>
5:13 pm - Saturday April 19, 0014

የምጣዱ እያለ የእንቅቡን፤ የእርስ በርስ ግጭት እና የመንግስት ምላሽ!?! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የምጣዱ እያለ የእንቅቡን፤ የእርስ በርስ ግጭት እና የመንግስት ምላሽ!?!
ያሬድ ሀይለማርያም
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም ግጭቶች መበራከታቸው እና መፈናቀል መቀጠሉ የአገራችንን ፖለቲካ አሳሳቢ እያደረገው እና አገሪቱንም ወደ ችግር ውስጥ እየከተታት ይመስላል። መንግስት ለችግሮቹ የሚሰጠው ትኩረት እና ፈጣን ምላሽ እንዲሁ አጠያያቂ እየሆነ ነው። በብዙዎቹ አካባቢዎች ግጭቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ቅድመ ምልክቶች እየታዩ አፋጣኝ እርምጃ ሲወሰድ አይስተዋልም። ከዛም አልፎ ግጭቶቹ ተከስተው ሰዎች ከሞቱ፣ በሺዎች ከተፈናቀሉ እና ወደ ለየለት ቀውስ ካመራ በኋላ ነው የፌደራል መንግስቱ ጣልቃ ገብቶ እርምጃ ሲወስድ የሚስተዋለው።
በአብዛኛዎቹ ግጭቶችም የመንግስት ባለሥልጣናት በአንድ ጉዳይ ላይ እርስ በርሱ የሚጣረስ መግለጫ ሲሰጡ መስማት የተለመደ ሆኗል። ከዛ ይልቅ ከመንደር ካድሬ እስከ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ድረስ ለግጭቶቹ መስፋፋት ማህበራዊ ድህረ ገጽ ትልቁን ድርሻ እንደተጫወተ ሲናገሩ እና በመገላጫ ሲጠቅሱ ማየት ሌላው አስገራሚው ጉዳይ ነው። አገሪቱ ጽንፍ በያዙና ጠርዝ በረገጡ፣ አፍንጫቸው ድረስ በታጠቁ አክራሪ ቡድኖች እየታመሰች እውነታውን እዛው መጋፈጥ ሲገባ ችግሩን ከማህበረ ድረገጾች ጋር ማያያዝ በፍጹም አግባብነት የሌለው፣ የራስን ኃላፊነት ካለመወጣት የሚመጣውን ተጠያቂነት ወደጎን የተወ እና የአፈና ዳርዳርታ ነው።
በመጀመሪያ ደረጃ የትኛው የኢንተርነት አገልግሎት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን ያህል ለግጭት በሚዳርግ ደረጃ ለቅስቀሳ የዋለው? እንኳን ግጭቶቹ በተቀሰቀሰባቸው ገጠራማ የአገሪቱ ክፍሎች አይደለም በመሃል አዲስ አበባ እንኳ ያለው የኢንተርኔት ሽፋን ይህን ያህል የሚያስደነፋ አይደለም። ሰሞኑን በኦነግ ታጣቂዎች እየታመሱ ያሉት ከደብረብርሃን እስከ ደሴ ያሉ ከተሞች እና መንደሮች አካባቢ የኢንተርኔት አገልግሎት እንኳን ሰውን ለጭት ለማነሳሳት ይቅርና ሕዝቡ የደረሰበትን በደል አቤ እንዳይል እንኳ ግንኙነቶች ተቋርጠው እንደነበር እና ወትሮውንም ያን ያህል የኢንተርኔት አገልግሎት በበቂ ሁኔታ በአካባቢው ያልተዳረሰ መሆኑ ይታወቃል።
መሬት ላይ ያለውን እውነታ ከመጋፈጥ ይልቅ በየመግለጫው ግጭቶቹ በማህበራዊ ድህረ ገጾች በሚደረጉ ቅስቀሳዎች እና የጥላቻ ንግግሮች እንደተጀመረ ወይም እንዲባባስ እንደተደረገ አድርጎ መግለጽ አሳፋሪ ነው። የጥላቻ እና ጸብ ቀስቃሽ የሆኑ ንግግሮችን የሚቆጣጠረው ሕግ አስፈላጊነትን ለማጉላት ከሆነ እዛ ላይ ብዙም ባትደክሙ ጥሩ ነው። አስፈላጊነቱ በሕዝቡም ዘንድ ታምኖበታል። ከዛ ይልቅ መንግስት መጀመሪያ የተጣለበትን ሰላም እና ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ስላልሆነ ሌላ ምክንያት ካላቸው ንገሩን። ከሌለም ኃላፊነታችሁ በአግባቡ ተወጡ።
መንግስት የዜጎችን ደህንነት ያስጠብቅ። የከረረ ብሔረተኝነት ከነፍጥ ጋር ሲገናኝ ተቀጣጣይ ፈንጂ ስለሆነ መጨረሻው መተላለቅ ነው። ይሄ ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያ ያመጣው ጣጣ ሳይሆን አገሪቱ ለአርባ መታት የተነደፈችው መርዝ እና ሥርዓቱ ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት ኮትኩታ ያሳደገው ዛፍ ፍሬ ነው። የእነ ኦነግም የጥላቻ ፖለቲካ የአርባ አመት ሥራ ውጤት ነው። ሶሻል ሚዲያ ሳይኖር በፊት እነ አርባጉጉ፣ በደኖ እና አርሲ ላይ እና በቅርቡም ቡራዩ ላይ በኦነግ ታጣቂዎች የተፈጸሙትን የዘር ማጥራት ወንጀሎች ታዝበናል።
መሬት ላይ ያለውን አክራሪ ብሄረተኝነት በሕግ ቁጥጥር ስር ማድረግ ሳይቻል አየር ላይ ስላለው ማህበረ ድረገጽ ደጋግሞ ማውራት የምጣዱ እያረረ የእንቅቡን እንደ እንደ ማገላበጥ ነው የሚሆነው።
ቸር እንሰንብት
Filed in: Amharic