>
5:13 pm - Monday April 19, 7773

ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ ጉዳችንን ስሙት፣ ደረጃችን አስታውሱት!  (አፈንዲ ሙተቂ)

ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ ጉዳችንን ስሙት፣ ደረጃችን አስታውሱት! 
አፈንዲ ሙተቂ
የቢቢሲ የአማርኛ ድረ-ገጽ በትናንትናው እለት አንድ አስገራሚ ዜና ለጥፏል። ዜናው “ኢትዮጵያ የአሜሪካን የፕላስቲክ ቆሻሻ አልቀበልም አለች” የሚል ነው። በስህተት የተለጠፈ ዜና መስሎኝ ሰዎችን ጠየቅኩ። እውነት ነው አሉኝ።
—-
እንግዲህ በሌሎች ዐይን ስንታይ ያለንበትን ደረጃ ተመልከቱት። በተለይም የዓለምን ፖለቲካና ኢኮኖሚ በሚዘውሩት የምዕራብ ሀገራት ዘንድ ያለን ደረጃ እንዲህ የወረደ ነው። ለኢራን ድሮን እና ሚሳየል ይላካል። ለእኛ ደግሞ የፕላስቲክ ቆሻሻ ተሰብስቦ ይላክልናል። ኢራን ባላት ዘይትና በገነባችው ኃይል የተነሳ ባለከባድ ሚዛን ሆናለች። እኛ ግን አሁንም ታች ነን።
ቆሻሻው ኦርጋኒክ ቢሆን ኖሮ እኮ ምንም አይደለም። እንዲያውም በሁለት እጃችን አጨብጭበን በተቀበልነው ነበር። Organic ቆሻሻ በቀላሉ decompose ሆኖ ከመሬት ጋር ስለሚዋሐድ አፈሩን በቀላሉ በንጥረ ነገር ያበለፅጋል። እንደዚያ ዓይነት ቆሻሻ በፋብሪካ ከተመረተ ማዳበሪያም ሊበልጥ ይችላል።
ነገር ግን የተላከልን ቆሻሻ በማንኛውም ተፈጥሮአዊ መንገድ Decompose የማይሆነው የፕላስቲክ ቆሻሻ ነው። ፕላስቲክ ተመልሶ ወደ ኡደት የሚገባው ሲቃጠል ብቻ ነው። ከተቃጠለ ደግሞ አየሩን CFC በተባለው አደገኛ ጋስ ይሞላዋል። ፈረንጆቹ ይህንን ስለሚያውቁ ነው ከራሳቸው አየር አርቀው ወደኛ አመጡት።
ወደ አውሮጳ ለምን አልወሰዱትም? ወደ ዐረብ ሀገራት ለምን አልወሰዱትም? ወደ ደቡብ ምስራቅ እስያ ለምን አልወሰዱትም? መልሱ አጭር ነው።
ድህነታችን ነው ያስደፈረን። ድህነታችን ነው ለዚህ ያበቃን። ደሃ በመሆናችንና ከድህነት ለመውጣት የማንተጋ መሆናችን ነው ክብራችንን ያስነካው።
—-
ትሰማኛለህ???
የአስር ሺህ ዓመት ታሪክ አለኝ ብለህ ቀኑን ሙሉ ብትለፍፍ፣ “ሀገሬ የሉሲ መገኛ ናት” ብለህ ብትጀነን፣ በጠላት ያልተያዘች ብቸኛዋ ጥቁር ሀገር እያልክ ብትኩራራ፣ የገዳ ዲሞክራሲ ባለቤቶች ነን ብለህ ብትቆነን፣ የአክሱምና የላሊበላ ቅርሶች ባለቤት ነኝ እያልክ ብትመጻደቅ፣ ደሃ እስከሆንክ ድረስ በአለም አቀፍ መድረክ ላይ የሚሰማህ የለም። አንተ ለምዕራባዊያን ምንጊዜም እንደ ትርፍ ነገር ነህ። ብሄራዊ ውርደት መቼም ቢሆን አይቀርልህም።
ቀላል ምሳሌ:
 በአንድ የህንድ ሰፈር አንድ አውቶቡስ ከመስመር ወጥቶ ስምንት ሰዎችን ቢገድል ከቢቢሲ እስከ ሲ ኤን ኤን፣ ከስካይ ኒውስ እስከ ፎክስ ኒውስ እየተቀባበሉ ይዘግቡታል። እዚህ ሀገራችን ውስጥ ስልሳ ሰው የገደለ የመኪና አደጋ ግን ዜና ሆኖ በውጪ ሀገራት አይዘገብም (ምናልባት ቢቢሲ Focus on Africa እና አልጀዚራ ከዘገቡት ነው)። ይህ ልዩነት ለምን ተፈጠረ? መልሱ ግልፅ ነው። ህንድ የናጠጠች ሀብታም ሀገር ባትሆንም Neuclear Power ናት። እኛ ደግሞ የጠብሻን power ነን። ስለዚህ ማንም ዞር ብሎ አያየንም።
ሌላ ምሳሌ
በኢትዮጵያ አስራ አምስት ተማሪዎች ሰልፍ ወጥተው ቢገደሉ በምዕራቡ ዓለም ዜና ሆኖ አይዘገብም። በኬኒያ ወይንም በዚምባቡዌ አንድ ተማሪ ከቆሰለ ግን ርእሰ ዜና ይሆናል። የኛ ሞት እነርሱ ዘንድ የሚዘገበው ከመቶ በላይ ሰው ሲገደልብን ነው። ምክንያቱም Ethiopia is not a viable news making country for the Westerns.
—–
ለነፃነታችን ተዋግተን ጨቋኙን መንግስት አስወግደናል ተብሏል። ጥሩ!! 
ብሄራዊ ክብር ተጎናጽፈን ደምቀን እንድንታይስ ምን እያደረግን ነው? አንድ ዓመት ሙሉ በውሃ ቀጠነ ሰበብ መወዛገብ፣ መባላት፣ መናቆር፣ መቋሰል! መጠላለፍ፣ መግደል፣ መገዳደል፣ መፈናቀል፣ ማፈናቀል!
አምና በዛሬዋ እለት (ሰኔ 15/2010) ከሞላ ገደል ተቀራራቢ ሐሳብና ራእይ ሰንቀን ሰኔ 16/2010 ለሚካሄደው ሰልፍ ራሳችንን እያዘጋጀን ነበር። ዘንድሮ ግን እንደዚያ ዓይነቱ ተስፋ ሰጪ የለውጥ መንፈስ የለም። ሁሉም ነገር እየተሸረሸረ ጠፍቷል። ለዚህ ተጠያቂው ማን ነው?  መንግስት ነው? ወይንስ እኛ?
ሁላችንም ተጠያቂዎች ነን። መንግስትም ተጠያቂ ነው። ፓርቲዎችም ተጠያቂ ናቸው። ደጋፊዎቻቸውም ተጠያቂ ናቸው። ሚዲያዎችም ተጠያቂ ናቸው። የሶሻል ሚዲያ አክቲቪስቱም ተጠያቂ ነው። አንባቢውም ተጠያቂ ነው። ሁሉም ተጠያቂ ነው።
—-
ብሄራዊ ክብራችንን መገንባትና በዓለም አደባባይ ማሳየት ከፈለግን ዐበይት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ (ተቀራራቢ) የሆነ አመለካከት ያለው ህብረተሰብ መፍጠር ያስፈልጋል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የስራ ፍቅርን ማንገስና ስራ ፈጣሪነትን ባህላችን ማድረግ ያስፈልገናል። በሶስተኛ ደረጃ፣ በአሰራሩ ግልጽ የሆነ፣ ተጠያቂነትን የሚቀበል፣ ከሙስና የፀዳ፣ ፍትሐዊነትን የሚያጠብቅ፣ ህዝቡንና ሀገሩን የሚወድ፣ የስራ ፍቅር ያለው፣ በስትራቴጂያዊ እቅድና በቁጠባ የሚመራ አመራርና መንግስት ሊኖረን ይገባል።
ሶስቱ ካልተሟሉ ህዝቡም ደሃ፣ ሀገሪቷም ቱጃሮች ለቆሻሻ የሚመኟት ሆነው መቅረታቸው ሳይታለም የተፈታ ነው።
Filed in: Amharic