>

ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ባለስልጣን ጋር በመተባበር የተቀሰቀሰ ትዝታ!?! (በእውቀቱ ስዩም)

ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ባለስልጣን ጋር በመተባበር የተቀሰቀሰ ትዝታ!?!
(በእውቀቱ ስዩም)
ወደዚች ምድር ስመጣ  ማንኩሳ በጭላጭ ኩራዝ ተቀበለችኝ፤  ኩራዙ  ያራት ነገሮች ጥምረት ነው፤ የኮኮስ ቅባት  ጠርሙስ፤  በምስማር ተበሳ ቆርኪ፤ የዝሃ ክር እና ላምባ ፡፡
በጊዜው የኩራዝ ማብሪያ መቅረዝ አይታወቅም፤ ከያንዳንዱ ጎጆ የውስጥ ግድግዳ  ማእዘን ላይ በጭቃ የተሰራ የኩራዝ ማስቀመጫ ይኖራል፤ስሙ ባማርኛ መዝገበቃላት ውስጥ ባይገኝም ከትውስታየ አልጠፋም፤ “ጭጎት” ይባላል ፤የጀንበር መውጫ ምስራቅ እንደሆነ ሁሉ፤ የኩራዝ አድማስ ጭጎት ነው፤
አንዳንዴ ናፍጣ ስለሚጠፋ  ኩራዝ ጦም ታድራለች፤ ደግነቱ፤ አንድ     የቶማስ ኤድሰን ውቃቤ የቀረበው ባለገር፤ ጫቅማ ከተባለ  ዛፍ ፍሬ ውስጥ የሚበራ ዘይት እንደሚገኝ ደርሶበታል፤የጫቅማ ፍሬዎች  በሰበዝ ተበስተው፤ እንደ መነኩሴ መቁጠርያ ተደርድረው  የሚሰሩት  ሻማ   እንደ ስንደል ሳሙና ላይ  ተሰክቶ ይንቀለቀላል፤ ሽታው ግን እንደ ፎጥ ፈስ ያስመርጥ ነበር፤ ለወጋገኑ  ስንል ከፍሬው የሚወጣውን  ቅርናት እንታገሰዋለን፤ እና በየምሽቱ፤ በቤታችን ሳሎን ውስጥ ድክምክም  ያለ መለስተኛ የብርሃን ደሴት ይዘረጋል፤ በቤቱ ውስጥ ከታደሙት አንዱ የጨለማውን ግርማ የሚጋፋ ጨዋታ ያመጣል፤
“አለቃ ገብረሃና የማሽላ እርሻ ነበራቸው …”ብሎ ይጀምራል፤
……..
ለመጀመርያ ጊዜ ኤሌክትሪክ የሚባለውን  ተአምር ያየሁት  ደብረማርቆስ ስገባ ነው፤ ባየሁት አጥብቄ ተደነቅሁ! እኔ የመጀመርያዋን አምፖላችንን ለማድነቅ  በቤታችን ጣርያ ላይ ያንጋጠጥሁትን ያህል፤ ጋሊልዮ ወደ ሰማይ  ያንጋጠጠ አይመስለኝም፤ እቺ እንደ ዘር በቆሎ ባጥ ላይ የተንጠለጠለች፤ ብርሃን ያረገዘች ፤በመስኮት   የገባ ነፋስ የማያጠፋት፤  ከሽቦ የተሰራ ሆድ አቃ ያላት ምን ጉድ ናት? እያልሁ ስገረም አመሽ ነበር፤ ካንድ ከሁለት ወር በሁዋላ  ያምፖሊቱ ብርቅነት አከተመ፤  እንዲያውም ናቅሁዋት፤  እንዲያውም የጎረቤታችን አይነት  አምፖል ቢኖረን ብየ መመኜት ጀመርኩ፤ ጎረቤታችን   የናጠጠ ሞጃ(ሀብታም) ስለነበር ፤  በጊዜው” “የሸንበቆ መብራት” ተብሎ የሚጠራ ክንድ የሚያህል  ፍሎረሰንት  አምፖል ነበረው፤
1ያኔ ያምፖሉን ያህል መብራቱ እንደ ልብ አይገኝም ነበር፤  መንግስት የሚሰፍርልንን የብርሃን ራሽን፤ ቀበሌውና ቤተሰብ ተጋግዘው ይቆጥቡታል፤በጊዜው በራችን ላይ የተገጠመው ባልቦላ፤   “ቆጣሪ ” ከሚባል ቁዋጣሪ ቢባል ያምርበታል! ፤እንዲያውም አንድ ጊዜ  መምህራችችን ጉዋደኛችንን  ማታ ማታ ፤ ለምን  የቤት ስራውን ሳይሰራ  እንደማይመጣ ሲጠይቀው የመለሰው ትዝ ይለኛል  “ አባቴ ከሶስት ሰአት በሁዋላ መብራቱ እንዳይቆጥር ብሎ ያጠፋዋል!  ያሜሪካን ድምፅ ሬድዮ  ጣብያ የሚፈልገው በእጅ ባትሪ ነው”
በዚህ አይነት፤ አምፖልና ሻማ እየተጋገዙ  አዲሳባ ዩኒበርሲቲ በር ድረስ መሩን፤  አሁን ሳስበው፤ እንዴት ያንን ዘመነ ዳፍንት እንደተሻገርነው ይገርመኛል ፤ አምሽተን ወደ ቤታችን ስንገሰገስ ጉቶ አያደናቅፈን የቆመ ዛፍ አይገጨን፤ተምሶ የተዘነጋ ጉድጉዋድ አይውጠን ! ሳስበው ለብዙ ዘመና በጨለማ ውስጥ በመኖራችን የተነሳ፤ በጨለማ  እንድናይ የሚያችለን የሌሊት ወፋዊ ችሎታ    ሳናዳብር አልቀረንም፤
ያገራችን ሰው ምኞት የሚንፀባረቀው በህልሙና በስሙ ነው፤   “ ኢብሳ “፤ብርሃን “፤ብርሃነ  “፤ ፀዳል ፤ ነጋ የሚባሉ ስሞችን ብዛት ያስተዋለ ሰው  የህዝባችንን የብርሃን አምሮት  መጠን መረዳት  ይቻላል፤ተፈሪ መኮንን ሁለተኛውን የአማርኛ ጋዜጣ “ብርሃንና ሰላም “ ብለው ስም ካወጡለት አምሳ አመት ያለፈ መሰለኝ ፤ ታድያ ዛሬ ድረስ ብርሃንም ሰላምም ብርቅ ናቸው፤
 ካምስት ሚሊዮኑ ራት ጥቂት ወራት አስቀድሞ የዳግማዊ ምኒልክ ቤተመንግስት  የመጎብኜት እድል ገጥሞኝ ነበር፤ግዙፍ  የፋና ማብሪያ መቅረዞቹ እስከዛሬ ድረስ  ጣራው ፤ላይ እንደተንጠለጠሉ ይታያሉ፤ በጊዜው አዲሳባ ቤተመንግስት ውስጥ የሚንቀለቀለው ፋና የሚመረተው ባባጅፋር ግዛት በጂማ ውስጥ ነበር፤የዛሬውን አያድርገውና አዲሳባን ቆማ እራት የምታበላት ጅማ ነበረች፤
ዩንበርሲቲ ስንገባ  መብራት መቆራረጡ ቀጠለ፤ ሁሌም መብራት በሚጠፋበት ጊዜ የሴቶችና የወንዶች ዶርም እሚያዋስነው አጥር ላይ ቅልጥ ያለ ሁካታ  ይኖራል፤ ጆሮ ጭው እሚያረግ ስድብ፤ ድርያ ብልግና  እንካስላንታያ ከሱም ከሱዋም ይወረወራል፤  ሰዎችን  ጨዋ የሚያደርጋቸው በውስጣቸው ያለው የስነምግባር ህግ ሳይሆን ፤የፀሃይና የኤሌክትሪክ ብርሃን መሆኑን ያኔ  ደረስኩበት፤ በሌላ አነጋገር ፤የሌሎች እይታና ግምገማ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ  ሰዎች ሴጣናቸውን ፈተውን ለመልቀቅ አይመለሱም
ሌላውን ሌላ ጊዜ እንቀጥለዋለን፤
……
“አለቃ ገብረሃና የማሽላ እርሻ ነበራቸው፤ ሌሊት ሌሊት ማሽላውን የዱር አሳማ(እርያ) እየበላ አስመረራቸው፤ ቢጨንቃቸው አንዱን ሽማግሌ  ባላገር ምክር ጠየቁት ፤ባላገሩ፦
“ጌታው ይሄማ  ቀላል ነው! በማሽላው ማሳ ፊትለፊት ደመራ እሚያክል እሳት ያንድዱበት ፤አሳማው ደፍሮ አይጠጋም” አላቸው፤
አለቃ ምክሩን ተቀብለው እንጨት አንኮላኩለው ፤በማሳው ፊት አነደዱ፤የዚያን ሌሊት  ያሳማው መንጋ እሳቱን ከቁመነገር ሳይቆጥር በማሳው ላይ ባዲስ ጉልበት  ተሰማራበት
በማግስቱ ጠዋት ባላገሩ ብቅ ብሎ፤
“ አለቃ እንዴት አደሩ?”
“ እድሜ ላንተ! ያንን የዱር አሳማ በመብራት ሳበላው አደርኩ”
Filed in: Amharic