>

"የመከነ ፖለቲከኛ የኢትዮጵያን ታሪክ ከሚኒሊክ ይጀምራል።" ዓለማየሁ አረዳ (ዶር)  

“የመከነ ፖለቲከኛ የኢትዮጵያን ታሪክ ከሚኒሊክ ይጀምራል።”
ዓለማየሁ አረዳ (ዶር)  
“ኦነግን እንመለከት…ከተመሰረተ ረጅም ጊዜ ሆኖታል፡፡ የኦነግ ትልቁ ችግር ደግሞ ታሪክን ከሚመቸው ቦታ ቆንጥሮ መውሰዱ ነው፡፡ በትንታኔውም የሚያካትተው ከሚኒሊክ ጀምሮ ያለውን የኢትዮጵያ ን ታሪክ ብቻ ነው፡፡ ለምን መለስ ብለው የ16ኛው ክ/ዘመን ታሪካዊ ክንውኖችን ለመዳሰስ አይሞክሩም፡፡
በደቡብ ሸዋ አካባቢ አዳዲ ማርያም በ12ኛው ክ/ዘመን በፊት የተቋቋመ ነው፤በጉራጌ ዞን የሚገኘው “ገዳመ ኢየሱስ” የተገደመው በዮዲት ጉዲት ዘመን ነው፤ዝዋይ ሐይቅ ላይ ያለው ዘዬ ደሴት ውስጥ የሚገኙ ገዳማት፣ምድረ ከብድ ፣ዝቋላ ገዳም እነዚህ ሁሉ በትንሹ ከ700 ዓመት በፊት የነበሩ ናቸው፡፡ ይህ ታሪክ በቦታው ክርስቲያን ማህበረሰብ እንደነበር ይናገራል፡፡ ይህ ህዝብ የት ሄደ? የት ገባ? አሁን አካባቢው የኦሮሞ ነው፡፡ ስለዚህ በዚያ አካባቢ የነበረው ህዝብ ተውጧል፡፡
ስለታሪክ ስናነሳ ከሚመቸን ቦታ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ እኔ የት ነበርኩኝ? ምን አድርጌ ነው የመጣሁት በማለት መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ይህንን መረዳት ስንጀምር ኢትዮጵያዊነት ትርጉሙ ይገባናል…፡፡”
—-
በጉራጌ  ተቋርጦ የነበረው የገዳ ስርዓት ከ158 ዓመት በሁዋላ ተግባራዊ መሆን የሚለው ዜና በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ከተላለፈ በሁዋላ ብዙ መነጋገሪያ እየሆነ ነው። ጊዜ ሰጠኝ ብሎ ለመጠቅለል እና የሕዝብን ማንነት ለመጨፍለቅ የተደረገ ነው ከሚሉት ጀምሮ ጉዳዩን በአግባቡ ያልተረዱትም አሉ። ትላንት የተለያዩ ወገኖች አስተያየት እየሰጡበት ባለው በዚህ ጉዳይ የጉራጌ ሕዝቦች ንቅናቄ ድርጊቱን አውግዞ ተቃውሞውን በመግለጫ ገልጿል። 
ከጉራጌ ህዝባዊ ንቅናቄ (ጉህን) የተሰጠ መግለጫ!!!
እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ማሕበረሰብ የየራሱ የታሪክ የባህል እና የእሴት ቅርስ ባለቤት መሆኑ አያከራክርም፡፡ በመሠረቱ የአንድ ማሕበረሰብ ታሪክ፣ ባህል እና እሴት እንዲሁም የአንድ ሀገር ታሪክ በአደባባይ ለመናገር ደፍሮ ከመነሳት አስቀድሞ በእጅጉ መዘጋጀትና መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም የጉራጌን የባህል፣ የታሪክ፣ እና የእሴት ቅርሶችን ማናናቅ፣ ማጣጣል፣ ማራከስ እና በሌላ ማንነት ለመተካት መሯሯጥ ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለውና ባለፉት ስርዓት ያበቃለት ጉዳይ ነው፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ የባለብዙ ብሔር ብሔረሰቦች ሀገር እንደመሆኗ መጠን በተለያዩ ቋንቋዎችና ባህሎች የበለጸገች መሆኗ ይመሰከርላታል፡፡ እነዚህ ብሔረሰቦች የማንነታቸው መለያ የሆነ ከየትኛውም ጋር ያልተደባለቀ የየራሳቸው ባህል፣ ታሪክ፣ እና እሴት እንዳላቸው ሁሉ ባህላዊ መተዳደሪያ ደንቦች እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ የጉራጌ ህዝብም እንደሌሎች ኢትዮጵያውያን ህዝቦች፣ እንደ ነባር ኢትዮጵያዊነቱ የራሱ የሆነ ባህል ያለው ህዝብ እንደመሆኑ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ እሳካለንበት ዘመንም ድረስ የዘለቀ አሁንም እየተገለገለበት ያለ የራሱ የሆነ ባህላዊ የመተዳደሪያ ደንቦች ያሉት ህዝብ ነው፡፡
የጉራጌ ባህላዊ የአስተዳደር ስርዓት የህዝቡን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ባህላዊ ህይወቱን የሚመራበት የደንብ ምንጭ ከመሆኑም በተጨማሪ የዳኝነት ስርዓት በማካሔድ የጉራጌ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ጭምር ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ ያለው የጉራጌ ባህላዊ የአስተዳደር ስርዓት መገለጫው በመብቶች መከበር፣ በስልጣን ሽግግር፣እና በሁሉም ማህበራዊ ጉዳዮች ውስጥ የሚገባ በእውነተኛ የፍትህ ስርዓት ላይ የተገነባ ፍፁም ዲሞክራሲያዊ የነበረ እና ያለ የቤተ ጉራጌ ህገ-ደንብ ነው፡፡ በዚህ የጉራጌ ባህላዊ አስተዳደር ስርዓት ውስጥ የተደነገጉ ህጎችና ደንቦች የሚያስፈጽሙ አባቶች የየራሳቸው የሆነ ባህላዊ ስያሜም ጭምር አላቸው፡፡
በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በቀን 30/09/2011 የተካሄደው ዝግጅት የኦሮሞ እና የጉራጌ ሽማግሌዎች በጋራ በመሆን ሀገራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት፣ የሁሉቱም ብሔሮች ባህላዊ የአስተዳደር ስርዓት ለማስተዋወቅ እና የልምድ ልውውጥ ከማድረግ አንፃር ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አይካድም፡፡ የኦሮሞ እና የጉራጌ ህዝብ ሀገርን ከጠላት ወረራ ከማዳን አንስቶ በጋብቻ እና በባህል የተሳሰረ ህዝብ እንደመሆኑ መጠን እንዲህ አይነት የጋራ መድረክ መዘጋጀቱ ከመደገፉም በተጨማሪ በሁለቱም ህዝቦች መካከል ያለውን ታሪካዊ ትስስር ለማጠናከርም ከፍተኛ ጥቅም ስላለው መበረታታት እንዳለበትም እንረዳለን፡፡
በቀጣይም ይህ ሂደት ቀጥሎ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ባህላዊ የአስተዳደር ስርዓት በማሳተፍ እና በማስፋፋት እንዲሁም የልምድ ልውውጥ በማድረግ በማንነት ውስጥ ብቻ ከመታጠር ለሀገራዊ መግባባት፣ እኩልነትና አንድነት በጋራ ልንታገል እንደሚገባ እናምናለን፡፡
በዚህም መሠረት የጉራጌን ባህላዊ የአስተዳደር ስርዓት በኦሮሚያ አና በሌሎች ከተሞች በመመስረት የጉራጌን ታሪካዊ ባህላዊ መተዳደሪያ ደንብ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ በማድረስ ላይ የጉራጌ ሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በጋራ መስራት እንደሚገባን እያሳሰብን ዞኑ በዚህ ጉዳይ ለሚንቀሳቀሱ የጉራጌ ተወላጆች ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ግዴታ እንዳለበት ጭምር ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡
ሆኖም ግን ጉዳዩን ወደ ሌላ አቅጣጫ በማዞር የባህል ወረራ በሚመስል መልኩ ታሪክን ቆርጦ ይዞ መጽሐፍም ይሁን መረጃውን ከታማኝ እና ከገለልተኛ ምንጭ ሳያጣሩ መረጃ መስጠት እና ለክርክር ማቅረብ በህዝቦች መካከል ያለውን መተሳሰብ እና መተቃቀፍ የሚሽር እንደመሆኑ በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት ስለማይኖረው በመንግስት ደረጃ ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ክትትል ሊደረግበት ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬት ከ158 ዓመት በፊት ተቋርጦ የነበረውን የገዳ ስርዓት በወልቂጤ ከተማ በድጋሚ ተቋቋመ በሚል ያሰራጨው ዜና ፈፅሞ ታሪካዊ እውነታም ማስረጃም የሌለው ተራ አሉባልታ ከመሆኑም በላይ የጉራጌን ባህላዊ አስተዳደር እንደሌለ ለማድረግና የህዝቦችን ትስስር ለመሻር የተደረገ የተወሰኑ ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎች አካሄድ በመሆኑ የመንግስት ሚዲያ እንደመሆኑ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ያስተላለፈው ዜና በማስተካከል በድጋሚ መዘገብ እንደሚገባው በጥብቅ እናሳስባለን፡፡
የጉራጌ ዞን አስተዳደር እና የዞኑ የሚመለከታችሁ አካላት በሙሉ የጉራጌን ታሪክ፣ ባህልና እሴት ከመጠበቅ እና ለትውልድ እንዲተላለፍ ከማድረግ ኃላፊነት አንፃር ህዝባዊ አካታችነቱ እስከምን ድረስ እንደነበረ፣ እና በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ ምሁራን፣ አባቶች፣ እና ወጣቶች ጋር አስቀድሞ በጉዳዩ ላይ ምን ያህል ምክክር እንደተደረገበት በአፋጣኝ በይፋ ለህዝብ ማብራሪያ እንድትሰጡበት እንጠይቃለን፡፡
ዝግጅቱን በተመለከተ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር፣ እና በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት በሚል በገጻችሁ ያስተላለፋችሁት መልዕክትና እና በተዘገበው ዜና መካከል ያለው ልዩነት በቂ ማብራሪያ በመስጠት ለህዝብ እንድታሳውቁ እንጠይቃለን፡፡
ለመላው ኢትዮጵያውያን ባለፉት ታሪኮቻችን የጠላናቸው እና የእኔነት ስሜት ብቻ የተንጸባረቀባቸው ያሳዘኑን ክስተቶች እና ጠባሳዎች ልናክማቸው ሲገባ ዛሬ በተራችን እኛ ልንደግማቸው እና በሌሎች ላይ ተጨማሪ ጠባሳ ፈጥረን ለልጅ ልጆቻችን ልናቆይ አይገባም፡፡አንድ በሚያደርጉን፣በሚያከባብሩን እና ሊያግባቡን በሚችሉ የታሪክ መዝገቦች ላይ ተንተርሰን ሀገር ከመገንባት ይልቅ በሚያለያዩን እና በሚከፋፍሉን ሴራዎች ተጠምደን ይችን ሀገር የብጥብጥ ቀጠና ለማድረግ የምንቀሳቀስ ኃይሎች ከድርጊታችን ልንቆጠብ እንደሚገባ አበክረን እንገልጻለን፡፡
ታሪካዊ ትስስር እና መስተጋብር ባላቸው በኦሮሞ እና በጉራጌ ህዝብ መካከል የተፈጸመው አይነት አሳፋሪ ድርጊት ለመፈጸም እጃቸውን ከተው የሚንቀሳቀሱ እና ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ አመራሮች፣ ሚዲያዎች እና አክትቪስቶች መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በጋራ በመሆን ሊያወግዛቸው እንደሚገባ እና አንድነቱን ይበልጥ ማጠንከር እንደሚገባው ለመግለፅ እንወዳለን፡፡
የጉራጌ ህዝባዊ ንቅናቄ (ጉህን)
Filed in: Amharic