>
5:13 pm - Friday April 19, 6639

የምኒልክን ቀኝ እጅ የአብቹ ኦሮሞውን ራስ ጎበና ዳጬን በጨረፍታ እናስታውሳቸው፣ (ሲሳይ ተፈራ መኮንን)

የምኒልክን ቀኝ እጅ የአብቹ ኦሮሞውን ራስ ጎበና ዳጬን በጨረፍታ እናስታውሳቸው፣
ሲሳይ ተፈራ መኮንን
 
ራስ ጎበና ዳጬ (ከ1810 ዓ.ም-1881 ዓ.ም) – ከአጼ ቴዎድሮስ እስከ አጼ ምኒልክ፣
1. አቶ በዛብህ ከአብቹ ኦሮሞው ከአቶ ጎበና ዳጬ ጋር ተማክሮ ከአጼ ቴዎድሮስ ለመክዳት ቁርጥ አሳብ አደረጉ፡፡ አብደላ አማን በሚባለው አገር አጠገብ አዙ የሚባለውን ዋሻ አስጠርጎ እቃውንና ገንዘቡን የምግቡንም አይነት ሁሉ ከሰልና እንጨት ሳይቀር በዋሻው አስገባ፡፡
2. ከዚህ በኋላም አቶ በዛብህ በሸዋ የነጋሲ ዘር የሌለ መሆኑን አይቶ በህዳር ወር 1857 ዓ.ም ወልደ ትንሣይ ከሚባለው ከተማው ተነስቶ ወደ ደብረ ብርሃን በመውጣት “የሸዋ ሰው ከአጼ ቴዎድሮስ መገዛት የማድንህ ገዥህ እኔ ነኝና ባለህ እርጋ፣ ባትገዛልኝ ግን ብርቱ ቅጣት ትቀጣለህ” የሚል አዋጅ አስነግሮ ነገሠ፡፡ ደብዳቤ ሲጽፍም “ዛቲ ጦማር ዘተፈነወት እምኅበ አቶ በዛብህ ንጉሠ ሸዋ” እያለ መጻፍ ጀመረ፡፡
ነገር ግን የሸዋ ሰው ሁሉ ስለናቀው በየአውራጃው እየሸፈተ የማይገዛለት ሆነ፡፡ አቶ ጎበናም አዙ ዋሻ ገብቶ አቶ በዛብህ የሰበሰበውን ገንዘብ ሁሉ ይዞ ሸፈተ፡፡ አጼ ቴዎድሮስም ሊወጉት ገስግሰው ቢመጡም አፍቀራ አምባው ላይ ወጥቶ ስለተቀመጠ ለጦርነት የማይመች ሆነባቸውና ሳይወጉት ተመለሱ፡፡ አቶ በዛብህ ግን ከአፍቀራ ወርዶ አልገዛልህም ያለውን አማራውንም ኦሮሞውንም እየፈጀ በሸዋ ላይ ዘጠኝ ወር ነገሠ፡፡
3. በ1870 ዓ.ም አጼ ዮሐንስ ‘ከወንድሜ ከንጉሥ ምኒልክ ጋር ታርቄያለሁና ከእንግዲህ ወዲህ አገር የምታጠፋ፣ ከብት የምትዘርፍ ወታደር ትቀጣለህ’ የሚል አዋጅ በማስነገር ወደ ሸዋ መጡ፡፡ አጼ ዮሐንስ ከምኒልክ ጋር የእርቁን ነገር ቢጨርሱም በአካል ተገናኝተው ከንጉሥ ምኒልክ ጋር ባለመነጋገራቸው ተጸጽተው ‘ተገናኝተን በአንድነትና በፍቅር ብንኖር መልካም ነው’ የሚል ቃል ጽፈው መስቀልና ስዕል ጨምረው በደጃዝማች ዋህድና በመምህር ግርማ ሥላሴ እጅ ወደ ምኒልክ በመላክ እርሳቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ ተጓዙ፡፡
 4. መልእክተኞቹም ምኒልክ ጋር በደረሱ ጊዜ፣ ምኒልክ ከመኳንንቶቼ ጋር ተነጋግሬ ምላሹን ነገ እነግራችኋለሁ በማለት መልዕክተኞቹን አሳደሯቸው፡፡ በማግስቱም ደጃዝማች ጎበና ዳጬ፣ ደጃ/መንገሻ አቲከምና ሊቀ ካህናት ኪዳነወልድ ከምኒልክ ጋር ከመከሩ በኋላ ‘አጼ ዮሐንስ በኔ ላይ ክፉ ነገር እንዳላሰቡ ከማሉና ከተገዘቱ በላካችሁብኝ ጊዜ መጥቼ እገናኛቸኋለሁ’ በማለት ለአጼ ዮሐንስ ባለወርቅ አልጋና ባለወርቅ ወንበር፣ ለአቡነ ቴዎፍሎስም ባለወርቅ ወንበር በረከት ጨምረው ምኒልክ መልክተኞቹን ወደ አጼ ዮሐንስ ሰደዷቸው፡፡
5. አጼ ዮሐንስ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን አንግሰው ወደ ትግራይ ከተመለሱ በኋላ ንጉሥ ምኒልክና ንጉሥ ተ/ሃይማኖት በምእራብ ኢትዮጵያ ያለውን የኦሮሞ አገር ለመያዝና ለማቅናት መሽቀዳደም ጀመሩ፡፡ የንጉሥ ምኒልክ የጦር አበጋዝ የነበሩት ራስ ጎበና ዳጬና የንጉሥ ተ/ሃይማኖት የጦር አበጋዝ የነበሩት ራስ ደረሶ ሁለቱም ስመጥር የጦር አበጋዞች ነበሩ፡፡
6. ንጉሥ ምኒልክ በ1871 ዓ.ም የእንጦጦ ከተማን ሲሰሩ፣ የጎጃም የጦር አበጋዝ ራስ ደረሶ አባጆቢር ከሚባለው ከጉማው ባላባት ጋር ተዋግቶ ገደለው የሚል ወሬ በመስማታቸው ራስ ጎበናን ወዲያው ወደስፍራው ገስግሰው እንዲሄዱ አዘዟቸው፡፡ ራስ ጎበናም ገስግሰው ከሄዱ በኋላ ‘ከራስ ደረሶ ጋር ጉማ ላይ ተገናኝተን በግብር የተቀበሉትን ከብት ሁሉ አስመለስናቸው፣ ለወደፊቱም ንጉሥ ምኒልክ ከፈቀዱላቸው አገር በቀር ወደሌላ እንዳታልፉ ብለን አስምለን አስገዝተን ሰደናቸዋል፣ እኔም ወደዛው እየመጣሁ ነው’ የሚል ደብዳቤ ለምኒልክ ላኩላቸው፡፡
7. በ1878 ዓ.ም ራስ ጎበና ከሌቃ መጥተው ከንጉሥ ምኒልክ ጋር በመገናኘት ብዙ ግብርና ገጸ በረከት አቀረቡ፡፡ በዳር አገር ያሉት ባላባቶች በሙሉ ራስ ጎበናን ተከትለው በመምጣት ከምኒልክ ጋር ተገናኙ፡፡ የጌራ ንግሥት ግን ልጇ ገና ህጻን ስለነበር ለመምጣት ሳትችል ቀረች፡፡
8. በ1880 ዓ.ም በወለጋ በኩል ብዙ ነፍጥ ያለው ደርቡሽ ተነስቶ ኢትዮጵያን ወረረ፡፡ ራስ ጎበናም ገስግሶ ሄዶ ግንባር በመግጠም ደርቡሹን ወግቶ ድል አድርጎ ፈጀው፡፡ ከዚያም ተመልሶ ግዳይ ጣለ፡፡ አጼ ምኒልክም ፈረስ ከነወርቅ መጣብሩ፣ ባለወርቅ ጋሻ፣ ባለወርቅ ጫማ፣ ጎራዴ፣ ማለፊያ ጠመንጃ፣ የወርቅ ዝናር፣ ባለወርቅ ለምድ፣ ወርቅ፣ ኩፈታ፣ ግምጃ ሱሪ፣ ግምጃ መታጠቂያ፣ ቀጭን ድርብ ለራስ ጎበና ሸለሙት፡፡
ምንጭ፣
1. የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥት ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ፣ ገጽ 96፣ 116፣ 124፣ 126-128፣ 152-153
2. ታሪክ ዘመን ዘ ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ፣ ከጸሓፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ ገጽ 150
3. የ20ኛው ክ/ዘመን መባቻ የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ካየሁትና ከሰማሁት፣ መርስዔ ኅዘን ወልደ ቂርቆስ፣ ገጽ 146፣ 432
በተያያዘው ምስል የሚታየው በደብረ ሊባኖስ ከሚገኘው የራስ ጎበና ዳጬ መቃብር ላይ እንደተገኘ ተገልጾ በመጽሀፍቱ የታተመ የራስ ጎበና ምስል ነው፡፡
Filed in: Amharic