>

ከአድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያ ያተረፈችውና ያጎደለችው (አምባሳደር ዓለማየሁ አበበ ሸንቁጥ)

ከአድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያ ያተረፈችውና ያጎደለችው

 

አምባሳደር ዓለማየሁ አበበ ሸንቁጥ

ከአድዋ ድል በኋላ ምን ተረፈን ምን ጎደለን በተከታታይ የአስተዳደሩን መሪውን የጨበጡት ለሕዝብ ምን ቱርፋት አስገኙላት ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ በሚከተለው የቀረበው ይሆናል፡፡

እናት አገራችን ለሺ ዘመናት ነጻነቷን ጠብቃ ለመኖሯ ቀደም ሲል በቅዱስ መጽሐፍ ስሟ ሲጠቀስ የኖረች በኋላም የእስልምና ሃይማኖት መሪና መሥራች ነቢዩ መሐመድ በሕግ የምትተዳደርና ፍትህ የሰፈነባት ሠላማዊ አገር መሆኗንና ተከታዮቻቸው ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ መጠለያ እንደሚያገኙ በመምከር እንደላኩዋቸውና ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በሠላም እየኖሩ እምነታቸውን ማራመዳቸውና ማስፋፋታቸው ይታወቃል፡፡

ነጻነቷን ለመግፈፍ፤ በለም መሬቱዋ ለመጠቀም በነፋሻ አየሩዋ ለመደሰት በሕዝቡዋ ጉልበት ተጠቅሞ የየአገሮቻቸውን ሕዝቦች ኑሮ ለማሻሻል ከቅርብም ከሩቅም ዓይናቸውን ኢትዮጵያ ላይ ያማተሩና በሐይላቸው ተመክተው ጦራቸውን የሰበቁ በርካታ አገራት ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ውርደትን መሸከም የማይፈልግ ነጻነቱን እንደዓይኑ ብሌን የሚንከባከባት በመሆኑ በየዘመኑ ጦር የመዘዙብንን መክቶ ሕዝቦችዋ ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ነጻነታቸውን አስከብረዋል፡፡

በ1800 ዎቹ የአውሮፓ መንግሥታት ለየአገሮቻቸው ብልጽግናን ለማጎናጸፍ በመመኘት ድንግል መሬት የሚገኝበትን አፍሪካን ለመቀራመት በጀርመን አገር በርሊን በተባለ ከተማ በስብሰባ ተቀምጠው ከፊታቸው የዓለም ካርታ ዘርግተው የአፍሪካን መሬት ሸንሽነው በተከፋፈሉበት ወቅት የጣሊያን መንግሥት ኢትዮጵያን በመመኘቱ ከዚያ ወቅት ጀምሮ ጣሊያን ኢትዮጵያን ወራ ለማስገበር ዝግጅት ጀመረች፡፡

ኢትዮጵያዊያንን አውሮፓዊያን በተለይም ጣሊያንና እንግሊዝ “Barbarian” ማለትም አረመኔዎች አድርገው ስለሚያዩን ኢትዮጵያን እናሰለጥናለን በማለት ይፎክሩ እንደነበር ብዙ መረጃዎች አሉ፡፡

ቀደም ሲል ኢትዮጵያና ጣሊያን በመልካም ግንኙነት ላይ ስለነበሩ መልዕክተኞች ይለዋወጡ ነበር፡፡ በመሃላቸው ንግድም ይካሄድ ነበር፡፡ መልካም ግንኙነትም ስለነበር አፄ ምኒልክ ቀደም ሲል በርከት ያለ መሣሪያና ጥይቶች ከጣሊያን ላይ መግዛታቸው ይታወሳል፡፡

በነገራችን ላይ በ1920 ዎቹ ፋሽስት ኢጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር ስትዘጋጅ በኢትዮጵያ በኩል አገር ለመከላከል የሚያስችል የጦር መሣሪያ ለመግዛት ዝግጅት አለመደረጉ የጣሊያን ጦር ሳይገታ አዲስ አበባን ሰተት ብሎ በመግባት ይዙዋል፡፡

አንድ የጣሊያን መልዕክተኛ ኮነትአንቶሊኒ የተባለ ከንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ጋር በፈጠረው መልካም ግንኙነት እንደልቡ ቤተመንግሥት ይገባ ይወጣ ስለነበር በሁለቱ አገሮች መካከል በመቻቻል በሠለም የሚያስኖራቸው ስምምነት እንዲመሠረት፤ ሁለቱም ሠላማዊ ግንኙነትን ለማጠናከር እንደሚፈልጉ ምኞታቸውን በመግለጣቸው የስምምነት ሰነድ በተዘጋጀበት ወቅት ኢትዮጵያ ቀና መንገዱን በመያዝ ሁለቱን አገሮች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ስትሻ ፤ ጣሊያን በሠላማዊ ስምምነት ሽፋን ኢትዮጵያን ለባርነት የሚዳርግ ሰነድ ቀርጻ የስምምነቱ ሰነድ ውጫሌ በተባለች መንደር ተፈረመ፡፡

የጣሊያን መልዕክተኛ ባቀረበውና በተፈረመው ሰነድ ኢትዮጵያ ከውጭው ዓለም ጋር የምታደርገው ግንኙነት በጣሊያን መንግሥት ብቻ እንዲሆን የተስማማች አስመስሎ በሸፍጥ በጣሊያንኛ ቋንቋን በመቅረጽ፤ የአማርኛውን ሰነድ ግን ኢትዮጵያ ከውጭ ዓለም መንግሥታት ጋር ለምታደርገው ግንኙነት የጣሊያን መንግሥት መርዳት እንደምትችል የሚገልጥ ሆኖ በመቀረጹ በሁለት አገሮች መካከል የማይታረቅ ትልቅ ውዝግ ብንፈጥር፡፡ ማንኛውም መንግሥት አስገዳጅ ችግር ካልደረሰበት በስተቀር በሠላማዊ መንገድ ልዑላዊነቱን አሳልፎ ለሌላ የሚሰጥ ሊኖር ይችላል ብሎ መገመት ያስቸግራል፡፡

ይህን ውዝግብ በጠረቤዛ ዙሪያ መፍታት አልተቻለም፡፡ የጣሊያን መንግሥት ተቻኩሎ ይህን ስምምነት ለአውሮፓ መንግሥታትበሙሉአ ስተላለፈው፡፡ ይህ ስምምነት በምንም መልኩ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት እንደሌለውና እንዲታረምም ከጣሊያን ልዩ መልዕክተኛ ጋር የተደረጉት ውይይቶች ፍሬ አልባ በመሆናቸው አፄ ምኒልክ ይህን ስምምነት ውድቅ አድርገው ለአውሮፓ መሪዎች ሁሉ በማስታወቃቸው ጣሊያን ቀደም ሲል በድብቅ ወደጠነሰሰችው ዓላማ በመሸጋገር ኢትዮጵያን ለመውረር ንቅናቄ ጀመረች፡፡ ቀደም ሲል ጣሊያን እግሯን አሰብ አስገብታ ስለነበር ከዚያ እየተንፏቀቀች የሰሜን ኢትዮጵያ ግዛት በቁጥጥሯ ሥር ማድረግ ጀመረች፡፡
ንጉሠ ነገሥት ምኒሊክ በኢትዮጵያ በተከሰተው የአየር መዛባት በሕዝብ ላይ የደረሰውን ችግርና ረሃብ በማጤን ወደ ጦርነት ማምራትን አልፈለጉም ነበር ግን ምኒልክ እንዳሉት የጣሊያን ጦር እንደ “ፍልፈል” በመንፏቀቅ መሬት መያዟን በመግፋት በትግራይ ያሉትን ከተሞችና መንደሮች ከሀይል ጠቅልላ በማያያዝ የኢትዮጵያን ልዑላዊነት በመድፈሯ አፄምኒልክ አገረ ገዢዎቻቸውን ወደ እንጦጦ ቤተመንግሥት አስጠርተው በመምከር የክተት አዋጅ አስነገሩ፡፡

አዋጁን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአራቱም ማዕዘናት ስንቁን በጀርባው መሣሪያውን በትከሻው አንግቶ አንድ ሞቶ ሺህ የሚደርሰው ሕዝባዊ ሠራዊት በባዶ እግሩ ወደ አድዋ ዘመመ፡፡ በዚያን ወቅት የጣሊያን ሠራዊት በዘመናዊ መሣሪያዎች ታጥቆ በአምባለጌ ተራራ ምሽጉን ሠርቶና አጠናክሮ ከሩቁ እየተጠባበቀ ነበር፡፡ አፄ ምኒሊክ አድዋ እንደደረሱ ለመጨረሻ ጊዜ ውዝግቡ በሠላም እንዲያልቅ ሙከራ ቢያደርጉም ትዕቢተኛው ጣሊያን በንቀት ጥሪውን ውድቅ አድርጎታል፡፡ ስለሆነም የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም ማለዳ ላይ ታላቁ ጦርነት ተከፍቶ ጣሊያን የዘረጋውን መሰናክሎች ሁሉ የኢትዮጵያ ሠራዊት ጥሶ ደሙን እያዘራ ኬላውን ሰብሮ የጠላትን ጉሮሮ በማነቅ እጀግአንጸባራቂ ድልን በአንድ ቀን የጦርነት ውሎ ተቀዳጅተዋል፡፡

ከታላቁ የአድዋ ጦርነት ድል የምንማረው እጅግ በርካታ እሴቶች አሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ ለዝንተ ዓለም ነጻነቷን ጠብቃ መኖሩዋን ከማረጋገጥ ባሻገር ለኢትዮጵያዊያን ልበ ሙሉነትን ያጎናጸፈ መሆኑን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተባብረው በአንድነት የሚኖሩና ጠላትን በአንድነት የሚመክቱ ሕዝቦች መሆናቸውን ያስመሰከረ ነበር ነውም፡፡

ሚና ሻሪ በሆኑት የምእራብ አውሮፓ ሀያላናን በተለይም የእንግሊዝና የአሜሪካን መንግሥታት ለኢሕአዴግ መንግሥት ድጋፋቸውን በመቸራቸው ከ28 ዓመት በፊት ሕዝብ ባልመከረበትና ባልዘከረበት የተዘረጋው በዘር ላይ መሠረት ያደረገ ፌዴራላዚም እራስን በራስማስተዳደር ጽንሰ ሃሳብን ያነገበ የተቀደሰ ዐላማን በጥላቻና በቂም በቀል ላይ በመጉዋዙ ለአገር አንድነት ችግርን ፈጥሩዋል፡፡ የአድዋውን መንፈስ የአንድነት መንፈስ የሚያላሽቅ ሆኖ ታይቱዋል፡፡

እነሆ የአድዋ ጦርነት ድልን የዛሬ 123 ዓመት ተጎናጽፈን ባለንበት ወቅት አገሪቱ ከችግር አላቆ ከመናቆር የሚያወጣን ለዜጎች ሁሉ ምቹ የሆነች አገር መዘርጋት አልቻልንም፡፡ ከዚያ አንጸባራቂ ድል በኋላ አገራችን በኤኮኖሚ በፖለቲካና በማህበራዊ ኑሮ በተሻለ ደረጃ ላይ ልንገኝ የሚገባንን ፖሊሲ መዘርጋት በተገባን ነበር፡፡ አፄ ምኒሊክ ለኢትዮጵያ እድገት አብዮታዊ እርምጃ መውሰድ አቅሙም ግንዛቤውም አልነበራቸውም፡፡ ያገራችን ሰው እንደሚለው ከልብ ካዘኑ እንባ አይገድምና በአውሮፓዊያን ስልጣኔ ልንቀናና ልንጠቀምበት በተገባ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ከአድዋ ጦርነት በኋላ በዓለም ዙሪያ ስሟ ገኖ ተዋቂነትም ተችሮዋታል፡፡ አፄ ምኒልክ ባላቸው ውስን እውቀት አንዳንድ ፈር ቀዳጅ የሆነ እርምጃዎችን በመውሰድ የሥልጣኔ ቱሩፋትን ዘርግተዋል፡፡ ያውም የመሳፍንቱና የቤተክርስቲያኗን አሉታዊ አስተያየት የሰይጣን ሥራ አመጡብን ተብለው እየተወገዙ፡፡ ሆኖም እነዚህ የተጠነሱስትና ተግባራዊ የሆኑት ወንዝ የሚያሻግሩ አልነበሩም፡፡

ከምዕራባዊያን ጋር የቀረበ ግንኙነት ፈጥሮ ለጠቅላላው ሕዝብ ተደራሽ የሆነ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ዝርጋታ ባለመኖሩ ሥልጣኔ እየተንቋቀቀ የሚሄድ እንጂ ፈጣንና አድማሱ የሰፋ አልነበረም፡፡

ከአጼ ምኒልክ በኋላ የእያሱና የዘውዲቱ አገዛዞች ሕዝብን የማበልጸግ ዓላማ መዘርጋት ቀርቶ ደህንነቱዋን እንኳን ለመጠበቅ የመምራት ብቃት ባለመኖሩ ለውይይት የሚበቃ ባለመሆኑ እንለፈውና ዙፋኑ አፄኃይለሥላሴ እጅ ሲገባ የዘመኑን ሥልጣኔ ለመገንዘብና ፈጣን እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችላቸው ጊዜ ቢሆንም በወቅቱ ስላልተጠቀሙበት እሰካሁንም ስንዳክር ቆይተናል፡፡ የእድገት አቅጣጫ በአዝጋሚ መልኩ በመካሄዱ የዘመኑን ትውልድ ሊያቅፍ ባለመቻሉ በወታደራዊ ኃይል መንግሥት ተለውጦ ከእጅ አይሻል ዶማ በመሆኑ የኢትዮጵያ እድገት ፎቀቅአላለም፡፡ ከአድዋ ድል በሁዋላ ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘመኑን በመከተል ተራምዳ ቢሆን ዜጎቹዋን በእኩልነት ለማበልጸግና ወደፊት ለመገስገስ ያስችላት ነበር፡፡

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት የዓለም ፖለቲካ ሁኔታ ውስብስብ ባልነበረበት ወቅት እድሉን ተጠቅሞ አገሪቱን ወደፊት ከማራመድ ይልቅ በጥቃቅን ለውጦች ላይ በማተኮሩ የትም የሚያደርስ አልሆነም ፡፡ የኮሎኔል መንግሥቱ መንግሥትም የኤኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮን እድገት የሚያፋጥንና የሚያመጣ የልማት ፕሮጄክቶች አልዘረጋም፡፡ ስለሆነም ሁለቱም ሥርዓቶች ሠፊውን ሕዝብ ባለሀብት ለማደረግ የሚያስችል ቅያስ አልነበራቸውም፡፡ ከዚህም በላይ የህዝቡንና የተፈጥሮ ሀብቱን የሚያበለጽግ ፕሮጄክት አልዘረጉም፡፡ ይህን ሥርዓት ተከትሎ የመጣውም ብልጽግና በሌለበት በዘር ላይያተኮረ አስተዳደራዊ መዋቅር መዘርጋቱ ከችግር የሚገላግል መስሎ ቀርቧል፡፡
ስለሆነም የኢሕአዴግ መንግሥት ዘርን በግንባር ቀደምትነት አንግቦ የዘረጋው የተደበቀ ቦምብ ይመስል እዚህም እዚያም መፈንዳት የጀመረው የጥላቻ ጥንስስ በመዘርጋቱ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን ከአንድ አውሮፓ ኃይል ጋር ጦርነት ውስጥ ገብተው በአሸናፊነት በመውጣታቸው የጃፓን ሕዝብ ነጮችም ይሸነፋሉ ወይ በሚል ለኢትዮጵያዊያን እጅግ ከፍተኛ ክብርና ሞገስ አጎናጽፈውላቸዋል፡፡ እንዲያውም እ.አ.አ. በ1904 ዓ.ም. ከራሻ ጋር ጦርነት ከፍተው የልብልብ የተሰማቸው ጃፓናዊያን የራሻን ጦር በአሸናፊነት ተወጥተዋል፡፡

ሙሶሊኒ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ጃፓኖች ከኢትዮጵያ ጎን በመሰለፍ በሺ የሚቆጠር የሳሞራይ ጎራዴ ወደ ኢትዮጵያ በመላክ አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡

ጃፓናዊያን ለሥልጣኔ በነበራቸው ከፍተኛ ጉጉት አጠቃላይ ሕዝቡን ተጠቃሚ እንዲሆን በነበራቸው ራዕይ ከምዕራቡ ዓለም ጋር በፈጠሩት ግንኙነት ፈጣን የኤኮኖሚ እድገት ማሳየታቸው ክቡር ዶክተር ከበደሚካኤል “ጃፓን እንዴት ሠለጠነች” በሚል ያሳተሙት መጽሐፍ አቅጣጫ ጠቁዋሚ ሃሳቦችን ዘርግተዋል፡፡ በ1923 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የተዘረጋው ሕገ-መንግሥት የጃፓንን ሕገመንገሥት መሠረት አድርጎ የተነደፈ ቢሆንም የሥልጣኔውን አካሄድ ግን አልተከተልነውም፡፡

አፄኃይለሥላሴ ከዳግማዊ ምኒልክ የልማት አካሄድ በተሻለ መለኩ ሊንቀሳቀሱ ቢችሉም የአገሪቱን ሁዋላቀርነት ሊቀርፍ የሚችል እርምጃ ባለመውሰዳቸው ወደኋላ ቀረን የሚለው የነቃ የሰው ኃይል በኃይል አገዛዙን ለማስወገድ የተለያዩ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ የጄ/ መንግሥቱ ንዋይና የደጃ/ታከለ ሙከራዎች የሕዝብን ተጠቃሚነት መሠረት ያደረጉ እንደነበር የታሪከ ተመራማሪዎች ይገልጣሉ፡፡

እንደረጋው ሃባለበት የሚቆም መንግሥት ጊዜውን ጠብቆ መወገዱ የታሪክ ሂደት ነውና በ1966 ዓ.ም. የተቀሰቀሰው የሕዝብ አመጽ የዘውዱን ሥርዓት ከሥሩ መንገሎ ጣለው፡፡

ከእጅ አይሻል ዶማ ሆነና የተተኩት መንግሥታት ለህዝብ መቆማቸውን በይፋ ይለፍልፉ እንጂ የባለታሪኩዋን አገር ሕዝቦች ከድህነት ከድንቁርና ከእርዛት በአጠቃላይ ከዘመኑ የሥልጣኔ ቱሩፋት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የዘረጉት አቅጣጫ ፎቀቅ ባለማድርጉ የዛሬ 123 ዓመት የተገኘው አንጸባራቂ ድል ነጻነትን አስከብሮ ልዑላዊነትን ከማስጠበቁ በላይ ሕዝቡ እርሻው እንደቀድሞው ሞፈሩንና ቀንበሩን ተሸክሞ በሬውን ጠምዶ የበሬ ጅራት ተከትሎ ከመሄድ የሚዘራው አዝመራ ጎተራ የሚጨምረው የዕለት ጉርስ አልሸፍን ብሎት ከዘመን ዘመን የልመና አቁፋዳ ይዘን በመዙዋዙዋር ላይ እንገኛለን ፡፡

ይህ አላወጣም ብለን የሚያጠግብ ሥራ ለመሥራት አልተነሳሳንም፡፡ ለማገዶም የከብት እዳሪ ለቅሞ ከመጠፍጠፍና ከመጠቀም አልወጣም፡፡ ከዚህ አዙሪት አሁንም በ21ኛው ክፍለ ዘመን አልወጣንም፡፡ የሚገርመው ግን ኤኮኖሚያችን ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ ባልቻለበት ወቅት አገሪቱ ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ልትሰለፍ አንድ ሐሙስ እንደቀራት ሲነገር ምን ማለት ነው፡፡ ዓይኔን ግንባር ያድርገው ተብሎ እንዴት ይነገራል፡፡ ትኩረታችን በአጠቃላይ ዜጎች በልተው ፤ መጠሌ አግኝተው ጤንነታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ ማድረግ ነው ቅድሚያ የሚሰጠው፡፡ ይህን ባለማድረጋችን ከታሪክ ተወቃሽነት አንድንም፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን በመዳፉ እንደጨበጠ ለሕዝብ ያስተዋወቀውና ተግባራዊ ያደረገው የኤኮኖሚናማህበራዊ ኑሮ ፖሊሲዎችሕዝብ ያልተወያየባቸውና ያልመከረባቸው እንደ አይ ኤም ኤፍና የዓለም ባንክ በመሳሰሉት ድርጅቶች የተደገፉ ስለነበር በነዚህ ድርጅቶች ተረጂ በመሆን በነጻ የመንቀሳቀስን አቅም በመገደብ የተቀረጸ በመሆኑ ለአፋጣኝ እድገት እንቅፋት ነበረ አሁንም መላቀቅ ካልተቻለ ተቆራኝቶ መዳከር ነው፡፡

በቢሊየን የሚቆጠር የአሜሪካን ዶላርና የእንግሊዝ ፓውንድ ወደአገራችን ገብተው ለሕዝብ ብልጽግናን ቀርቶ የመኖር ዋስትናን ሳናረጋግጥበት ሰምጦ ትርፉ ለልጆቻችን እዳችንን ማስረከብ ሆኗል፡፡
ስለሆነም ቆም ብለን በማሰብ አጠቃላይ ማህረሰቡ ትልቅ ጠላቱን ድህነትን ድንቁርናን በአንድነት በመተባበር ወገናዊ አመለካከትን በመጠየፍ በአጭር ጊዜ ለመላው ሕዝብ ተደራሽ የሆነ ኤኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ኑሮን ካለንበት በአፋጣኝ የሚያላቅ ቀን እቅድ መክረንና ዘክረን በዘርግት እንደ ጃፓን ፤ሲንጋፖር፤ ደቡብ ኮሪያና ታይዋን ለህዝባችን ተደራሽ የሚሆን መንግሥታችንና ሕዝባችን ቀበቶዋችንን ጠበቅ አድርገን የከብት እዳሪ ከመሰብሰብ ልንወጣ ይገባል፡፡

እርስ በርስ በመናቆር የሚተርፈን የለም፤ከመተባበር ግን በቆራጥ አመራር ችግራችንን በአጭር ጊዜ በመቅረፍ ለሁሉም ዜጋ ተደራሽ የሚሆን ብልጽግና ማስገኘት ያስችለናል፡፡ ይህ ሲሆን የአድዋን የድል ትንሣኤ በክብር እንዘክራለን፡፡ 

አምባሳደር ዓለማየሁ አበበ ሸንቁጥ

 

 

 

Filed in: Amharic