>
5:13 pm - Sunday April 19, 4359

ሞኝ ከራሱ ብልህ ከሞኝ ይማራል!!!” (አስማማው በቀለ)

ሞኝ ከራሱ ብልህ ከሞኝ ይማራል!!!”
አስማማው በቀለ
 
“መገናኛ ብዙኃን ለተወሰኑ ቡድኖች፣ ፖለቲከኞች፣ ጓደኞቻቸው… ዓላማ ማስፈጸሚያ ከሆኑ ሥራቸው ጋዜጠኝነት ሳይሆን የቡድን መሣሪያነት ነው፤ ይህም ለሀገር አደጋ ነው፤ ሩዋንዳ ላይ የታየውም ይህ ነበር፡፡”  የሩዋንዳ ጋዜጠኛ
  ወቅቱ እ.አ.አ. 1994 ነው፤ ሩዋንዳ ውስጥ፡፡ በሰው ልጅ ታሪክ አስከፊ ከሚባሉት ሰብዓዊ ጥፋቶች አንዱ ሆኖ በታሪክ የተመዘገበ ድርጊት የተፈጸመበት ነው፡፡ ሁቱዎች በቱትሲዎች ላይ እንዲዘምቱ ታቅዶ ቢጀምርም ሁቱዎችንም ሰለባ አድርጓል፡፡ ፀረ ቱትሲ ጭፍጨፋው በያኔው የሩዋንዳ ፕሬዝዳንት ጁቬናል ሀቤሪማና እና በሀገሪቱ ትልልቅ የፖለቲካ ኃላፊነት ቦታዎችን በያዙት የሁቱ ጎሳ ልሂቃን የተቀነባበረው እንደሆነ ይታመናል፡፡
በወቅቱ ከሚያዝያ እስከ ሐምሌ ባሉት ወራት ለተፈጸመው ጥፋት ዋና ተዋናይ ተደርጎ የሚነገረው አርቲ ኤል ኤም (RTLM) የተሰኘው የሬዲዮ ጣቢያ ነው፡፡ በእርግጥም የሬዲዮ ጣቢያው ከተፈጸመው አሳዛኝ ድርጊት አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ለዚሁ ዓላማ ታስቦ እንደተቋቋመ ነው የሚታወቀው፡፡ ጣቢያው የተቋቋመበት ዓላማ ለእልቂት ነበርና ሁቱዎች በቱትሲዎች ላይ እንዲዘምቱ የጥፋት ልሳኑን ከፍ አድርጎ አስተጋባ፡፡  800 ሺህ የሚደርሱ ሩዋንዳውያን እንዲገደሉም ትልቁን የቅስቀሳ እና የማነሳሳት ድርሻ ተወጣ፡፡
ለመሆኑ ሩዋንዳዉያን ያንን እልቂት እንዴት አለፉት? ወደ እርቅ እና ብሔራዊ መግባባት እንዲመጡስ የመሪዎች እና የመገናኛ ብዙኃን ሚና ምን ነበር? አብመድ ለዓለም የፕረስ ነፃነት ቀን በአዲስ አበባ ከተገኙት የሩዋንዳ ጋዜጠኞች ጋር ቆይታ አድርጎ ተከታዩን ጥንቅር አዘጋጅቷል፡፡
ኢማኑኤል ሙጊሻ- ጋዜጠኛ እና የሩዋንዳ ሚዲያ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ፣ ፖል ታምባራም ጋዜጠኛ እና በሩዋንዳ የመገናኛ ብዙኃን ማኅበራት ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡
በሀገራቸው ለተፈጸመው የእርስ በርስ እልቂት ዋነኛ ተዋንያን መሪዎች፣ ልሂቃን እና አር ቲ ኤል ኤም (RTLM) የተባለው ሬዲዮ ጣቢያ ስለመሆናቸው ነው ሙጊሻ እና ታምባራ የተናገሩት፡፡ ጎልቶ እየተነገረ ያለው የሚዲያው ጥፋት መሆኑን፣ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ግን በስተጀርባ ሆነው እልቂቱን ሲያቅዱ እና ሲያስፈጽሙ የነበሩ የሁቱ ጎሳ ልሂቃን እና ፖለቲከኞች እንደነበሩ ነው ጋዜጠኞቹ የተናገሩት፡፡ ሚዲያው ደግሞ የፖለቲከኞችን የጥላቻ እና የመከፋፈል ዓላማ ማስፈጸሚያ መሆኑ ሀገራቸውን እንዴት አደጋ ላይ ጥሎ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡
እንደ ኢማኑኤም ሙጊሻ ሐሳብ  አሁን ያ ሁሉ ጥፋት ከትውስታ ያለፈ ቦታ የለውም፤ ድርጊቱ ባይረሳም ከመማሪያነት አልፎ እንዳያገረሽ ሆኗል፡፡ ማስታወስ የሚያስፈልገውም ጥፋቱ እንዳይደገም በማሰብ ነው፡፡ “ምሥጋና እርቅ እና ሠላምን ለሰበኩት ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ እና አመራሮቹ አሁን መሪዎችም፣ መገናኛ ብዙኃንም ፊታቸውን ወደ ሠላም እና አብሮነት አዙረዋል” ነው ያለው ጋዜጠኛው፡፡
አመራሮችም ሆኑ መገናኛ ብዙኃኑ ስለማንነታቸው፣ ሀገራቸው ስላለፈችባቸው ፈተናዎች እና አሁን ምን መሥራት እንዳለባቸው እንደሚገነዘቡም ነው ኢማኑኤል ሙጊሻ የተናገረው፡፡ ይህም ለእርቅ፣ ለሠላምና ለአብሮነት ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሠሩ አድርጓቸዋል፡፡ እርቁ እውነተኛ መሆኑ ጥሩ መማሪያ እንደሆናቸው፤ ለዚህ ደግሞ የሠላም ፈላጊ መሪዎች እና የመገናኛ ብዙኃን ሚና ትልቅ እንደሆነ ነው የተናገረው፡፡
 “ሩዋንዳ ውስጥ ከሠላም፣ ከእርቅ እና ከአብሮነት ይልቅ ጥላቻ እና መለያዬትን መዘገብ እንደማይቻል በሕግ ተቀምጧል፤ ከዚህ አኳያ ክትትል ይደረጋል፤ በሀገር ላይ ጨዋታ አይታሰብም፤ ያስከፈለው ዋጋ ይታወቃልና” ነው ያለው ጋዜጠኛ እና የሚዲያ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊው ኢማኑኤል ሙጊሻ፡፡ በወቅቱ የጥፋት ልሳን የነበሩ መገናኛ ብዙኃን ሳይቀሩ እርቅ እና ሠላምን መስበካቸውንም በማሳያነት ጠቅሷል፡፡ እንደ ሙጊሻ አስተያዬት ከመሪዎች እስከ መገናኛ ብዙኃን እርቅ እና ሠላምን ዋነኛ ሥራዎቻቸው ማድረጋቸው ለሩዋንዳ ከአስከፊው መጠፋፋት መውጫ መንገዶች ነበሩ፡፡
“ሚዲያው ያን የጥፋት መንገድ መድገም እንደሌለበት ይልቁንም ስለ እርቅና ስለሠላም እንዲሠራ መደረጉ፣ መሪዎቹም በቀል የሌለባትን ሩዋንዳ መመሥረት እንዳለባቸው በማመን መሥራታቸው ለአሁኗ ሩዋንዳ መሠረቶች ናቸው”  ያለን ደግሞ ጋዜጠኛ እና የሀገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ማኅበራት ዋና ዳይሬክተር ፖል ታምባራ ነው፡፡ ‹ዐይን ላጠፋ ዐይን› የሚለው መንገድ ሀገርን ጨለማ ውስጥ እንደሚከት፣ ቂም በቀልም ጥፋትን ከማባዛት ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው መገናኛ ብዙኃን ማስተማራቸው ለብሔራዊ መግባባት እንዳገዛቸውም ነው የተናገረው፡፡
ኢትዮጵያን ከድንቅ የጎብኝዎች መዳረሻ እና ከሰው ዘር መገኛነቷ ባሻገር እንደሚያውቃት የተናገረው ፖል ታምባራ ሩዋንዳን ሰለባ ባደረገው የጥፋት ወጥመድ ላይ ላለመውደቅ “ከእኛ ተማሩ” ነው ያለው፡፡ ለጥቁር ሕዝቦች መመኪያውን ታላቅ ታሪክ አንድ ሆነው የሠሩ ሕዝቦችን አንድ በማድረግ ከጥላቻ እና ከመቃቃር መጠበቅ እንደሚገባም ነው የመከረው፡፡ ‹‹በዓድዋ እኮ መላው ጥቁር ይኮራል፤ ይህን ያደረጋችሁት ደግሞ እናንተ በአንድነት እና በመተባበር ነው›› ያለው ጋዜጠኛው በዓድዋ ድል ጊዜ የታየውን አንድነት አሁን ላይ መድገም እንደማያስቸግር ነው አስተያዬቱን ከታሪክ ጋር በማስተሳሰር የተናገረው፡፡
ኢማኑኤል ሙጊሻ ደግሞ መገናኛ ብዙኃን ነጻነትን ከኃላፊነት ጋር መተግበር እንዳለባቸው ነው የተናገረው፡፡ ይህ መሆኑ ሀገራቸውን ከነበረችበት የጥፋት ሰባኪ ፖለቲከኞች መሣሪያነት አላቅቆ የእርቅ እና የሠላም ልሳን እንዳደረጋቸውም ገልጿል፡፡ ሚዲያው ማንንም ይደግፍ ፈጽሞ ወደ ጥላቻ ንግግር እና ወደ ጥላቻ ዘገባ መግባት እንደሌለበት እና በዚህ ላይ መደራደር ማለት ሀገርን ለጥፋት አሳልፎ መስጠት መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም ነው የተናገረው፡፡ “መገናኛ ብዙኃን ለተወሰኑ ቡድኖች፣ ፖለቲከኞች፣ ጓደኞቻቸው… ዓላማ ማስፈጸሚያ ከሆኑ ሥራቸው ጋዜጠኝነት ሳይሆን የቡድን መሣሪያነት ነው፤ ይህም ለሀገር አደጋ ነው፤ ሩዋንዳ ላይ የታየውም ይህ ነበር” ነው ያለው ሙጊሻ፡፡
ለዚህ ደግሞ ተግባራዊ አሠራር እንደሚያስፈልግም አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ጋዜጠኞችም ከሩዋንዳ መጥፎውን ታሪክ በመማር ገለልተኛ እና ሚዛናዊ ሆነው መሥራት፤ ከሕዝብ እና ከሀገር ፍላጎት ያፈነገጡ አዘጋገቦችም ችላ ሊባሉ እንደማይገባ መክሯል፡፡ መሪዎቹም በእውነተኛ እርቅ፣ ሠላም እና ሀገርን ወደ አንድነት በሚወስዱ ተግባራት ላይ በማተኮር እና ዓርዓያ በመሆን የመገናኛ ብዙኃንን ቅኝት መግራት እንደሚችሉ ነው የሀገሩን ልምድ ማሳያ በማድረግ የተናገረው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎች፡- The Failure of Humanity in Rwanda እና A Rwandan Journey ከተሰኙ መጻሕፍት
Filed in: Amharic