>
3:37 pm - Tuesday July 5, 2022

ኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ታሪክ፣ አፈ-ታሪክና ቀዶጥገና የተካሄደበት ታሪኮች ተደባልቀዋል!!! (ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ)

ኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ታሪክ፣ አፈ-ታሪክና ቀዶጥገና የተካሄደበት ታሪኮች ተደባልቀዋል!!!

የጂኦፖሊቲክስና ሶሻል ጂኦግራፊፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ

የአካባቢው በየአጋጣሚው እዚህም እዚያም የሚስተዋሉችግሮች በእርሳቸው እምነት ለውጡ ሲመጣ ይገጥማልብለው ከገመቱት አንፃር አነስተኛ መሆኑን የነገሩን በአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ እና የሦስተኛ ዲግሪ መምህሩፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ ናቸው።

በጂኦ ፖለቲክስ፣ በፍልሰት እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይምርምር የሚያካሂዱት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ተወልደውያደጉት ቢሾፍቱ ሲሆን፤ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃትምህርታቸውን የተከታተሉትም በዚያው በቢሾፍቱ ነው።የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ አዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ ያቀኑ ሲሆን፤ ከተመረቁ በኋላ ለሃያዓምስት ዓመታትም ከረዳት መምህርነት እስከ ሦስተኛዲግሪ መምህርነት በዩኒቨርሲቲው ሲሠሩ ቆይተዋል።በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የአፍሪካና ኦሪየንታል ጥናትናምርምር ማዕከል፣ የጂኦፖሊቲክስና ሶሻል ጂኦግራፊፕሮፌሰር ከሆኑት ከተስፋዬ ታፈሰ ጋር የወቅቱን የኢትዮጵያፖለቲካ ሁኔታ በሚመለከት የነበረንን ቆይታ እንሆ ብለናል

አዲስ ዘመን፡–የወቅቱን የፖለቲካ ሁኔታ አስመልክቶ ምንይላሉ?

ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡– የዛሬ አንድ ዓመት ገደማ ከኢሕአዴግ ውስጥ ፈንቅሎ የወጣው ኃይል ለኢትዮጵያ ትልቅ ዕድልን ፈጥሮላታል። የለውጥ ኃይሉ አገሪቱን ወደ ገደል ጫፍ እየገፋት የነበረውን የፖለቲካ ውጥረት እንዲረግብ ዕድል ፈጥሯል። ነገር ግን ሥልጣኑ፣ ቢሮክራሲው፣ መከላከያው፣ ደህንነቱ፣ ሀብቱ በተወሰኑ ቡድኖችና ግለሰቦች የበላይነት (በሞኖፖል) ተይዞ በነበረበት ሁኔታ ለውጡ ካለምንም እንቅፋት ይጓዛል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። በኔ እይታ ለውጡ አሁን ከምናየው በላይ ብዙ መሰናክሎችና ተግዳሮቶች ሊያጋጥሙት ይችል ነበር። ኢትዮጵያ ማህበራዊ እሴቷ ጠንካራ አገር በመሆኗ ህዝቡ ፈጣሪውን ስለሚፈራ እንጂ ሌላ አገር ቢሆን ከዚህም በላይ ችግር ያጋጥም ነበር። ሥልጣን ሲነጠቅ ብዙ ነገር ሊፈጠር ይችላል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንደተናገሩት “ተዘግቶ የቆየ ቤት ሲከፈት ይሸታል::”

እነዚህን ውስብስብ ሁኔታዎች አቅልሎ በማየት ወይም ባለመጠበቅ እንዲሁም የለውጡን ውጤቶች አሁኑኑ ለማየት ከመጓጓት የተነሳ አላስፈላጊ ንትርክና ግጭቶች ውስጥ የመግባት ሁኔታ ይታያል። ይህ የሚጠበቅ ነው። ነገር ግን ለውጥ ሂደት ስለሆነ ሰፋ ያለ ጊዜና ትዕግስትን ይጠይቃል። “ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም” ሁሉም የሚመኛትና የሚፈልጋት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያም በአንድ ጀምበር ልትፈጠር አትችልም። የለውጥ ኃይሉን ጊዜ በመስጠት ካላገዝነው፣ ለውጡ በሚፈለገው ጊዜና በለውጥ ኃይሉ ላይ በሚደረገው ጫና ምክንያት የሚፈጠረው ክፍተት ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይወስደን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። ወደፊት ልናያት የምንፈልጋትን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የሚመጥን የፖለቲካ አስተሳሰብና ቁመና ያስፈልጋል። በዚህ ቁመና የታነፀ እይታ ከሌለ ወደኋላ ተንሸራትተን ወደ ጀመርንበት ቦታ እንመለሳለን። ይህንን ደግሞ ብዙ ኢትዮጵያውያን በተለይ ደግሞ ይህ ለውጥ እንዲመጣ የታገሉ ወጣቶች ማየት የሚፈልጉ አይመስለኝም።

የለውጥ ኃይሉ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር አለመቻል፣ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች አገሪቷን ከራሳቸው ዓላማ በላይ ማየት ባለመፈለግ አገሪቱን አደጋ ላይ መጣል፣ ወጣቱ የትግሉን ፍሬ አሁኑኑ ለማየት መቸኮል፣ ስልጣን ሳያስቡትና ሳይገምቱት ከጉያቸው ስር አፈትልኮ ያመለጣቸው ኃይሎች አርፎ ያለመተኛት አገሪቱን አጣብቂኝ ውስጥ ከቶ መስቀለኛ መንገድ ላይ እንድትቆም አድርጓታል። ከዚህ ውስብስብ ሁኔታና አጣብቂኝ ለመውጣት የፖለቲካ ቡድኖች፣ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ቆም ብለው በጥሞና ማሰብ ይጠበቅባቸዋል። ይህ ካልሆነ ሁሉም ተሸናፊ የሚሆንበትና ማንም አሸናፊ የማይሆንበት ሁኔታ ውስጥ እንገባለን።

አዲስ ዘመን:-  የሚፈጠሩት ችግሮች መንስኤያቸው ይህብቻ ነው?

ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡– በእርግጥ መብራራት ያለባቸው ብዙ ዝርዝር ጉዳዮች አሉ። ወጣቶቹ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ከመወለዳቸው ጀምሮ የተነገራቸው ብዙ የተሳሳተ የፈጠራ ትርክት አለ። በተደጋጋሚ ስለተነገራቸው የፈጠራ ትርክትን እንደእውነት የመውሰድ ሁኔታ ይታያል። በእርግጥ እውነተኛው እና የፈጠራ ትርክቱ የትኛው ነው የሚለው ቢያከራክርም ነገር ግን ሚዛኑን የጠበቀ ታሪክ ባለመነገሩ ወጣቱ ስሜታዊ መሆኑ አንደኛው ችግር ነው። ይህ አደገኛ በመሆኑ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል።

ማህበራዊ ሚዲያው በተለይ (ፌስቡክ) አግባብ ባልሆነ መንገድ አፍራሽ ለሆኑ ተግባራት የመጠቀም ሁኔታ ይስተዋላል። የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ብዙ አገሮችንም እያተራመሰ ይገኛል። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አሉባልታ፣ በሬወለደ የሚል የፈጠራ ወሬ፣ የተሳሳተ ዜና እና የግልና የቡድን ስሜት ይስተዋላል። አፍራሽ ማህበራዊ ሚዲያዎች ዘዴ ካልተፈጠረላቸው እሳት ለመጫርም ሆነ ነዳጅ ለማርከፍከፍ ዕድሉ እንዳላቸው መታወቅ አለበት። ይህን አፍራሽ ተግባር ለመቀነስና ለመቆጣጠር ራሱን የፌስቡክን ኩባንያ ትብብር መጠየቅ ይቻላል ወይንም የኢትዮጵያ መንግሥት አቅሙን አዳብሮ ቁጥጥር ማድረግ መቻል አለበት።

ፌስቡክ የራሱ ሕግ አለው። ለምሳሌ አንደኛው ሕግ “ግለሰቦችና ድርጅቶችን ለማጥቃት የሚቃጡ፣ ጥላቻ የሚያስፋፉ እና የማይፈልጓቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች እንዲገለሉ የሚያደርጉ በፌስቡክ ቦታ የላቸውም” ፌስቡክ እንዲህ ዓይነት ድርጅቶችና ግለሰቦችን አገልግሎት እንዳያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ አክራሪዎችን የሚያደንቁና የሚደግፉ ግለሰቦችና ቡድኖች አገልግሎቱን እንዳያገኙ ያግዳል። ለምሳሌ ያህል እንደብሪቲሽ ብሔራዊ ፓርቲ (British National Party)፣ የእንግሊዝ መከላከያ ሊግ (The English Defence League) እና ብሔራዊ ግንባር (National Front)ን ጨምሮ ከሰሞኑ 12 የሚሆኑ የእንግሊዝ ቀኝ አክራሪ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው ላይ ፌስቡክ ማዕቀብ ጥሏል።

ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ታሪክ፣ አፈ-ታሪክ፣ ትርክትና ቀዶጥገና የተካሄደበት ታሪክ (doctored history) ተደባልቀዋል። እነዚህ ታሪኮች ሕዝቡን ግራ እያጋቡ ነው። አሁን ብዙ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች እያሉ ለምን የአዲስ አበባ ይገባኛል ጥያቄ እየተነሳ መሆኑ ያጠያይቃል። የሽግግር ጊዜው አልፎ፣ አገር ተረጋግቶ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ከተካሄደ በኋላ በሰከነ መንፈስ ተረጋግቶ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያቀፈ ውይይት አካሂዶ መፍትሔ ማምጣት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ። ይህ እስኪመጣ አዲስ አበባ “የኔነች” “ያንተ አይደለችም” የሚለው ጊዜውን ያልጠበቀና ብዙ ነገሮችን ያላገናዘበ ንትርክ ሊቆም ይገባል።

ሌላው ጋዜጠኝነትና ፖለቲካ ተንታኝነት በተሳሳተ መንገድ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ መሆናቸውም ሌላው መንስኤ ነው። እነኚህ ሁለት የተለያዩ ሙያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ተደበላልቀዋል። የጋዜጠኝነት ሙያ እና ፖለቲካ ተንታኝነት የሚገናኙበት ነገር ቢኖርም ራሳቸውን የቻሉ ሙያዎች ናቸው። ለዚህ ነው የዓለም አቀፍ ዜና አውታሮች ሲ ኤን ኤን፣ አልጀዚራ እና ቢ ቢ ሲ የሚሠሩ ጋዜጠኞች የተለያዩ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ጉዳዮች ሲኖሩ የተለያዩ ፖለቲካ ተንታኞችን እያቀረቡ ያወያያሉ። ይህ ለውጥ ከመጣ ጀምሮ ላለፈው አንድ ዓመት ጋዜጠኞች ብቻ ሳይሆኑ ሙያቸው ከፖለቲካ ዕውቀት ራቅ ያሉ ሰዎች ሁሉ ተንታኝ ሆነው የተሳሳተ ትንተና ሲሰጡ ይታያል። ሞያተኛ የፖለቲካ ተንታኞች ስላልሆኑ ወገንተኝነት ያጠቃቸዋል፤ እንዲሁም ትንተናቸው ሚዛኑን ያልጠበቀ ይሆናል። ይህ ደግሞ በሕዝቦች መካከል ከፍተኛ የሆነ ውዥንብር ይፈጥራል። ጋዜጠኞች በሙያቸው ምክንያት የተለያዩ አቅጣጫዎችን የማየት ዕድል ቢኖራቸውም ከሙያቸው የሚጠበቀው ሚዛናዊነት እንዳይጎዳ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። ጋዜጠኞች ከወገንታዊነት የነፃ ሂሳዊ ድጋፍ (critical support) ቢሰጡ ለአገርም ሆነ ለሕዝብ ይጠቅማል።

አዲስ ዘመን፡– በመንግሥት በኩል የበዛ መለሳለስ እንዳለይገለጻል ይህ አለን? መለሳለስ ካለስ ተገቢ ነው?

ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡– አዎ ተገቢ ነው። የለውጡ ኃይል ብዙ ታሪካዊ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ድል አስመዝግቧል። ይህ ትልቅ ነገር ነው። ከሃያ ዓመት በላይ በእስራት ውስጥ የነበሩትን ፈትቶ እንደገና መልሶ ማሰር ከጀመረ ከበፊቱ በምን ይለያል? ግጭቱ በጊዜ ሂደት መቀዝቀዙ አይቀርም። ሁሉም ኃላፊነት እየተሰማው ይሄዳል የሚል ተስፋ አለኝ። መንገድ መዝጋትም ሆነ ሰው መግደል ትርፍ የለውም፤ ትርፍ የሌለው ነገር ደግሞ መቆሙ አይቀርም። በመግደል ማንም ቢሆን አሸናፊ አይሆንም። መጨረሻው ሁሉም ተሸናፊ ስለሚሆን ሁሉም ኃላፊነት ሲሰማው ግጭቱ ይቆማል ብዬ አምናለሁ።

አዲስ ዘመን፡– የለውጥ ኃይል የሚባለው አካል በምንሁኔታ ላይ ነው ብለው ያምናሉ?

ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡– የለውጥ ኃይሉ ዋልታ በረገጡ ኃይሎች መሃል ነው። ሃገሪቱን እየመራ ያለው ኃይል ከተወጠረባቸው ችግሮች አንዱ ይመራቸው ከነበረበት ክልሎች ሳይቀር በተለያየ አቅጣጫ እና ሊታረቁ የሚችሉ የማይመስሉ አስተሳሰቦች መሀል መገኘት ነው። በሌላ በኩል ገሚሱ “ለውጡ ተቀልብሷል” ሲል ሌላው “ቀድሞውንም ከዘር ስሌት የማይወጣ ጅምር ነበር” ይላል። የፖለቲካ ሂደት ነውና የለውጥ ኃይሉ ይህን መሰል ጉዳዮች አይጠብቅም ነበር ብሎ መናገር ስህተት ይመስለኛል። ዋናው ጉዳይ ግን ጫፍና ጫፍ ተይዞ የሚጎተት ነገር ላለመበጠሱ ዋስትና ስለሌለ የለውጥ ኃይሉን ሂሳዊ እና ገንቢ ድጋፍ (criti­cal support) ብንሰጠው ይሻላል።

አዲስ ዘመን፡– እየታየ ያለውን ችግር የዘር ማጥፋትወንጀል እየተፈፀመ ነው በሚል የሩዋንዳውን ጉዳይበማንሳት ሰዎች ስጋታቸውን የሚገልጹበት ሁኔታይስተዋላል። ስለዚህ ምን ይላሉ?

ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡– የሩዋንዳውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ (genocide) በአስተማሪነቱ ሳይሆን “እኛም ወደእዝያ እየሄድን ነው” አገሪቷ እንደአገር መንቀሳቀሷን አቁማለች። የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች መፈጠር (doom and gloom) የሚሰብኩ ሰዎች መኖር በጣም አደገኛ ነው። እነኚህ እሳቤዎች እጅግ አሳሳቢ ናቸው። በአስተማሪነታቸው ቢጠቀሱ ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ከ800 ሺ እስከ አንድ ሚሊዮን ሕዝቦችን ሰለባ ያደረገውን የሩዋንዳውን ዘር ማጥፋት በኢትዮጵያ ሊደገም ነው እያሉ ማነፃፀሪያ የሚያቀርቡ ሰዎች አንድ ነገር ከማለታቸው በፊት ሁለቴ ቢያስቡ የተሻለ ነው። እንዲህ ያለ ጨለምተኝነትን በቋፍ ላይ ባለችው አገራችን ላይ መለጠፍ አንድምታው ጥሩ አይሆንም።

በዘር ማጥፋት ጭፍጨፋው ጊዜ በሩዋንዳ የነበረው ሁኔታና አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በብዙ መልኩ አይመሳሰሉም። ሩዋንዳ ውስጥ የቤልጅየም ቅኝገዥዎች ቀብረውት የሄዱት ፈንጂ እ.ኤ.አ በ1994 በመፈንዳቱ ያን ሁሉ ሕዝብ ሰለባ አድርጓል። የቤልጅየም ቅኝ ገዥዎች የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲያቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ሁቱዎችንና ቱትሲዎችን ለመከፋፈል ይረዳቸው ዘንድ የፊት ቅርፅን በመሳል፣ የአፍንጫ ስፋትንና የከናፍር ውፍረትን በመለካት ሁቱ፣ ቱትሲ እያሉ መታወቂያ ማደላቸው በኋላ በዘር ማጥፋት ዘመቻው ጊዜ ላይ እንደታየው ያ የብሔር ማንነትን የያዘ መታወቂያ ብዙ ቱትሲዎች ሸሽተው እንዳያመልጡ እንኳ በየኬላው መታወቂያ እየተጠየቁ እንዲታረዱ አድርጓቸዋል።

እርግጥ ነው እኛምጋ ሕዝቡ የተጣመረባቸውን ማህበራዊ እሴቶች (social capital) ጭምር የሚፈታተኑ ንግግሮችና አቅጣጫዎች እንዳሉ ይታወቃል። ይህን ለመግታት ሩዋንዳን መደጋገም አስተማሪ አይሆንም። ሌሎች ገንቢ የሆኑ ሂደቶች ለምሳሌ ያህል የሕዝቡን ባህልና ልምዱን ማዕከል ያደረጉ ጉዳዮች ላይ ማተኮሩ ይጠቅማል። እንደኔ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ምን እንደሚመስልና መዘዙ ምን ያህል የከፋ መሆኑን ለማስገንዘብ የተወሰኑ የዘር ማጥፋቱን ዘመቻ የሚያሳዩትን ዕትሞችን ተርጉሞ ማቅረቡ ጠቃሚ ነው።

አዲስ ዘመን፡– ከፖለቲካ ሁኔታው ጋር ተያይዞ አሁን ያለውን የኢኮኖሚ መቀዛቀዝን እንዴት ያዩታል?

ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡– በአገሪቱ ጤናማ ያልሆነ የኢኮኖሚ ሁኔታና ሥራ አጥነት እየጨመረ ነው። ሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር እንዲሁም ወደ ከተሞች በተለይም ወደ አዲስአበባ የሚደረገው ፍልሰት በኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል። ጤናማ ኢኮኖሚ እንዲኖር ከተፈለገ እንዲሁም ወጣቱ ሥራ ማግኘት የሚችልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ከታሰበ አገሪቷ መረጋጋት አለባት፣ ሰዎች በፈለጉበት ቦታ ሄደው መሥራት መቻል አለባቸው። ማንም ሰው ካለስጋት ጠዋት ወጥቶ ወደ ሥራ መሰማራት፤ ማታ ካለስጋት ወደ ቤት መግባት መቻል አለበት። አገሪቷ ኢንቨስተሮችን መሳብ የምትችል መሆን አለባት። ባለፈው አንድ ዓመት ይከሰቱ የነበሩ ችግሮች በመብዛታቸው ኢኮኖሚውን አዳክመውታል። የዋጋ ግሽበት (inflation) እና የኑሮ ውድነት (cost of living) አሻቅቧል። መንግሥት እነኚህን ነገሮች ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት አገር ማረጋጋትና ሕግ ማስከበርን ተግባራዊ ካላደረገ ኢኮኖሚው የባሰ ሊወርድ ይችላል። እንዲሁም ሥራ አጥነቱ ይቀጥላል። እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሕዝብን ወደ አመፅ ሊወስዱት ይችላሉ።

አዲስ ዘመን፡– የማንነት፣ የዞን እና የክልል እንሁንጥያቄዎችን እንዲሁም ስለፌዴራሊዝም ምን ይላሉ?

ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡– እንደእኔ እይታ ፌዴራሊዝም በራሱ ችግር የለበትም። በቅርብ የማውቃቸው አገሮች ጀርመንና ስዊዘርላንድ የፌዴራሊዝም አወቃቀራቸውና አተገባበራቸው በጥናትና ዕውቀት ላይ ተመርኩዞ ስለተሠራ ሕዝቡም ዕድል ተሰጥቶት ተሳታፊ እንዲሆን ተደርጎ ስለነበር አገሮቹ በጥሩ ሁኔታ ተጠቅመውበታል፤ እየተጠቀሙበትም ነው። የእኛ አገር ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ዓላማውም፣ አወቃቀሩም፣ አተገባበሩም ችግር ያለበት ነው። ሥልጣን ላይ ለመቆየት ያገለገለ ይመስለኛል። አወቃቀሩም ግራ የሚያጋባ ነው።

ብዙዎቹ የአገራችን አካባቢዎች ቋንቋን ማዕከል ያደረገ የፌዴራሊዝም አወቃቀር ሲኖራቸው የደቡብ ክልል ግን መልክአምድርን ታሳቢ አድርጎ የተዋቀረ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሲዳማን የሚያክል በሕዝብ ብዛትም ሆነ በቆዳ ስፋት ከብዙ ክልሎች የማያንሰውን አካባቢ የፌዴራል አወቃቀሩ ዞን ሲያደርገው ትንሽዋን (city-state) ሐረሪን ደግሞ ክልል አድርጓታል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም አወቃቀር እርስ በራሱ የሚጋጭና አንድ ወጥ ያልሆነ ነው። አተገባበርና በጀት አመዳደቡም ላይ ከፍተኛ ችግር ያለውና ብዙ ጥያቄዎችን የሚጭር ነው። ከላይ የጠቀስኳቸው ችግሮች ባሉበት ሁኔታ “ሲዳማ” እና ሌሎችም በደቡብ ክልል ያሉ ዞኖች ክልል እንሁን ብለው ቢጠይቁ የሚያስደንቅ አይመስለኝም። እንዲያውም ወደፊትም ጠያቂዎቹ ቁጥራቸው እየጨመረ ሊሄድ ይችላል። አሁን ትልቁ ችግር የአንዱ ጥያቄ በተመለሰበት ሁኔታ ሌላው ባይስተናገድ ምን ሊያመጣ ይችላል? የሚለውን ነው። ከዚህ በተጨማሪ ላለፉት 25 ዓመታት የደቡብ ክልል ርዕሰ ከተማ ሆና ያገለገለችው “የሃዋሳ ጥያቄ”በምን ሁኔታ እንደሚስተናገድ አሁኑኑ ማሰብ ያስፈልጋል። “ምን መሆን አለበት?” እና “የት” የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ብዙ ሥራ ይጠብቀናል። እንደኔ “ክልል” የሚለው ፅንሰ ሃሳብ ራሱ አግላይ (exclusionary) ነው። አሁን የሚታየው “የኔ” እና “ያንተ” ጣት መጠቋቆም እና “የውጡልኝ” ጥያቄ የእዚህ ሰንካላ ፅንሰ-ሐሳብ ውጤት ነው። ይህ ራሱ በፅኑ ታስቦ መስተካከል አለበት።

አዲስ ዘመን፡– ክልል እንሁን ጥያቄ መቅረቡ መብት ነው።ነገር ግን ካለው ውጥረት አኳያ ጥያቄው ጠንከር ብሎየመጣበትን ጊዜ አስመልክቶ ምን ይላሉ?

ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡– ይሄ ትንሽ ከባድ ነው። ራስን በጠያቂው ቦታ ማስቀመጥን ይጠይቃል። ጉዳዩ በዚህ ጊዜ ምላሽ ካላገኘ በኋላ ዕድሉን ማግኘት አይቻል ይሆናል የሚል እምነት ሊኖር ስለሚችል ጥያቄውን እንደስህተት መውሰድ አዳጋች ነው። በእርግጥ ከወቅቱ ውጥረት አንፃር አሁን ባይጠየቅ የኔም ፍላጎት ነው።

አዲስ ዘመን፡– በቀጣይ ምን መሆን አለበት?

ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡– ወደ ኋላ እያዩ ወደ ፊት ለመሄድ የሚፈልጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች መኖር የለባቸውም። በታሪክ እንደሚታወቀው በዓለም ላይ የተለያዩ ነገሥታትና መሪዎች አገር ለማስፋፋት ሲፈልጉ፣ ቅኝ ገዥ ለመሆን ሲመኙና ኃያልነታቸውን ለማሳየት ሲፈልጉ በሰው ልጆች ላይ የተለያዩ በደሎችን ፈፅመዋል። በቅርብ ጊዜ እንኳን ደቡብ አፍሪካ ከጫንቃዋ ላይ የጣለችው የአፓርታይድ አገዛዝ በጥቁሮች፣ በሕንዶችና «ከለርድ» በሚባሉ ክልሶች ላይ ይህ ነው የማይባል ግፍና በደል ለብዙ ዘመናት ተፈፅሟል። ይህን ያየ ከአፓርታይድ ፍፃሜ በኋላ ጥቁሮች ከነጮች ጋር በሰላም ይኖራሉ ብሎ ለማሰብ አዳጋች ነበር። ነገር ግን የኋላውን ትተው ይቅርታ በመጠያየቅና በመቻቻል አብረው እየኖሩ ነው።

ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ የትኛው ትክክለኛ ታሪክ፣ የትኛው አፈታሪክ፣ የትኛው ትርክት፣ የትኛው ቀዶጥገና የተደረገለት ታሪክ መሆኑን ለመለየት አዳጋች ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥም አነሰም በዚያም በታሪካችን ችግሮች እንደነበሩ መካድ አይቻልም። ትልቁ ነገር ከኋላው ታሪካችን ተምረን፣ ስህተቶች እንዳይደገሙ መተማመን ላይ መድረስ መቻል ነው የሚበጀው እላለሁ።

አዲስ ዘመን፡– ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስምእጅግ አመሰግናለሁ።

ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡– እኔም አመሰግናለሁ፡፡

Filed in: Amharic