>
5:13 pm - Saturday April 19, 4628

የታሪክ ባለቤቶች እና የትርክት ጠባቂዎች!?!  (ሞሀመድ እድሪስ)

የታሪክ ባለቤቶች እና የትርክት ጠባቂዎች!?!
ሞሀመድ እድሪስ
በኢትዮጵያ ታሪክ ይዘት እና አተራረክ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ አካላት ባሉት መረጃዎች ላይ በመንተራስ የራሳቸውን የታሪክ አረዳድ ወደገበያው ለማስገባት ሲሰሩ ይስተዋላል፡፡ በተለይም ባለፉት ሶስት አስርት አመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ መሰረታዊ የሚባል የታሪክ ግንዛቤ ልዩነት ተፈጥሯል፡፡ ይህ ጊዜ አጭር የማይባል በመሆኑ አንድ ትውልድ በአዲስ የተለየ የታሪክ አረዳድ ውስጥ እየተቀረፀ ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡ ምናልባት ለዚህ ቀዳሚውን ሚና የተጫወተው ደግሞ የኦሮሞ ብሄርተኛ እንቅስቃሴን በምሁራዊ ስራዎች ለመደገፍ የተደረገው መጠነ ሰፊ የጥናት እና የምርምር ጥረት ነው፡፡ ይህ ምሁራዊ የታሪክ ክለሳ እና መልሶ የመፃፍ ዘመቻ በዋነኝነት በኦሮሞ ታሪክ ጥናት ላይ ቢያተኩርም በአጠቃላይ «የኢትዮጵያ ታሪክ» በመባል የሚታወቀውን ነባር አረዳድ የተፈታተነ እና ደካማ ጎኖቹንም ለትችት አጋልጦ የሰጠ መሆኑ ግን አልቀረም። ካሁን ቀደምም ቢሆን በተቋም ደረጃ ባይሆንም እንደ ፕሮፌሰር ላጲሶ እና ሁሴን አህመድ ያሉ አንጋፋ ምሁራንም የአዲሱ ትውልድ የታሪክ አረዳድ መሀንዲሶች ነበሩ፡፡ በ60ዎቹ ፖለቲካ ተፅእኖ ስር የተፃፉ የተለያዩ የብሄር እና ብሄረሰብ ታሪኮች፣ እንዲሁም የትርጉም ብርሀን ያገኙ የውጭ አገር ስራዎችም በዚህ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ እስካሁን በተሰሩ የታሪክ ስራዎች ውስጥ የሚገኙ መረጃዎችን በማቀናጀት እና በማዳቀል ሚዛናዊ በሆኑ ፀሀፍት የተዘጋጁ ታሪክ ነክ ስራዎችም በቁጥር እየበረከቱ ሲሆን ብዙሀኑን በመድረስና ተፅእኖ በማሳደርም ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ይገኛል፡፡
አዲሱ የታሪክ አረዳድ እና የቀረቡበት ክሶች
ያልተነገሩ ታሪኮችን የመፃፉ እና የተፃፉትን መልሶ የመተንተኑ ጥረት ሁለት ትላልቅ ክሶች ቀርቦበታል፡፡
1/ «የታሪክ ክህደት» እና «የአገርን መሰረት ማናጋት» ክስ፤  የመጀመሪያው ከሀገር ክህደት ክስ የማይተናነስ የሆነው «ታሪከን የመካድ» እና «አገር የቆመችበትን መሰረት የማናጋት» የተሰኘው ክስ ነው፡፡ የዚህ ክስ አቅራቢዎች በቁጥር አናሳ ቢሆኑም የደቀ መዛሙርቶቻቸው ድምፅ ግን ከፍ ብሎ ይሰማል፡፡ እነዚህን ቡድኖች ጠለቅ ብለን ካየናቸው የነባሩ ትርክት ጠባቂዎች አድርገው ራሳቸውን የሾሙ ናቸው። ውገናቸውንም ከታሪክ እና ከእውነታ ጋር በኃይለኛው የሚጣረስ ሆኖ እናገኘዋለን።፡ «ታሪክ» እና «ትርክት» በጣም የተለያዩ ናቸው፡፡ ታሪክ የተፃፈውንም ያልተፃፈውንም፣ ወደፊት የሚፃፈውንም፣ ምናልባትም ጭራሽ የህትመት ብርሀን የማየት እና የመነገር እድል የማይገጥመውንም ሁሉ የሚያጠቃልል ያለፈ ክስተት ጥቅል ስያሜ ነው፡፡ በዚህ አተረጓጎም ታሪካቸው ያልተነገረና ያልተፃፉላቸው ህዝቦች በራሳቸው «ታሪክ የሌላቸው ህዝቦች» አይደሉም። ታሪካቸው የሚቀርበውም በነበረው ይዘት እንጂ በአንድ ወቅት ለተፈጠረው ትርክት በሚኖረው ተስማሚነት ላይ በመንተራስ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ትርክት በአፈታሪክ እና በሰነድ በተገኙ መረጃዎች፣ ምናልባትም በፈጠራም ላይ በመንተራስ ስላለፈው ዘመን በአንድ ወቅት ተደራጅቶ የቀረበ የትናንት መግለጫ ነውና፡፡ በዚህ አተረጓጎም መሰረት ትርክት መፍጠር የቻለ ክፍል ሁሉ የታሪክ ባለቤት አይደለም፡፡
Eric Foner  ‘Who Owns History? Rethinking the Past in a Changing World’ በሚለው መፅሀፉ የታሪክ ባለቤቶች በአንድ በኩል ሁሉም ሰዎች ሲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ ማንም ነው ይለናል፡፡ ታሪክም ሁሉን በአንድ ቋት ለመክተት እስካላጠበብነው ድረስ በየዘመኑ ባሉ ለውጦች በመንተራስ በድጋሜ የሚተነተን የሁሉም ግን ደግሞ የማንም ሀብት ነው፡፡ የትርክት ባለቤቶች ግን ከዚህ እውነታ በተቃራኒ ታሪክ የኛ እና የኛ ብቻ ነው በሚል ከመርህም ከተጨባጨ ሁኔታም ተቃርነው ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ጥቅል ማዕቀፍ አንጻር አዲስ ታሪክ በተነገረ እና የተለየ ትንተና በቀረበ፣ እንዲሁም ትርክታቸው በተናጋ ቁጥር ከላይ የጠቀስናቸው ቡድኖች «የአገር መሰረትን የማናጋት» ክስ ሲያቀርቡ ይታያሉ፡፡ ከዚያም አልፈው ትርክታቸው ዛሬ ላይ ባሉ ለውጦች ሊበረዝ እና ሊከለስ የመቻሉን እድል ለመግታት «Where is the Now?» ለሚለው መሰረታዊ ጥያቄ «ዛሬ ትናንት ነው» ዓይነት ቅኝት ያለው ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት ትናንት የተፈጠረውን ትርክት ከማስቀጠል ውጭ የዛሬው ትውልድ ሌላ አማራጭ እንደሌለው ለማሳመን ደጋግመው ይሰብካሉ፡፡
የታሪክ ባለቤቶች 
ከትርክት ባለቤቶች (ጠባቂዎች) በተቃራኒ የታሪክ ባለቤቶች ይገኛሉ፡፡ የታሪክ ባለቤቶች በረዥሙ የአገራችን ታሪክ ውስጥ ቀናውን እየተቀበሉ፣ የጎበጠውን በመረጃ እያቀኑ ባለቤትነታቸውን በተግባር የሚያሳዩት ናቸው፡፡ ከአንድ ንጉስ የ30 እና 40 ዓመት የንግስና ታሪክ ውስጥ የአንድ ወቅት ስህተቱን ማውገዛቸው፣ አልያም ከአንድ አገር ዘርፈ ብዙ የአስተዳደር ፖሊሲዎች ገሚሱን በአግላይነት መተቸታቸው ከያገባኛል ስሜታቸው የፈለቀ እና በአገራቸው እና ታሪካቸው ላይ የሚያሳዩት የባለቤትነት ስሜት ነጸብራቅ እንጂ ሌላ ሆኖ አናገኘውም፡፡
እነዚህ ወገኖች የታሪክ ባለቤቶች እንጂ የትርክት ጠባቂዎች አይደሉም፡፡ የታሪክ ባለቤቶች የባለቤትነት ስሜታቸው ጥያቄ የማንሳት እና የማስተናገድ ስልጣን ይሰጣቸዋል፡፡ ትርክት ጠባቂዎች ባለመሆናቸው ላልተነገሩ ታሪኮች የማይሸበሩ፣ ስለአገራቸው ሙሉ ኃላፊነት የመውሰድ የሞራል ልዕልና ያላቸው ናቸው፡፡ የዚህች አገር መፃዒ እድልም በእኒህኞቹ ትከሻ ላይ የወደቀ ሳይሆን አይቀርም። የሁሉንም ህዝቦቿን ታሪክ የአገሪቱ መሰረታዊ የታሪክ ክፍል አድርጎ ለማስተናገድ መወሰን የሚችሉ የታሪክ ባለቤቶች በእርግጥም ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው።
2/ «በትናንት የመባዘን» እና «የበታችነት ስሜት» ክስ፤ ሁለተኛው የክስ ዓይነት በመሰረታዊነት ከታሪክ ባለቤቶች ለታሪክ ባለቤቶች የሚቀርብ ውስጣዊ የአካሄድ ጥያቄ ሊባል የሚችል ነው፡፡ የክሱ አንደኛው መገለጫ «ታሪክ ያለፈ ነገር እንደመሆኑ በነጋችን ላይ ማተኮር ይበጀናል፤ ግዜ እና ጉልበታችንን በትናንት ላይ አናባክን» የሚል ነው፡፡ በጥቅሉ ቀና እና ተራማጅ ሀሳብ ይመስላል፡፡ ይህ ሐሳብ ልክ የሚሆነው ግን በተፈጠረው ትርክት ላይ በመንተራስ የዛሬውን የህብረተሰቦች ግንኙነት እና የኃይል አሰላለፍ ልወስን የሚል አካል እስከሌለ ድረስ ብቻ ነው፡፡ በተጨማሪም አሁን የምንገኝበት ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ደረጃ ከታሪክ ተፅእኖ የተላቀቀ፣ አነስ ካለም የሚካሄዱ ማሻሻያዎች በታሪክ የማይጎተቱበት፣ ነገን ብቻ ታሳቢ ያደረገ መስተጋብር መስፈኑን ሳያረጋግጡ እዚህ መደምደሚያ ላይ መድረስ ከባድ ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ ደግሞ እነዚህ አካላት ተመሳሳዩን ጥያቄ ለትርክት ጠባቂዎችም የማቅረብ ወኔ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ «የፈጠራችሁት ትርክት ቆሞ ቀር ነውና ዛሬ ላይ ተመስርታችሁ ስለነገ አሳቢ፣ ተራማጅ ሁኑ» ብለው የመገሰፅ አቅሙ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ትርክት ጠባቂዎች የአገርን ታሪክ እና ማንነት የብርጭቆ ውሀ ይመስል አንዴ ከሞላ ተጨማሪ የማይቀበል ያለቀለት እውነታ አድርገው ማሰባቸውን እንዲያቆሙ የማድረግ ቁርጠኝነቱ ሊኖራቸውም ግድ ነው፡፡ ይህ ወኔ የማይኖራቸው ከሆነ እነሱንም «የትርክቱ ሰለባዎች» ከመባል አያድናቸውም፡፡
የዚህ ክስ ሁለተኛው መገለጫ «የታሪክ ጨለማ ጥጋጥጎችን እየመረጡ ማቅረብ ከበታችነት ስሜት የተወለደ እና የህብረተሰብን አብሮነት የሚያናጋ ደካማ አካሄድ ነው» የሚለው ውንጀላ ነው፡፡ የዚህ ወቀሳ ሠንዛሪዎች እንደመፍትሄ «በጎ በጎውን እየመረጥን እናውራ» የሚል ፎርሙላ ሲሠጡ ይስተዋላል፡፡ ይህ ግን እነሱ በግላቸው «የተሻለ ነው» ብለው የተቀበሉት የታሪክ ዘገባ ቅኝት እንጂ ሳይንሳዊም ምክንያታዊም አካሄድ ሆኖ አናገኘውም፡፡ እንደውም ይህ አካሄድ በታሪክ ጥናት ውስጥ ትልቅ ቦታ የተሰጣቸውን «construction, deconstruction and reconstruction»ን የመሳሰሉ መሰረታዊ የታሪክ ቅኝት ስልቶችን የሚቃረን ነው፡፡
በማህበራዊ ሳይንስ ጥናት ‘false consensus effect’ የሚባል ፅንሰ ሀሳብ አለ፡፡ በተለያዩ የትምህርት መስኮች የተለያዩ አረዳዶች ቢኖሩትም በዋነኛነት ይህ ፅንሰ ሐሳብ ሰዎች ከሚቀርቡላቸው አማራጮች ፊት ለፊት ያለውን እና የቀለላቸውን በመምረጥ «ቀላል» ምርጫቸው ለብዙሀኑ ተገቢ የሆነ ብቸኛ ትክክለኛ ምርጫ እንደሆነ የሚደመድሙበትን ስሁት አካሄድ የሚገልፅ ነው፡፡ ለዚህ ተፅእኖ ከሚያበቁ ምክንያቶች ውስጥ በቂ መረጃ አለመኖር፣ ሁልጊዜ ቀላል ነገሮችን መመኘት፣ የራስን እይታ ከተገቢው በላይ አልቆ መመልከት፣ በአማራጮች መካከል ያሉ ጥቅምና ጉዳቶችን በጥልቀት ለመመዘን መስነፍ፤ የተለየ ሀሳብን በመምረጥ ሊመጣ የሚችልን ጣጣ መሸሽ ተጠቃሽ ናቸው። ከሞላ ጎደል ሌሎች ሥነ ልቦናዊ መንስዔዎችም አሉት፡፡ የዚህ ችግር ሰለባ መሆን በአንድ በኩል ሁልጊዜ ቀላል የሆኑና ብዙ ተቀናቃኝ የማያስነሱ አመለካከቶችን ብቻ ወደማራመድ ይገፋል። የሚያስከትለው ትልቁ አደጋ ግን በሂደት የዚህ ችግር ሰለባዎች የራሳቸውን አረዳድ ብቸኛ የንቃተ ኅሊና መለኪያ አድርገው ወደማየት መገፋታቸው ነው። በግሌ የተሻለው አማራጭ እነዚህ ወገኖች እነሱ ባመኑበት የታሪክ አረዳድ ስራቸውን ወደገበያ ማቅረብ ይመስለኛል። ከዚያ ውጭ ግን «እኛ እንድናወራ ሌሎች ዝም ይበሉ» ዓይነት የ«ቆማችሁ አሳልፉኝ» ስልት መከተላቸው በጭራሽ የሚያዋጣ አይሆንም፡፡
Filed in: Amharic