>

ጥያቄ ቢከመር መልስ አይሆንም፤ እኛ እና ጥያቄዎቻችንን !!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ጥያቄ ቢከመር መልስ አይሆንም፤ እኛ እና ጥያቄዎቻችንን !!!
ያሬድ ሀይለማርያም
የሰው ልጅ ህይወት በጥያቄ የተሞላ ነው። ጥያቄዎች የሰው ልጅ አዕምሮ ብስለት ማሳያዎችም ናቸው። አካባቢያችንን መቃኘት ከጀመርንበት የጨቅላ እድሜ ጀምሮ ከአለም ጋር ያለን ትውውቅ በጥያቄዎች ላይ የተመሰረተ ነው። አዕምሯችን ያለማቋረጥ ጥያቄዎችን ያፈልቃል፤ ምላሽ ይሻል። ምላሾቹን ለማግኘት በተጋነው መጠን ደግሞ የእውቀት መነሻ ይሆነናል። የአዕምሮ ብስለታችንም ይጨምራል። አዕምሯችን ሲሰንፍ ጥያቄ ማፍለቁን ያቆማል። ጥያቄ ማፍለቅ ያቆመ አዕምሮ ደግሞ በእውቀት እና በሃሳብ ድርቀት ይመታል። የሃሳብ እና የእውቀት ድርቀት የገጠመው ሰው .ለራሱም ሆነ ለአገር አይበጅም። አካባቢው ላይ ላሉ ችግሮች መፍትሔ ሊያፈልቅ ወይም ሃሳብ ሊያመነጭ አይችልም።
ጥያቄ የእውቀት መነሻ እና መሰረት ብቻ ሳይሆን የስኬታችንም መሰላል እና የህይወት ምዕራፎቻችንም መክፈቻ ቁልፍም ነው። ከአንድ የህይወት ምዕራፍ ወደ ሌላኛው የምንሸጋገረውም ሆነ ወደ አዲስ ህይወት የምንገባው አዕምሯችን ለሚያፈልቃቸው ጥያቄዎች ምላሽ ፍለጋ በምናደርገው መዳከር እና እረዥ ጉዞ ውስጥ ነው።  የአዕምሮ ስንፍና የገጠመው ሰው ጥያቄዎችን ለማመንጨትም ሆነ ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለማግኘትም ስለሚሰንፍ በእውቀትም ሆነ በሃብት አይበለጽግም።  የሁሉም ሳይንሳዊ ምርምሮችና ጥናቶች መነሻው ጥያቄ ነው። ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎችን ለመመለስ ነው ሰው እድሜውን ሙሉ በጥናት እና ምርምር የሚያሳልፈው። ዛሬ መልስ ያላገኘላቸውን ጥያቄዎች እንኳ አዕምሮ ውስጥ በይደር ያኖራቸዋል። በሳይንሱም ምላሽ ያልተገኘላቸው ጥያቄዎች ጥቁር ሳጥን (Black box) ውስጥ በይደር ይቆያል እንጂ መልስ የለውም ተብሎ አይጣለም።
በመንፈሳዊ ሕይወትም የተመለከትነው እንደሆነ አዳም እና ሔዋን አዕምሯቸው ውስጥ የተፈጠረን ክፉና ደጉን ለይቶ ለዋወቅ የመፈለግ ጥያቄ ነው የተከለከሉትን የዛፍ ፍሬ እንዲበሉ ያደረጋቸው። ከዛም አይነ ጥላቸው ተገፎ እርስ በርሳቸውም ለመተያየትም ሆነ አለምን በጥልቀት ለማየት የእውቀት መንገድ የሆናቸው። የእነሱ የእውቀትን ፊሬ መብላት ዛሬ ላለንባት አለም መፈጠር ምክንያት ሆኗል።
በሰው ልጅ እና በጥያቄ መካከል ያለው ቁርኝት ከላይ ባጭሩ ለመግለጽ ከሞከርኩትም በላይ እጅግ ጥልቅ ነው። ሰዎች መልስ ላላገኙበት ጉዳይ ወይም ማወቅ ስለሚሹት ነገር ምላሽ ፍለጋ የሚጀምሩት ጉዞ የህይወት መዳረሻቸው ይሆናል። ያላንኳኳ እንደማይከፈትለት ሁሉ ያልጠየቀም ምላሽ ወይም እውቀትን አያገኝም። ጥያቄና መልስ ሲዋሃዱ ሙሉ እውቀት ይሆናል። ሙሉ እውቀት ደግሞ ሙሉ ሰው ያደርጋል። ሙሉ ሰው መሆን ደግሞ ለሌሎች ብርሃን እንድንሆን እድል ይፈጥርልናል። በተማሪና በአስተማሪ መካከል ያለው የሙሉ እና የጎዶሎ ሰው ውህደት ቁልፍ ሚስጥሩም ይሔው ነው።
ባጭሩ የሰው ልጅ ቢያንስ በሁለት ምክንያቶች ጥያቄዎችን ይጠይቃል። የመጀመሪያው አዲስ ነገር ለማወቅ ከመጓጓት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከጥርጣሬ (doubt) ይመነጫል። በሰማው እና ቀድሞ በሚያቀው ጉዳይ ላይ እርግጠኛ ሳይሆን ሲቀር ወይም ያወቀውን ነገር ትክክለኛነቱን ሲጠራጠር ጥያቄ ያነሳል።
እኛ እና ጥያቄዎቻችን፤
ወደ ዋናው የጽሑፌ መልዕክት ልግባና በማህበረሰባችን ውስጥ አንዳንድ የታዘብኳቸውን ነገሮች ለውይይት መነሻ እንዲሆኑ ላቅርብ። ልክ እንደ ግለሰብ ማህበረሰብም የራሱ ጥያቄዎች አሉት። የማህበረሰብ ጥያቄዎች የሁሉንም ወይም የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ፍላጎት የሚያንጸባርቁ ናቸው። ባላፈው አንድ አመት በአገራችን ውስጥ የታየው የለውጥ ጭላንጭል የማህበረሰባችንን ስነ ልቦና እንድንረደ ሰፊ እድል የፈጠረ ይመስለኛል። ታፍኖ እና ታምቆ የቆየው የሕዝብ ትንፋሽ ማቆሚያ በሌላቸው የማህበረሰብ ጥያቄዎች ታጅሎ በየመድረኩ ሲንጸባረቅ ለማየት እድል ፈጥሮልናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ ህይወቱ፣ በኃይማኖታዊ እና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ያሉትን ጥያቄዎች ዘርግፎ አደባባይ ላይ አስጥቷቸዋል።
ዶ/ር አብይ ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በየሔዱበት ሥፍራ ሁሉ፤ ከአገር ውጭም ተጉዘው ኢትዮጵያዊያንን ባወያዩባቸው መድረኮች ሁሉ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከፊታቸው በሰልፍ እየቀረበ በኖረበት ዘመን ሁሉ መንግስታት ያልመለሱለትን ጥያቄዎች ጭምር ሲያቀርብ አስተውለናል። እንደ እኔ እምነት መቶ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ እድል ቢያገኝ መቶ ሚሊዮን ጥያቄዎች ሊያቀርብ ይችል። ለመግስት የሚቀርቡትን ጥያቄዎች አብዛኛዎችን ለማጤን እንደሞከርኩት ከሁለት እሳቤዎች የሚመነጩ ናቸው። አንደኛው መንግስት መፍትሔ ይሰጠናል ከሚል ስሜት የሚመነጭ ነው። በመሆኑም አብዛኛው ሰው ችግር የሆኑበትን ጉዳዮች ሁሉ በጥያቄ መልክ አቅርቦ ከመንግስት ምላሽ ይጠብቃል። በዚህ መነሻ የሚጠየቁት ጥያቄዎች ብዙን ጊዜ ከማህበራዊ እና ኢኮኖሚያጉ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ናቸው። የኑሮ ውድነት፣ የሥራ ማጣት፣ የመኖሪያ ቤት ዋስትና፣ የፍትህ መጓደል፣ የአስተዳደራዊ በደሎች እና ሌሎች በደል ተኮር ጥያቄዎች ናቸው። የሃኪሞቻችን የሰሞኑ ጥያቄም በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ይወድቃል።
ሁለተኛው እሳቤ ደግሞ ከጥርጣሬ ወይም በመንግስት ላይ እምነት ከማጣት የሚመነጩ ጥያቄዎች ናቸው። ሕዝብ ካሳላፋቸው ክፉ ግዚያቶች ተነስቶ መንግስት ላይ እምነት የለውም። የለውጡን ኃይልም በጥርጣሬ አይን ነው የሚመለከተው። ኮሽ ባለ ቁጥር ተክጃለው፤ አታለውኛል የሚል ስሜት እየተሰማው ውግዘቱን ሲያዥጎደጉደው እያየን ነው። ስለዚህ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስጋት እና ጥርጣሬ አድሮበት ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ሁሉ የመንግስትን ምላሽ መስማት ይፈልጋል። በዚህ ማዕቀፍ የሚነሱት ጥያቄዎች ደግሞ በብዛት የፖለቲካ ይዘት ያላቸው ናቸው። የማንነና አስተዳደራዊ ድንበር መካለል፣ የከተማዎች ይዞታና ባለቤትነት፣ ስለ ሕገ መንግስት ማሻሻል፣ ከምርጫ ጋር የተያያዙ፣ የልውጥ ኃይሉ ተአማኒነት፣ ሰላም እና ጸጥታን ስለማስፈን፣ ከብሔር እና ዜግነት ፖለቲካ ጋር የተያያዙ፣ ምስናን፣ የመንግስት ሥልጣን አሿሿምና የሃብት አጠቃቀምን የሚሳሰሉ ጥያቄዎችን ያካትታል።
እነዚህ ጥያቄዎች ማህበረሰባችን እንደ ሕዝብ እና ኢትዮጵያም እንደ አገር ያለችበትን ሁኔታ ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። በጥያቄዎቹ ብስለት ልክ ማህበረሰባዊ ብስለታችን፤ በጥያቄዎቹ ጥሬነተ ልክ ደግሞ በእውቀት ያልበሰለውን እኛነታችንን እናይበታለን። ከጥያቄዎቻችን በተጓዳኝ አብረው ሊጤኑ ሲገባቸው ብዙም ትኩረት ያልተሰጣቸውን ሦስት መሰረታዊ ችግሮች ጠቂሜ ጽሑፌን ልደምድም፤
+ የመጀመሪያው፤ የቅደም ተከተል (priority) ጉዳይ። ጥያቄ መጠየቅ ብቻውን መልስ አያስገኝም፤ የጥያቄዎች ክምርም ትልቅ ጥያቄ ይሆናል እንጂ መልስ አይሆንም። በተለይም እንደ ማህበረሰብ የቅደም ተከተል ጉዳይ ሊያሳስበን ይገባል። የትኛው ጥያቄ አንገብጋቢ ስለሆነ ቅድሚያ ይመለስ፤ የትኛው በይደር ይቆይ፣ የትኛውስ ጥያቄ በየትኛው ወቅት ይጠየቅ ብለን ቅደም ተከተል ልናወጣ ይገባል። ሁሉንም ጥያቄዎቻችንን አውጥተን እንደ ተራራ በመከመር መልስ መጠበቅ ብስጭትን እና ተስፋ መቁረጥን ያስከትል ይሆናል እንጂ መልስ አያስገኝም።
+ ሁለተኛው፤ የመላሹን አቅም ታሳቢ ማድረግ ነው። ችግሮቻችን ብዙ ስልሆኑ ሁሉንም ጥያቄዎቻችንን  በመንግስት፤ በተለይም አሁን ባለው እና ገና ባረጋው የሽግግር አስተዳደር ይመለሱልኛል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ያለውን አስተዳደር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና መዋቅራዊ አቅም የማይመጥን ጥያቄዎችን ቆልለን ቆልለን ምላሽ ሳናገኝ ስንቀር ወይም መልስ ሲዘገይብን አስተዳደሩን ማውገዝ እኛኑ ከግምት ውስጥ ይጥለን ይሆናል እንጂ መልስ አያስገኝም።
+ ሦስተኛው፤ ሁሌም እራስን ጠያቂ ብቻ አድርጎ ማስቀመጥ መልስ አያስገኝም። ለምናነሳቸው በተለይም አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ምላሻ ለማግኘት የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይግድ ይላል። መጠየቅ ብቻውን መልስ አያስገኝም። እኛ ወደ መልሱ መሄድ አለብን። የመልስ ፍለጋ ጉዞ በተግባር የሚገለጽ ስለሆነ እንደ መጠየቅ ቀላል አይደለም። የሚከፈለውን ዋጋ መክፈል አለብን።
ዛሬ በአገሪቱ ውስጥ ያለው አንጻራዊ ነጻነት ጠያቂ ማህበረሰብን ፈጥሯል። እሰዮው ነው የሚባለው። ነገር ግን ጠያቂ ብቻ ማህበረሰብ ወንዝ አይሻገርም። መንግስትን ጨምሮ መላሽ የሆነ ማህበረሰብም መፈጠር አለበት። እንደ ማህበረሰብ ለሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ምላሽ እስኪያገኝ እንቅልፍ የማይተኛ፣ ምላሽ ፍለጋ ተራራ የሚቧጥጥ፣ ቆላ ደጋ የሚወርድ፣ የሚያሰላስል እና የሚመራመር ማህበረሰብ አብሮ መፈጠር አለበት።
የኢህአዴግ  ባለሥልጣናት ባለፉት ሁለት አመታት ጠያቂ ትውልድ ፈጥረናል እያሉ ባደባባይ ሲመጻደቁ ሰምቻለው። ጠያቂ ብቻ የሆነ ትውልድ እንደ ተጠመደ ፈንጅ ያህል አደገኛ እንደሆነ የገባቸው አልመሰለኝም። ጠብቆ ጠብቆ ምላሽ ሲያጣ ተናዳፊ እና ሥርዓት አልበኛ ነው የሚሆነው። ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለማግኘት በጥበብ ሳይሆን በነውጥ እና በጉልበት መንቀሳቀሱ አይቀሬ ነው። አሁንም አልፎ አልፎ የሚታዩት የደቦ የጥቃት እርምጃዎች ከዚህ አይነቱ ችግር የሚመነጩ ናቸው። ትውልዱ በዋናነት፤ እንዲሁም እንደ አንድ አገር ሕዝብ ጠያቂዎች ብቻ ሳንሆን ለራሳችን ችግሮች መፍትሔ እና መልስ አፍላቂዎችም መሆን አለብን።
ውይይቶቻችንም በዚህ መልኩ ሊቃኙ ይገባል። አብዛኛው የሚዲያም ሆነ የሕዝባዊ መድረክ ውይይቶች ጠያቄዎች እንጂ መላሾች አይደሉም። መፍትሄ አመላካች (Solition oriented) የሆነ እና መልስ ጠቋሚ ውይይቶች እና ክርክሮ ያስፈልጉናል። ለዚህም የውይይት መድረኮች ከፖለቲከኖች ይልቅ በተመራማሪዎች እና ጥናት ባደረጉ ሰዎች እንዲሞሉ ማድረግ የግድ ይላል። የፖለቲከኞች አብዛኛው ዲስኩር በጭግሮች ላይ የሚያጠነጥኑ ስለሆኑ ሕዝቡን የበለጠ ሆድ ከማስባስ ያለፈ ሚና አይኖራቸውም። አጥኒዎችና ተመራማሪዎችም የምርምር ትኩረታቸው መሬት ላይ ባሉ የሕብረተሰብ ችግሮች ላይ እንዲሆን እና መፍትሔ የሚያፈላልጉ እንዲሆኑም የከፍተኛ ተቋማት ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይገባል።
ተመራማሪ ምሁራን እና ማህበረሰብ በተላለፉበት ወይም ባልተናበቡበት ስፍራ ሁሉ ጥያቄዎች እንደ ተራራ ገዝፈው አገራዊ እይታችንን ጭምር ይጋርዳሉ። የጥያቄዎች ተራራም ተስፋችንን ስለሚጋርድ ጨለምተኝነትን ያሰርጻል። መጪው ዘመን ብሩህ እንዲሆን ጠያቂም፤ መላሽም እንሁን።
ቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic