>
5:18 pm - Monday June 15, 5536

ከስያሜው ጀምሮ አወዛጋቢው ፌደራሊዝም!!! (በፍቃዱ ዘ ሀይሉ)

ከስያሜው ጀምሮ አወዛጋቢው ፌደራሊዝም!!!
በፍቃዱ ዘ ሀይሉ
የኢትዮጵያ ፖለቲካ የቋንቋ እና ባሕል ማንነት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ጥገኛ ከመሆኑ የተነሳ ስለ ርዕዮተ ዓለም እምብዛም ግድ አይሰጠውም። ይሁን እንጂ የማንነት ፖለቲካው ላይ የአገላለጽ እንኳን በቂ መግባቢያ የለም።

“የጎሳ ፖለቲካ ይታገድ” የሚል ንቅናቄ የጀመሩ ሰዎች አሉ። ከዘመቻው አራማጆች መሐከል ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መሪ የሆኑት ኦባንግ ሜቶ ይገኙበታል። ምን ያህል ይሳካላቸው ይሆን?

የማንነት ሥያሜዎች ምን ይነግሩናል?

የኢትዮጵያ ሀገር ዐቀፍ ንቅናቄ (ኢሀን)ኢሥራ አስፈፃሚ አባል ወይንሸት ሞላ እና የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ) አመራር አባል የሆኑት ሌንጮ ለታ በሒልተን ሆቴል በተዘጋጀ አንድ የውይይት መድረክ ላይ ተገናኝተው ነበር። ወጣቷ ወይንሸት አሁን ኢትዮጵያ ለገባችበት የፖለቲካ ፈተና የዳረጋት “የጎሳ ፖለቲካ” እንደሆነ ደጋግማ ገልጣለች። ሌንጮ ለታ፣ ለእሷ ምላሽ ሲሰጡ “ጎሳ” የሚለውን ቃል አማርኛ የተዋሰው ከኦሮምኛ እንደሆነ በመግለጽ ወይንሸት የተጠቀመችበት አገባብ ትክክል እንዳልሆነ ለማስረዳት ሞክረዋል።

ጎሳ የሚለው ቃል በኦሮምኛ የጠቅላላው የኦሮሞ ማኅበረሰብ ንዑስ አባላትን የሚወክል እንደሆነ ይነገራል። ይሁን እንጂ በተለይም የኢትዮጵያን የፌዴራል አወቃቀር ስርዓት የሚቃወሙ ፖለቲከኞች ፌዴራሊዝሙን “የጎሳ” ፌዴራሊዝም ይሉታል። የፌዴራል አወቃቀሩን የሚደግፉት ፖለቲከኞች ደግሞ አገላለጹ አወቃቀሩን የሚያንኳስስ ነው በሚል አይቀበሉትም። እነዚህኞቹ ብሔር ከጎሳ የሰፋ ወይም ብዙ ጎሳዎችን በውስጡ ያቀፈ ስብስብ እንደሆነ ነው የሚናገሩት። የፌዴራል አወቃቀሩም መሠረታዊ ፍልስፍና ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ራሳቸውን የቻሉ ብሔሮች አሉ፤ ፌዴራሽኑ እነሱን አሰባስቦ ያቅፋል የሚል ነው።

በሌላ በኩል “ዘር” የሚለውን ቃል በመግለጽ የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚጠቅሱትም አሉ። ምንም እንኳን በዘር ደረጃ “ሁላችንም ጥቁር ነን፤ ውስጣዊ ልዩነታችን የባሕል ነው” የሚል መከራከሪያ ቢቀርብበትም። “ብሔር” የሚለውም ቃል ከግዕዝ በተውሶ የተገኘ እንደመሆኑ “አገር” የሚል ትርጉም አለው። ስለሆነም ለዚህ የብሔርነት ማዕረግ መብቃት ያለባት ኢትዮጵያ ብቻ ነች ብለው የሚከራከሩም አሉ። ፖለቲከኞቹ እንደ ክርክራቸው አደረጃጀታቸውም ለየቅል ነው። በአብዛኛው የብሔር እና ኅብረ ብሔራዊ እየተባሉ ይጠራሉ። ሆኖም በዚህ አጠራር ሐሰተኛ ሁለትዮሽ (false dichotomy) የማይሥማሙም አሉ። አንዳርጋቸው ፅጌ ከማይሥማሙት አንዱ ናቸው።

አንዳርጋቸው ፅጌ “ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጪ” በሚለው መጽሐፋቸው በእንግሊዝኛው “ethnicity” ለሚባለው ቃል “ዘውግ” የሚል አቻ መጠቀምን መርጠዋል። እንደ አንዳርጋቸው አገላለጽ ራሳቸውን የብሔር እና ኅብረብሔራዊ ብለው የሚጠሩት ድርጅቶች – ሁለቱም አባሎቻቸውን በብሔር መነፅር ነው የሚመለከቱት በሚል፥ በርዕዮተ ዓለም የሚደራጁትን ድርጅቶች “ዘውግ ዘለል” በሚል መጥራት እንደሚሻል ጠቁመዋል።

ፌዴራሊዝሙን “የጎሳ” ከሚሉት “ኅብረ ብሔራዊ” እስከሚሉት ድረስ የተለያየ አረዳድ አለው። የጎሳ ወይም የብሔር የሚሉት ብዙ ጊዜ ነቀፋን ያዘለ አስተያየት ሲኖራቸው፥ ኅብረ ብሔራዊ ብለው የሚጠሩት ግን የብዝኀነት አርአያ አድርገው ይስሉታል።

ብዙ ፌዴራሊዝሞች የሚመሠረቱት አባል መንግሥታቱን በማሰባሰብ (bringing together) ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ግን ከአንድ አገር በመልሶ በማዋቀር ክልሎቹ የተፈጠሩ በመሆኑ እንዳይለያዩ ጠባቂ (holding together) ፌዴራሊዝም ነው ይሉታል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕገ መንግሥት መምህሩ ሙሉጌታ አረጋዊ በተለያዩ መድረኮች እንደገለጹት “የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ሁለቱንም ነው ማለት አይቻልም”። ክልሎቹን አሰባሰባቸው እንዳይባል፥ ቀድሞም በአንድ መንግሥት ሥር ነበሩ። አብረው እንዲዘልቁ ዋስትና ሆናቸው እንዳይባል ለዘውግ ብሔርተኝነት (ethno-nationalism) መጎልበት መንገድ ጠርጎ ክፍፍላቸውን አጉልቶታል። ሙሉጌታ ‘ፌዴራሊዝሙ በአግባቡ ቢተገበር ኖሮ ኢትዮጵያ ልትበታተን ትችል ነበር’ የሚል ጥርጣሬ አላቸው።

ለአንዳንዱ በረከት፣ ለሌላው መርገምት!

አሁን በኢትዮጵያ ላሉት ማንነትን መሥረት ያደረጉ ግጭቶች እና ማፈናቀሎችን የፌዴራሉን አወቃቀር ከሚወቅሱት ጀምሮ “አተገባበሩ ስለጎደለ ነው” እስከሚሉት ድረስ ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥትም በቅርቡ ባወጣው መግለጫ “ብሔርተኝነት የአገሪቱ የደኅንነት ሥጋት እስከመሆን ደርሷል” ብሏል። ማሕሙድ ማምዳኒ የተባሉ ፕሮፌሰር ‘ለኒውዮርክ ታይምስ’ እንደጻፉት የመለስ ዜናዊ የዘውግ ፌዴራሊዝምም ሆነ የደርግ የተማከለ አስተዳደር መፍትሔ አልሰጡም፤ ስለሆነም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር አዲስ ዓይነት (የዘውግ ያልሆነ እና በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ላይ የተመሠረተ) ፌዴራላዊ አወቃቀር ማምጣት አለበት ይላሉ። አለበለዚያ ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማለች ነው የሚሉት።

ፊሎሪያን ቢበር እና ወንድማገኝ ታደሰ የተባሉ ምሁራንም “ኢትዮጵያን ዩጎዝላቪያ እንዳያደርጓት” በሚል ‘ፋይናንሻል ታይምስ’ ላይ በጋራ በጻፉት መጣጥፍ፥ በዘውግ ብሔርተኝነት በተዋቀሩ አገራት ውስጥ የፖለቲካ ምኅዳሩ መከፈት የብሔር ግጭቶችን ሊያቀጣጥል እንደሚችል ተከራክረዋል። እንደ ጸሐፊዎቹ በዘውግ የተደራጁ ፖለቲከኞች ከድርድር ይልቅ ዋልታ ረገጥነትን ይመርጣሉ።

‘ፍሬድሪክ ኧርበርት ስቲፍቱንግ’ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ቁልፍ ተናጋሪ ሆነው ቀርበው የነበሩት የሕወሓት ሥራ አስፈፃሚ አባሉ ጌታቸው ረዳ፣ በኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓቱ በአንድ ወቅት ችግር ለመፍታት የተሰጠ መላ እንደሆነ አስታውሰው፥ አሁን ደግሞ ራሱ አዲስ ችግር መፍጠሩን አምነዋል። ጎይቶም ገብረልዑል የተባሉ በካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ የዶክትሪት ዲግሪያቸውን በመሥራት ላይ ያሉ ምሁር ግን በዚህ አይሥማሙም።

በአልጄዚራ ድረገጽ “ኢትዮጵያ የዘውግ ፌዴራሊዝሟን ይዛ ትቀጥል ይሆን?” ብለው በጠየቁበት መጣጥፋቸው መልስ ሲሰጡ፥ በኢትዮጵያ የነበረው ችግር የተማከለ አስተዳደር መኖሩ ብቻ ሳይሆን የባሕል መዋዋጥም ነው ብለዋል። ለእርሳቸው የፌዴራሊዝም አወቃቀሩ ችግር በተግባር አለመፈፀሙ ብቻ ነው፤ ከዚህም በላይ ፌዴራሊዝሙ በብዙኀን ከፍተኛ ቅቡልነት ስላለው፣ ለማፍረስ መሞከር ሌላ ችግር መጥራት ነው ይላሉ።

ፌዴራሊዝሙ እና አወቃቀሩ ለተለያዩ ሰዎች የተለያየ ትርጉም ይሰጣል። በዚህ መሐል “የጎሳ ፖለቲካ ይታገድ” የሚለው ዘመቻ ውጤታማነቱ አጠራጣሪ ነው። የፌዴራል አወቃቀሩ ማንነትን መሠረት ያደረገ ሆኖ ሳለ በማንነት መደራጀት ሊታገድ የሚችልበት ዕድል የለም።

መንግሥት የማንነት እና አስተዳደራዊ ወሰን አከላለሎችን የሚያጠና ኮሚሽን አቋቁሟል። ኮሚሽኑ እስካሁን ምን እየሠራ እንደሆነ አይታወቅም። ሥራውን (ጥናቱን) ሲጨርስ ግን የፌዴራሊዝሙ አወቃቀር የተለየ እንዲሆን የሚጠይቅ ውጤት ሊያቀርብ ይችላል። ይህ በእንዲህ እያለ የ54 ያህል ብሔር ብሔረሰቦች ስብስብ የሆነው የደቡብ ክልል በመፍረስ ቋፍ ላይ ነው። በክልሉ ውስጥ በአንድ ታቅፈው የነበሩና ከፍ ያለ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ብሔረሰቦች “ክልል እንሁን” ጥያቄ አቅርበዋል።

የሁለትዮሽ ሙግቶቹ በቀጣይ ስለሚፈጠሩት ግምባሮችም የሚያመላክቱት ነገር አለ። በማንነት መደራጀትን እና የፌዴራል አወቃቀሩን የሚደግፉ ባንድ ወገን፣ ይህንን የሚቃወሙት ደግሞ በሌላ ወገን ሆነው ከፍተኛ የፖለቲካ ፍጥጫ ውስጥ መግባታቸው የማይቀር ይመስላል።

Filed in: Amharic