲስ አበባ ችግርም ከዚህ የተለየ አይደለም። አሁን ያለው የአዲስ አበባ ምክር ቤት እምብዛም ተቀባይነት በሌለው ምርጫ በ2005 የተሰየመ ነበር። አምና ለዘንድሮ የተራዘመው የምክር ቤት አባላቱ ምርጫም ዘንድሮ የሚካሔድ አይመስልም። ይሁን እንጂ ነጻ እና ርትዓዊ ምርጫ ቢያንስ ችግሩን ለመፍታት የሚሠሩት ሰዎች በሕዝብ የተወከሉ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፤ እናም ብቸኛው እና አዋጩ መፍትሔ ይኸው ነው።
Filed in: Amharic