>

ሀገሬን ምን ነካት? (አባይነህ ካሴ)


ሀገሬን ምን ነካት?
አባይነህ ካሴ
ከሰቀቀናሟ ዕለተ ቀዳሚት ሰኔ ፲፭ እስከ ዛሬዋ ዕለተ ሰኑይ ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም. ሕይወታቸውን በጥይት ላጡት ሁሉ እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በቅዱሳን እቅፍ በገነት ያኑርልን፣ ለሐዘንተኞች በሙሉ ሁሉም ሟቾች የኢትዮጵያ ቤተሰቦች ናቸውና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ አረጋጊው መንፈስ ቅዱስ አጽናኝ መልአክን ይዘዝላችሁ፡፡ ሞት ማንም ይሞታል ብርቆች ሲሞቱ ግን ራሱ ሞት ያነጋግራል፡፡
ከሩቅ ከአድማሱ ሥር የብርሃን ብልጭታ ሲታየን ሊነጋ ነው ስንል፣ የሳቀልንን ወገግታ ተከትለን በተስፋ ዓለም ስንፏልል፣ ደረስንብህ ስንለው ብርሃናችን ወዴት ሔደብን? በጥሩር ፀሐይ ሰማይ ሥር የውኃ ሽታ ያዘለ ነጭ ባዘቶ ደመና ሊያዘንብልን ነው ስንለው እንዳንጋጠጥን መና ቀረ፡፡ በርኅቀት ሳይኾን በርቀት ተሰወረ፡፡ እኛን ቀርቶ ሊቃውንቱን አደናገረ፡፡ መጣ ያልነው እጃችን ገባ ያልነው ሁላ እየጣለን በረረ፡፡ ማር ያልነው ከምን ጊዜው መረረ፣ ወተት ስንለው የነበረው ከመቼው ጠቆረ፣ ሰላም ምነው ኢትዮጵያችንን አፈረ?
እኔ እኔ እኔ ከሚለው ባሕር እኛ እኛ እኛ የሚል የቡድን ውሽንፍር ውስጥ ገባንና ኢትዮጵያን ረሳናት፡፡ እርሷም እነዚህ ከንቱዎች እንኳን ለእኔ ለራሳቸው የማይኾኑ ገልቱዎች ብላ መታዘቡን ቀጥላለች፡፡ የደሟን እንባ ወደ ውስጧ ሕቅ ብላ ታነባለች፡፡ ከላይ ከላይ ደማቅ ፈገግታ እያሳየች፡፡ የጣቷ አንጓዎች እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ሲሉ ሲገዳደሉ ዝም ብላ ታለቅሳለች፡፡ የጠጒሮቻ ዘለላዎች በራሷ ላይ ሲሻኮቱ በሐዘኗ በግናለች፣ በክፉ ጦር ልቧን ተወግታለች፡፡ ሀገሬን ምን ነካት? ምንስ ነው የሚበጃት?
አብረው ማልቀስ እንጅ አብረው መቆም የማይችሉ ማሽንኮች ተፈልፍለው ሀገሬን ዕረፍት ነሷት፡፡ ለቅሶ ቤት ለመድረስ አዛኝ ቅቤ አንጓች ሁላ ከአለባበሱ እስከ አነጋገሩ አሳምሮ ይግተለተል እንደኾነ እንጅ፣ መቃብር ላይ ለመላቀስ ቀብር ለማስፈጸም ይደምቃል እንጅ ቁም ነገር ላይ ነጥፎ በጠመንጃ መፈላለጉን ትውልዱ ጀብድ አድርጎታል፡፡ እየሳቁ መግደል ሕገ መንግሥቱ ኾኗል፡፡ የመግለጫ ቃል በማዥጎድጎድ የሸፍጥ ኑሮውን ተክኖታል፡፡
በተመቸ ግርድፍ ቃል ወንድምን በመዝለፍ ድንበር በመዝለል ከልክ በላይ በማለፍ አጥንት የሚወጋ የቃል ጦር በማላጋት እና በመወራወር ሀገር መቁሰሏን ማን የወደዳት ተረዳላት? ንክንኩ ድንጋይ ይፈልጣል፣ የመከራ መዓት በአፍላጋቱ ይጓፍጣል፣ አላውቅም የሚል ጠፍቶ ሁሉም ሁሉን ያውቃል፡፡ አዎ ሁሉ ዐዋቂ ሲኾን ሁሉም ይታመማል ያን ዕለት ያን ሠዓት መድኃኒት ይጠፋል፡፡
ለሞቱት አሟሟት የሰማነው ትርክት፣ ልብ አያሳርፍም ገና አበቅ አለበት፡፡ እርሱ ሲጠራ የሚታይ ለጊዜው ግን የተሸፈነ እውነት እንዳይኖር ያሰጋል፡፡ ከአንድ ወገን ብቻ የሚሰማ በጥፍር የሚያቆም ንግግርም ቢኾን ታማኝነቱ ምን ጊዜም ከአጠራጣሪነት አይዘልልም፡፡ ጊዜ እያወጣ የሚያሰጣው እውነት ይኖራል፡፡
ወታደር ዘር የለውም እኔ የኢትዮጵያ ወታደር ነኝ ሲል የነበረውን መልካም ወላዲቷ አምጣ የወለደችውን ጀግና እንደዋዛ ማጣት አለው ብዙ ንዴት አለው ብዙ ቁጭት፡፡ ገዳይ የተባሉት ወይ በተኩስ ልውውጥ ወይ ራስን በመግደል እየተባለ ሞታቸው ይነገራል፡፡ አይታመንም ባይባልም ተጠግቶ ላየው ምኑም አያሳምንም፡፡
አንደኛ፡- ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ባሕር ዳር አጠገብ ዘንዘልማ በሚባለው አካባቢ መገደላቸው መነገሩ ጥርጣሬውን ከፍ ያደርገዋል፡፡ እኒህ ሰው ተሳዳጅ (fugitive) ኾነው ባለበት ጊዜ አብሯቸው ከነበሩም እንኳ ከጥቂት ተከታዮች በስተቀር ብዙ አጃቢዎች እንደማይኖሯቸው ይታወቃል፡፡ ዘንዘልማ ከባሕር ዳር ከተማ ዓባይን ተሻግሮ ያለ አካባቢ እንደመኾኑ በርከት ያለ አጃቢ ይዘው ሊሻገሩ ይችላሉ ብሎ መገመት አይቻልም፡፡ በሦስት ምክንያት አንደኛ በከፍተኛ ጥበቃ ሥር ባለችው ከተማ ውስጥ ተሰውረው ቆይተው ነበርና፡፡ ኹለተኛ በድልድይ የሚሻገሩ ከኾነ ከፍተኛ ጥበቃ እንደሚደረግበት በመገመት በርከት ብሎ ለማለፍ ቀርቶ ራሳቸው ለፉበት መንገድ እንኳ ያነጋግራል፡፡ ሦስተኛ በድልድይ ካልተሻገሩ ወይ በዋና ወይ በታንኳ ምናልባትም በጨለማ ዓባይን አቋርጠው ሊኾን ይችላል፡፡ ይህም በርከት ለማለት የሚመች አይደለም፡፡
እኒህ ሰው የነገሩ ሁሉ መነሻ እና አቀነባባሪ ተደርገው ስማቸው እየተነሣ ይገኛል፡፡ እንደዚህ ያለውን ቀንደኛ በከበባ መያዝ ሲገባ ወደ መግደል የተሔደበት መንገድ ሌላ ጥያቄ ከማስነሣት አያድንም፡፡ በዚህ ላይ ሰውዬው ሲታኮሱ ጥይት አልቆባቸው እንደነበር መረጃ ተሰጥቷል፡፡ ይህ ከኾነ ደግሞ አስጊነታቸውን በብዙ ደረጃ ቀንሶት ነበርና ለመያዝ የበለጠ ምቹ እንደነበር ያመላክታል፡፡ የተባሉት ሁሉ ትክክል ከኾኑ መረጃ ማጥፋት ዓይነተኛ ተልእኮ ለነበረው ዘመቻ (operation) ብቻ የተፈጸመው ድርጊት ትክክል ይኾናል፡፡ ሰውዬው በአካል ቢያዙ የሚያወጡት መረጃ እንደሚኖር በመስጋት በሕይወት ከሚቆዩ ሞታቸውን ማቅረቡ ተመርጦ ሊኾን ይችላል፡፡ ራሳቸውን ገደሉ ሳይኾን የተባለው በተኩስ ልውውጥ ተገደሉ ነው፡፡ ቀባብቶ ማምጣት ሊኖር ይችላል፡፡ እውነትን መልሶ በማቋቋም አይ ሰውየው ራሳቸውን ነው የገደሉት የሚል ዜና ከመጣ ደግሞ ነገሩ ዘወርዋራ የኾነበትን ምክንያት ማወቁ ይሻላል፡፡
ኹለተኛ፡- የምግባሩ ከበደ ሞት፡፡ ሌላው ተስፋ ሊሰጥ ወደ እውነተኛው መረጃ ሊያደርስ ይችል የነበረው የምግባሩ ከበደ ሞት መረጃ የማጥፋቱን ሥራ አቀላጥፎታል ብሎ ላለማሰብ የሚከለክል ነገር የለበትም፡፡ ይህ ሰው በሠዓታት ውስጥ ቅርብ ሀገር እስራኤል ደርሶ ሊታከም ይችል እንደነበር መገመት የማንችልበት ዘመን ላይ አይደለንም፡፡ መሞኛኘት እንዳይኾን እንጅ ወዲያው የጸጥታ ቁጥጥር እንደተደረገ ሲነገረን አምሽቷል፡፡ በሄሊኮፕተር በታገዘ መንገድ ለተሻለ ሕክምና መወሰድ ነበረባቸው፡፡ ይህ ለምን አልኾነም?
ሦስተኛ፡- የጀኔራል ሰዓረ ጠባቂ ሞት፡፡ ተይዘዋል እየተባለ በየዜና ማሠራጫው ሲነገር የነበረው ሰው ራሱን ገድሏል ወደሚል ዜና የተቀየረበት መንገድ እንድንጠረጥር እንጅ እንድንተማመን የሚያደርገን አይደለም፡፡ ራሱን የገደለን ሰው ተይዟል ብሎ ዜና የሚሠራባት ምክንያት ሴራን (conspiracy) ያሻትታል እንጅ ቅቡልነት አያስገኝም፡፡
ዐራተኛ፡- በዚያ ጭንቅ ሠዓት ጀኔራል ሠዓረ ቤት መኾናቸውም ሌላው ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ከቤቱ ኾኖ “የመንግሥት ግልበጣ” የተባለን ነገር የሚከታታል ጀኔራል አለ ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡ ሰውዬውም እንደዚህ ዓይነት ጠባይ የለባቸውም፤ ሀገር ሳታርፍ የሚያርፉ ሰው አልነበሩምና፡፡ በቢሯቸው ኾነው ከፍተኛ የአመራር ሥራ ሊሠሩ በሚገባበት ሠዓት ቤታቸው የተኙበት ምክንያት ምንድን ነው? እውን ነገሩን ዐውቀውት ነበርን?
ዐምስተኛ፡- ጉምቱዎቹ ባለሥልጣናት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን በግል ጉዳይ፣ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ገዱ አንዳርጋቸው ለሥራ ብለው አንዱ አሜሪካ ሌላው ጀርመን እግራቸው በረገጠበት ቀን የመኾኑ ግጥምጥሞሽስ እንዴት በዋዛ ይታለፍ ዘንድ ይችላል?
እነዚህ ሁሉ ሲጠቀለሉ አቅጣጫቸው ሌላ ያሳያል፡፡ ከተነገረን ምሕዋር በዘለለ ሁኔታ አንዳች የተቀነባበረ ሴራ ካልነበረ በቀር ወንድም በወንድሙ ላይ እንደዚህ ዓይነት ጭካኔ ያሳያል ብሎ መገመት ይከብዳል፡፡ ገና ደብዛዛ መረጃ ላይ ተቀምጠን ጣት ወደ መጠቋቆሙ መሔዱ አያዋጣም፡፡ ይሄኛው መንገድ ሌላ ጥፋት ያመጣልና፡፡
በዶክተር አምባቸው መኮንን፣ በምግባሩ ከበደ፣ በእዘዝ ዋሴ፣ በጀኔራል ሠዓረ መኮንን፣ በብርጋዴር ጀኔራል ገዛኢ አበራ፣ በብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ሞት  በእጅጉ አዝነናል፡፡ ስማቸው ባልተነገረን በሌሎችም ሰዎች ሞት በእጅጉ አዝነናል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን የምትታየን ኢትዮጵያ ናት፡፡ ቁስል የኾንባት እስኪ እንራገፍላት፡፡
ምንጯ ደፈረሰ እንጅ አልነጠፈም፡፡ እስኪጠራ መታገስ ዋጋ ቢያስከፍልም ድፍርሱን ጠጥቶ ከመታመም ታግሶ ጥሩውን መጠጣት ጥምን ይቆርጣል፣ ጤናም ይጠብቃል፡፡ በደፈረሰ ውኃ ውስጥ ምን እንዳለ ማወቅ አይቻልም፡፡ ሲጠራ ግን ይለያል፡፡ የሦስቱን ቀን ሁናቴ በጥሞና እንየው፣ ድፍርሱን ለማጥራት ጊዜ እንስጠው፡፡ ለመኮነኑ አንቸኩል፡፡ ለመቧደንም አንጣደፍ፡፡ እነዚህ ከላይ የተነሡት እና ሌሎችም ጥያቄዎች ሲመለሱ የሚወገዘው ይወገዛል፡፡
ይህ ጥቁር ደመና መግፈፉ አይቀርም፡፡ እስከዚያው ግን ጨለማ መንገሡን ተቀብሎ ለብርሃኑ መትጋት መውጣት እና መውረድ ብቻ ነው አማራጩ፡፡ የዘሩን ዘጋተሎ አምዘግዝጎ ወዲያ ጥሎ፣ የሀገርን ሕመም ለመታመም አብሮ ቆስሎ የእናት ልጅ የእናቱን ልጅ ሲደክመው አዝሎ፣ ወድቆ እንዳይቀር ውኃ በልቶት ጉልበቱ ዝሎ፣ እየቆረሰ አጉርሶ እየቀደደ አልብሶ፣ ወደ ብርሃን መውጫው ሥር ካልተጓዘ በማለዳ፣ ተከፍሎ አያልቅም የእናት ሀገር የአደራ ዕዳ፡፡
Filed in: Amharic