>

ሕወሓትን እና ሻእቢያን ለማስታረቅ የፌዴራል መንግሥቱ ዕገዛ ተጠየቀ!!! (ሻሂዳ ሁሴን)

ሕወሓትን እና ሻእቢያን ለማስታረቅ የፌዴራል መንግሥቱ ዕገዛ ተጠየቀ!!!

ሻሂዳ ሁሴን

 

የኤርትራ ገዥ ፓርቲ ሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) እና የትግራይን ክልል የሚያስተዳድረውን ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይን (ሕወሓት) ለማስታረቅ የፌዴራል መንግሥቱ ዕገዛ ተጠየቀ፡፡

‹‹ዳስ ዕርቂ አሕዋት ውድባት›› (የዕርቅ ዳስ) በሚል በሴሌብሪቲ ኢቨንትስ በተዘጋጀው የዕርቅ መድረክ፣ ሁለቱን ፓርቲዎች ለማስታረቅ፣ ድርጅቱ ማዕከላዊ መንግሥት ዕገዛ እንዲያደርግለትና ለእንቅስቃሴውም ዕውቅና እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረው ሰላም በሕወሓትና በሻዕቢያ መካከል አለመፈጠሩን የሚናሩት የሴሊብሪቲ ኢቨንትስ መሥራች ወንድማማቾቹ አቶ አብርሃምና አቶ ሀብቶም ገብረ ሊባኖስ፣ በሁለቱ ድርጅቶች ውስጥ የሚታየው ጥላቻና እልህ የአገርን ደኅንነት ሥጋት ላይ የሚጥሉ ድርጊቶች እስከ መፈጸም መድረሱን ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ የተደረጉ ጥናቶችም እንደሚያሳዩት፣ ሕወሓትን ያገለለው የኢትዮጵያና ኤርትራ ዕርቅ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የነበረውን መጠራጠርና ጥላቻ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ እንዲከር ማድረጉንም አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአየር ትራንስፖርት መግባትና መውጣት ቢቻልም ድንበር አካባቢ ምንም የተቀየረ ነገር የለም ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው ድባብም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሰላምም ጦርነትም የሌለበት እንደሆነ የሚናገሩት ወንድማማቾቹ፣ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ያለው እልህ ዕርቁ መሬት እንዳይወርድ እንቅፋት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በድርጅቶቹ መካከል አለ የሚባለው የከረረ ፀብ በተለይ ድንበር ላይ ላሉ ነዋሪዎች ከባድ ፈተና እንደሆነ፣ በሁለቱም ወገን መከላከያ ሠራዊት ሰፍሮ እንደሚገኝና አካባቢውን የማፅዳት ሥራ እንዳልተሠራ በመግለጽ፣ ‹‹በአገሮቹ መካከል የተፈጠረው ሰላም በድንበር ላይ ለሚኖሩ ዜጎች ጠብ አላለም፡፡ በነበረው ግጭት ተጎጂ የነበሩት በድንበር የሚኖሩ ዜጎች እንጂ የመሀል አገር ሰው አይለደም፤›› ሲሉ የተፈጠረው ሰላም የመሀል አገር ነዋሪዎችን የጠቀመውን ያህል የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ለሆነው የድንበር ነዋሪ ልዩነት እንዳልፈጠረ አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም ድንበር ላይ የሚኖረው ማኅበረሰብ የሚቀራረብበት ሕጋዊ መንገድ እንዲኖርም ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ የሚዋሰኑበት ከኢሮብ እስከ ዓድዋ የተዘረጋ 1,000 ኪሎ ሜትር ድንበር ላይ የሚኖሩ ዜጎች ሰላም በመፈጠሩ፣ ያገኙት የተለየ ጥቅም አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ በዚህን ያህል ቦታ ላይ በጦርነቱ ወቅት የተቀበረ ፈንጂ ባለመፅዳቱ በአካባቢው ማረስ፣ ማልማት፣ ትምህርት ቤት ወይም የጤና ኬላ መገንባት የማይታሰብ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የመከላከያ ሠራዊትም ከድንበሮች ባለመነሳቱ አካባቢው ከውጥረት ነፃ አይደለም ብለዋል፡፡ ድንበር ላይ ያለው ቦታ ለልማት ባለመመቻቸቱ ወላጆች ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ሲሉ፣ አሁንም ድረስ ሥራ ሊያገኙባቸው ወደሚችሉባቸው አካባቢው ርቀው እንደሚሄዱ  አብራርተዋል፡፡

ከዕርቁ በኋላ ድንበር ተከፍቶ የሁለቱ አገሮች ዜጎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ የተቻለ ቢሆንም፣ መንግሥት የጉምሩክ ሥርዓት  ተበጅቶለት ሕጋዊ እንቅስቃሴ እስኪፈጠር ተብሎ መልሶ መዝጋቱ የሚታወስ ነው፡፡ ‹‹እስካሁን ምንም አዲስ ነገር አላየንም፡፡ ሥርዓቱን ለመዘርጋትም ዓመት አይፈጅም፤›› በማለት በአገሮቹ ግንኙነት መካከል የጠራ ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡

‹‹የጦርነቱ የመጀመርያ መንስዔ የሆኑት ሕወሓትና ሻዕቢያ ወደ ዕርቁ ካልመጡ ድንበር አካባቢ ያለው ጉዳይ መፍትሔ እንደማይኖረው በጥናት ደርሰንበታል፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ ሁለቱን ድርጅቶች በማስታረቅ ረገድ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግና ለእንቅስቃሴውም ዕውቅና እንዲሰጥ የሚጠይቅ ደብዳቤ ባለፈው ሳምንት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ማስገባታቸውንም፣ ወንድማማቾቹ ገልጸዋል፡፡ ከሕወሓትና ከሻዕቢያም ጥሩ ምላሽ እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡

በአገሮቹ መካከል የወረደው ዕርቅ ፖለቲከኞች የሚዘውሩት ሲለው ሞቅ ሲለው ደግሞ ረገብ የሚል የስሜት ማዕበልም እንዳይሆን፣ ተመሳሳይ ባህልና ማኅበራዊ እሴቶች ለሚጋሩ ለሁለቱ አገር ሕዝቦች ፍላጎት ቅድሚያ እንዲሰጥ ሴሌብሪቲ ኢቨንትስ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ሰኔ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በሐርመኒ ሆቴል ባዘጋጀው ዓውደ ጥናት በተሳታፊዎች ተጠይቋል፡፡

በዕርቅ መድረኩ ምሁራን፣ አርቲስቶች፣ ዲፕሎማቶችና በዘርፉ ልዩ ልዩ መጽሕፍት የጻፉና ጥናት ያደረጉ ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል፡፡ በቀጣይ በሚዘጋጁ መድረኮች በድንበር ላይ የሚኖሩ ዜጎችን እንደሚያወያዩም ታውቋል፡፡

Filed in: Amharic