>

ከዐቢይ አሕመድ ይልቅ "የውጭ ኃይሎች" የተሻሉበት ምክንያት/መሥፈርት ምን ይኾን? (አባስ ከሳሁን)

“የውጭ ኅይሎች ጣልቃ ገብተው የሽግግር መንግሥት ይመሥርቱልን!!!”    “ሻለቃ” ዳዊት ወልደጊዮርጊስ
ለመኾኑ ከዐቢይ አሕመድ ይልቅ “የውጭ ኃይሎች” የተሻሉበት ምክንያት/መሥፈርት ምን ይኾን?
አባስ ከሳሁን
ብዙ ጊዜ በተቻለኝ መጠን ስለ ገለሰቦች ባላወራ እመርጣለሁ። አንዳንድ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ሲገጥሙ ያው እገደዳለሁ።
አቶ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣን ኾነው አገሪቷ በታሪኳ ካየቻቸው ክፉ አበሳና ፖለቲካዊ ቅርቃር ውስጥ ከከተቷት በኋላ ጥለዋት ጠፉ። ባለፉት 30 ዓመታት ስለ ኢትዮጵያ ምንም ያልተናገሩት አቶ ዳዊት በሕዝብ አመጽ ኢሕአዴግ በትንሽም ተሻሽሎ (ተዳክሞ) ወደ አገር ለመግባት እድሉን አገኙ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሁን ያለውን ሥርዓት ሙሉ በሙሉ በፍጥነት አፍርሰው በሌላ እንዲተኩት በግልጽ (ባለኝ መረጃ ለዐቢይም በግል ነግረውታል አሉ፥ ግን እርግጠኛ አይደለሁም) መምከር ጀመሩ ። ያ ሳይሆን ቀረ።
ከዚያ በኋላ ሻለቃ የሚለው ሥማቸውን ደርበው  የሚገርም አስተያየት መስጠትን የየእለት ተግባራቸው አደረጉ። (ለምን ሻለቃ እንደሚባሉ ግራ ይገባኛል። ማዕረጉ አሁን የላቸው፣ ጥለውት ነው የጠፉት። ያው አንዳንድ ሰው ረዳት ፕሮፌሰር እከሌ ካልተባልኩ እንደሚለው አጉል ተቀጽላ ፈላጊነት ይመስለኛል)።
 በመሠረቱ ማንኛውም ሰው የፈለገውን ሐሳብ/ሰው/ድርጅት/ሥርዓት መደገፍም ኾነ መቃወም መብቱ ነው። ሁላችንም ያንን እናደጋለን። ተፈጥሮአዊም ነው።
የአቶ ዳዊት ላይ አስተያየት ልስጥ።
አቶ ዳዊት የሚሠነዝረአቸውን ትችቶች አንዳንዱ በጣም የምስማማበቸውና እጅግ ወሳኝ አስተያየቶች ኾነው ነው የማገኛቸው። ለዚህ ያለኝን አድናቆቴንና አክብሮቴን ሳልቸራቸው ካለፍኩ ንፉግነት ይኾንብኛል። ነገር ግን የአገሪቱ ችግር ልየታ (diagnosis) ላይ አንዳንዴ ከዛሬ 40 ዓመታት በፊት ላይ የተቸነከረ፣ የመነቸከና ከጊዜ ጋር መኼድ ይቅርና ያኔ ራሱ ትክክል ያልነበረ ነው። ለደርግም ውድቀት ምክንያት የኾነ “የብሔሮች ጥያቄን” ከመጠን በላይ አቅልሎ የማየት፣ ነገር አለባቸው። 1970 ደርግ የብሔሮች ጥያቄን በተመለከተ ያዘጋቸው መጽሐፍ አለ። “የጥቂት ወንድበዴዎች” አጀንዳ ነው ከማለት በዘለለ በጣም ስሁት የ Stalin ጽንሰ ሐሳብን misread ያደረገ ሰነድ ነበር። (በነገራችን ላይ ይህ ስሁት አረዳድ አሁንም በሕገ መንግሥቱም ጭምር ውስጥ አለ፣ የኢሕአዴግ አረዳድም ችግር ያለበት ነው)። ስለሱ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። ሌላው የችግር ልየታ ችግራቸው ጥላቻ የተጫነው እንደኾነ ብዙ ማስረጃ ከጽሑፋቸው ማውጣት ይቻላል።
ሌላ ችግራቸው ደግሞ የተሣሣቱ እውንታዎችን በአኃዝ በማከሸን አቅርበው “Ethiopian is a failed state” ለማለት ደረሱ። ኢትዮጵያ fragile/weak state መባል የጀመረችው ከመለስ ሞት በኋላ ለብዙ ተከታታይ ዓመታት ነው። አዲስ ነገር አይደለም። ይኼ ማለት ግን አሁን ከጽጥታ መደፍረስ ጋር ተያይዞ ያለውን የከፋ ሁኔታ ለማቅለል ፈልጌ አይደለም።
በጣም የገረመኝን ትልቅ አጀንዳ ነው ብዬ የማስበውን ነገር ላንሳና ላብቃ።
በብሔር ፖለቲከ ባያምኑም ዐቢይ ሥልጣን ይልቀቅና “ከኦሮሞና አማራ ውጪ ያለ ሰው ይምራን” ይላል?  ለምን matter ያረጋል ታዲያ አማራ/ኦሮሞ መኾን ብሔር issue ካልሆነ በአገራችን?
ያ ሰውስ ሰላምን እንዲያመጣ ምን ዋስትና አለ?
የአገሪቱ የአገረ መንግሥት ምሥረታ መዋቅራዊ ግድፈት (structural deficit of/due to state formation ኾኖ ሳለ የመሪን  ብሔር ቀይረን ለውጥ ይመጣል ብሎ ማን ነገራቸው?
የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብተው የሽግግር መንግሥት ይመሥርቱልን ያሉት ነገር ሳይገርመኝም ሳያስቆጣኝም አልቀረም። በጦርነት ያልተሸነፈችና አንድም ጊዜ ቅኝ አልተገዛችም የምንላት ኢትዮጵያን በውዴታ አሳልፈን ለባርነት እንስጣት ማለታቸው ነው።
ለአቶ ዳዊት ይኼ ቀላል ነው። ምክንያቱም ጥለዋት ሲጠፉ “የድርሻዬን ወስጃለሁ” አሉ አሉ ገንዘብ ይዘው ጠፍተው እንደኾነ ሲጠየቁ። በቀላሉ የውጭ ኃይል መንግሥት ይመሥርትልን ሲሉ ሌላ ተጽዕኖ አድርጎባቸዋል ብዬ የማስበው የወላጅ አባታቸው ታሪክ ይመስለኛል። ጣሊያን 5 ዓመት ኢትዮጵያን ስትገዛና አርበኛ የገር ልጆች በሕይውታቸው ተወራርደው ሲዋጉ አባታቸው በጊዜው የጣሊያን “መንግሥታዊ” ጋዜጣ የነበረቺው “ልሣነ ቄሣር” ዋና አዘጋጅ/ዓርታዒ ነበሩ ይባላል። ዜሬም የውጪ ኃይሎች ጣልቃ ገብተው ከሽግግር መንግሥት ይመሥርቱልን ማለታቸው ከዚህ የባንዳነት ተጽዕኖ እንዳይሆን እሰጋለሁ እንጂ በፍጹም የአገር ፍቅር ነው ብዬ ማሰብ ይከብደኛል።
በዚህ ሰዓት አስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ መኾናችን ምንም ጥርጥር የለውም። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ነገሮችን በሚገባ አጢነውት አገር እየመሩ ነው ወይ የሚያስብሉ ነፍ ጉዳዮች አሉ። ነገር ግን መንቻካ ሐሳብ፣ አወናባጅ አኃዛዊ “ማስረጃዎችን” በማቅረብ ዘመቻ ማካኼድ፣ በራሥ ፈቃድ ቅኝ ልገዛ፣ አገር ትማረክ ዓይነት አርበኝነት ቢለቀን ጥሩ ነው። የኢትዮጵያ አገር ችግር መፍትሔ የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅ ብቻና ብቻ ነው ያለውና!
ለመኾኑ ከዐቢይ አሕመድ ይልቅ “የውጭ ኃይሎች” የተሻሉበት ምክንያት/መሥፈርት ምን ይኾን?
Filed in: Amharic