>
5:07 pm - Wednesday July 6, 2022

መንግስት በሰብአዊ መብት አያያዝ የኋሊት እየተንሸራተተ ነው!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

መንግስት በሰብአዊ መብት አያያዝ የኋሊት እየተንሸራተተ ነው!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
በቅርቡ በባህርዳርና በአዲስ አበባ የተፈጠረውን አሳዣኝ ክስተት ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በፖሊስ ተጠርጥረው መታሰራቸውን በመንግስት ተገልጸዋል። ከታሳሪዎቹ መካከል የፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ የመብት አቀንቃኞች፣ ጋዜጠኞች እና የሕግ ባለሙያዎችም ይገኙበታል። የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች እና የሕግ አማካሪዎቻቸው እንደሚናገሩት የተወሰኑት ታሳሪዎች በቤተሰብብ እንዳይጎበኙ እና አንዳንዶቹም በጨለማ እና ቀዝቃዛ ክፍሎች ውስጥ እንዲቆዩ መደረጉ እየተገለጸ ነው።
መንግስት ኮሽ ባለቁጥር እየተነሳ ዜጎችን በጅምላ የማሰር እርምጃ እጅግ የተሳሳተ እና ከፍተኛ የመብት ጥሰትን የሚያስከትል አድራጎት ስለሆነ ይህ አይነቱ አሰራር ማስወገድ ይኖርበታል። በመቀጠል ፖለቲካ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ከሚፈጸሙ የወንጀል አድራጎቶች ጋር በተያያዘ የሚታሰሩ ሰዎችን በአለም አቀፍ ደረጃ ሲወገዝ በቆየው እና መንግስትም ይህንኑ አምኖ እያሻሻለው ባለው የጸረ ሽብር ሕግ በመጠቀም እንደ በሽብርተኛነት መክሰሱ ሌላው ትልቅ ስህተት እና የመብት ጥሰት ነው።
አንድን ጋዜጠኛ ወይም የመብት አቀንቃኝ በሽብርተኛነት ነው የምንከሰው ብሎ ችሎት ፊት ማቅረብ ባለፉት አሥርት አመታት የተፈጸመውን አሳፋሪ ስህተት መድገም ብቻ ሳይሆን እየታዩ የነበሩ አንዳንድ በጎ ጅምሮችንም የጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ተቋም ወደ ኋላ እየቀለበሳቸው መሆኑን ነው የሚያሳየው።
 መንግስት ያለ በቂ ማስረጃ ያለአግባቡ የታሰሩ ጋዜጠኞችን፣ የመብት አቀንቃኞችን እና የሕግ ባለሙያዎችን እንዲሁም ሌሎች ዜጎች በአፋጣኝ ሊፈታቸው ይገባል። እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኙትንም በሕገ መንግስቱ ለአንድ እስረኛ የተቀመጡ የመብጥ ጥበቃዎች ሊሟሉላቸው ይገባል።
Filed in: Amharic