የስደተኞች መከራ በእስር ቤቶች
(አሸናፊ በሪሁን ከSeefar)
ብዙዎቹ ስደተኞች ከአፍሪካ እየተነሱ ወደ መካከለኛው ምስራቅ እና አውሮፓ የሚያደርሰውን ጎዳና ሲያያዙ የዕርስ በርስ ጦርነት ቀጠና የሆኑትን የመንን እና የሊቢያን ምድር ማቋረጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ከፊታቸው ባሕር ከጀርባቸው ደግሞ በረሀንም አቆራርጠው ብዙ ሰደተኞችን የበላውን ክፉ ማዕበል ተጋፍጠው በለስ ቀንቷቸው በሕይወት ለሚደረሱት አጋጣሚው መልካም ነው፡፡ ላልተሳካለቸው እና ለማምለጥ ሲሞክሩ ለሚያዙት እና በህገ-ወጥ አስተላላፊዎችና እጅ ለሚወድቁት ግን የመን እና ሊቢያ የገሃነም ደጆች ይሆኑባቸዋል፡፡
የሰብአዊ ቀውስ እና ጦርነት ወደ አደቀቃት የመን የሚገቡት ስደተኞች ቁጥር በጣም ብዙ ነው ፡፡ እንደ የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ግምት 2018 ዓ/ም መጨረሻ ወደ 150,000 ሺ ስደተኞች የመን ገብተዋል ፡፡ በ2018 ዓ/ም ወደ የመን ከተሰደዱት መካከል 92% የሚሆኑት ደግሞ የተሰደዱት ከኢትዮጵያ ነው፡፡ ብዙዎቹም በህገወጥ ደላሎች ተታለሉ የመን እንደደረሱ የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት መረጃ ያመላክታል ፡፡ በጦርነት አውድማ ውስጥ በሆነችው የመን የድንበር ቁጥጥሩ የላላ ነው፡፡ ስደተኞችም በደላሎች ድጋፍ በቀላሉ የየመንን ምድር አቆርጠው ይገባሉ ፡፡ በዚህ ሂደትም ስደተኞች የሚያጋጥሞቸው ችግሮች ብዙ ናቸው ፡፡ የፈንጅ ወረዳዎችን ማለፍ ግድ ነው የተኩስ ለውውጥም ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህን ሁሉ አልፈውም ታዲያ ክፉውን በደል ሁሉ ፈፅመው በማይጠየቁት ህገ-ወጥ አስተላላፊዎችና እጅ ላይ ይወድቃሉ፡፡
የሜዲቴራኒያን ሶማሊያ እየሆነች ነው በምትባለው ሊቢያም አውሮፓ ለመድረስ የሚፈልጉ ሕገወጥ ስደተኞች እንደ ዋና መሸጋገርያቸው የሚጠቀሙባት ዕምብርት ናት፡፡ ከዓመታት በፊት ከሰሃራ በታች ያሉ አፍሪካውያን የሥራ ዕድል የሚያገኙባት ማዕከል የነበረችው ሊቢያ ዛሬ የዘግናኝ አድራጎቶች መናኸርያ ሆናለች።
ሜድስንስ ሳንስ ፍሮንቴሪስ (MSF) የተባለ የህክምና እርዳታ የሚሰጥ ተቋም በመጋቢት 2019 በትሪፖሊ ሳቢያ በተባለ የማቆያ ማእከል ያሉ ስደተኞች ከፍተኛ የሆነ የምግብ ዕጥረት ችግር ተጋርጦባቸው ብሎል ፡፡ ይህ ከ3000 በላይ ስደተኞች የታጨቁበት ማዕከል ከያዛቸው ስደተኞች መካከል አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ህፃናት ናቸው። ከግማሽ በላይ ደግሞ ከስድስት ወር በላይ እዚሁ ታጭቀው የቆዩ ናቸው፡፡ የሊብያ መንግስት በአሁን ሰዓት ከ 5,700 በላይ ስደተኞችን እንደ ሳቢ በመሳሰሉ መንግስት የሚቆጣጠራቸው የስደተኞች ማቆያ ማዕከላት ዉስጥ እንደሚገኙ ይናገራል።
በሊቢያ ሆነ የመን ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ስደተኞች ታዲያ ለህገወጥ የሰው አዘዋዋሪ መረቦች እጅግ የተጋለጡ ከመሆናቸውም በወንበዴዎች የከፈ ስቃይ ይደርስባቸዋል ፡፡ ሃይ ባይ የሌላቸው እነዚህ ሰው አዘዋዋሪዎችም ታዲያ ጭካኔ እንጂ ርህረሄ የሚባል ነገር አልፈጠረላቸውም፡፡ ስደተኞችን ሲፈልጉ ጭካኔ የተሞላበት ሁኔታ ይደበድቦቸዋል ፣ ሲያሻቸው ይደፍሮቸዋል ፣ እንዳንዴም እንደ ዕቃም አጫርተው ለባርነት ይሸጥዋቸዋል ፡፡ተደጋጋሚ የሆነ ጥቃት ያደርሱባቸዋል፡፡ ዛሬም በርካታ ስደተኞች በእስር ቤቶች ለብዙ ጊዜ ይማቅቃሉ፡፡ በእስር ቤቶች የግዳጅ ሥራ መደበኛ ከመሆኑም በላይ ለእስረኞቹ የሚሰጠው ምግብና ሕክምና እጅግ አነስተኛ ነው፡፡
በቅርቡ የወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ( ተመድ) ሪፖርት ሊብያ ውስጥ እዚህም እዚያም ሕግ እናስከብራለን የሚሉ የታጠቁ ቡድኖች፣ ህገወጥ አስተላላፊዎችና በአገር ግዛት ሚኒስቴር ሥር የሚገኙ እጅግ ሰፋፊ እሥር ቤቶችን የሚያስተዳድሩ ባለሥልጣኖች ስለሚፈፅሙት የስቃይና የባርነት አያያዝ፣ ፆታዊ ጥቃትና የዝርፊያ ተግባር በዝርዝር አስፍሯል።
“ሊብያዊያን ድንበር ላይ በጎማ ቧምቧ ይደበድቡናል። አሸዋ ይዟቸው መንቀሳቀስ ያልቻሉትን ተሽከርካሪዎች ገፍተን እንድናወጣ ያስገድዱናል። ፊታችን ሆነው እየበሉና እየጠጡ በሚጠብሰው ፀሃይ አሰልፈው ያቆሙናል።” ሲል አንድ ሊቢያ ውስጥ ታስሮ ስቃይ ላይ ይገኘ የነበር እስረኛ ለተመድ ተናግሮል፡፡ ስደተኞች በየመንም ተመሳሳይ ስቃይ እና በደል ይደርስባቸዋል ፡፡ ስቃይ የበዛባቸው ስደተኞችም ከእስር ቤቶች ይፈቱ ዘንድ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጩኸታቸውን ማሰማት ጀምረዋል ፡፡ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅትም በደቡባዊ የመን ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ የታሰሩ 3 ሺህ ስደተኞች እንዲለቀቁ በቅርቡ ጠይቋል ።
አብዛኛዎቹ በእስር ላይ የሚገኙት ስደተኞችም ኢትዮጵያውን ናቸው። ስደተኞቹ የታሰሩት በኤደንና ላህጅ በተባሉ ከተሞች ውስጥ ነው ፡፡ከእዚህም ውስጥ 2 500 የሚሆኑት ስደተኞች ኤደን በሚገኝ አንድ ስታዲየም ውስጥ ታጉረው የሚገኙ ናቸው ፡፡ በእነዚህ እስር ቤቶች ውስጥ ኮሌራ እና ሌሎች መሰል ተላላፊ በሽታዎች ከተከሰተ አደጋው የከፍ ነው የሚሆነው ፡፡ ብዙዎቹ ስደተኞች ለእስር የተዳረጉት በደላሎች ተታለው መደበኛ ባልሆነ እና በህገወጥ መንገድ ከአገራቸው ስለወጡ ነው፡፡ መደበኛ ያልሆኑ የስደት መንገድን መከተል የሚያስከትለውን ስቃይ እና መከራ ለአመታት ለእስር ተዳርገው ከሚሰቃዩት ከእነዚህ እስረኞች ታሪክ ልንማር ይገባል ፡፡ እኛም የእነዚህ ስደተኞችም ሕይዎት አደጋ ላይ የጣለውን መደበኛ ያልሆነውን ስደት መንገድ በመከላከሉ ረገድ የድርሻችን ልንወጣ ይገባል እላለው፡፡