>
5:13 pm - Monday April 19, 6624

ማልኮም ኤክስ (Malcom X) (ዶ/ር ምህረት ደበበ

ማልኮም ኤክስ (Malcom X)
ዶ/ር ምህረት ደበበ
በስድስት አመቱ አባቱ በነጭ ዘረኞች ተገደሉ። ከሰባት አመት በኋላም በአእምሮ ሆስፒታል ውስጥ እንዳሉ፡ እናቱ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ። ሌላ መሄጃ የሌለው ይህ ጥቁር አሜሪካዊ፡ ከማደጎ ቤት ወደ ማደጎ ቤት ሲሸጋገር ልጅነቱን ጨረሰ። ገና የሀያኛ አመቱን ልደት ሳያከብር፡ የሰው ቤት ሰብሮ በመግባትና በስርቆት ተከሶ፡ ከእስር ቤት
ተወረወረ ። ከስድስት አመት በኋላም ከእስራቱ ሲፈታ፡ ወጣቱ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ ነበር።
 የለውጡ አብይ ምክንያት ሲጋራ ማጨስ ማቆሙ፡ የአሳማ ስጋን መብላት መተዉ፡ የሚጻጻፋቸው ደብዳቤዎች ወይንም ደግሞ የ”Nation of Islam” አባል መሆኑ አልነበረም። ወዳጆቹ፡ የጥቁሮች መብት ተከራካሪ፡ ነጮችንም በጥቁሮች ላይ ለፈጸሙት በደል ተፋራጅ እያሉ የሚያሞግሱት፡ ጠላቶቹ ደግሞ ዘረኝነትን እና ሁከትን ሰባኪ እያሉ የሚተቹት ማልኮም ኤክስ፡ ”The Autobiography of Malcolm X” በሚለው የግል ህይወቱን በሚተርከው መጽሀፉ ውስጥ ህይወቱን ምን እንዳዳነው እራሱ እንዲህ ይነግረናል፦
“በአካል ያገኙኝ፡ በቴሌቪዥን የተከታተሉኝ ወይንም ደግሞ የጻፍኩትን ያነበቡ፡ ከስምንተኛ ክፍል በእጅጉ ርቄ የኮሌጅ ትምህርት ሁሉ እንደተከታተልኩ ሊያስቡ ይችላሉ።
 እውነታው ግን ያስተማረኝ እና የሞረደኝ እስር ቤት ነው።”
“በእስር ቤት ቆይታዬ ቢምቢ ከሚባል እስረኛ ጋር ተዋወቅኩ። ከእስረኞቹ ሁሉ በሙሉ፡ ጥሩ አስተያየት የነበረኝ ለሱ ብቻ ነው። ቢምቢ የወህኒ ቤቱ፡ ቤተ መጽሀፍት ቋሚ እና ዋነኛው ደንበኛ ነበር። በማንኛውም ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ያለውን ዝርዝር እውቀት ስመለከት፡ እደነቅም፡ እቀናም ነበር። በቃላት ብቻ ክብሩን ሲያስጠብቅ ያየሁት የመጀመሪያው ሰውም ቢምቢ ነበር።”
“ሁሌም ከስራ መልስ አንድ አስራ አምስት እስረኞች ሆነን፡ ቢንቢን ከበን እንቀመጣለን። ‘ምን ታውቅና?’ ለሚለው ንቀት-አዘል አስተያየት፡ በቸልታ መልስ ሳይሰጥ ያየሁት አንድ እስረኛ፡ ቢምቢን ብቻ ነበር። በተለምዶ ነጭ እስረኞች፡ ለጥቁር እስረኞች አስተያየት ብዙም ግድ የላቸውም። ቢምቢ ሲናገር ግን፡ ጠባቂዎቻችን ሳይቀር እሱን ለመስማት ያሰፈስፋሉ፤ ጆሮዋቸውንም ይጥላሉ።”
“ቢምቢም ያላሰብነውን ርዕሰ ጉዳይ ዱብ ያደርግና በኛ እና ከእስር ቤቱ ውጪ ባሉት ሰዎች መሀል ያለው ልዩነት እኛ መያዛችን ብቻ መሆኑን ያስገነዝበናል። ቢምቢ ግልጽ እስኪያደርግልን ድረስም Henry David Thoreau ስለተባለው ጸሀፊ ሰምቼ የማላውቀው እስረኛ፡ እኔ ብቻ አልነበርኩም።”(በዚህ አጋጣሚ Thoreau በሁለት መጽሀፍቶቹ ይበልጥ ይታወቃል—Walden እና Civil Disobedience። በተለይ civil disobedience የተሰኘው መጽሀፍ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞን እንዴት መግለጽ እንደሚቻል የሚያስገነዝብ፡ ጋንዲ እና ማርቲን ሉተር ኪንግም ጽንሰ-ሀሳቡን በተግባር ያዋሉት፡ ድንቅ መጣጥፍ ነው) “ቢምቢ ስለ ሀይማኖት ማውራት ሲጀምር ይበልጥ ቀረብኩት።
ከዛ በፊት እራሴን ከፈጣሪ በላይ አድርጌ ነበር የምመለከተው—ሰይጣን ነበርኩ። የሱ ማስተዋል ሲልቅብኝ፡ ሲረቅብኝ ግን፡ አለማመኔን እርግፍ አድርጌ ተውኩት።”
“ከእለታት አንድ ቀንም፡ እንዲያው በድንገት ጥሩ ጭንቅላት እንዳለኝና፡ የእስር ቤቱን የርቀት ትምህርትና የቤተ መጽሀፍት አገልግሎት እንድጠቀም መከረኝ። ሌላ እስረኛ እንዲህ ቢመክረኝ ኖሮ እጣላው ነበር፤ ከቢምቢ ጋር ግን ማንም አይጣላም።“
”ድሮ፡ ከስምንተኛ ክፍል ትምህርቴን ሳቋርጥ፡ ሰዎችን ከመዝረፍና ከማወናበድ በቀር ሌላ ጉዳይን የተመለከተ ነገር ዳግም እማራለሁ ብዬ አስቤም፡ አልሜም አላውቅም። ከዚያ በፊት የተማርኩትንም፡ ጎዳናው እና ውንብድናው ሙልጭ አድርጎ አጥፍቶታል። ምኑንም ከምኑ ለይቼ አላውቅም። እህቴም እንግሊዝኛ ቋንቋን እና የጽሁፍ ዘዴን በእስር ቤቱ ውስጥ እንድማር ሀሳብ አቀረበችልኝ። ከዚህ በፊት በጎዳና ላይ አደንዛዥ ዕጽ በምሸጥበት ወቅት፡ የላኩላትን ፖስትካርዶች አንብባ መልእክቱን መረዳት
አልቻለችም ነበር።“
”በዚህም መሰረት አሁንም ቢሆን በቂ ግዜ እንዳለኝ በማመን፡የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርቴን በትኩረት መከታተል ጀመርኩኝ። በእስር ቤቱ ውስጥም፡ መጽሀፍት ከክፍል ክፍል ሲዞሩ፡ ያልተወሰዱትንና ይበልጥ የሳቡኝን መርጬ እወስዳለሁ።“
”በትምህርቴ ገፍቼ መልመጃዎቹን በብቃት መስራት ስጀምር፡ ረስቼያቸው የነበሩት የሰዋሰው ህግጋት ቀስ በቀስ፡ ትዝ እያሉኝ መጡ። በግምት ከአንድ አመት በኋላም፡ ምንም ግድፈት የሌለው ደብዳቤ መጻፍ ቻልኩኝ።”
“የታሰርኩበት Norfolk Prison Colony እየተባለ የሚጠራው ወህኒ ቤት፡ ከሌሎች እስር ቤቶች የላቀ፡ በንጽጽርም የተሻለ፡ ህይወትንም በተስፋ የሚሞላ ቦታ ነበር። ከሁሉም ከሁሉም ግን የእስር ቤቱ ቤተ-መጽሀፍት ድንቅ የሚባል ነበር።
አንድ ፓርክኸርስት የሚባል ሚሊየነር በሞት ሲለይ፡ የራሱን ቤተ-መጽሀፍት ለእስር ቤቱ ተናዘዘ—ምናልባት የእስረኞችን ጠባይ ከማረም አንጻር ፍላጎት ሳይኖረው አይቀርም። በተለይ ለታሪክ እና ለሀይማኖት ትምህርት፡ ትኩረት ይሰጣል። በሺህ የሚቆጠሩ መጽሀፍቶቹ፡ ቤተ-መጽሀፍታችንን አጨናንቀውታል፤ ቦታ ጠፍቶላቸው በሳጥን ውስጥ እንደታሸጉ የተቀመጡ መጽሀፍቶችም የትየለሌ ናቸው። በNorfolk ማንም እስረኛ ቢሆን ፍቃድ ጠይቆ ወደ ቤተ መጽሀፍቱ መግባትና፡ ከመደርደሪያው ላይ ፈልጎም የሚፈልገውን መጽሀፍ መርጦ መውሰድ ይቻል ነበር።
በመቶ የሚቆጠሩ ባለ ትላልቅ ቅጽ መጽሀፍት፡ አንዳንዶቹም በቀላሉ የማይገኙም
ነበረቡት። ማንበብ ስጀምር ያገኘሁትን ሁሉ ዝም ብዬ ነበር የማነበው፤ ከጊዜያቶች በኋላም ርዕስ መርጬ፡ እንዴት በአትኩሮት ማንበብ እንዳለብኝ እየተለማመድኩ መጣሁ።“
”ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት የቢምቢ ዘርፈ-ብዙ እውቀት ያስቀናኝም፡ እንደሱ ለመሆንም እጥር ነበር።
 ነገር ግን ለማንበብ የሞከርኳቸው መጽሀፍት ሁሉ፡ ከጫፍ እስከጫፍ ወይንም ጥቂት፡ ትርጉማቸውን የማላውቃቸው ቃላትንና አረፍተ ነገሮችን ይይዙ ነበር፤
ጭራሽም በሌላ በማላውቀው ቋንቋ የተጻፉ ይመስል ትርጉማቸው ግራ ያጋባኝ ነበር። ብዙ ቃላቶችንም እያለፍኳቸው ሲመጣ፡ ስለ መጽሀፉ ያለኝ ጠቅላላ ሀሳብና መረዳት እያነሰብኝ መጣ።“
”በመጨረሻ ግን ፍንትው ብሎ የታየኝ ሀሳብ መዝገበ-ቃላትን መጠቀም ነበር—አዳዲስ ቃላትን ለማወቅና ለማጥናት። ቀጥ ባለ መስመር ለመጻፍ እንኳን ስለማልችል፡ የጽህፈት ችሎታዬን ማሻሻል እንደሚገባኝም ተገነዘብኩ። ከወህኒ ቤቱ አስተዳደርም መጽገበ ቃላትና እርሳስ በጥያቄዬ መሰረት ተሰጠኝ“
”ለሁለት ቀናት ያህልም፡ የተሰጠኝን መዝገበ ቃላት በነሲብ ሳገላብጥ ቆየሁ። ይህንን ያህል ቃላትም በእርግጥ መኖራቸውን አስተውዬ አላውቅም ነበር!የትኛዎቹን ቃላት ማወቅና ማጥናት እንዳለብኝ እንኳን አልተገነዘብኩም። ግን አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ በማመን፡ መገልበጥ ጀመርኩኝ።“
”በጣም እየተጠነቀቅኩ፡ በዝግታ በምጽፈው የእጅ አጣጣሌ፡ በመዝገበ-ቃላቱ የመጀመሪያ ገጽ ያሉትን ቃላት በሙሉ ከነስርዓተ-ነጥቡ፡ በወረቀት ላይ ገለበጥኩኝ። አንድ ቀን ሙሉ ሳይወስድብኝ አልቀረም። ከዚያም የጻፍኩትን በሙሉ አንድም ሳላስቀር፡ ለራሴ ጮክ ብዬ ማንበቡን ተያያዝኩት። ደጋግሜም የራሴን የእጅ ጽሁፍ ለራሴ ማንበቤን ቀጠልኩበት”
“በሚቀጥለው ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃም ስለነዛ ቃላት እያሰብኩ ነበር—በጣም ብዙ መጻፌም ብቻ ሳይሆን ከነመፈጠራቸው የማላውቃቸውን ቃላት ጭምር መገልበጤ ለራሴ ኩራት ፈጠረልኝ። የቃላቶቹን ትርጉምም ከትንሽ ጥረት በኋላ ማስታወስ ችዬ ነበር።
ያላስታወስኳቸውን የቃላት ትርጉሞችም ከለስኩኝ“
”በጣም በመደነቄም፡ ከሚቀጥለው የመዝገበ ቃላቱ ገጽ ላይ ያሉትን መገልበጥ ቀጠልኩ። በየእንዳንዱ ተጨማሪ ገጽ ስለ ሰዎች፡ ቦታዎች፡ እንዲሁም የታሪክ ክስተቶች እያወቅኩ መጣሁ። እንደ እውነቱ ከሆነ መዝገበ ቃላቱ የመለስተኛ ኢንሳይክሎፒዲያን ያህል ነበር። በዚሁ አይነት በአጠቃላይ የእስር ቤቱ የቆይታ ጊዜዬ፡ ከአንድ ሚሊየን ያላነሱ ቃላትን ጻፍኩ።“
”የቃላት አቅሜ እየጎለበተ ሲሄድ፡ ማንኛውንም መጽሀፍ አንብቤ ሀሳቡን ለመረዳት እየቀለለኝ እንደሚመጣ ግልጽ ነው። ብዙ መጽሀፍትን ያነበበ ሰውም፡ በምናብ የሚከፈቱ አዳዲስ አለሞች መኖራቸውን ይረዳል።ይህንንም እነግራችኋለሁ እነሆ ከዚያን ግዜ ጀምሮ እስር ቤቱን እስከምለቅበት ቅጽበት ድረስ፡ በነበረኝ ትርፍ ሰአት ሁሉ፡ ሁሌም እያነበብኩኝ ነበር፤ ቤተ መጽሀፍቱ ውስጥ እያነበብኩኝ ካልሆነ፡ አልጋ ላይ ተኝቼ እያነበብኩኝ ነኝ ማለት ነው። ከመጽሀፍት ጋር በተአምር እንኳን ማንም ሊያላቅቀኝ አይቻለውም ነበር።
ለወራትም ወንድሞቼ እየጠየቁኝ፡ ትምህርቴንም እየተከታተልኩ፡ መጽሀፍቶችንም እያነበብኩ፡ ከነጭራሹ መታሰሬንም ረሳሁ። እንደውም በመላው የህይወት ዘመኔ፡ እንደዚህ ነጻነት ተሰምቶኝም አያውቅም“
”የወህኒ ቤቱ ቤተ መጽሀፍት፡ ህንጻውን ከትምህርት ቤቱ ጋር ይጋራል። ከሀርቫርድና ቦስተን ዩኒቨርስቲዎች ጭምር በመጡ መምህራን አማካኝነት ትምህርት ይሰጣል። ሳምንታዊው የእስረኞች ክርክርም እዚሁ ይካሄዳል።
 ‘ህጻናት ወተት ሊሰጣቸው ይገባልን?’ አይነት ርዕሰ-ጉዳዮች፡ ስሜታዊ እስረኞች የሚያደርጉት የጋለ ክርክር በጣም ያስደንቃል”
“በእስር ቤቱ የመጽሀፍት መደርደሪያ ላይ፡በማንኛውም ርዕሰ-ጉዳይ ላይ የተጻፉ መጽሀፍት አይጠፉም። ሚሊየነሩ ለቤተ መጽሀፍቱ ካበረከታቸው በሺህ የሚቆጠሩ አሮጌ መጽሀፍት፡ አብዛኞቹ አሁንም በሳጥን እንደታሸገባቸው ከጀርባ ተቀምጠዋል። አንዳንዶቹ ጥንታዊ፣ ሽፋናቸው የተላላጠና የደበዘዘ ናቸው። ቀደም ብዬ እንደገለጽኩላችሁ መጽሀፍቱን የለገሰው ፓርክኸርስት፡ የሀይማኖትና የታሪክ መጽሀፍት ላይ ያተኩራል። ገንዘቡም ፍላጎቱም ስለነበረው በቀላሉ ከገበያ የማይገኙ ብዙ መጽሀፍት ከእርሱ ስብስብ ውስጥ ነበሩ።
ይህንን ስብስብ ማግኘት የሚችል ማንኛውም ተቋም፡ ኮሌጅ እንኳን ቢሆን፡ በጣም እድለኛ ነው”
“በቀላሉ መገመት እንደሚቻለውም፡ የጠባይ ማረም ከፍተኛ ትኩረት ከሚሰጥባቸው እንደ እስር ቤት ባሉ ተቋማት፡ የማንበብ ልምድ ይበረታታል። በደንብ ያነበቡ፡ በተለይ ደግሞ በክርክር የሚሳተፉ እስረኞች ቁጥር ቀላል አይደለም። እንደውም አንዳንዶቹ ‘ባለ ሁለት እግር ኢንሳይክሎፒዲያዎች’ ተብለው ይጠራሉ። የዝነኛ ሰዎችን ያህል ትኩረትም ይስቡ ነበር። ማንበብና መረዳት ስችል፡ አዲስ አለምም ሲከፈትልኝ፡ ያነበብኳቸው መጽሀፍት፡ ማንኛውም የዩኒቨርስቲ ተማሪ እንዲያነብ ከሚጠበቅበት የመጽሀፍት ብዛት በእጅጉ የላቀ ነበር።“
”ከቤተ መጽሀፍቱ በላይም በክፍሌ ውስጥ በብዛት አነብ ነበር። በብዛት እንደሚያነብ የታወቀለት እስረኛም ብዙ መጽሀፍትን ከቤተ መጽሀፍቱ መውሰድ ይፈቀድለት ነበር። ከሰዎች ተለይቼ፡ በክፍሌ ውስጥ ብቻዬን ማንበብን እመርጥም ነበር“
”በንባቤ ተመስጬ ባለሁበት ከምሽቱ አራት ሰአት ላይ መብራቱን ሲያጠፉት ሁሌም እበሽቅ ነበር። እንደ እድል ሆኖ ግን፡ ከክፍሌ ፊትለፊት ሆኖ ብርሀን የሚሰጥ የኮሪደር መብራት ነበር። ብርሀኑን አይኔ ከለመደው በኋላም፡ ለማንበብ በቂ የሚባል ያህል ነበር። ስለዚህ ዘወትር ‘መብራት ጠፍቷል’ ተብሎ ሲለፈፍ ወለሉ ላይ ተቀምጬ ማንበቤን እቀጥላለሁ።”
“በየአንድ ሰአቱ ልዩነት፡ ጥበቃዎች ከክፍል ክፍል ሲዞሩ ዘልዬ ከአልጋው እወጣና እንቅልፌን የተኛሁ እመስላለሁ። ፍተሻው ሲጠናቀቅም ተመልሼ ከአልጋው እወርድና፡ ብርሀኑ በሚደርስበት የወለሉ ጫፍ ሆኜ እንደገና ማንበቤን እቀጥላለሁ—ጥበቃው
ተመልሶ መጥቶ እስከሚጎበኝበት የ58 ደቂቃዎች ግዜ ድረስ። በዚሁ አይነትም እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ወይም አስር ሰአት ድረስ አነባለሁ። የሶስት ወይም የአራት ሰአት እንቅልፍ በጣም በቂዬ ነበር።”
Filed in: Amharic