>
5:13 pm - Tuesday April 19, 5261

አሕያውን ፈርቶ ዳውላውን ....!!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

አሕያውን ፈርቶ ዳውላውን ….!!!!
አቻምየለህ ታምሩ
በኢትዮጵያ ውስጥና  በውጭ አገራት ዐቢይ አሕመድን «እኛም አለን አትርሳን» የሚሉ የበላተኛ ድምጾች ከዚህም ከዚያም እየበዙ ነው። እነዚህ የበላተኛ ድምጾች ባለፉት 28 ዓመታት  ኢትዮጵያ  በአማራ ግፍና በደል ስትጨቀይ አንድ ነገር  ትንፍሽ አላሉም። ዛሬ የያዛቸው ጉዳይ  የኅሊና ጉዳይ ቢሆን ኖሮ  ከሁሉ በፊት ለመክሰስና ለማውገዝ መነሳት የነበረባቸው የጥላቻውን  ምንጭ  እንጂ  የጥላቻ ፖለቲካ  ሰለባ የሆኑት ግፉዓን  በሚሰጡት መልስ መሆን አልነበረም።
ኢትዮጵያ ውስጥ በጥላቻ  ሰው ይጠየቅ ከተባለ በቅድሚያ እጃቸው በመጫኛ ታስሮ ለፍርድ መቅረብ የነበረባቸው የጥላቻ መምህሮቹ  ናዚ ኦነጋውያንና ፋሽስት ወያኔዎች ናቸው። ሕገ መንግሥት የሚባለውን  የጥላቻ ደንብ ሕጋዊ ያደረጉት እነዚህ ሁለት የኢትዮጵያ የጥላቻ መምሕሮች ናቸው። ዛሬ አትርሱን እያሉ ለአገዛዙ ልሳኖች መግለጫችንን ዜና ስሩበት ሲሉ የሚውሉት ግን  እነዚህ የጥላቻ መምህሮችና ያወጡት  ደንብ በአማራ ላይ  ምድራዊ የሲኦን በር በርግዶ ሲከፍት አልነበሩም፤ አማራ መባልም  ይጠየፉ ነበር።
ሌላው ቢቀር የኦሮሞ ወጣቶችን ከኦሮሞ ውጭ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ሁሉ  እንዲጨፈጭፉ [የአንጋሳን ምስክርነት ልብ ይሏል] ጥላቻ ያስተማሩት የኦነግ መሪዎች አዲስ አበባ ውስጥ የዐቢይ አሕመድ  የአፓርታይድ አገዛዝ ጠባቂ  መድቦላቸው  ሽር ብትን እያሉ ይገኛሉ። ይህ ግን  «እኛም አለን፤ ዐቢይ አትርሳን » ለሚሉት በላተኞች አይታያቸውም።
ሻሸመኔ ላይ ጃዋርን ለመቀበል የወጡ ቄሮዎች  ምስኪኑን የድሀ ልጅ ግዳይ ጥለው እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ የአይሁድ ታሪክ ርቃኑን ዘቅዝቀው ሰቅለውታል። ሜንጫና ሚስማር የተጠቀጠቀበት አጣና ይዘው  ወደ አደባባይ የወጡ ቄሮዎች አዲስ አበባ ውስጥ ያለ ኦሮሞ ፈቃድ እጣን እንኳ የማጨስ መብት እንደሌለው ለአዲስ አበቤው በግልጽ አስታውቀውታል። ዛሬ «እኛም አለን ዐቢይ አትርሳን» የሚል መግለጫ ይዘው የወጡት  ሰዎች የዐይን ሌንሶች ግን ይህንን ሁሉ  በአገዛዙ የሚደገፉ ኃይሎች የሚፈጽሙትን  ነውርና ግፍ አያዩም።
ባጭሩ «ዐቢይን አትርሳን» የሚሉ ሰዎች ወደ አደባባይ ይዟቸው የመጣው ጉዳይ  የሆድ እንጂ የኅሊና ደወል ቢሆን ኖሮ ውግዘቱና ክሱ መቅደም የነበረበት በአማራ ድምጾች ላይ ሳይሆን  ሰው እንዲጠሉ ባሰለጠኑት፣ ንጹሐንን በአደባባይ ዘውቅዘው በሚሰቅሉት፣ የድኀ ቤት በሚያፈርሱትና የጥላቻ ስርዓትን ተቋማዊ ባደረጉት ናዚ ኦነጋውያንንና ፋሽስት ወያኔዎች ላይ  መሆን ነበረበት። ሆኖም ግን ነገሩ ሆድ ሲያውቅ ድሮ ማታ ነውና የነ አትርሱን መግለጫ አሕያውን ፈርቶ ዳውላውን ነው።
Filed in: Amharic