>

አባ ባሕርይ ወይንስ አባ ኦሮሞ? (አቻምየለህ ታምሩ)

አባ ባሕርይ ወይንስ አባ ኦሮሞ?
አቻምየለህ ታምሩ
የአባ ባሕሬይን መጽሐፍ አንብቦ ለጨረሰና የአጻጻፉን ጥራትና የስነ መዋቅሩን ልቀት ላስተዋለ ፊልም የማየት ያህል ቢሰማው አይፈረድበትም። መጽሐፉ በትዝታ አምስት መቶ ዓመትን ወደ ኋላ መልሶ ታሪኩ የተነገረበትን ዘመን የኖሩ ያህል ስሜት ይፈጥራል። ብዙዎቹ ኦነጋውያን ግን የአባ ባሕርይን መጽሐፍና መጽሐፉን ከግዕዝ ወደ አማርኛ በስተ እርጅና ዘመናቸው እረፍት ሳያምራቸው የተረጎሙልንን ፕሮፈሰር ጌታቸው ኃይሌን ሲያብጠለጥሏቸው ይውላሉ። ይህ የውለታ ቢሶቹ ኦነጋውያንና ተከታዮቻቸው አስጸያፊ ተግባር ግን የእውቀት ጾመኛነታቸውንና ድንቁርናቸውን እንዲሁም የበሉበትን ወጪት ሰባሪና የጎረሱበትን እጅ ነካሽ መሆናቸውን ከማሳየቱ በስተቀር ፋይዳ ያለውም።
ኦነጋውያን ሕሊና አልባ ነውረኞች ስለሆኑ እንጂ የአስራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መነኩሴ አባ በሕርይ ፍጹም ሞያዊነትንና ስነ ምግባርን በተላበ መልኩ ባይናቸው ያዩትን የኦሮሞ እውነተኛ ታሪክ በመመዝገባቸው መታሰቢያ ሊቆሙላቸው በተግባና የሚገባቸውን የታላቅ ሰውነት ክብር ሊያጎናጽፏቸው በተገባ ነበር።
ዛሬ ታሪክ እንጽፋለች የሚሉን ኦነጋውያን የታሪክ ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች ሁሉ የአባ ባሕርይን ሩብ ያህል ሞያዊና ሚዛናዊ የታሪክ አመዘጋገብ የላቸውም። የአባ ባሕርይን ጠንቃቃ ጸሐፊነትና ሞያዊ ስብዕና ለመገንዘብ ሩቅ ሳንሔድ ራሳቸው አባ ባሕርይ ያስቀመጡልንን ታሪክ ብቻ በማንበብ መጽሐፋቸውን ሲቋጩ ያሰፈሩትን መደምደሚያ ማየቱ ይበቃል። አባ ባሕርይ በመጽሐፋቸው በሙሉ የኦሮሞ አባ ገዳዎች ከደቡብ ኢትዮጵያ ተነስተው ወደ ሰሜን በሚፈልሱበት ወቅት የተቀዳጇቸውን ድሎች እንደወረዱ ሲዘግቡ በተለምዶ በራስ ወገን ወይንም በሌላ አቅጣጫ የተፈጸመን ተግባር እንደ ጀብዱ ማንሳት ባልተለመደበት ዘመን ሆነው ያንን ታሪክ መጻፋቸው የርሳቸውን የተለየ የአጻጻፍ ዘዴና ሚዛናዊ አቀራረብ የሚያሳይ ነው።
የአባ ባሕርይ በዘመናቸው ወደር የማይገኝላቸው ምሁርና የማያዳሉ ሀቀኛ ጸሐፊ መሆናቸውን በማያወላውል መልኩ ለመገንዘብ በድርሳናቸው ክፍል 18 ላይ በቀረበው ታሪክ ለሚዛናዊነታቸው በሰጡት ምክንያት ውስጥ የዘረዘሩትን አመክንዮ ማየት ይቻላል፤
“የቦረን ሙልአታ የዳሞትን ክርስቲያን አዳከማቸው፣ በታተናቸው፣ አገራቸውን አጠፋው። በሱ ዘመን ሸዋና ዳሞት ምድረ በዳ ሆኑ።
አንድ ጊዜ የጋላን ድል፥ አንድ ጊዜ የክርስቲያን ድል ብጽፍ፥ ዛሬ ላንተ ፥ ነገ ለሌላህ የሚለው የመጽሓፍ ልማድ ነው። ድሉም አንድ ጊዜ ለዚህኛው ሌላ ጊዜ ለዚያኛው ነው። ሁል ጊዜ የሚያሸንፍ አንድ እግዚአብሔር (ብቻ)ነው። ሀገሪቱም በጋላ እጅ ገባች፤ የተረፈ የለም።
ይህ መጽሐፍ በተጻፈበት ጊዜ የቢፎሌ ልጅ የሙልአታ ሹመት ሰባት ዓመት ሆኖታል። በዘመናቸው የሚሆነውን ውጊያና እልቂት በሕይወት ካለሁ እጽፈዋለሁ። ከሞትኩም ታሪኬንና የሚመጣውን ሉባ ታሪክ ሌሎች ይጽፉታል። ግን የሞተ ብፁዕ ነው፤ አርፏልና።”
[ምንጭ፡ ጌታቸው ኃይሌ (1995)፥ የአባ ባሕርይ ድርሰቶች፤ ኦሮሞዎችን ከሚመለከቱ ሌሎች ሰነዶች ጋር፥ ገጽ 89]፤
ይህ አባ ባሕርይ አሳዝኝ በሆነ መልኩ የጻፉት ታሪክ በዘመኑ ሲሆን ያዩትን የዐይን ምስክርነት ነው። ይህ እንግድህ በወቅቱ ስለ ነገሥታት ገድል ቀባብተውና አሰማምረ ይጽፋሉ በሚል «ደብተራ» እየተባሉ ከሚሰደቡት መካከል የሆኑት የኢትዮጵያዊው የጋሞው መነኩሴ የአባ ባሕርይ የአጻጻፍ ዘይቤ ነው። ስለ እውነት ለመናገር ይህ የአባ ባሕርይ ሞያዊና ሚዛናዊ የአጻጻፍ ዘዴ ዛሬ ካሉትን ሁሉም ብሔርተኛ የታሪክ ደራቾችና ጸሐፍት ጋርም የሚወዳደር አይደደም።
እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን አለም በሙሉ በጨለማ ይኖር በነበረበት በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንድ አባ ባሕርይ የሚባሉ የብርብር ማርያም መነኩሴ ቄስ ከፍ ሲል በተጠቀሰው የሕሊና ሚዛን እየመዘኑ በነበሩብት ወቅት ሲፈጸም ያዩትን ታሪክ ለብርሃን ለማብቃት ታሪካችንን አሳምረው ስለጻፉ የምስጋና ሐውልት ሊቆምላቸው ሲገባ ተማርን በሚሉት ኦነጋውያን ግን የኖሩበትን ዘመንና በዐይናቸውን ያዩትን ታሪክ ስለጻፉ ብቻ ሲያብጠለጥሏቸው ይውላሉ።
የኦሮሞ ብሔርተኞች ውለታ ቢስ ሆነው ነው እንጂ እንደ ሰው ቢያስቡ ኖሮ አባ ባሕርይ በጻፋቸው የኦሮሞ መገልገያዎችና ልዩልዩ ስያሜዎችን በሙዚየምነት የያዘውና አዲስ አበባ የተገነባው «የኦሮሞ ባሕል ማዕከል» የኦሮሞን ባሕል፣ አደረጃጀትና አኗኗር በተሟላ መልኩ ስዕላዊ ይዘት ሰጥተው በጻፉት በአባ ባሕርይ ስም የባህል ማዕከሉን በሰየሙት ነበር። ይህንን ማድረግ ባይቻል እንኳ ልክ እንደ ኤሮፓዊው ኢራስመስ መንደስ ሁሉ በቀለሙ ሰው በአባ ባሕርይ ስም «አባ ባሕርይ ነጻ የትምህርት እድል» ወይንም Abba Bahrey Scholarship Program ተቋቁሞ ሕዳግ ሰጥተው የአማርኛውን ትርጉም ሙሉዕ በማድረግ ከፍ ወዳለ ደረጃ ላደረሱት ለፕሮፈሰር ጌታቸው ኃይሌ መጦሪያ እንዲሆናቸው «ኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት» የሚባለው የገንዘብ ሽልማት፤ ከፕሮፌሰር ጌታቸው በፊት የአባ ባሕርይን ጽሑፍ ወደ አማርኛ በተሳካ መልኩ ለመለሱት ለብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ደግሞ የክብር ዶክትሬት ሊያበረክቱላቸው በተገባ ነበር።
በነገራችን ላይ ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ የአባ ባሕርይን መጽሐፍ ወደ አማርኛ የተረጎሙት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት የተሰጠው ኤርትራዊው አስመሮም ለገሰ ስለ ገዳ ምርምር ማድረግ ሳያስብ ነው። ጥላቻ ካልሆነ በስተቀር የአባ ባሕርይን መጽሐፍ ተጠቅሞ የዶክትሬት ማሟያ የጻፈውን አስመሮምን የክብር ዶክትሬት ሸልሞ ፕሮፌሰር ጌታቸውንና ብላታ መርስዓ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ የሚገባቸው ክብር የማይሰጡበት አንዳች ምክንያት የለም።
ኦነጋውያን አገር ለመመስረት ሲነሱ ስለ ኦሮሞ ባሕል ያስተጋቡትን እድሜን መሰረት ያደረገውን የገዳ አደረጃጀት ከስራ ስምሪት ጋር አዋደው ለታሪክ ያበረከቱት አባ ባሕሪ እንጂ አስመሮም ለገሰ አልነበረም። የገዳ ስርዓትን ለሁሉም ትውልድ እድሜን መሠረት አድርጎ ኦሮሞ በሚስፋፋበት ወቅት እያንዳንዱ የያንንዳንዱን ሰው ዕጣ ፈንታ የሚወስንና ዕድል የሚሰጥ መሆኑን የመዘገቡት አባ ባሕርይ እንጂ አስመሮም ለገሰ አልነበረም። ኦነጋውያን ባባሕርይ የተጻፈውንና በየ ስምንት አመቱ የሚካሄደውን የኦሮሞ ስልጣን ልውውጥ ታሪክ በማውሳት ፑልቶ ዲሞክራሲን ከኦሮሞ እንደወሰደ ለማያሳየት በማጣቀሻነት የሚያቀርቡት ብቸኛው ምንጭ የአባ ባሕርይን እንጂ የአስመሮምን የዲግሪ ማሟያ መጽሐፍ አይደለም። ሆኖም አስመሮም ለገሰን አክብረው አባገዳነትና የክብር ዶክትሬት ሲሰጡ አባ ባሕሬን ግን ደብተራ እያሉ ማውገዝ እንጂ ስማቸውን እንኳ በክብር ማውሳት አይሹም።
ደብተራ እየተባሉ በኦነጋውያን ዘንድ የሚንቋሸሹት አባ ባሕሪ ግን ከኦነጋውያን የተሻለ የሞያና የሕሊና ታማኒነት ነበራቸው። የትኛውም የኦነግ ዶክተርና ፕሮፌሰር ሲራቀቅ ቢውል ከአባ ባሕርይ ስራ የተሻለ ጽሑፍ ስለ ኦሮሞ እስከዛሬ ሊያቀርብና ሊያገኝ አልቻለም። እንዴውም አንዳንዶቹ ለምሳሌ እንደ ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን ያሉ የኦሮሞ ብሔርተኞች የአባ ባሕርይን መጽሐፍ እየኮነኑ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የተረጎሙትን የአባ ባሕርይን መጽሐፍ ግን የቻሉትን ያህል ዝቀው መጽሐፍ አሳትመዋል። ለነገሩ ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን ይህንን የሚያደርጉት አስተማሪዎቻቸው ፈረንጆቹ የኦሮሞን ታሪክ በሚመለከት ሲጽፉ የሚተነትኑት የተዋጣለቱን የአባ ባሕርይን መጽሐፍ ስለሆነ ነው። እንዴውም ኦነጋውያን ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች «ታሪካችን» የሚሉትን አጣመውና ፈጥረው ሲጽፉ ደብተራ እያሉ ከሚጠሏቸው ከአባ ባሕርይ የተሻለ የታሪክ ምንጭ ግን የላቸውም፤ አያቀርቡምም።
እንደ እውነቱ ከሆነ አባ ባሕርይ እንኳን በሌጣዎች ኦነጋውያን አንደበት ግዕዝ ጠንቅቀው በሚያውቁ በኢትዮጵያ ልሒቃን ዘንድ እንኳ ለማጣጣል የማይመቹ ምሁር ናቸው። «ኦሮሚያ» የሚባለው ክልል መስተዳደር የኦሮሞ ታሪክና ባሕል ጉዳይ የሚያሳስበው ቢሆን ኖሮ የኦነግንና የተስፋየ ገብረአብን ፈጠራ የኦሮሞ ታሪክ አድርጎ በሌለ ታሪክ የጥላቻ ሐውልት ከሚያቆም በየቦታው የተቀበሩ የአብያተ ክርስቲያን ድርሳናትንና መዛግብቶችን ለማፈላለግና ለመፈተሽ ባጀት ቢመድብ ጥሩ ስራ በሰራ ነበር። በተስፋዬ ገብረ አብ ልብወለድ ላይ ተመስርቶ ኦሮምያ ክልል የሚባለው አካል ወጪውን ሸፍኖ በወያኔ ኮንትራክተሮች የተገነባበው የአኖሌ ሐውልት ላይ የባከነው ገንዘብ በየ አብያተ ክርስቲያናት ተቀብረው የሚገኙትን ድርሳናትና መዛግብቶች ለመፈተሽ ጥቅም ላይ ቢውል ኖሮ ስለ ኦሮሞ የተጻፈውን ታሪክ ይበልጥ የተሟላና የነጠረ እውቀት እንዲኖር ባገዘ ነበር።
ኦነጋውያን የሚያወግዙት ስለ ገዳና ኦሮሞ ታሪክ የሰማይ ያህል ርቀት ከፍ ብለው እንዲናገሩ ያስቻሏቸውን አባ ባሕርይን ብቻ ሳይሆን አባ ባሕርይን ያፈራችውን የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጭምር ነው። ግብዝ ባይሆኑ ን ኖሮ ዶክተርና ፕሮፌሰር የሚሆኑበትን የአባ ባሕርይ ታሪክ ጥናት ዶሴ ጠብቃ ለብርሃን ያበቃችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መሆኗን ያውቁ ነበር። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አሁንም ልክ እንደ አባ ባሕርይ አይነት ገና ያልተመረመሩ ድርሳናትና መዛግብቶች አሏት። ከአባ ባሕርህይ ድርሰትና በኦሮሞ ታሪክ ዙሪያ ካበረከተቻቸው አስተዋጽኦዎች የምንማራቸው ቁምነገሮች መካከል አንዱ ቢኖር ከፍ ሲል ለመግለጽ የሞከርነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ማክበር ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ያፈራቻቸው አባ ባሕርይ የኦሮሞ ወታደራዊ ጭፍራ ጥንካሬ ተንትነው ሲያበቁ ባንጻሩ ደግሞ የኢትዮጵያን መንግሥት ድክመት ሲነቅፉ፣ እንደ እርሳቸው ካህን የሆኑ ሰዎችና ካህን ያልነበሩ ሰዎች ከውጊያ ለመሸሸ ሲሉ ካህንነትን መምረጣቸውን በመተቸት እውነታውን ሲያስቀምጡ፤ ኦሮሞን ጠላት ብለው አሳንሰው፣ የኢትዮጵያን መንግሥትና ወገኖቹን ወዳጅ ብለው አግዝፈው አልጻፉም። በእውነቱ እንደዚህ አይነቱ የኦሮሞ ታሪክ ፀሐፊ አባ ባሕርይ ሳይሆን አባ ኦሮሞ መባል በተገባቸው ነበር።
Filed in: Amharic