አብርሀም አለሙ
ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሀገራዊ ሰላምና ህልውናዋን የሚፈታተን ከባድ ውስጣዊ አደጋ ተደቅኖባታል፡፡ በህዝብ ትግል ከዓመት በፊት በሀገሪቱ የመጣዉን ፖለቲካዊ ለውጥ ጅማሮ በርካታ ዜጎች ተስፋ ጥለውበት የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ያለው የሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ ከተስፋ ይልቅ ከፍተኛ ስጋት ያንዣበበበት ሆኗል፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ብሄርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀልና የዘር-ማጽዳት ጥቃቶች ተከስተዋል፡፡ በዚህ ረገድ ሰኔ 15፣ 2011 ዓ. ም. በባህር ዳርና በአዲስ አበባ የተፈጠሩት ሁነቶች፣ በአሁኑ ወቅት የሀገራችን ብሄራዊ አንድነትና ዘላቂ ህልውና አሳሳቢ አደጋ እንደተደቀነበት ያመለክታሉ፡፡ በእለቱ በባህር ዳር አራት የአማራ ክልላዊ መንግስት መሪዎች፣ በአዲስ አበባ ሁለት ከፍተኛ ወታደራዊ ጄነራሎች፣ እንዲሁም ሌሎች የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላትና የክልሉ ልዩ ጥበቃ አባላት መገደላቸው በመንግስት ተገልጿል፡፡ በመንግስት መግለጫ መሰረት በባህር ዳር ስብሰባ ላይ እያሉ የተገደሉት አመራሮች፦
1. ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ የአማራ ክልላዊ መንግስት ፕረዚደንት፤
2. አቶ እዘዝ ዋሴ፣ የፕሬዚደንቱ የህዝብ አደረጃጀት አማካሪ፤
3. አቶ ምግባሩ ከበደ፣ የክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ (በእለቱ ቆስለው ከሁለት ቀን በኋላ ያረፉ) ናቸው፡፡
በተመሳሳይ እለት በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም፦ ጄነራል ሰዓረ መኮንን፣ እና በጡረታ ላይ የነበሩት ጄነራል ገዛኢ አበራ በኢታማጆር ሹሙ መኖሪያ ቤት በግል ጠባቂያቸው መገደላቸው ተነግሯል፡፡ እነዚህንም ተከተሎ የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ የተለያዩ መንግስታዊ ኃላፊዎች፣ ምንም ዓይነት ማጣሪያ ሳይካሄድ በሁለቱም ከተሞች የተፈጠሩት ግድያዎች ተያያዥነት እንዳላቸውና የአማራ ክልል የሰላምና ደህነነት ኃላፊ በነበሩት ጀነራል አሳምነው ፅጌ በተመራ “የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ” የተቀነባበሩ እንደሆነ በመገናኛ ብዙሃን ለኢትዮጵያ ህዝብና ለዓለም ገልጸዋል፡፡ ይኸውም “የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ” በመከላከያ ሰራዊቱና የፌደራል ጸጥታ ሀይላት እንዲከሽፍ ከመደረጉም በላይ፣ ሙከራውን የመሩት ጄነራል አሳምነው ጽጌም ሰኔ 17፣ 2011 ልዩ ስሙ ዘንዘልማ በተባለ ቦታ ከጸጥታ ሀይሉ ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ መገደላቸው ተገልጿል፡፡
መንግስት ይህን ሁነት ገና ከጅምሩ “የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ” ብሎ ቢጠራዉም፣ በርግጥ መፈንቅለ መንግስት ስለመሆኑም ሆነ በሁለቱም ከተሞች የተፈጠሩት ሁነቶችና ግድያዎች ተያያዥነት ያላቸውና የመንግስትን ስልጣን በሀይል ለመቀማት የተደረጉ ስለመሆናቸው ከመንግስትም ሆነ ሌላ ገለልተኛ አካል የተሰጠ ተጨባጭ ማስረጃ የለም፡፡ “መፈንቅለ መንግስት ተሞከረ” የተባለው ከሀገሪቱ የመንግስት መቀመጫ በ 550 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ እንደሚደረገው የሀገሪቱ መሪ፣ የመከላከያና ደህንነት ተቋማት፣ የብዙሃን መገናኛዎችና ኤርፖርቶች ኢላማ ባልተደረጉበትና “የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ነበር” ለማለት የሚያስችሉ ተጨባጭ ማስረጃዎች ሳይቀርቡ፣ መንግስት ጉዳዩን በጥቂት ሰዓታት ውስጥ “መፈንቅለ መንግስት ነው” ብሎ ደምድሞ ለሀገር ውስጥና ለዓለም የብዙሃን መገናኛዎች ማሰራጨቱ የዜናውን ተዓማኒነት አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡ በተጨማሪም መፈንቅለ መንግስት የዜጎችን ደህንነትና የሀገርን ሰላም አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችል ከመሆኑም በላይ፣ በአንድ ሀገር ጠቅላላ ገጽታና የውጭ ግንኙነት፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያስከትል እንደሚችል ሊጤን ይገባል፡፡ የሰኔ 15ቱን “የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ” መግለጫ ተከትሎ መንግስት የወሰዳቸው እርምጃዎችና የተከተላቸው የተግባር አቅጣጫዎች፣ ለዚህም ሊሰጡ የሚችሉ አጸፋዊ ምላሾች፣ በሀገራችን ሰላም፣ ብሄራዊ አንድነት፣ የፍትህ ስርዓትና ዘላቂ ሀገራዊ ህልውና ላይ አስከፊ አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ የሚል ክፍተኛ ስጋት አድሮብናል፡፡ ለአብነት የሚከተሉትን ይመለከቷል፤
1. ጉዳዩ በገለልተኛ ወገን ሳይጣራ፣ ምን፣ በነማን፣ የትና እንዴት እንደተፈጠረ በዝርዝርና በተጨባጭ ማስረጃ ሳይረጋገጥ ድምዳሜ ላይ መደረሱና ለህዝብ፣ እንዲሁም ለዓለም መገለጹ፤ በቀጣይም ለማጣራት ምን እየተሰራ እንደሆነ አለመታወቁ፤
2. የአማራ ክልል የአስተዳደርና ፀጥታ ተቋማት አንዳንድ ኃላፊዎች መታሰርና የክልሉ መንግስት መዋቅር በቀጥታ በፌደራል መንግስት ቁጥጥር ስር መውደቅ፣ የክልሉን ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ፣ የብሔርና ፖለቲካዊ ቅራኔን (ግጭትን) ሊፈጥርና ሊያካርር፣ ብሎም የሀገራችንን ብሄራዊ አንድነትና ዘላቂ ህልውና ሊጎዳ የሚችል መሆኑ፤
3. ኢንተርኔትና በኢንተርኔት የሚካሄዱ ግንኙነቶች (ማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ) በመላው ሀገሪቱ በመዘጋታቸው፣ ዜጎች ወቅታዊ መረጃ በቀላሉ እንዳያገኙና ሀገሪቱ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ለማወቅ አዳጋች መሆኑ፤
4. ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች በብዙሃን መገናኛዎች ተጠርጣሪዎችን በተጠርጣሪነት ከመግለፅ ይልቅ፣ ፍጹም ወንጀለኛ እንደሆኑ አድርገው ማቅረብና ተገቢነት የሌላቸው ቅጽሎችን (ወንጀለኛ፣ ፋሺስት፣ ናዚ፣ እብድና የመሳሰሉ ቃላት) በመጠቀም መፈረጅ፣ የሀገራችንን የፍትህ ሂደት ሊያዛባ ከመቻሉም በላይ፣ የዜጎችን በህግ (በፍርድ ቤት) አግባብ ጥፋተኝነታቸው (ወንጀለኝነታቸው) እስካልተረጋገጠ ድረስ ንጹህ እንደሆኑ የመቆጠር መብት (Presumption of Innocence) የሚጋፋ መሆኑ፤
5. ልዩ ልዩ መንግስታዊ አካላትና መሪዎች በብዙሃን መገናኛዎች የሚሰጧቸውና የሚያወጧቸው መግለጫዎች፣ እርስ በርስ የሚጋጩ፣ በበቂ ማስረጃ ያልተደገፉና ተዓማኒነት የሚጎድላቸው መሆናቸው፣ ዜጎች በሀገራቸው ፖለቲካዊ እንቅስቃሲዎችና መንግስታዊ ውሳኔዎች ትክክለኛነት ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው ያደርጋል፤ የመንግስትን በህዝብ መታመንና ቅቡልነትም ያሳጣል፤
6. የሰኔ 15ቱን ሁነት ተከትሎ በባህር ዳር፣ በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች የአዲስ አበባ ባልደራስ ምክር ቤት አመራሮች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች መንግስትን የሚቃወሙ ግለሰቦች በጅምላ እየታፈሱ መታሰራቸው፣ አንዳንዶችም በአፋኙ “የጸረ ሽብር ህግ” መከሰሳቸው በ27ቱ ዓመታት የአፈና ስርዓት መሻሻል ወይም መለወጥ ላይ ጥርጣሬ ያጭራል፤
7. በባህር ዳርና አዲስ አበባ የተፈጠሩ ግድያዎችና የሀይል እርምጃዎች፣ እንዲሁም ባለፉት ከዓመት ባላይ በሆኑ ወራት በሀገራችን ልዩ ልዩ ክፍሎች የተከሰቱ ብሄርን መሰረት ያደረጉም ሆነ ሌሎች ግጭቶች፣ የዜጎች ከመኖሪያ ስፍራቸው መፈናቀል፣ በህይወትና ንብረት ላይ የደረሱ መጠነ ሰፊ ጥፋቶች፣ ዘረፋዎችና መሰል ሁከቶች፣ የመንግስትን ህግና ስርዓትን የማስከበር፣ የሀገሪቱንና የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ አቅም አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡
ከላይ ባጭሩ ለማመልከት የሞከርናቸውና ተዛማጅ የሀገራችን ብሄራዊ አንድነትና ዘላቂ ሰላም ስጋቶች እንዲወገዱ ለማድረግ ይቻል ዘንድ፣ የሚከተሉት መሰረታዊ እርምጃዎች ባስቸኳይ እንዲወሰዱ እንጠይቃለን፤
1. ሰኔ 15፣ 2011 ዓ ም በባህር ዳርና አዲስ አበባ የተፈፀሙት ግድያዎችና ህገወጥ ተግባራት በገለልተኛ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ቡድን እንዲጣራና እውነቱ ለህዝብ እንዲገለጽ፤
2. የፌደራል መንግስት የተቆጣጠረውን የአማራ ክልል አስተዳደር መዋቅርና የደህንነትና ፀጥታ ተቋማት ለክልሉ መንግስት አስረክቦ እንዲወጣና በክልሉ መንግስት ስልጣንና ተግባራት ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆም፤
3. የተዘጉ የኢንተርኔት መስመሮች እንዲከፈቱና የዜጎች ስለ ሀገራቸውም ሆነ ስለ ዓለም ወቅታዊ መረጃ የማግኘት መብታቸው እንዲከበር፤
4. የሰኔ 15ቱን ሁነት ተከትሎ በመንግስትና መንግስታዊ ተቋማት ከህግ አግባብ ውጭ ዜጎችን በወንጀለኛነት መፈረጅ፣ ማንገላታት፣ ማዋከብና ማሰር እንዲቆም፤
5. ይህንኑ ተከትሎ መንግስትን ወይም የመንግስትን ውሳኔና ፖሊሲዎች ስለሚቃወሙ ወይም ተጨባጭነት በሌላቸው ሰበቦችና በጥርጣሬ በጅምላ እየታፈሱ የታሰሩ የአዲስ አበባ ባልደራስ ምክር ቤት አመራሮች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎችም ከህግ አግባብ ውጭ የታሰሩ ዜጎች እንዲፈቱ፣ እንዲሁም የኢህአዲግ መንግስት አፋኙን “የጸረ ሽብር” ህግ ስልጣኑን ለማራዘም በመሳሪያነት መጠቀሙንና ዜጎችን ማሰሩን እንዲያቆም፤
6. ሀገራችን ከተጋረጠባት አስከፊ የጥፋት ስጋት እንድትድንና ወደ ተሻለ የእኩልነት፣ ሰላም፣ ፍትህና የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መግባት እንድትችል፣ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚወክልና ሁሉንም የፖለቲካ ሀይሎች ያካተተ ብሄራዊ የእርቅ፣ የሰላምና ሽግግር ጉባኤ እንዲጠራ እንጠይቃለን፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ኢትዮጵያ ወዴት የውይይት ፎረም፤
ጁን 26፣ 2019፣ ዋሽንግተን ዲሲ፡፡