>
6:37 am - Wednesday December 7, 2022

“የዘንድሮው ኢድ  ምናልባትም በመቶ ዓመት ያገኘነው ታሪካዊ ኢድ ወይንም ረመዳን ነው” (ኡስታዝ  አቡበከር አህመድ)

የዘንድሮው ኢድ  ምናልባትም በመቶ ዓመት ያገኘነው ታሪካዊ ኢድ ወይንም ረመዳን ነው” ኡስታዝ  አቡበከር አህመድ

 

(ኢፕድ)

ይህንን ቀን አላህ አሳየን፣ በእኛ ዕድሜ ዕውን ሆነልን የሚሉ ሰዎች ደስታ ተናንቋቸው  አስተውያለሁ  ይላል ኡስታዝ  አቡበከር።  ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት እንደ አገር ያለው ችግር ለኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከባድ ጊዜያት ነበሩ። የዘንድሮው  የኢድ በዓልም ሆነ ረመዳን የተለየ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ምናልባትም በ100 ዓመት ያገኘነው ታሪካዊ ኢድ ወይንም ረመዳን ነው ብዬ አስባለሁ። ሁሉም በሚስማማበት፣ ጠንካራ ሊባል በሚችልና የሁሉንም ውክልና የያዘ ተቋም እንዲሆን የአንድነት መሰረት የተጣለበት ኢድ ነው፡፡ የዛሬው የኢድ በዓል የሚከበረው በእዛ ስሜት ነው፡፡

ያለማንም ጣልቃ ገብነት፣ ያለምንም እስር፣ ያለምንም ጫና እና ያለምንም መገፋት ሰው ሃሳቡን፣ የጠየቀው የለፋበትና የደከመበት ነገር ያገኘበትና በደስታና በሰላም የተጾመ ጾም ነው፡፡ አዲስ ዘመን በዛሬ ግንቦት 27 ቀን 2011 ዓም ኡስታዝ  አቡበከር አህመድን ይዘላች።  ለሙሉው  ቃለመጠይቅ  ሊንኩን  ይጫኑ።

ይህንን ቀን አላህ አሳየን፣ በእኛ ዕድሜ ዕውን ሆነልን የሚሉ ሰዎች ደስታ ተናንቋቸው  አስተውያለሁ  ይላል ኡስታዝ  አቡበከር።  ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት እንደ አገር ያለው ችግር ለኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከባድ ጊዜያት ነበሩ።

የዘንድሮው  የኢድ በዓልም ሆነ ረመዳን የተለየ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ምናልባትም በ100 ዓመት ያገኘነው ታሪካዊ ኢድ ወይንም ረመዳን ነው ብዬ አስባለሁ።

ሁሉም በሚስማማበት፣ ጠንካራ ሊባል በሚችልና የሁሉንም ውክልና የያዘ ተቋም እንዲሆን የአንድነት መሰረት የተጣለበት ኢድ ነው፡፡ የዛሬው የኢድ በዓል የሚከበረው በእዛ ስሜት ነው፡፡

ያለማንም ጣልቃ ገብነት፣ ያለምንም እስር፣ ያለምንም ጫና እና ያለምንም መገፋት ሰው ሃሳቡን፣ የጠየቀው የለፋበትና የደከመበት ነገር ያገኘበትና በደስታና በሰላም የተጾመ ጾም ነው፡፡

ኢድን ስታስብ ቀድሞ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው

ኡስታዝ አቡበከር፦ ኢድ ከሶላቱ ጀምሮ ሁልጊዜ አብሮነትን፣ ስብስብን ያመጣል፡፡ ከጾም በኋላ የሚገኝ ደስታ አለ፡፡ በሀዲስ እንደሚገለጽ አባባል ለጾመኞች ሁለት ደስታ አለ፡፡ አንደኛ ጾማቸውን ሲፈቱ ወይንም ሲያፈጥሩ፣ ሁለተኛው ደግሞ ከፈጣሪያቸው ጋር ሲገናኙ ነው ይላል፡፡ ከ29 እና ከ30 ቀናት ካፈጠሩ በኋላ በተለይም ደግሞ የደስታ ቀን ነው፡፡ በህብረት የሚሰገደው ሶላት ለእኔ ልዩ ስሜት አለው፡፡ ወንድ፣ ሴት፣ ትንሽ፣ ትልቅ ሳይል ሁሉም በአንድነት ተሰብስቦ ለፈጣሪ ምስጋና የሚገልጽበት ስለሆነም ልዩ ድባብ አለው፡፡

፦ የዘንድሮ የኢድ በዓልን ልዩ የሚያደርገውምንድነው?

ኡስታዝ አቡበከር፦ የ2011 ዓ.ም የኢድ በዓልም ሆነ ረመዳን የተለየ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ምናልባትም በ100 ዓመት ያገኘነው ታሪካዊ ኢድ ወይንም ረመዳን ነው ብዬ አስባለሁ። ሁሉም በሚስማማበት፣ ጠንካራ ሊባል በሚችልና የሁሉንም ውክልና የያዘ ተቋም እንዲሆን የአንድነት መሰረት የተጣለበት ኢድ ነው፡፡ የዛሬው የኢድ በዓል የሚከበረው በእዛ ስሜት ነው፡፡ ያለምንም መገፋፋት ስሜት ሙስሊሙ ሲመኘው የነበረውን ጠንካራ ተቋም መፍጠር ዕውን የሆነበት ነው፡፡ ለእዚህ ደግሞ ያለማንም ጣልቃ ገብነት፣ ያለምንም እስር፣ ያለምንም ጫና እና ያለምንም መገፋት ሰው ሃሳቡን፣ የጠየቀው የለፋበትና የደከመበት ነገር ያገኘበትና በደስታና በሰላም የተጾመ ጾም ነው፡፡ በእዛ ላይ ደግሞ እንደዚህ ጠንካራ ተቋም እንዲመሰረት ታሪካዊ መግባባት የተደረሰበትና ያ መሰረት የተጣለበት በመሆኑ አንድ ኢድ አይደለም ሁለት ሶስት ኢድ ነው ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ የዛሬው ኢድ ለእኛ ትልቅ ቀን ነው፡፡

፦ የዘንድሮው ኢድ በአንድነትና በመሰባሰብመከበሩ በሙስሊሙ ህብረተሰብ የፈጠረው ስሜት እንዴትይገለጻል ?

ኡስታዝ አቡበከር፦ ከህብረተሰቡ ጋር ባለኝ ቅርበትና ባገኘሁት መረጃ መሰረት የተፈጠረውን ስሜት ሁሉም ቦታ ላይ በምስጋና ነው የሚገለጸው፡፡ መጀመሪያ በሚመስል መልኩ በመላው የአገሪቱ ክፍል የጋራ አፍጥር ያደርጋል፣ አብሮ ይበላል ዱአዎቹና ጸሎቶቹን በጋራ ያደርጋል፡፡ ይህ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሚስተዋል ነው፡፡ በረመዳን ወቅት ከአገር ውጭም ተጉዤ ነበር፣ ሳዑዲም ለኡምራ ሄጄ ነበር፤ ያየሁት የተለየ ነው፡፡ ከደስታው ብዛት ሁሉም ሰው እያለቀሰ ሲቀበል አይቻለሁ፡፡

‹‹ይህንን ቀን አላህ አሳየን፣ በእኛ ዕድሜ ዕውን ሆነልን›› የሚሉ ሰዎች ደስታ ተናንቋቸው ይስተዋላሉ። ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት እንደ አገር ያለው ችግር ለኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከባድ ጊዜያት ነበሩ። የአሁኑ ስሜት የተለየ ነው፡፡ ሁሉም ቤት ደስታ፣ ሰላምና ፍቅር አለ፡፡ በዓሉን እንዴት እናሳምረው የሚልና የጋራ ስሜት ይታያል፡፡ በአጠቃላይ በጣም ደስ ይላል፡፡

፦ የዘንድሮ ረመዳን የግማሽ ጾምናየመጨረሻ አርብ በመንግስትና በሃይማኖት አባቶችምትኩረት ተሰጥቶት ተከብሯል፡፡ እነዚህ በዓላትን ልዩየሚያደርጋቸው ምንድን ነው? በሙስሊሙ ማህበረሰብስምን ስሜት ፈጥሯል?

ኡስታዝ አቡበከር፦ ወላሂ እነዚህ የረመዳን ቀናት ልዩ ናቸው፡፡ ረመዳን ባጠቃላይ በሙስሊሙ ህብረተሰብ ልዩ ቦታ የሚሰጠው ትልቅ ጊዜ ነው። ቁርአን የወረደበት፣ ፈጣሪ ለምህረት ባሪያዎቹን ዕድል የሚሰጥበት ትልቅ የእርቅና የምህረት ጊዜ ነው፡፡ በይቅርታ፣ በአውፍታብ ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት እንዲሁም ከፈጣሪ ጋር ባለ ግንኙነት ውዴታ የምንከጅልበት ትልቅ ጊዜ ነው፡፡ ይህንን ስሜት ነው እንድንጎናጸፍ የሚያደርገው፡፡ ረመዳን ባጠቃላይ መንፈሱ ይህ ነው፡፡

የመጨረሻዎቹ 10 ቀናቶች የተለዩ ጊዜያቶች ናቸው፡፡ በውስጡ ለይለት አልቀድር የሚባለውን የያዘ ከአንድ ሺ ወራቶች በላይ የሆነች አንዲት ለሊት አለች ትባላለች፡፡ ያቺ ቁርአን የወረደባት ዕለት ናት፡ በእዛ ቀን የሚሰራ በጎ ስራ ከ 83 ዕድሜ በላይ እንደሰራ ነው የሚቆጠር፡፡ ያ ነው ልዩ የሚያደርገው። በጣም ዕጥፍ ድርብ ምንዳ፣ ዋጋ የሚሰጥበት ጊዜ ነው። ከእዛ ደግሞ ትልቁ ጊዜ ተብሎ የምትጠበቀውና የምትታሰበው የረመዳን የ27 ኛው ሌሊት ነች፡፡ 27 ኛው እና 29 ኛው ላይ በጣም ትኩረት ይደረጋል፡፡ ያ ስለሆነ ነው በልዩ ሁኔታ የተደረገው፡፡ ዛሬ ደግሞ እንደ አገር በብዙሃን መገናኛ ሽፋን ተሰጥቶት፣ ያንን ስሜት ተጋርተውት፣ የአንድነቱ መገለጫ ሁሉም የተሳተፈበት ከሙስሊሙ ህብረተሰብ አልፎ ሌሎች ወገኖችም ይህንን ስሜት መጋራት የሚችሉበት ሁኔታ የተፈጠረበትና የተገለጸበት ስለሆነ ስለህዝቡ የሚጨነቅ መሪ የመጣበት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ይህ ለሙስሊሞች ዕድል ነው፡፡ ቤተ እምነቶች ላይ ያለ ልዩነት፣ ችግር፣ በተቋሞቻቸው ላይ የተፈጠረ ክፍተት ለአገር አይበጅም ለህዝቦችም አይጠቅምም። የሚጠቅመን አንድነታችሁ ነው የሚል መሪ መጥቶ ከመመልከትና ከመደገፍ በላይ ደስ የሚያሰኝ ነገር ለሙስሊሙ የሚኖርም አይመስለኝም። ይህ ነገር ተፈጥሮ ሲስተዋል ቀናቶቹን የበለጠ ውብ ያደርጋቸዋል፡፡ እነዚህ ቀናቶች በመላው አለም በመካ፣ መሲ ደላክሳ፣ ፍልስጥኤም ምድርና በሌሎቹም ቦታዎች ላይ በድምቀትና በልዩ ሁኔታ ሚሊዮን ሙስሊሞች በአንድ ላይ ተሰብስበው አላህን እየለመኑና እያመሰገኑ የሚያሳልፏቸው ጊዜያቶች ናቸው፡፡ ያ ደግሞ በኢትዮጵያም በተለያዩ መስጊዶች ላይ በቀጥታ የመገናኛ ብዙሃን ተላልፏል፡፡ ይህ ለሙስሊሙ ልዩ ክብር ነው፡፡ ሀቂቃ ውስጥ የሚፈጥርብህ፣ የአገራዊነት፣ የማንነት እና የባለቤትነት ስሜት እንደ ዜጋ የተሰጠህና ከምትገፋበት፣ ከምትሸማቀቅበትና ከምትፈራበት አየር ወጥተህ የሰላም፣ የአንድነት፣ የጋራና የእኩልነት አየር የሚፈጥር በመሆኑ ውብና ልዩ ያደርገዋል፡፡

፦ የጾም ወቅት ላይ መንግስትምየማህበረሰቡ አጋር የሆነበት አጋጣሚ ነበረ። ለምሳሌምጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለውጭዲፕሎማት ያደረጉት የኢፍጥር ፕሮግራም ምን አንድምታአላቸው?

ኡስታዝ አቡበከር፦ እነዚህ የአገር መረጋጋትና የሰላም መኖር መገለጫዎች ናቸው፡፡ መንግስትና ህዝቦች ላይ ያለ ግንኙነት ወይም ድልድዮች ብዙ ጊዜ በገዢና በተገዢ መካከል ሳይሆኑ የአብሮነትና የጋራ ስሜት ሊሆን ይገባል፡፡ መንግስት የእኛ ነው፣ ህዝብ የመንግስት ነው የሚለውን ማዳበር የሚችሉ ስሜቶች ናቸው፡፡ ስላንተ ህይወት፣ ስለማንነትህ፣ ስለአምልኮትህ የሚጨነቅ መንግስት አለ የሚለውን ስሜት ነው የሚፈጥረው፡፡ ሀቂቃ የዘንድሮውን የተለየ ያደርገዋል፡፡ ይህ አገራዊነት ለአንድ አገር እድገትና ብልጽግና እንዲሁም በህዝብና በመንግስት ደረጃ የተሻለ ድልድይ ነው፡፡ ብዙ ነገርን ያድናል ብዙ ነገርን ያክማል፡፡

ከሚነገር በላይ ማሳያ ነው፡፡ ከጎንህ አገር የሚያስተዳድር አካል አንተ የእኔ አካል ነህ፣ የአንተ ቀን የእኔ ቀን ነው ብሎ አስቦና እውቅና ሰጥቶ መምጣቱ የህዝብና የመንግስት ግንኙነት ምን ያክል ወደ ተሻለ ደረጃ እየተሸጋገረ መሄዱንና አገሪቱ ተስፋ እንዳላት ማሳያ ነው፡፡ የሚግባቡ፣ የሚቀራረቡ መሪና ተመሪ ያላት አገር መሆኗን የሚያሳይና የተለየ ስሜት የሚፈጥር ነው፡፡ ሁሉም እምነቶች የጋራ ክብር ይገባቸዋል፣ ለሁሉም እምነቶች የጋራ መንፈስ አለኝ የሚል መንግስት ሲመጣ አገሪቱ ተስፋ እንዳላት በትክክል ማሳያ ነው፡፡ ለየትኛውም ቤተ እምነቶች ክብር ማሳያና መገለጫም ነው፡፡

፦ተቀዳሚ ሙፍቲህ ሀጅ ኡመር ኢድሪስንእንዴት ትገልጻቸዋለህ ?

ኡስታዝ አቡበከር ፦ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በአገር ይመሰላሉ፡፡ ማህበረሰብን የሚወክል ሰው ይፈጠራል፡፡ ሲጠሩ ግለሰብ ያልሆኑ ብዙሃንን የሚወክሉ አሉ አይደል ? ቁርአን ኡማ የሚባል አገላለጽ አለው፡፡ አንዳንድ ነቢያቶችን አብርሃምን/ ኢብራሂምን ሲጠራቸው እንደ አንድ ማህበረሰብ ነው የጠራቸው፡፡ ግለሰብ ሆኖ ማህበረሰብ አለ አይደል ሙፍቲህ ሀጅ ኡመር ኢድሪስ ማለት ያ ናቸው። የብዙሃንን ሰው ውክልና ያላቸው ሰው ናቸው፡፡ ለሙስሊሙ ብቻ አይደለም ለኢትዮጵያ ባጠቃላይ እንዲህ አይነት አባት መኖራቸው ይህች አገር ብዙ ዕድልና ተስፋ እንዳላት ያመለክታል፡፡ እንዲህ የሚያለቅሱላት፣ የሚጨነቁላት፣ የሚጸልዩላት፣ ወደ አንድነት የሚጣሩላት፣ ስለ ሰላም የሚሰግዱላት፣ የሁሉም የሆኑ፣ የፍቅር አባቶች አሏት፡፡ የእርሳቸው ስብእና ለእኔ ግለሰብ ሳይሆን ማህበረሰብ አይነት ነው፡፡

፦ በእስልምና እምነትና ምዕመናኑ ዘንድአንድነትን እና ሰላምን ለመፍጠር ጠቅላይ ሚኒስትርዶክተር አብይ አህመድ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ እንዴትትገልጸዋለህ?

ኡስታዝ አቡበከር ፦ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ሊገነዘቡት የሚገባ ነገር ቢኖር አንድ ሴኩላር የሆነ መንግስት ለቤተ እምነቶች ምን ያክል ቅርበት ወይንም ርቀት ሊኖረው ይገባል የሚለው ነው፡፡ የተቀላቀሉ ስሜቶች ሊስተዋሉ ይችላሉ፡፡ ዶክተር አብይ የሄዱበት ትክክለኛ የመንግስትና የህዝብ ግንኙነት ስሜት ነው። ዶክተር አብይ በየትኛውም በሴኩላር ስርዓት ውስጥ መንግስት መፈጠር፣ መኖር ማለት የዜጎችን እምነት የሚንድ ማለት አይደለም፡፡ ሁሉንም እንደ ዜጋ አክብሮና አይቶ ያንንም በመልካም ጎኑ ማገዝና መተቸት የሚችል ስርዓት ማዘጋጀትና ማደራጀት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ያ እንዲመጣ ነው ዶክተር አብይ ያደረጉት፡፡ በእኛም ሂደት ውስጥ ይህ እንዲፈጠር ቀና፣ በጎና እና ነጻ የሆነ ድጋፋቸውንና መንግስታዊ ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ብዬ አምናለሁ፡፡

በተለይ የኢትዮጵያ ሙስሊም ችግር የተቋም እጦት ችግር ነበር፡፡ የሚወክለኝ መሪ የለኝም ብሎ ነበር ለብዙ ዘመናት የጮኸው፡፡ ይህ ተቋም እውን እንዲሆንና ህዝቡ የሚያምናቸውና የሚወክላቸው መሪ እንዲፈጠር፣ ቁጭ ብሎ ተመካክሮ መፍታትና የማስተካከል ሃላፊነት አለባችሁ ብለው መጥተው አግዘዋል፡፡ በሲኖዶስም ተመሳሳይ ነገር ነው የሚታየው፡፡ ይህ ትክክለኛ የመንግስት ባህሪ መሆን አለበት ብዬ ነው የማምነው፡፡ መንግስት ከህዝቡ ተለይቶ የሚኖር አካል አይደለም፡፡ የራሱ እምነት ሊኖረው ይችላል እምነት አልባም ሊሆን ይችላል፡፡ ግን እንደ መንግስት ዜጎችን በእኩል አይን የሚያስተዳድርና የሚመራ፣ ባላቸው ነገርና በሚጠቅማቸው ማንነታቸው የሚደግፍና ከጎናቸው የሚቆም መሆን ያለበት፡፡ ዶክተር አብይ አህመድ ይህንን ስሜት አንጸባርቀዋል። የሰሩት በዕምነት ውስጥ ገብቶ አስተያየትና ሃሳብ መስጠት አይደለም፡፡ መልካም ነገር እንዲሰራ በሩን መክፈት፣ መደገፍ፣ ማገዝና እንቅፋቶችን ማንሳትን ነው ተግባራዊ ያደረጉት፡፡ ይህ ደግሞ እንደመንግስት ስንመኘው የነበረ ስለሆነ ትልቅ ርምጃ ተራምደዋል። እንደመሪም ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

፦ ከኢድ ጋር በተያያዘ የምታስታውሰው የተለየገጠመኝ ይኖርሃል?

ኡስታዝ አቡበከር፦ በተለያየ መልኩ ከልጅነት እስከ እድገት ኢድ በእኔ ህይወት ውስጥ አልፏል፡፡ በልጅነት ኢድ ልዩ ነው፡፡ ከምትበላው፣ ከምትለብሰው ጀምሮ ይህ የደስታ ቀን በጉጉት የሚጠበቅ ነው። በኢድ ላይ ለእኔ ልዩ ስሜት የነበራቸው ጊዜያቶች ሁለት ናቸው፡፡ በእስር ያሳለፍኳቸው ኢዶች ለእኔ ልዩ ናቸው፡፡ የብዙሃኖችን የተጎዳ ስሜት ጠግነህ እንዲድን ማድረግ ከባድ ነው፡፡ ማረሚያ ቤት ያሳለፍኳቸው ኢዶች በተለየ ሁኔታ የማስታውሳቸው ናቸው። በቤተሰቦቻችን ሙሉ ወጪውን ሸፍነን ታራሚው እንዳለ ተደስቶ እንዲውል አድርገናል፡፡ አልባሳትና ምግብ ጨምሮ ቤት ውስጥ ያሳለፉ እስኪመስላቸው ድረስ ልዩ ዝግጅት አድርገን ያሳለፍንበት ያ ጊዜ ልዩ ትዝታና ትልቅ ስሜት የሰጠኝ ነበረ፡፡

ከዚህ ውጭ በኢድ ቀን በኢድ ቀን እቤት ከማሳልፋቸው የበለጠ የሚያስደስተኝ ምስኪን ሰዎች ጋር ሄጂ ማፍጠርና ለእነርሱ ማስፈጠር ነው፡፡ በበዓል በጎ ነገሮችን እናደርጋለን፡፡ እናም እንደነዚህ አይነት ጊዜያቶች ለእኔ ሁሌም የደስታ ጊዜያቶች ናቸው፡፡ ኢድ ለእኔ ለሌሎች ደስታ የሚፈጠርበት ጊዜ ሆኖ ሲያልፍ ነው ኢድ ነው ብዬ የማስበው፡፡ እኔ እቤት ከማሳልፈው ወገኖቼ ጋር ወይንም የተቸገሩ የማህበረሰብ አካላት ጋር ተገኝቼ ያ ሰው ተደስቶ ሲያልፍ ሳየው ነው ለእኔ ኢድ የተለየ ስሜት የሚሰጠኝ፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የመጣው ለውጥበተለየ ለሙስሊሙ ህብረተሰብ ይዞ የመጣው ነገርምንድን ነው?

ኡስታዝ አቡበከር፦ አገራዊ ለውጡ ለኢትዮጵያውያን በሙሉ የመጣ ለውጥ ነው። የጋራ የሆነ፣ ሁሉም ያለቀሰበት የዘመናት የትግል ውጤት ነው፡፡ የቅብብሎሽ ውጤት፣ ሁሉንም ዜጋ ያማከለና ብዙ ዋጋ ተከፍሎበት የተገኘ ነው፡፡ ለውጡ አንዱ ካንዱ በዕምነትና በብሄር የሚለይበት ነው ብዬ አላምንም፡፡ የሆነ አካል የሚገፋበትና የሆነ አካል የሚገንበት ከሆነ የለውጡን ምሉዕነት ያጓድለዋል ብዬ አምናለሁ፡፡

ስለዚህ ለውጡ ለዜጎች የጋራ የሆነ ነጻነትና ስሜት የተፈጠረበት የሰላም አየር ሆኖ ነው የሚሰማኝ። ያ እንዲሆንም ነው የምመኘውና የምፈልገው። ሁሉም ዜጎች እኩል ስሜትና እኩል የጋራ ደስታ እንዲጎናጸፉ፡፡ ማንም የማይገፋበት በይቅርታና በፍቅር የምንሻገርበት እንዲሆን አስባለሁ፡፡ መሰረታዊ ስሜቱ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

እንደማንኛውም ዜጋ ሙስሊሞችም የአገራዊ ለውጡ ተቋዳሽ ነን ብለን እናምናለን፡፡ ይህ አገራዊ ለውጥ እንዲመጣ ምናልባት ይህ ማህበረሰብ ዋጋ ከፍሏል፡፡ ድምጻችን ይሰማ ብሎ በፍርሃት ወቅት አደባባይ ወጥቷል፡፡ የተፈለገው ሌላ ነገር አይደለም። ዜጎች በእምነታቸው፣ በአመለካከታቸውና በአስተሳሰባቸው የተከበሩባት አገራቸው እንድትኖር ነው፡፡ የእኛ ፍላጎት፣ ጩኸትና ልመናም የነበረውም ይህ ነበረ፡፡ ይህ ደግሞ ዛሬ ተግባራዊ ሆኖ እያየነው ነው፡፡ ስለሆነም ከማንም በላይ ደስተኞች ነን፡፡ ትናንት ስንናፍቀው፣ ስንመኘው የነበረና የታገልንለትን ጠንካራ ተቋም የመመስረት ህልም ዕውን እየሆነ ይገኛል፡፡ እዚህ አገር ላይ ከባድ ችግር የነበረው መብት መስጠት እንደውለታ የሚቆጠርበት ሁኔታ ነው። መንግስት ለዜጎቹ መብት ሲያከብር እንደውለታ ይቆጥራል፡፡ ዜጎች ግዴታቸውን መወጣት አገራዊ ሃላፊነት አለባቸው፣ ለዜጎች መብታቸውን ማክበር ደግሞ የመንግስት ግዴታ ነው፡፡ ይህ ሁለቱ አካላት ተጋግዘው የሚፈጥሩት ነገር ነው፡፡ ይህ ነገር ነው ዕውን ሆኖ እያየነው ያለው፡፡ እንደሙስሊም ማህበረሰብ ያንን ነገር ጅምሩን አይተነዋል፡፡ በጣም ብዙ ጅምሮች አሉ፡፡ ለውጥ ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉ የተለያዩ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ እነዚህን የመጠበቅና የማስተካከል ሃላፊነት ደግሞ የዜጎችም የጋራ ነው፡፡ አደራ የምለው ይህ ለውጥ በምንም መልኩ እንዲቀለበስና ወደ ኋላ እንዲመለስ አይገባም፡፡ እንዲቀለበስ ዕድል ሊሰጥ አይገባም፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ ሁላችንም በመከባበር ዕውቅና በመሰጣጣት፣ በመተሳሰብ፣ በመፈቃቀርና በይቅርታ ብቻ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን የሚገፋበት ስርዓት ዛሬም ከመጣ ይህች አገር አገር ሆና ለመቀጠል በጣም ከባድ ነው፡፡ ማንም የሚገፋበት መሆን የለበትም። ሁሉም ዜጎች እንደ ዜጋ አገራችን ብለው ወደው የሚቀበሏት አገር መሆን አለባት፡፡ የትናንት ቁርሾን እያነሳንና የትናንት ጥፋትን እየቆጠርን መቀጠል የለብንም፡፡ አንዱ ሌላውን ለመውጋትና ለማጥቃት የሚሄድበት እሳቤም ካለ ለውጡን በሚገባ ለማስቀጠል አያስችልም፡፡ ኢዱ የፍቅር፣ የሰላምና የይቅርታ ኢድ ነው፡፡ በይቅርታና በፍቅር፣ በመከባበርና በመተሳሰብ አንድ ላይ በመሆንና እጅ ለእጅ በመያያዝ ይህችን አገር የተሻለች እናድርጋት፡፡

፦ በለውጥ ጊዜ ያለን እንደመሆኑ የሰላምዕጦት፣ የሰዎች መፈናቀልና አንዳንድ ተገቢ ያልሆኑተግባራት በአንዳንድ አካባቢዎች ሲከሰቱ ይስተዋላል፡፡በእንዲህ አይነት ሁኔታ የሃይማኖት አባቶች ሚናቸው ምንሊሆን ይገባል? ከህብረተሰቡስ ምን ይጠበቃል ?

ኡስታዝ አቡበከር፦ ለውጥ የሚያልፍባቸው ባህሪያት አሉት። የራሱ እንከኖችም ይኖራሉ። ለውጥ አዲስ ነገር ነው። የሚቀበለውም የማይቀበለውም አለ። ከጎረቤቶቻችን አገራት በመካከለኛው ምስራቅ ካየናቸው ተጨባጭ ክስተቶች በአንጻራዊነት ኢትዮጵያ በጥሩ ሁኔታ ላይ ናት ብዬ አስባለሁ። ከዛ ባሻገር ደግሞ የምንከፋበት ከእኛ የማይጠበቁ ከኢትዮጵያዊነት ስሜት ሊንጸባረቁ የማይገባቸው መገለጫዎች ደግሞ አሉ። የመገፋፋት ስሜትና አንዱ ሌላውን ያለመቀበልና ስሜት ጠቃሚ አይደለም። የኢትዮጵያዊነት ባህሪም አይደለም። ከዛ ውጭ አማኝ ተብለን የምንታሰብ ህዝቦች ነን። የኢትዮጵያ ህዝብ አማኝ የሚባል ማህበረሰብ ነው። ለእምነት ቅርብ የሆነ አካል ዕምነቱ ከሚያዘው ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ ይቅርታ ማንነት ወጥቶ ጎኑ ያለውን ወንድሙን ለማጥቃትና ለመጥላት በማንነቱ መርጦ ባልተወለደ ብሄሩ፣ ራሱ ባላመጣውና ባልፈጠረው ማንነቱ እርሱን ለመግፋት የሚደረገው እንቅስቃሴ ተገቢነት የለውም። ይህ አይነት ነገር ከአማኝ ማህበረሰብ ሰው ከሆነ ፍጡር የሚመጣ ነው ብዬ አላስብም። ስለዚህ ይህ ነገር መቆም ያለበት ጉዳይ ነው። ይበቃናል፤ አይጠቅመንም። አገራችን ደሀ አገር ናት። ዘር ቆጥረንና ተነካክተንና ቁርሾ አንስተን ተበቃቅለን ቀርቶ ያለንን ሙሉ ጊዜያችንንና ሃይላችንን ሰጥተን በፍቅርና በመተሳሰብ ተግተንም ይህችን አገር ጎረቤት አገሮች ከደረሱበት ደረጃ ለማድረስ እንኳን ብዙ ስራ ይቀረናል።

አባቶቻችን ያለፉበት እርከን አለ። ልጆቻችን ከእኛ የተሻለ አገር፣ ዕድገትና መልካም ነገር ማግኘት አለባቸው። ለእዛ ደግሞ ያንን ሁኔታ ማመቻቸት የእኛ ሃላፊነት ነው። ይህንን የምንፈጥረው ደግሞ በፍቅርና በአንድነት ነው። የዚህ ትልቅ ሚና ደግሞ የቤተ እምነቶች ነው። አማኝ የሆነ ማህበረሰብ ዕምነቱ ከሚያዝዘው ማንነትና ቀኖናው ከሚያዘው ህግጋት ከቤተ ክርስቲያንና መስኪዶች አፈንግጦ ወጥቶ ሰውን ስለመግደል፣ ስለመግፋት፣ ስለማሳደድ ስለማፈናቀል ካሰበ፣ ከተገፋና ከተቸገረ ወገኑ ጎን መቆም ካልቻለ ዕምነቱ በትክክል አልተተገበረም። ይህም አማኝና በተለይ ቤተ ዕምነቶች፣ የቤተ ዕምነት አመራሮችና አዋቂዎች የቤት ስራችን ብዙ መሆኑን ማሳያ ነው። ይህችን አገር ሊታደጋት የሚችልም አካል ይህ ሃይል ነው። ቤተ ዕምነት ላይ ያሉ አካላት ቢጮኹ ወደ ፈጣሪያቸው ሊያለቅሱ፣ አላህን ሊለምኑና ዱአ ሊያደርጉ ይገባቸዋል። ከእዛ አልፎም አማኞቹ ማህበረሰባቸውን የማስተማር፣ የመቅረጽና አቅጣጫና መስመር የማስያዝ ሃላፊነቱ በእነርሱ ላይ ተጥሏል። ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን መስራት አለብን። ሁሉም ቤተ እምነቶች ሊሰሩበት ይገባል። ህልውናው የተበላሸ፣ ስነ ምግባሩ የወደቀ፣ ከሰዋዊ ስሜት የወጣ አማኝ እንዳይፈጠር መስራት ይጠበቃል። አማኞቻችን ለእምነታቸው እንዲኖሩ፣ ለፈጣሪያቸው እንዲታዘዙ መልካምነትን እንዲላበሱ መደረግ ይኖርበታል። አንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው ከኢትዮጵያዊነት ያፈነገጠ ተግባር የቤት ስራችንን ባግባቡ እንዳልተወጣን ማሳያ ነው።

፦የአንድ እምነት ተከታይ የሆኑ ወጣቶችየሌላውን ቤተ እምነት የማጽዳት ተግባርስ እንዴትይታያል ? ምን መልዕክትስ ያስተላልፋል?

ኡስታዝ አቡበከር፦ ከመቻቻል ያለፈ ማንነት ሊኖር ይገባል ብዬ አምናለሁ። ሁሉም የሚከባበርበትና የሚተሳሰብበት አገር ሊፈጠር ይገባል። ይህ የመከባበር ስሜት ነው። ባለህ አመለካከት፣ በብሄርህ፣ በዕምነትህና በአስተሳሰብህ አክብሬ ወንዴሜ አድርጌ ተቀብዬህ ስኖር ላንተ እውቅና የመስጠቴ መገለጫዎች ናቸው። ያንን ነው የሚያሳየኝ። በእምነት፣ በብሄር፣ በአመለካከት ተለይተኸኝ ግን የእኔ ነህ ማለት ነው። ይህ ነው የሚፈለገውም ስሜት። ይህ መልካም ጅማሮ ነው። መስኪዱን፣ ቤተክርስቲያኑን የእራሱ አማኝ ከበቂ በላይ ያጸዳዋል፣ ያስውበዋል ግዴታው ስለሆነ። የእምነቱ ግዴታ በመሆኑ። ይህ ግን እኔ ካላንተ የለሁም፣ አንተ ካለእኔ የለህም የሚለውን ስሜት ማንጸባረቂያ ናቸው። እነዚህ ናቸው ማደግና መጎልበት ያለባቸው። ሰዎች በያዙት እምነትና አስተሳሰባቸው በፍጹም አንዱ ከሌላው የሚጠላበት ሁኔታ የለም።

፦ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለሰላም፣ ለልማት፣እንደ ችግኝ ተከላ ባሉ አገራዊ ጉዳዮች ሚናው ምንመሆን አለበት?

ኡስታዝ አቡበከር፦ አሁን በአገራችን ያለው አንጻራዊ የሰላም አየር ነው። ያ ትልቅ ደስታ ይሰጣል። እንደ ዜጋ መሆን አለበት ብዬ የማምነው ነገር አለ። ይህች አገር የጋራ አገራችን ናት። ደሃ አገር ላይ ነው ያለነው። ደሀ አገር ላይ ያሉ ዜጎች አገራቸውን እስኪለውጡ ድረስ ሁልጊዜም ተረጋግተውና ሰላም ሆነው አይኖሩም። ድህነታቸውን ቀርፈው ዜጎች እኩል የሚደሰቱባት አገር ሲሆን ነው ጀግንነታችንም ጥንካሬያችንም ማሳያ የሚሆነው። ጀግንነት በታሪክ አይሆንም። የአባቶቻችንን ታሪክ ብናነሳ አይጠቅመንም። ከእዛ ያለፈ ታሪክ መስራት አለብን። የተሻለ ሆነን መገኘት ይኖርብናል።

ይህንን ለማድረግ ደግሞ የጋራ ጥረትና ስራ ያስፈልጋል። አሁን ማህበረሰቡን ጠርቶ የሚያናግር መሪ መጥቷል። የጋራ አገርን የመገንባትና የማልማት ጥሪ ነው። የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ማከናወን ጀምረናል። ይህ በመላው አገሪቱ ሊቀጥል ይገባል። አገር መውደድና ማሰብን ማሳያ እንጂ ስራ አይደለም። እኛ ስንተባበር ይህችን አገር በምንፈልገው ደረጃ መቀየር እንችላለን። የአገር ፍቅራችንንና መልካምነትን በተግባር ማሳየት ይገባናል። አብሮ የሚሰራ መሪ አግኝተናል። ተከትለን እንፈጽመውና አገሪቱን እንለውጥ።

፦ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን እንዴትትገልጻቸዋለህ?

ኡስታዝ አቡበከር፦ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት። ኢትዮጵያ እንደ ስሟ፣ እንደታሪኳና ማንነቷ እንድትሆን እፈልጋለሁ። በእምነቷ ስትታይ የአብርሃም ተብለው የሚታወቁት የአይሁድ፣ የእስልምናና የክርስትና እምነቶች በጋራ የተስተናገዱባት አገር ናት። በታሪኳ ብዙሃነትን ጠብቃ የኖረች አገር ናት። ይህች አገር ከዚህም የበለጠ ማንነት አላት ብዬ አስባለሁ። ትናንት ኢትዮጵያን ታሪካዊ ያደረጓት የነበሩት ሰዎች ናቸው። ትውልዱ ርቀት ያለው ይመስለኛል። ትናንት የምናውቃት ኢትዮጵያ እና እኛ በብዙ ማንነታችን ተራርቀናል ብዬ አስባለሁ። እዚህች አገር ላይ ሌሎች ተጠልለው፣ ተሰድደው፣ መጠጊያ ፈልገው፣ ጋሻ ሆኗቸው ነብዩ መሀመድ በእዛ ዘመን ውስጥ በመካከለኛው ምስራቅ ለተነሱ ከሌሎቹ አገራት ሁሉ መርጠው ኢትዮጵያን የፍትህና የዕውነት አገር ብለው ነው የገለጿት። በወቅቱ የነበሩት መሪ እኮ የክርስትና እምነቱን ተከታይ ነበሩ።

ኢትዮጵያ ፍትህና ደህንነትን የሰጠች አገር ናት። የትናንቷን ኢትዮጵያ አሁን ካለችዋ ኢትዮጵያ ጋር ሳነጻጽራት የተለያየች ናት። ጀግንነት የፌስ ቡክ አርበኛ በመሆን አይገለጽም። በብዙሃን መገናኛ በመቀስቀስና አንዱን ሌላው ላይ ማነሳሳትም ጀግንነት አይደለም። ለእኔ ጀግንነት ሃሳብን የመቀበል ስሜትና አቅም ያለን ሆኖ መገኘት ነው። ሃሳብ የምንፈራ ሰዎች ጀግኖች ልንሆን አንችልም። ሃሳብ የሚፈራ ትውልድ ነው ሃይልን፣ መጥላትንና መግፋትን የተጠቀመው። ስለዚህ ሃሳብን የፈራ ትውልድ ጀግና አይሆንም። በሃሳብ መከባበርና መወያየት የሚችል ትውልድ ነው ይህችን አገር በጀግንነት ማሻገር የሚችለው። የተሻለችውን ኢትዮጵያ ለመፍጠር በዚህ ስሜት ውስጥ ማለፍ ይገባል።

፦ ለኢድ በዓል የምታስተላልፈው መልዕክትካለህ?

ኡስታዝ አቡበከር፦ አጠቃላይ ለኢትዮጵያውያንና በአለም ለሚገኙ ሙስሊሞች የኢድ በዓል የተከበረ፣ ያማረ የደስታ ኢድ ያድርግላችሁ። ኢድ ማለት አዲስ ልብስ መልበስ አይደለም። መልካም ምግብ መመገብም አይደለም። ፈጣሪን በመፍራት የሚከበር ነው። ሰው ለፈጣሪው ታዝዞና ለፈጣሪው ትዕዛዝ ቀናኢ ሆኖ ያደረባቸው ቀናቶች ሁሉ የእርሱ ኢዶቹ ናቸው። ፈጣሪ የማይከፋባቸው ስራዎችን መስራት ነው ኢድ ነው ብዬ የማስበው። ፈጣሪ ያልተከፋባቸው ስራዎችን የሰራንባቸው ቀናት ኢድ ናቸው። የኢድ ቀናትን ለእራሳችንና ለሌሎችም እንዴት ደስታ እንደምንፈጥርባቸው ማሰብ አለብን።

በአገራችን ላይ ዛሬ ብዙ ወገኖች ተገፍተዋል፣ ተሰድደዋል፣ አገርም ወድቋል። ይህ እንዲቀየር፣ እርቅ እንዲመጣ፣ ሌሎች የሚታሰቡበት የሌሎችን ችግር የምንካፈልበት፣ ለተራቡ የምንደርስበት፣ ለታረዙ የምናለብስበት ኢድ መሆን ይኖርበታል። የተራቡትን ማብላት፣ የታረዙትን ማልበስና የተቸገሩትን ከደረሰባቸው መከራ ማውጣትና ኢድ መሆኑ እንዲሰማቸውና በዓል መሆኑን እንዲያስቡት ማገዝ ይገባናል። ሙሉ ኢዳችንን ከተቸገሩ፣ ከተፈናቀሉ፣ ከተገፉ ወገኖች ጎን በመቆም እናሳልፍ። የሰላም፣ የፍቅር፣ የመከባበር ኢድ ያድርግልን።

፦ ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስምአመሰግናለሁ!

ኡስታዝ አቡበከር፦ እኔም አመሰግናለሁ!

Filed in: Amharic