>
1:02 pm - Sunday December 4, 2022

ንግድ ባንክ ኦሮሚያ ክልል ወለጋ ተዘረፈ (ውብሸት ሙላት)

ንግድ ባንክ ኦሮሚያ ክልል ወለጋ ተዘረፈ
ውብሸት ሙላት
* መንግሥት የሕግ ማስከበር ኃላፊነቱን ይወጣ ሲባል ዜጎች ከተገደሉ፣ ከተፈናቀሉ በኋላ  ማለቃቀስ ሳይሆን ቅድሚያ ጥንቃቄም ሆነ እርምጃ ይውሰድ፤
* ባንኮች እንዳይዘረፉ ጥበቃ ያድርግ፤  በአጋጣሚ ከተዘረፈም በፍጥነት ምርመራና ክትትል በማድረግ ወደ ፍትሕ ተቋም ያቅርብ ማለት ነው። 
—–
 በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን አሁንም ስርዓት አልበኝነት መቀጠሉንና ታጣቂዎች ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን መዝረፋቸውን መረጃዎች ያመለክታል።
በምዕራብ ወለጋ ጊሊሶ ወረዳ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አይራ ቅርንጫፍ ላይ ታጣቂዎች ዝርፊያ አካሂደው ስምንት መቶ ሰማንያ ስድስት ሺህ ብር መዝረፋቸው ታውቋል።
ታጣቂ ዘራፊዎቹ ወንጀሉን በሚፈፅሙበት ወቅት የአካባቢው ፖሊስ እርምጃ ለመውሰድ ዘገምተኛ መሆኑንም ጉዳዩን የሚያውቁ ይናገራሉ። ከቀናት በፊት የተዘረፈው የንግድ ባንክ አይራ ቅርንጫፍ ከከተማይቱ ፖሊስ ጣቢያ ብዙም ሳይርቅ የሚገኝ ቢሆንም ዝርፊያውን ለማስቆም መድረስ እንዳልቻለ ምንጮቻችን ጠቁመዋል። ዘራፊዎቹም ማንነታቸውን ለመደበቅ ሙከራ እንኳ አለማድረጋቸውን እማኞች ያስረዳሉ።
ዘራፊዎቹ በባንኩ ሰራተኞች ላይ ድብደባ የፈፀሙ ሲሆን 886,000 ብር ወስደው ሄደዋል። የንግድ ባንክ አይራ ቅርንጫፍ ቀደም ሲል ስድስት መቶ ሺህ ብር ተዘርፎ ለሶስት ወራት ያህል ተዘግቶ የነበረ ቅርንጫፍ ነው።
በጥር ወር መጀመሪያ ላይ በኦሮሚያ በሁለት ቀናት ውስጥ አስራ ሰባት ባንኮች ተዘርፈው እንደነበር ይታወሳል።
በምዕራብ ወለጋ ግድያ ዝርፊያን ሰርዓት አልበኝነት በስፋት የሚታይ መሆኑን የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች የመከላከያ ሰራዊት በኣአካባቢው ቢኖርም ተመጣጣኝ እርምጃ እየወሰደ አይደለም። ይልቁንም የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ላይ ታጣቂዎች ጥቃት ለማድረስ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርጉ ታይተዋል። በሰራዊቱና በታጣቂዎቹ መካከል ውጊያ ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ነዋሪዎች ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
* ዕለት ዕለት ቦታ እየቀያየሩ፣ ለዚያውም ተደራጅተው፣ ሕዝብን የሚገድሉ፣ የሚያሸበሩ ቡድኖችን መንግስት ልክ ባለፈ ትእግስት አልያም እዚህ ላይ በማይገለጽ ምክንያት ዝም በማለት ዜጎችን ለአደጋ እያጋለጠ ነው።
መንግስት እንደመሆኑ አስቀድሞ እንዲህ ዓይነት የሽብር ቡድኖችን ይቆጣጠር። ባለመቆጣጠሩ ዜጎች የሕይወት ዋስትና እያጣ –  እየገደሉ፣ እየዘረፉ፣ ሀብት ንብረት እየመወደሙ ያሉ ቡድኖችን ቀድመው እንዳይፈጽሙ፣ በድንገት ከፈጸሙ ደግሞ በአፋጣኝ በሕግ መሠረት እርምጃ ይውሰድ ማለት ነው። ዜጎች ለአደጋ ተጋለጡ ነው ጥያቄው።
* መንግስት ሕግ የማስከበር ግዴታውን ይወጣ ማለት የፀጥታ ኃይሉ እንዳሻው  ዜጎች ላይ ይተኩስ፣ ይግደል ወዘተ…. ማለት በፍጹም ሊሆን አይችልም። አቅም አለው ወይስ የለውም የሚለው ጸጥታ፣ ሰላም፣ ደኅንነት የማስከበር አቅም ማለት ነው። ቀድሞ መረጃ በመሰብሰብ ወንጀል እንዳይፈፀም የመከላከል፣ በአገሪቱ ግዛት ሁሉ የሚገኙ የወንጀል ቡድኖችን መቆጣጠር የሚያስችል የሰው ኃይል፣ የቴክኖሎጂ፣ የአሠራር፣ የተቋም ወዘተ ስብጥር የሆነ አቅም (Regulative Capability) ማለት ነው።
* መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን ይወጣ ሲባል ዜጎች እንዳይፈናቀሉ መጠበቅ አለበት። አፈናቃዮችንም ለሕግ ማቅረብና እርምጃ መውሰድ አለበት ማለት ነው። አፈናቃዮችን ወደ ፍትሕ ሥርዓቱ ለማምጣት ዳተኛ መሆን የለበትም ማለት ነው።
* መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን ይወጣ ሲባል፣ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ተንደላቆ እየኖረ ቀን ከሌሊት እረብጣ ብር እየረጨ ሕዝብን እያጫረሰ ያለን ሰው እርምጃ ውሰድ፤ አንዳንዱን በመተው አስገዳይ፣ ሌላውን እንዲሞት መንግሥት እያመቻቸ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ዳተኝነት ይተው ማለት ነው።
*ሕግ የማስከበር ሥራ መቼም ቢሆን ፣ ለአፍታም እንኳን፣ አይቋረጥ፣ ፖሊሱ፣ ዓቃቤ ሕጉ፣ ደኅንነቱ ወዘተ ሥራው በትክክል ይሥራ፣ በሌላ ጊዜ ከእንደገና ‘ሀ’ ተብሎ የሚጀመር ሥራ አይደለም። የሽግግር፣ የለውጥ ጊዜ ስለሆነ ጉልበተኛ ይዝረፍ፣ ይግደል…. ማለት አይደለም። የሚሞት የራሱ ጉዳይ ይሙት ማለት አይደለም። በማን ሞት ላይ ነው ሽግግር እና ለውጥ የሚመጣው?
* የዜጎችን በየእለቱ መፈናቀል፣  መሞት፣ አካልና ንብረትን ማጣት  ‘ናቹራል’ ማለት እንደ እውነቱ “unnatural” ነው የሚመስለኝ። የዜጎችን  እልቂትን በማናቸውም ሁኔታ የማይቀር፣ የሚያጋጥም፣ የሚጠበቅ ነው ብሎ ማመን/ መውሰድ በዜጎች እልቂት ላይ ተባባሪ ገዳይ መሆን ነው። ጎልቤዎችና ወመኔዎች እንዳሻቸው ሊገድሉ ቢችሉም የለውጥ ወቅት ነው natural ነው ማለትን  መንግሥት ይተውና ጎልቤዎችንና ወኔንዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል የዜጎችን ደኅንነት ያስጠብቅ ማለት ነው። ሌሎች ነጥቦችንም መጨመር ይቻላል!
Filed in: Amharic