>
5:13 pm - Thursday April 19, 2159

የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ አመራር አንድ ዓመት ዝክር!!! (ዶ/ር ታደሰ ብሩ)

የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ አመራር አንድ ዓመት ዝክር!!!
ዶ/ር ታደሰ ብሩ
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ሥልጣን ላይ ከወጡ አንድ ዓመት ሞላቸው።  ከዚህ ጊዜ ውስጥ ምን መልካም ነገሮች ተሠሩ፤ ምንስ ችግሮች ገጠሙን። 
መልካም ነገሮች 
1. ለኔ ትልቁ ለውጥ የአስተሳሰብ ለውጥ ነው።  “ቃላት ዓለሞችን ይፈጥራሉ“ (Words create worlds) በሚለው አባባል ውስጥ እውነት አለ  ብዬ  አምናለሁ። የአስተሳሰብ ለውጥ ያደረገ  ሰው ተግባራቱ መቀየራቸው የማይቀር ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ማኅተማ ጋንዲ ረዘም ያለ  ጥቅስ አላቸው “Keep your thoughts positive because your thoughts become your words. Keep your words positive because your words become your behavior. Keep your behavior positive because your behavior becomes your habits. Keep your habits positive because your habits become your values. Keep your values positive because your values become your destiny.” ባለፈው ዓመት ያገኘው ትልቁ ነገር የአስተሳሰብ ለውጥ ያደረጉ የለውጥ መሪዎች መገኘት ነው ብዬ አምናለሁ።
2. የነፃነት አድማስ ሰፍቷል።  መንግሥት የፓለቲካ ፓርቲዎችንና  ሚዲያ ማፈኑን ትቷል።ፓርቲዎችና የሚዲያ ተቋማት በነፃነት ይንቀሳቀሳሉ። አጠቃቀሙን አለማወቃችን ግን እየጎዳን ነው። የሚዲያ ነፃነት ያለ ቢሆን ያ ነፃነት እውቀትና እውነትን እየመገበን ስለመሆኑ ከፍተኛ ጥርጣሬ አለኝ።
3. በፌደራል ተቋማት ላይ ለውጥ እየተደረገ ነው። መከላከያ፣ የደህንነቱ መሥሪያ ቤት፣ ፌደራል ፓሊስ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ምርጫ ቦርድ ውስጥ ለውጥ እየተደረገ ነው።  በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደረገውም ለውጥ የሚበረታታ ነው። የሰላም ሚኒስትር መቋቋሙ እጅግ የሚበረታታ ነው።  የሴቶች በከፍተኛ የስልጣን እርከኖች መውጣት፤ በርካታ ሙስሊም እህቶችና ወንድሞች በከፍተኛ የስልጣን እርከኖች ላይ መመደባቸው በጣም የሚያበረታታ ጉዳይ ነው።
4. ህግጋት እየተቀየሩ ነው። መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚተዳደሩበት ህግ ተቀይሯል። የፀረ-ሽብር፣ የሚዲያ፣  የምርጫ፣ የፓርቲዎች ህግጋት ላይ ክለሳ  እየተደረገባቸው ነው።  የህገመግሥት ማሻሻያን የሚያጠና ቡድን መቋቋሙ ተነግሯል።  አፋኝ ህግጋት ገና ያልተሻሩ ቢሆንም እንኳን ሥራ ላይ ሲውሉ አይታይም፤ የሚሻሻሉ የመሆናቸው ተስፋም ይታያል።
5. የሰላምና የእርቅ እንዲሁም በማንነነትና  በወሰን ጉዳዮች የሚነሱ ግጭቶችን በተመለከተ ጥናት የሚያደርጉ ሰፊ የሕዝብ ተሳትፎ  ያለባቸው ኮሚሽኖች ተቋቁመዋል። የመንግሥት ንብረትን ወደ ግል በማሸጋገሩ  ሂደትም የሕዝብ ተሳትፎ እንዲጨምር ተደርጓል። በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የለውጥ አመራር ሕዝብን ለማሳተፍ የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው።
እነዚህን ለውጦች ላሳዩን የለውጥ አመራር በበኩሌ ከፍተኛ አክብሮት አለኝ።
ተግዳሮቶች
1. የሀገር ውስጥ ሰላም ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። መፈናቀል እንደቀጠለ ነው፤ በየቦታው ግጭቾች አሉ።  ሰዎች ተዘዋወረው መኖር አለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን ለዘመናት ከኖሩበትም ቦታ “ይህ አገራችሁ  አይደለም፤ ልቀቁ” መባላቸው ቀጥሏል። ወንጀሎች ተበራክተዋል፤ ሕግና ሥርዓት የማስጠበቅ ሥራዎች ተዳክመዋል።
2. ፓለቲካችን ሁሉን አሳታፊ ከመሆን ይልቅ አካባቢና ብሔር ተኮር ሆኗል። ቀበሌዎች ወረዳ፤ ወረዳዎች ዞን፤ ዞኖች ክልል፤ ክልሎች አገር መሆን ያምራቸዋል። ሁሉም “ተጠቃሁ፤ ተበደልኩ” የሚል በመሆኑ ፓለቲካችን የብሶት ፓለቲካ ሆኗል።  ይህን የብሶት ፓለቲካ የተቀላቀሉ አዳዲስ አዳዲሶቹ ድርጅቶች ከቀድሞዎቹ ይልቅ ብሶተኞች ሆነዋል። የብሶት ፓለቲካ ወዳጅን ከማብዛት ይልቅ ጠላት ማብዛትን የስኬት መገለጫው ማድረግ ቀጥሏል።
3. በፊደራል መንግሥትና በክልል መንግሥታት መካከል ያለው መናበብ ላልቷል። ክልሎች የራሳቸው ጡንቻ እያጠነከሩ የፊደራሉን መንግሥት መገዳደር ጀምረዋል። ብዙዎቹ የክልል መንግሥታት መደበኛ የመከላከያ ሠራዊትን የሚያስንቅ የጦር ኃይል “ልዩ ኃይል” እና “ሚሊሻ” በሚል ስያሜ  አደራጅተዋል፤ የራሳቸው የስለላ መዋቅርም ዘርግተዋል። የየራሳቸው ሚዲያም አደራጅተዋል። የክልል ታጣቂዎች በአካባቢና ብሔር ተኮር ፓለቲካ ተጽዕኖ ስር እየሆኑ ነው።
4. በሁሉም ክልሎች ያሉ ወጣቶች የለውጡ ባለቤት መሆን አልቻሉም። የኢትዮጵያ ወጣቶች አምባገነን ሥርዓትን ለማፍረስ ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል፤ በተቀየረው አዲስ አስተሳሰብ የተቃኘ  አዲስ ስትራቴጂና አደረጃጀት ሊይዙ ሲገባ እስካሁን ይህ አልሆነም። አምባገነን አገዛዛዝን ማዳከም ትልቅ ሥራ  ነው፤ የኢትዮጵያ ወጣቶች ይህን በብቃት ተወጥተዋል። በአባገነን ሥርዓት ምትክ ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ደግሞ ከበፊተኛው የበለጠ ትልቅ ሥራ ነው። ይህን በግንባር ቀደም የወጣቱ ኃላፊነት ነው። መንግሥት (የሰላም፣ የወጣቶች፣ የትምህርት፣ የከፍተኛ ትምህርት ጉዳዮች ሚኒስትሮች በጋራ) ከዜጎች ጋር በመተባበር ወጣቶችን በንቃት ማሳተፍ የሚቻልባቸው መንገዶች መሻት ይገባል።
5. ቀድሞ የመሪ ችግር የነበረባት አገር ዛሬ የተከታዮች ችግር ገጥሟታል። በዞኖችና በወረዳዎች የሚገኙ ከሕዝብ ጋር የዕለት ተዕለት ግኑኝነት ያላቸው ባለስልጣናት የመሪያቸውን ርዕይ የሚጋሩ አይመስሉም። መሪ የተከታዮች ውጤት ነው። ጠንካራ ተከታዮች የሌሉት መሪ ውጤታማ  መሆን ይቸግረዋል።
 
የመፍትሄ ሀሳቦች 
1. ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት የለውጡ ግቦች ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ብልጽግና፣ ብሔራዊ አንድነት፣ ፍትሕና እና  ብሔራዊ ኩራት መሆናቸው ገልፀው ነበር። ይህ በዝርዝርና ተደጋግሞ መብራራት አለበት። እነዚህ በርግጥ ያጣናቸው፤ እጅግ የሚያስፈልጉ ማኅበራዊ ሀብቶችም እሴቶችም ናቸው።  የመንግሥት አካላት ትኩረት ሰጥተው እነዚህን እሴቶች መስበክ መቀጠል አለባቸው። በእነዚህ እሴቶች ላይ የጋራ አስተሳሰብ ከተያዘ ሌላው ሁሉ ቀላል ነው የሚል እምነት አለኝ።
2. መፈናቀልና ስደትን ማስቆም (ያም ባይቻል በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ) ይገባል። የተፈናቀሉት ተመልሰው እንዲቋቋሙ የተቻለው ሁሉ ጥረት ሊደረግ ይገባል። ለሕዝብ መፈናቀልና ለእርስ በርስ ግጭቶች ተጠያቂ የሆኑ ሹመኖችም ይሁኑ ሌሎች ዜጎች ለፍርድ መቅረብ ይኖርባቸዋል።
3. በፈደራል መንግሥት ደረጃ ላይ ብቻ የሚደረግ  ለውጥ ውጤቱ እምብዛም ነው። ለውጡም በክልሎች እስከ ወረዳና ቀበሌዎች ማውረድ ይገባል።  በቀበሌዎች ደረጃም የለውጥ ኃይሎች ለውጡን የማስቀጠል ኃላፊነት ሊሰጣቸው ይገባል። “የለውጡ ባለቤት ሕዝብ ነው” የሚለው አባባል በአደረጃጀት የሚገለፀው እንዴት ነው ብሎ ማሰብና መተግበር ይገባል።
4. በፌደራልና በክልል መንግሥታት መካከል ያለው መናበብ እንደገና መጤን አለበት።  የፌደራል መንግሥት ብቻውን አገር አይሆንም፤ ክልሎችም ብቻቸውን አገር አይሆኑም።  የፌደራል መንግሥት ህግን የማስከበር ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል። የሕዝብ ተወካይ ምክር ቤት አባላት ከሕዝብ ጋር ወርደው መነገር መጀመር አለባቸው።
5. የወጣቶች ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። ኢትዮጵያ የወጣቶች አገር ናት።  የኢትዮጵያ ወጣት ለጠቅላዩ ሚኒስትሩ ስድስት ትላልቅ ግቦች  (ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ብልጽግና፣ ብሔራዊ አንድነት፣ ፍትሕና እና  ብሔራዊ ኩራት) መሳካት እንዲታገል ሁኔታዎች መመቻቸት ይኖርባቸዋል።  በተለይ ብልጽግና፣ ብሔራዊ አንድነትና ብሔራዊ ኩራት ወጣቱን የሚያነቃቁ ግቦች ማድረግ ይቻላል።
Filed in: Amharic