ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ
ስለ ኢትዮጵያ ፊደል ሌላ ጊዜ ጽፌ ሌላ ቦታ ያሳተምኩትን በመጠኑ ለዋውጬ ላካፍላችሁ።
ኢትዮጵያ የትም ከሌላ አገር የማይገኝ የራሷ ፊደል አላት። የሩቅ ምሥራቁን (የቻይናን፥ የኮሪያን . . .) ለብቻ ትተን የቀረውን ስናየው የተለያዩ ቋንቋዎች ፊደሎቻቸው ዝምድና እንዳላቸው ምልክት እናያለን። በላቲንና በኢትዮጵያ ፊደል መካከል ያለው ዝምድና እንኳን ደብዛው ፈጽሞ አልጠፋም። ለምሳሌ፥ እነዚህን እናስተያያቸው፤ አ (A), ተ (t), መ (m), ወ (w), ቀ (q).
እዚህ ላይ የኦሮሞ ልሂቃን ቢሰሙት የማይወዱት ነገር አለ። ቁቤ የሚሉት የላቲን ፊደል በብዙ ተዘዋዋሪ ከኛ ፊደል የተወሰደ ነው።
ግን ከፊደሎች ሁሉ ከኢትዮጵያው ፊደል ጋር የበለጠ ዝምድና የሚታይበት “የደቡብ ዐረብ” ወይም “የሳባውያን” የሚባለው ፊደል ነው። ሆኖም፥ ብዙ ጥናት ሳይደረግ፥ የፊደሎችን ተመሳሳይነት በማየት ብቻ፥ “ዝምድናቸው አንዱ የሌላውን ከመውሰድ የመጣ ነው” ማለት አይቻልም። ከተቻለ፥ የኢትዮጵያው ከሳባው ወሰደ ከማለት ይልቅ የሳባው ከኢትዮጵያው ቢወስድ ነው የማይባልበት ምክንያት የለም። “አንድ ጥንታዊ ሕዝብ ለራሱ ቋንቋ የፈጠረውን ፊደል ሌሎች ሕዝቦች ወስደው ለራሳቸው ቋንቋ መጻፊያ እንዲሆን አስተካክለውታል። ከነዚህ ሕዝቦች ውስጥ ኢትዮጵያውያንና ሳባውያን ይገኙበታል” ማለትም ይቻላል።
ስለ ዓለም ፊደሎች ስንነጋገር በኢትዮጵያ ፊደል ላይ አንድ የሚገርም ነገር እናያለን፤ የሌሎቹ ፊደሎች በ “አ” ጀምረው ሲዘልቁ፥ የኢትዮጵያው የሚጀምረው በ “ሀ” ነው። ይኸ አሰላለፍ ምን ምስጢር ይዞ ይሆን? መልሱ አልተገኘም።
ሌላ ተዛማጅ ጥያቄ፥ በያንዳንዱ ቋንቋ ውስጥ ያሉ የቋንቋ ድምፆች እጅግ የተወሰኑ ከሆኑና ማንኛውም ሕዝብ ለቋንቋው ፊደል የሚቀርጸው ለአንድ ድምፅ አንድ ፊደል ብቻ ከሆነ፥ ታዲያ በአማርኛ ውስጥ ለአንድ ድምፅ ለምን ሁለት ፊደል (አ፥ ዐ፤ ሰ፥ ሠ፤ ፀ፥ ጸ)፥ እንዲያውም ሦስት ፊደል (ሀ፥ ሐ፥ ኀ) አስፈለገ? ፊደሉ የግዕዝ ፊደል ነው። ግዕዝ ፊደል የቀረጸ ጊዜ እነዚህ ፊደሎች የሚያገለግሏቸው ድምፆች ነበሩት። ድምፆቹን ትናጋው ሊያሰማቸው የማይችል ሕዝብ አማራ ስለሆነ ጠፍተዋል። ታዲያ ፊደሎቹን አሁን ምን እናድርጋቸው? እርግጥ፥ “ሐሳብ፥ ኀይል፥ ዐይን፥ ሠናይ፥ ፀሓይ” እያልን በመጻፍ ፈንታ “ሀሳብ፥ ሀይል፥ አይን፥ ሰናይ፥ ጸሀይ” እያልን ልንጽፍ እንችላለን። እንዲያውም፥ ሐሳቡ ቀርቦ ተቀባይነት እያገኘ ሄዷል። ግን በእነዚህ ፊደሎች የተጻፉትን የጥንት መጻሕፍት ምን እናድርጋቸው? እነሱንም እንፋቃቸው? ቃላቱ አማርኛ ውስጥም አሉ፤ ሐሳብ፥ ኀይል፥ ዐይን፥ ፀሐይ፥ ወዘተ. ዛሬም ጥንትም አማርኛ ናቸው። እነዚህንና መሰሎቻቸው ቃላትን ስንጽፍ ምርጫችን የጥንትነታቸውን አክበረን እንደዱሮው መጻፍ፥ ወይም የዱሮ መልካቸውን ማስቀረት ነው። እንደዱሮው መጻፍ spelling መማርንና ዕውቀትን ይጠይቃል፤ ማበላሸት ግን ማንም ይችልበታል።
የኢትዮጵያ ፊደልና የኢትዮጵያ ቋንቋዎች፤
የኢትዮጵያ ፊደል ከምንጩ የተቀዳውና የተስተካከለው የግዕዝን ቋንቋ ለመጻፊያ ነበር። በዚያ መሠረት፥ ግዕዝን እስከዛሬ እያገለገለ ነው። ከዚያ ቀጥሎ የአማርኛ መገናኛነት ሲስፋፋና የትምህርቱ ኀላፊዎች፥ ማለትም አስተማሪዎቹና ደራሲዎቹ፥ አማሮች ሲሆኑና፥ በዚያ ላይ የውጪ ሰዎች ሃይማኖታቸውን በአማርኛ ማስተማር ሲጀምሩ፥ ላለመቀደም፥ በአማርኛ መጻፍ አስፈለገ። “አንድ ቋንቋ የሌላውን ፊደል መውሰድ ሲያስፈልገው፥ መምህራኑ የሚወስዱት አጠገባቸው ያገኙትን ፊደል ነው” ባልኩት መሠረት፥ የአማራ መምህራን የግዕዝን ፊደል ወሰዱ።
የወሰዱትን የግዕዝ ፊደል ለአማርኛ እንደሚያስፈልገው አስተካክለው እነሆ እየሠራንበት ነው። ማስተካከል ማለት የግዕዝ ፊደል ኆኅያት ለአማርኛ ቋንቋ አልበቃ ስላለ የሚያባቁ ኆኄያት ፈጠሩለት ማለት ነው። ለምሳሌ፥ በግዕዝ ፊደል “ጀመረ”፥ “ጨረሰ”፥ “ሸኘ”፥ “ቸኮለ” ብሎ መጻፍ አይቻልም። ምክንያቱን በግዕዝ ፊደል ውስጥ “ጀ”፥ “ጨ”፥ “ሸ” ፥ “ኘ”፥ “ቸ” የሉም። ስላላስፈለገው አልፈጠራቸውም። አማሮች የነዚህ ኆኄዎች ምንጮች የቶቹ የግዕዝ ኆኄዎች እንደሆኑ አጥንተው፥ “ጀ”ን ከ “ደ”፥ “ጨ”ን ከ “ጠ”፥ “ሸ”ን ከ “ሰ”፥ “ኘ”ን ከ ”ነ”፥ “ቸ”ን ከ “ተ” አስወለዱ። (ውሰድ–› ውሰጂ፤ ጠጣ –› ጠጪ፤ ተመለስ –› ተመለሺ፤ በተነ–› በትኚ)።
ማንኛውም ፊደል ለማንኛውም ቋንቋ መጻፊያ ሊሆን ይችላል ባልኩት መሠረት፥ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በገበያ ላይ ካሉት ፊደሎች (የግሪክ፥ የላቲን፥ የዐረብኛ፥ የቻይና፥የኢትዮጵያ . . . ፊደሎች) የትኛውንም ፊደል መርጠው ሊወስዱ ይችላሉ። ግን በሚወሰድበት ጊዜ፥ እንኳን ፊደልን ያህል ትልቅ ነገር ቀርቶ፥ ነገ አርጅቶ የሚጣል ዕቃ እንኳን የሚገዛው አማርጦ፥ አገላብጦ አይቶ፥ ይበልጥ የሚስማማ የመሰለው ተመርጦ ነው። አውጥተን አውርደን፥ የሩቁን አስበን ስናየው፥ ምርጫው ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች መጻፊያ ከሆነ፥ በብዙ ምክንያት፥ የኢትዮጵያ ፊደል ከመምረጥ የተሻለ ምርጫ የለም።
አንደኛ፥ አጻጻፋችን ከቋንቋው ጋር አብሮ ይሄዳል። ቋንቋው ሲለወጥ አጻጻፉም (the Spelling) አብሮ ይለወጣል፤ ተለውጦ በጊዜው ትክክል የሆነው ቃል ይጻፋል። ለምሳሌ፥ ዱሮ “ኸየት”፥ “አንቲ” ነበር የሚባለው። ወደሸዋ ስንመጣ “ኸየት” ተለውጦ “ከየት” ሆኗል፤ “አንቲ” ከሁሉም አገር “አንቺ” ሆኗል። አጻጻፉ አብሮ የማይለወጥ ቢሆን ኖሮ፥ አሁንም የትም ቦታ “ኸየት”፥ “አንቲ” እያልን እየጻፍን፥ “ከየት”፥ “አንቺ” እያልን (ያልተጻፈውን) እናነብ ነበር። ምሳሌውን ከእንግሊዝኛ ባመጣ የበለጠ ይብራራ ይሆናል። ለምሳሌ፥ በእንግሊዝኛ laugh, doubt የሚሉ ቃላት አሉ። የቃላቱ ድምፅ ተለውጦ ሳለ፥ አጻጻፉ (the spelling) ባለመለወጡ አሁንም የሚጻፈው laugh, doubt እየተባለ ነው። የቃላቱ ድምፅ ግን ተለውጦ laf, dout ሆነዋል። የአጻጻፍ ልምዳችን የተማርነውን ሳይሆን የምንሰማውን ነው።
የአማርኛ ፊደል የሚመረጥበት ሁለተኛው ምክንያት “ሳይቸግር ጤፍ ብድር” የሚባለው ነው። የሚፈለገው ለመጻፍ ከሆነ የሌላ አገር ፊደል የሚመረጥበት ምክንያት የለም። ስለኦሮምኛ አጻጻፍ በምንወያይበት ጊዜ፥ “የላቲኑ ፊደል የተመረጠው፥ በጥናት ላይ ተመርኩዞ ነው” የሚለው ክርክር ይነሣል። አያዋጣም፤ “የአማራ ፊደል አንፈልግም” ብሎ እቅጩን መናገር እውነተኛ ያደርጋል። አጥኒዎቹ ምርጫ የሚደረገው ለመጻፍ መሆኑን ብቻ ዓላማቸው ያደረዱ ገለልተኞች የቋንቋ ምሁራን መሆን አለባቸው።
ሦስተኛው ምክንያት፥ ብሔራዊ አንድነት ነው። አንድ አገር፥ አንድ ፊደል፥ አንድ ባንዲራ ይመረጣል።
አራተኛው ምክንያት፥ አንድ የተማረና መማር ያለበት ዜጋ ቋንቋው ያልሆነ ሌላ የኢትዮጵያ ቋንቋ ለመማር ቢፈልግ አዲስ ፊደልና አዲስ አነባበብ መማር አያስፈልገውም።
የኢትዮጵያ ፊደል የሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መጻፊያ እንዲሆን ተሞክሮ ፈተና አልፏል። “ወድቀሃል” አንበለው። “የአማራን ባህል አታሳዩን፥ አታሰሙን” ከሚሉ ሰዎች መካከል፥ “የኢትዮጵያ ፊደል እንኳን ለሌላዎቹ ቋንቋዎች ለአማርኛም አይስማማውም” የሚሉ አሉ። እንዲህ የሚሉት ወሬ ሰምተው ፊደላችንን ለማጣጣል እንዲመቻቸው ነው እንጂ፥ እውነት ለአማርኛ አዝነውለት ወይም በአማርኛ የሚጽፉ ሰዎች ሲቸገሩ አይተው አይደለም። የትኛውን የግዕዝና የአማርኛ መጽሐፍ ነው በኢትዮጵያ ፊደል ስለተጻፈ ሳናነበው ያለፍነው? አንዳንዶቹን መጻሕፍትማ ከመውደዳችን የተነሣ፥ ከእጃችን እንዳይወጡ እስከምንፈልግ ድረስ እንንከባከባቸዋለን።
አንባቢ ልብ ብሎት ከሆነ፥ “ፊደል የሚመረጠው ለመጻፍ ከሆነ” የሚል ሐረግ ደጋግሜ ጽፌያለሁ። ፖለቲካም አለበት ለማለት ነው። ለአማርኛ ባህል ቢደብቁት የማይደበቅ፥ እንደ እሳት የሚያቃጥል ጥላቻ አለ። “ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወገጥ” እንደሚሉ፥ አማርኛም በአማሮች ላይ ከተሰነዘረው ጥላቻ ገፈት ቀማሽ ሆኗል። የአማርኛን ቋንቋ ለልጆቻችን አናስተምርም ማለት የፍቅርና የአብሮ መኖር ምልክት አይደለም። አንዳንዶቹማ፥ “ኦሮሞዎች የኢትዮጵያን ባንዲራ ተሸክመው ማይጨው የዘመቱት ተገድደው ነው” እስከ ማለት ደርሰዋል። ይህን ለማለት እነ ክቡር ጀኔራል ጃገማ ኬሎ እስኪያልፉ ድረስ መታገሥ አልቻሉም።
“የኦሮሞ ሊቃውንት ባደረጉት ጥናት መሠረት ለኦሮምኛ የሚስማማውን ፊደል (ላቲንን) መርጠውለታል፤ ይህ ያለቀ፥ የደቀቀ ጉዳይ ነው፤ ኦሮሞ ያልሆኑትን የሚገዳቸው ጉዳይ አይደለም” የሚሉም ሰምቻለሁ። የኦሮሞ ሊቃውንት በኢትዮጵያው ፊደል ላይ ያገኙት ዋናው ድክመት “ለሚጠብቅ ድምፅ ምልክት የለውም” የሚል ነው። ሊቃውንቱ የቋንቋ ተመራማሪዎች ከሆኑ፥ ላቲን እንኳን ለሚጠብቅ ድምፅ ምልክት ሊኖረው እስከጭራሹም የሚጠብቅ ድምፅ የለውም። እንደሌለው እያወቁ በዚህ የመሸፈን አቅም በሌለው ሽፋን ጀሌውን ሕዝብ አታለውታል ማለት ነው። የብዙ ሕዝብ ፊደሎች (ዓረቢኛንና ዕብራይስጥን ጨምሮ) ለቋንቋዎቻቸው ለሚጠብቅ ድምፅ ምልክት የላቸውም። ግን መፍትሔ ፈልገውለታል። የኦሮሞ ሊቃውንት የሀገራቸውን ፊደል ወስደው ለዚች ትንሽ ችግር እንኳን መፍትሔ መፈለግ አቅቷቸዋል።
ጉዳዩ የሚገደው ኦሮሞዎችን ብቻ ከሆነና ኦሮሞዎች ከተስማሙበት በጥላቻ ላይ የተመሠረት ምርጫ ሊያደርጉ ይችላሉ። ኦሮምኛ ብሔራዊ ቋንቋ እንዲሆን ከታሰብ ግን፥ ጉዳዩ ብሔራዊ እንጂ ኦሮሞዎች ብቻቸውን የሚወስኑበት የኦሮሞዎች ጉልማ ሊሆን አይችልም። ጥያቄውም ከሌሎቹ ቋንቋዎች ይልቅ በኦሮምኛ ላይ የሚነሣው በዚህ ምክንያት ነው። የእነሱ ፖለቲከኞች ቋንቋቸውን የአማርኛ ባላንጣ አላደረጉም።
አማሮች ኢትዮጵያን የመሰለች አገርና መንግሥት ለመፍጠር፥ ትምህርት ለመዘርጋትና ሕዝቧን በዓለም ደረጃ ለማስከበር ምክንያት ሆኑ እንጂ፥ በአገሪቱም ሆነች በመንግሥቱ በረይቱማና ቦረን የተጠቀሙትን ያህል አልተጠቀሙም። በረይቱማና ቦረን ነባሩን ሕዝብ ጨርሰው በሰባው መሬት ላይ ሰፍረዋል። ኦሮምኛ ተናጋሪ ያልሆኑ አንዳንድ የአማራ ቤተ ሰብ በአጠገባቸው ቢያዩ፥ ለወያኔ ዕድሜ እየለመኑ ፈጇቸው። አማሮች “የኦሮሞ ደም ደማችን ነው” እያሉ ሲጮሁ፥ እነሱ “የኢትዮጵያን ባንዲራ አታሳዩን” እያሉ ይጮኻሉ። ምነው የኦሮሞ ፖለቲከኞች ነገር “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” ሆነብን!!