>

ጸረ ፋሽስቱ አርበኛ ደጃዝማች ወንድ ወሰን ካሣ (አቻምየለህ ታምሩ)


ጸረ ፋሽስቱ አርበኛ ደጃዝማች ወንድ ወሰን ካሣ
አቻምየለህ ታምሩ
የዛሬው  የድል ቀን እልቁ መሳፍርት የኢትዮጵያ አርበኞች ተቆጥሮ የማያልቅ መስዕዋትነት የከፈሉበት ክቡር ቀን ነው። ሆኖም ግን   የአርበኞች ልጆች አንቀላፍተው አገራችን በባንዶች ልጆች እጅ በመውደቋ  ኢትዮጵያ የወደቁላትን ጀግኖች ውለታ ቅርጥፍ አድርጋ በልታ የከዷትንና ከጠላት ጋር ሆነው የወጓትን እነ ዚያድ ባሬ ኢትዮጵያን ስለወጉ የጀኔራልነት ማዕረግ ለሰጧቸው ለነ ዋቆ ጉቱ ሐውልት ስታቆም ትውላለች።
አገር ላቆዩ አርበኞች ስም መጥሪያ ይሆን ዘንድ ንጉሠ ነገሥቱ ላርበኞች ያቆሙት  መታሰቢያ  ሁሉ በባንዳ ልጆች  በነመለስ ዜናዊና ሐየሎም አርአያ ስም ተለውጦ የዛሬውን የድል በዓል ስናከበር ልንዘክረው የምንጎበኘው የጀግና መታሰቢያ የለንም!
ከጀግኖች አርበኞቻችን መካከል ዛሬ አንድ ያልተዘመረላቸው ጀግና ደግሜ ላስተዋውቃችሁ ወደድሁ። አዚህ ጀግና አርበኛ ለእናት አገራቸው ሰማዕት የሆኑት ደጃዝማች ወንድ ወሰን ካሣ ናቸው።  ደጃዝማች ወንድ ወሰን ካሣ የራስ ዳርጌ የልጅ ልጅ የታላቁ ራስ ካሳ ኃይሉ ልጅ ናቸው። ለአገራቸው ሊዋደቁ ከመሰማታቸው በፊት ራስ ጉግሣ ወሌን ተክተው የበጌምርድ እንደራሴ ሆነው ነበር። አገራቸው በፋሽስት ጦር በተወረረችበት ወቅት ብሔራዊው ጦር ሲደራጅ ራስ ሥዩም የሚመሩት በተንቤን ግንባር የተሰለፈው የሰሜን ጦር ስር ከተሰለፉት የጦር መሪዎች አንዱ ነበሩ።
ሚያዚያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም. ጠላት አዲስ አበባን ሲቆጣጠርና እልቆ ቢስ ደጃዝማቾችና ራሶች ለጥሊያን ሲገቡ ደጃዝማች ወንድ ወሰን ከሣ ግን እምቢ ለሀገሬ በማለት ጦራቸውን አስከትለው ዱር ቤቴ በማለት ለአገራቸው ነጻነት ይፋለሙ ነበር። የመጨረሻው የሕይዎታቸው ፍጻሜ የሆነው ኅዳር ወር 1929 ዓ.ም. ነው። በሕይዎታቸው ዘመን ፍጻሜ ያደረጉትን ተጋድሎና ጠላትና ባንዳው የተፈጸመባቸውን ግፍ የዘመን ምስክሩ አቶ ገሪማ ታፈሪ «ጎንደሬ በጋሻው» በሚለው የአርበኞች ማስታወሻ ታሪካቸው እንዲህ አቅርበውታል።
በኅዳር ወር 1929 ዓ.ም. ደጃዝማች ወንድ ወሰን ካሣ ታድነው እንዲገደሉ የሚል ትዕዛዝ የአማራ ግዛት በሆነው በሙሉ ቴሌግራም ተላለፈ። በደብረ ታቦር ማጆር አጎሊኒና ቴሌንቲ ሚላኖ የራሱን ጦርና ባንዳውን ይዞ ወደ ተከዜ ዘመተ። የሰቆጣው ፋሽስት የጦር ደግሞ ሠራዊቱን አደራጅቶ ከሰሜን ወደ ደቡብ በተከዜ አንጻር ማዶ ለማዶ ተላለፈ።
የወሎ የጠላት ጦር ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ተከዜን ከራሱ ጀመሮ እየመረመረ ወንዝ ለወንዝ ወረደ። በዚህ ዓይነት ክቢ ተከዜ ተከበበ። ይሁን እንጂ ከደብረ ታቦር ከቴንቲ ሚላኖ ጋር የዘመቱት መኳንንቶች ሁሉም የደጃዝማች ወንድ ወሰን ባለሟሎች ስለነበሩ የሚያመልጡበትንና ክፍት የሆነውን በር እየገለጹ በሚስጢር ስለሚልኩባቸው ቴሌንቲ ሚላኖ «በዚህ በኩል ተፈልጎ አልተገኘም» ሲል ጻፈና ከመኳንንቶቹ ጋር ተመለሰ።
ይህንኑ መሠረት በማድረግ ጥቂት ጊዜ ከአደናቸውና ካሰሳቸው በኋላ የሰቆጣውና የበለሣው የጠላት ጦርም ተመለሰ። ከወሎ የመጣው ግን በየጊዜው እየተለዋወጠ በርትቶ ያድናቸው ጀመር። ደጃዝማች ወንድ ወሰን ከሣ ቦታ ሳይለውጡ የተከዜን ውስጣ ውስጥ ተጠግተው፤
1ኛ. ግራዝማች መለሰ ሐማሴናይ፣
2ኛ. ፊታውራሪ ካሣ ወልደ ማርያም፣
3ኛ. ፊታውራሪ አውራሪስ
የሚባሉት ታማኝ አጋሮቻቸው በር በሩን በመትረየስ ዘግተው ብዙ ጊዜ ካሳለፉ በኋላ ቃፊር ከሆኑት ወታደሮች ውስጥ አንዱ እህል ውኃ ለመፈለግ ወደ አገር ቤት ሲሄድ የወሎ ባንዳ አገኘውና የማነህ? ወዴት ትሔዳለህ? ብሎ ቢጠይቀው በሐሰት የአገር ሰው ነኝ፤ ቤቴም ከዚያ ማዶ መንደር ነው፤ ብሎ ተናገረ። በዚህ ጊዜ ባንዶች «ቤትህ ከዚያ ማዶ መንደር ነው ከሆነ ቤትህን አሳየን» አሉና ያስጨንቁት ጀመር። እርሱም በደፈናው «ቤቴን አሳያለሁ» አለና ከመንደሩ ቢደርስ ቤቱ የሰው ቤት ሆነበት። ከዚህ ጊዜ ባንዶች የመንደሩን ሕዝብ ሰብስበው «ይህንን ሰው ታውቁታላችሁ?» እያሉ ቢጠይቁ የሚያውቀው ጠፋ።
እንግዲህ የደጃዝማች ወንድ ወሰን ካሣ ሰው መሆኑ ሊታወቅ ምንም አልቀረውም። ጠላት ጦር አዝማቹ ካፒቴን በብዙ ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ ሥቃይ እንዲሞክሩት ወታደሮቹን አዘዘ። በአንድ በኩል ደግሞ ደጃዝማች ወንድ ወሰን ያሉበትን ቦታ ያሳየኸኝ እንደሆነ ብዙ ገንዘብና ከፍ ያለ ሹምት እሰጥሀለሁ እያለ አታለለውና የተያዘው ሰው ጠላትን እየመራ ደጃዝማች ወንድ ወሰን ወዳሉበት ሲዘልቅ ከበሩ የተቀመጡት ቃፊሮች ከወዲያ የሚመጣው ጠላት መሆኑን ስላረጋገጡ በሩን ለሚጠብቁት መትረየስ ተኳሾች ለግራዝማች መለስና ለፊታውራሪ ካሣ ወልደ ማርያም የተኩስ ርችት አሰሟቸው።
ጠላትም ወደፊት እየገፋ ዘለቀና ጦርነቱ ከሁለቱም ወገን ይጋጋልና ይጋጋም ጀመር። በዚህ ጊዜ የጠላት ኃይል በሌላው በኩል ያለውን ውጊያ ለጥቂት ወታደሮች ሰጥቶ በመትረየስ ተኳሾች ላይ ያለውን ኃይል ሁሉ አዘመተ። በዚህ የጭንቅ ጦርነት በመጀመሪያ ጊዜ የመትረየሱ ኃላፊው ግራዝማች መለስ ሐማሴኔ ግንባራቸውን ተመትተው ስለወደቁ በሩ ተከፈተ። በሁለተኛው የጨበጣ ጦርነት ፊታውራሪ ካሣ ወልደ ማርያም ዓይኑን ተመትቶ ወደቀ። ከዚህ በኋላ የጦርነቱ ወላፈን ደጀን ሆነው ያዋጉት ከነበሩት ከደጃዝማች ወንድ ወሰን ካሣ ሳይ ላንቃውን ጣለ።
አሁን ባለቤትዮው የእጅ ጠመንጃ በመለዋወጥ መሐል ለመሐል እየከፈተው ዘለቀና ከተያያዘው የጦር ቃጠሎ ብቻውን ገብቶ ከመካከሉ ቆመ። በዚህ ጊዜ ጠላት ተመቸውና በእጅ ቦንብ ብቻ የጨበጣ ጦርነት እንዲያደርግ አዘዘ። ከቦንቡ ነጎድጓድ የተነሣ መሬት ተጨነቀች፤ አርበኞች አለቁ፤ ተከዜ የውኃው አወራረድ በደም ተበከለ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ከአገሬው በኩል ይደረግ የነበረው እርዳታ ጠላትን ለመጥቀም ከታሰበው በስተቀር ለደጃዝማች ወንደ ወሰን ከሣ የሚያጽናና መልዕክትም ሆነ እርዳታ አልደረሳቸውም። በዚህ ኃይለኛ ጦርነት ደጃዝማች ወንድ ወሰን ካሣ ሲዋጉ ዋሉና በ12 ሰዓት ተያዙ። መማረካቸውን የሚያስረዳ ለፋፊ ወጥቶ «ደጃዝማች ተማርከዋል» እያለ ይለፍ ጀመር። በዚህ ጊዜ ጦራቸው ተፈታና ጦርነቱ እረጅም ጊዜ ሣሳይፈልገው በየጦር ግንባር የተኩስ ድምጽ ጠፋ። ወታደሮቻቸውም ተማረኩ።
ወዲያው ጥቂት ሳይቆይ ፋሽስቱ ካፒቴን ወንበር አስመጣና ተማራኪውን ደጃዝማች ወንድ ወሰን ካሣን አስቀመጣቸው። ከዚያ ቀጥሎ እድሜያቸውን ጠየቃቸውና ከወንበሩ ላይ እንደተቀመጡ ግንባራቸውን በሽጉጥ መታቸውና በፊታቸው ተደፉ። ፋሽስቱ ካፒቴን ከዚያው ከወደቁበት ቦታ አፈርና ድንጋይ አለባብሷቸው በችኮላ ወደ ሰፈሩ ተመለሰ። በበነጋታው ፎቶግራፍ ሣያነሳቸው በመቅረቱ ተጸጽቶ ኖሮ እንደገና ሔዶ ከቀበረበት አስወጥቶ ፎቶግራፍ አንስቷቸው ተመለሰ።
በሦስተኛው ቀን አብረዋቸው ሲዋጉ የነበሩ ያልተማረኩ አርበኞች ሬሳቸውን አውጥተው ቅዱ ሃርቤ በተባለ ቤተክርስቲያን ከመቅደሱ አስገብተው ቀበሯቸው። የገደላቸው ፋሽስት ካፒቴን ራሳቸውን ቆርጦ ለበላይ ባለሥልጣን ሳያበረክት በመቅረቱ የተነሳ ከፍ ያለ ወቀሳ ስለደረሰበት እንደገና መጥቶ ራሳቸውን ለማስቆረጥ መቃብራቸውን ቢያስከፍት አስከሬኑን ስላጣው ተናዶ እጅ የሰጡትን የደጃዝማች ወንደ ወሰን ካሣ ወታደሮች ጨፈጨፋቸው።
የደጃዝማች ወንድ ወስን ካሣ አስከሬን በመቃብር ለመተኛት የሚያበቃው አጥቶ ሦስት ጊዜ ሙሉ ወጥቶ መቀበሩንና መውጣቱን ተመልክተው የላስታ ካህናት  «ወሥጋሆሙኒ፡ ለአግብርቲክ፡ ለአራዊተ ገዳም ወከዓው ደሞሙ ከመ ማይ አውዳ መኃጥዑ፡ ዘይቀብሮሙ» የሚለውን መዝሙረ ዳዊት ሰበኩ።
ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ድል አድርጋ መያዝዋ፥ የጀግናውን አርበኛ የደጃዝማች ወንድ ወሰን ካሳን  ጀግንነት ሊቀማው አይችልም! ደጃዝማች ወንድ ወሰን የወደቁበት ቦታ ተከዜ  ምድርን ከነታሪኳ የሚያጠፋ መአት እስካልመጣ ድረስ፥ ጀግንነታቸው፣ ሰማዕትነቸውና   ስማቸው ከከተዜ ወንዝ ጋር ለሁልጊዜ ይኖራል።
Filed in: Amharic