>

ይህ እውነት ለትውልዱ ይድረስ !! (ጋዜጠኛ  ተመስገን ደሳለኝ)

ይህ እውነት ለትውልዱ ይድረስ !!
ጋዜጠኛ  ተመስገን ደሳለኝ
የኛ አባቶች አገር የሰሩበት የሃሳብ ልዕልና ይህ ነበር…በትዕግስት አንብበ/ቢ/ው አገራችንን ከየትኛው ከፍታ አውርደው ፈጥፍጠው አማራ ጨቋኝ ነው የሚል የእንቶ ፈንቶ ትርክት እንደፈጠሩ ፍንትው አድርጎ ያሳይሃ/ሻ/ል    !!
                          ****
“በጎሳ መለያየት የአገርን አንድነት የሚያፈርስ ነው። እኛው እርስ በእርሳችን በጎሳ የምነጯጯህ ስንሆን የበለጠ ሁከት ተፈጥሮ እስከ ደም መፋሰስ ስንደርስ በራሳችን ላይ ጉዳይ አድርሰን አገራችንንና ዓላማችንን ለገላጋዮች ሲሳይ ማድረግ
 ይሆናል።”
ቀ.ኃ.ሥ  ሐምሌ 16፣ 1884 ዓ.ም. የተወለዱት ንጉሠ-ነገሥት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ ዘእመ ነገደ ይሁዳ ከሦስት ቀናት በኋላ 127ኛ የልደት ቀናቸው ይሆናል።
ግርማዊነትዎ፣ እንኳን ተወለዱ!
—————————————
ከ60 ዐመት በላይ ኢትዮጵያን እና ፖለቲካዋን ለማዘመን ላይ-ታች ታትረዋል። የተበተነውን አንድ አድርገው ሰብስበዋል።  በፊውዳሎች መረን-የለሽ የግፍ አገዛዝ ያዘመመን አገር አቅንተዋል። የፖል ሄንዝ  “Layers of Time፡ A History of Ethiopia” መጽሐፍ፣ ዘመናይዋን ኢትዮጵያ ለማዋለደ ዳግማይ ምኒልክ መንገዱን ቢደለድሉም፣  ዕጣ-ፈንታዋን ከጨበጡት ዐፄ ኃይለሥላሴ ነጥሎ ማሰብ እንደሚቸግር አትቷል። ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ፣ “ቀዳማዊ ኃይለስላሴ፣ የዐፄ ቴዎድሮስን አሀዳዊ መንግሥት የማንበር ራዕይን አሳክተዋል፣” ማለታቸውም በድርሳኑ ተጠቅሷል።
ጉልበታቸው በዛለበት፣ ዕድሜያቸው በገፋበት፣ ዘመናቸው በጨለመበት የማታ-ወራት… አዋክበው እና አወናብደው ለ‘ሥር-ነቀል’ ውድቀት የዳረጓቸው ግራ-ዘመሞቹ የ ያ-ትውልድ አባላት፣ ከአራት ዐሥርታት በኋላ፣ የነቀፉቱን አስተደዳር በፀፀት ለማስታወስ ተገድደዋል። አቶ ያሬድ ጥበቡ፣ የአምባሳደር ዘውዴ ረታን “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” ጥራዝ አንብበው ባዘጋጁት የዳሰሳ መጣጥፍ ንስሓ መግባታቸውን ነግረውናል። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌም “ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር” በተሰኘው ዐዲሱ መጽሐፍ፣ “አንድ የቀድሞ አይሮፕላን ጠላፊ አብዮተኛ ምሁር እንዳለው ‘የአፄ ኃይለሥላሴን መንግስት ባንነካካው ኢትዮጵያ ይህን ጊዜ ሲንጋፖር ትሆን ነበር’ ያለውን ተቀብዬ ሲንጋፖርን ባትሆንም ከናይጄሪያ የተሻለች አገር ትሆን ነበር ለማለት እኔም እደፍራለሁ፣”  ሲሉ መፀፀታቸውን ጠቁመዋል።
በዚህ አውድ፣ አንድም የልደት ቀናቸውን፣ ሁለትም አገሪቷ የገባችበትን ወቅታዊ ቅርቃር አስታክከን ግዝፈት-የነሱ አበርክቶአቸውን በሦስት ከፍለን እናያለን። እግረ-መንገድም፣ ዛሬ ድረስ ያልተገታው የኋሊት ጉዞ ይነጻጸርበታል።
ራስ ተፈሪ ገና በወጣትነታቸው በንግሥት ዘውዲቱ እንደራሴነት የተሸሙበት ዋነኛ መስፈርት ተራማጅ መሆናቸው እንደ ነበረ የታሪክ ዘጋቢዎች ያቆዩት ሰነድ ያስረግጣል። በዚህ ወቅት ነው፣ በነባራዊ ሁነቶች አስገዳጅነት፣ በፊውዳሎች መዳፍ የመንከላወስ ክፉ ዕጣ የተጋፈጠችን አገር የመታደግ ተጋድሎ የጀመሩት። የምዕራብ አውሮፓን አገራት ጎብኝተው መመለሳቸው ደግሞ የመነቃቃቱ ገፊ-ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል። የሳምንታት ቆይታቸው ሥልጣኔን ለማንበር፣ የዐፄ ምኒልክ የትምህርት ፖሊሲን ማስፋፋት ቀዳሚነት በጥልቅ አርድቷቸዋል። ለስኬቱ ደግሞ ቁርጠኛ ሆነዋል። ፊት-አውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ “ራስ ተፈሪ፣ የፈረንጆቹን አገር አይቶ ከመጣ በኋላ፣ አገሬ ለሥልጣኔ መፍጠን አለባት ብሎ እንቅልፍ አጥቷል፣” ማለታቸውን የአምባሳደር ዘውዴ ረታ “ተፈሪ መኮንን ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ” መጽሐፍ አስነብቦናል።
የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ድረስ የሰነበቱትና አገር የተበጀባቸው መንግሥታዊ ተቋማት በሙሉ ‘ሶፍትዌር’ የንጉሠ-ነገሥቱ ነው። መከራ-ጠሪውን መሳፍንታዊ ሥርዐት በአሐዳዊው ለመተካት ብቸኛው መፍትሔ ዘመናዊ ሰራዊት መገንባት በመሆኑ፣ የጦር ትምህርት-ቤቶችን ከፍተዋል። አየር ኀይል እና ባሕር ኀይልን በጠንካራ አደረጃጀት፣ ወቅቱን በሚመጥን ዕውቀት እና ዲሲፕሊን መሥርተው ነበር። “Transformation and Continuity in Revolutonary Ethiopia” ደራሲ ክርስቶፎር ክላፋማ፣ ዐፄው በ1960ዎቹ (እ.ኤ.አ.) መጀመሪያ በአፍሪካ ተገዳዳሪ-አልባ ጦር መገንባታቸውን መስክሯል።
ጎትጓች በሌለበት፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ግፊት ባልታየበት፣ ጠያቂ ሕዝብ ባልተፈጠረበት… የጨለማ ዘመን፣ ከእነ ድክመቱም ቢሆን፣ የመጀመሪያው ሕገ-መንግሥት ተረቅቆ እንዲፀድቅ ፈቅደዋል። ከአዋቃሪዎቹ አንዱ የነበሩት ፊት-አውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም የሕጉን መንፈስ ያስረዱበትን አውድ አምባሳደር ዘውዴ ረታ “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት” መጽሐፍ ላይ ገልጸውታል፦
“ይህ የሚዘጋጀው ሕገ መንግሥት፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ በዘር ሥሪት ሆነ በሹመት፣ በጌትነት ሆነ በድህነት፣ ሳይከፋፍል ለሁሉም እኩል የሆነ መብት የሚሰጥ መሆን አለበት።”
ኤርትራ ትተዳደርበት የነበረው ፌዴሬሽን ፈርሶ እንደሌለው ጠቅላይ ግዛት ከእናት አገርዋ ጋር መቀላቀሏን ተንተርሰው ማሻሻያ ይደረግበት ዘንድ ተስማምተዋል። በኩነቱ ላይ ትልቅ ተሳትፎ የነበራቸው የጆን ስፔንሰር “Ethiopia At Bay” መጽሐፍ የዐማርኛ ትርጉም የሆነው “ጥርስ የገባች አገር” ሁነቱን አስታውሶታል፦
“አስተዳደራቸውን ዘመናዊ የማድረግ የጃንሆይ ጥረት ህጎችን በማውጣት ብቻ አልተወሰነም። ከጦርነቱ በኋላ የመጣውን ትውልድ ግፊትና ጊዜው እጅግ ተገንዝበውታል። በኤርትራ ውስጥ የህገ-መንግስት መኖር ከ1848 የፕሩሲ ህገ-መንግስትና ከ1889 የጃፓን ህገ-መንግስት ተወጣጥቶ ወጥቶ በስራ ላይ የነበረውን የ1930 የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት አስቸኳያ ማሻሻል አስገድዷል። ስለዚህም በወልደጊዮርጊስ ሊቀመንበርነት የሚመራው ኮሚቴ የእለት ተእለት ስራውን ሲያከናውን ግርማዊነታቸው ከዘውድ መማክርት ፅህፈት ቤት ተቀምጠው ይጠባበቃሉ። ከወልደጊዮርጊስ ጋር አክሊሉ፣ ጋረትሰን እና ከዋሽንግተን ዲ.ሲ የመጣው ስመጥር የአለም አቀፍ ህግ ሊቅና ከአሜሪካን ጆርናል ኦፍ ኢንተርናሽናል ሎው አዘጋጆች አንዱ የሆነው ኤድጋር ተርሊንግተን ነበሩ።”
በተሻሻለው ሕገ-መንግሥት ውስጥ ከዓለም-ዐቀፍ ሰብኣዊ መብቶች ድንጋጌ፣ እንዲሁም፣ ከአውሮፓ እና አሜሪካ ሕግጋት የተወጣጡ ሰብኣዊ መብት ላይ የሚያጠነጥኑ 27 አንቀጾች መካተታቸውን አርቃቂው በተጠቀሰው መድብል መስክረዋል። “Layers of Time፡ A History of Ethiopia”ም የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ ሦስት፣ ለሁሉም ዜጎች የሃይማኖት እና የመናገር ነጻነትን እንደሰጠ ጠቅሷል።
‘ታዲያ ለምን አልተተገበረም?’ የሚል ጠያቂ፣ እንኳን ያኔ፣ ዛሬም ገና ሕግ መከበረ አለመጀመሩን ግድግዳው ላይ ከተጻፈው ጉልህ እውነታ እንዲረዳ ይመከራል። የወንጀለኛ መቅጫውም ሆነ የፍትሐ ብሔሩ በተለያየ ጊዜ ከተደረገባቸው ማሻሻያ በስተቀር፣ የዐፄው በረከት ስለመሆናቸው መዘንጋት የለበትም። “እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የጃንሆይ መንግስት ከመላው አፍሪካና ከመካከለኛው ምስራቅ ሃገሮች ይልቅ የበለጠ ለቀቅ ያለ በመሆኑ የተሻለ ነው፣” የሚል ምስክርነት በመጽሐፋቸው ላይ የሰጡት ጆን ስፔንሰር መነሾም ይኸው ነው። አንድ ሃያማኖት ተነጥሎ (የሥልጣናቸው መሠረትነቱ ሳይረሳ) ብሔራዊ ተደርጎ የቀጠለበት ኀጢአት እንደተጠበቀ፣ በ1935 ዓ.ም. በወጣ አዋጅ ቁጥር 2 የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሃይማኖት-ነክ ጉዳዮችን የምትመለከትበት ፍርድ-ቤት እንድታቋቁም ሲያደርጉ፣ በ1936 ዓ.ም. ደግሞ፣ በአዋጅ ቁጥር 62 ለእስልምና ተመሳሳዩን መፍቀዳቸውን የአቶ በሪሁን ከበደ “የአፄ ኃይለሥላሴ ታሪክ” ድርሳን አትቷል።
“በኢትዮጵያ የስልምና ሃይማኖት ነክ በሆኑ ጉዳዮች በሦስት ደረጃ ፍርድ ቤቶች አሉ። እነዚህም ሀ/የሸሪያ ለ/የቃዲያዎች ሐ/የናይባዎች ናቸው።  ለእነዚህ ፍርድ ቤቶች የተሰጣቸው መንፈሳዊ ሥልጣን በአዋጁ ላይ ተዘርዝሮ ይገኛል።”
የድኅረ-ዘውድ የቤተ-መንግሥት ቡድኖች፣ ሰብኣዊ መብትን በተመለከተ፣ ከንጉሡ ያነሰ አረዳድ መያዛቸው በግላጭ የሚታይ ሐቅ ነው።
በሕዝባዊ እምቢተኛነት የተሰናበቱትን ወደ ጎን ብለን፣ ዘመነኛውን ኦዴፓ ብንወስድ፣ በ’የጊዜው የሚያወጣቸው መግለጫዎቹ እና የከፍተኛ አመራሮቹ ንግግሮች የክሱ ማሳያ ይሆናሉ። የሕወሓት የግፍ-ሰለባዎች እንደማንኛውም ዜጋ ለሚሰነዝሩት ተቃውሞ፣ ትችት (ምክር ጭምር)፣ ‘እኛ አስፈትታናችሁ’ በሚል ስሑት ፕሮፓጋንዳ ሊያሸማቅቁ የሚሞክሩበት መንገድ የድርጅቱን ፖለቲካዊ የብስለት ደረጃ እርቃን ያሰጣ ነው። ያም ሆኖ እንዲህ ዐይነቱ ስልት ዐዲስ አይደለም። ደርግ 17 ዐመት ሙሉ ‘ከጭሰኝነት ገላገልኩህ’፣ ‘አብዮት አካሄድኩልህ’ እያለ ጨፍልቆ የገዛበት፣ ሕወሓት ከሩብ ክፍል-ዘመን ፈቀቅ-ላለ ጊዜ በብሔሮች ነጻ-አውጪ ስም የበዛ መሥዋዕትነት ያስከፈለበት ነው። የአሁኖቹ ደግሞ ‘ወከልነው’ ከሚሉት ማኅበረ-ሰብ ባፈነገጠ የግብረገብ ዝቅጠት፣ ከእስር-ቤት የተፈቱ ሰዎች ዕቃዎቻቸውን በሸከፉበት ፌስታል እስከ መሳለቅ ደርሰዋል። ነገሩን ቧልት የሚያደርገው ግን በሐሰት ለማሰር መተባበራቸውን ዘንግተው፣ የ‘አስፈቺ’ነት ውለታ የጠየቁበት ድፍረት ነው። ይሄም ነው ትግሉ፣ ገና፣ መድራሻው ሩቅ የመሆኑን እውነታ የሚመሰክረው። በርግጥ፣ መነሻው ጎሣውን ለሥልጣን ማብቃት የሆነ ጠርዘኛ ከአብዮቱ ባቡር መንጠባጠቡ ሳያዘናጋ፣ ኢትዮጵያን ዐቃፊ-ደጋፊ ለሚያደርገው ቀሪው መንገድ መበርታት ግዴታ ነው።
እስከ አሁን የመጣናቸው ዳገት፣ ያቋረጥናቸው ኩርባ፣ ያለፍንበት ሸለቆ… የአክራሪ ብሔርተኛነትን ዋሾ እና ቀጣፊነት፣ ምክንያት-አልቦነት፣ እና መደዴነት… አስረግጦልናል። የትላንቱ ሕወሓትም ሆነ የዛሬው ኦዴፓ በፖለቲካ ኃይል ለሚገፋ እብደት በቂ ማሳያ ናቸው። በአገሪቱ ታሪክ እስከ አሁን ድረስ ሥልጣን መጠቅለሉ የሰመረላቸው ዘውጌ ድርጅቶች ሁለቱ የመሆናቸውን እውነታ ልብ ይሏል። (በነገራችን ላይ፣ አዴፓም በለስ ቢቀናው፣ ‘ከእነርሱ የተለየ ፍትሓዊና ከአድሎ-የነጻ ሥርዐት ሊያነብር ይችላል፣’ ብሎ መጠበቅ የበዛ ዘረኛት ነው።)
የዘውግ-ተኮር ድርጅቶች ተፈጥሮ አንድ ጎሣን ማገልገል በመሆኑ፣ ከብሔረሰባቸው ውጪ ላለ ዜጋ ራሮት-የለሽ መሆናቸው ተጠባቂ ነው። የ‘ለውጥ ኀይሉ’ አራት ኪሎን በረገጠበት ቅጽበት ያሳደረው ተስፋ፣ ዛሬ የአንድ ማኅበረሰብ የብቻ-ሕልም ሆኗል። በተረኛነት እና ዘረኛነት የሚነዱ ደጋፊዎቻቸውም በነጻነት-በካይ ፕሮፓጋንዳ ለመሸንገል ሲታትሩ መመልከት ልብ ይሰብራል። በርግጥ፣ የዚህ ሁሉ ክሽፈት መነሾ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ሽግግሩንም፣ ሽምግልናውንም ‘በእኔ ጣሉት’ ያሉ ጊዜ ነው።
‘አክራሪው ኀይል አላሠራ ብሏቸው ነው’ ዐይነቱ ሰበብ ከነፈሰበት እና ከሻገተ ሰንብቷል። በየትኛውም መመዘኛ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር የዐፄውን ያኽል ብርቱ ፈተና እንዳልገጠመው ይታወቃል። ንጉሡ በታላቅ ጥበብ መሬት ያወረዱት ቢሮክራሲም ሆነ አንድ የተማከለ-መንግሥት የማንበር ሂደት ዋነኛው ተገዳዳሪ የራሳቸውን ሰራዊት ያደራጁት ወግ-አጥባቂ መሳፍንቱ ሲሆኑ፣ የአብዛኞቹ የቅርብ ዘመድነት ደግሞ መፍትሔውን አወሳስቦታል። ያም ሆኖ፣ ነባሩን የሥልጣን ዕሳቤ ነቅለው መደብ-የለሽ የማድረጉን አደገኛ ግብ-ግብ በድል መወጣታቸውን የታሪክ ሰነዶች ያስረግጣሉ። ከፍተኛ መንግሥታዊ ኃላፊነቶችን ከሥርወ-ግንድ ውጪ ባሉና በተማሩ ኢትዮጵያውያን መዳፍ እንዲገባ ያደረጉት ጥረት በከፊል ተሳክቷል። የውጤቱ መግፍኤ ከመሳፍንቱ መደብ ተነጥለው መውጣታቸው እና ጠንካራ አቋም መያዛቸው መሆኑን ማስታወሱ ለዶ/ር ዐቢይ ጠቃሚ ትምህርት ነው። የታጀሉበትን የብሔር ቅርፊት ሳይሰብሩ እንደምን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ከእርሳቸው በቀር ‘ዐውቃለሁ’ የሚል አልገጠመኝም። ’እሹሩሩ’ው እስከ መቼ እንደሚቀጠል ግልጽ አይደለም።
የፖለቲካው ሃዲድ እንዲስተካከል መምከር፣ ስሕተትን መጠቆም፣ ጥፋትን ማጋለጥ ‘አገር ማፍረስ ነው’ የሚል ዐዲስ ትርጓሜ አግኝቷል። ጉዳዩን በቅንነት እንውሰደው’ና፣ ምናልባት፣ እንደ’እኔ ብዙኃኑ ያልተረዳው፣ እናንተ ብቻ የምታውቁት አደገኛ ችግር ካለ ይፋ አውጡት፣ ለምፍትሔው እንተባበራለን። ከዚህ ባለፈ፣ ’አፍራሽ’ የሚለው ፍረጃ ገበያ አይጠራም። የቀድሞዎቹም በዚሁ መንገድ ተጉዘው ከሸለቀቁበት ‘ትሪክ’ ትምህርት ወስዷል።
ሥርዐተ-መናፍቃኑን ያበዛው ዋነኛ ምክንያት የፌደራል መንግሥቱ እና የኦዴፓ ድንበር-የለሽ ትቅቅፍ ነው። ይህ ደግሞ ለተናጥል ድጋፍ ያስቸግራል። ጠቅላዩን ለማመን ሲያመነታ፣ ድርጅቱ ኦነግን ተመስሎ ግርዶሽ ይሆናል። የሰሞኑ የአቶ ሽመልስ አብዲሳ ምክንያታዊነት-የነጠፈበት ንግግርም ይህንኑ ያስረግጣል። ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ቀለም የተሞላ ጠርሙስ እየወረወሩ የዜጎችን ሞት ባወጁበት፣ አቶ መለስ ዜናዊ በደም አጨቅይተው ያሸነፉትን ‘ምርጫ’ ባወደሱበት፣ የጀማይካዊው ቦብ ማርሌ ልደት በዳንኪራ በተከበረበት… ዓለማዊው መስቀል አደባባይ ለኢሬቻ መሰባሰብ ተፈጥሯዊ መብት እንጂ፣ የፖለቲካ ድል ማረጋገጫ መሆን አልነበረበትም። ተደጋጋሚ ጊዜ ጫፍ-እየረገጡ የጎራ መደበላለቅ የሚፈጥሩት አቶ ሽመልስ ሰሞኑን በዚህ በኩል የተከሠቱት ባህሉ፣ ከኢትዮጵያ ዐልፎ፣ በዓለም ሕዝብ ቅርስነት የመመዝገቡን አንድምታ በመዘንጋት አይደለም። የኦነግ ተለዋጭነት ያጎነው ግፍጫ እንጂ።
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን በኢሕአዴጋዊ የብሔር ብያኔ ካጠየቅናቸው ወደ ኦሮሞ ማዘመማቸው አይቀርም (ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምንም ይጨምራል)። ይሁንና፣ የሁለቱም መሪዎች ሥነ-ልቦና በኢትዮጵያዊነት ስለ ተቃኘ፣ ጉዳዩን አስታውሰው ስለ ማወቃቸው የሚጠቁም መረጃ አላየሁም። በግሌም፣ ብሔራቸው ትዝ ያለኝን ጊዜ አላስታውስም።
በአገሪቱ ታሪክ የጃንሆይን ያኽል ሥርዔ-መንግሥት፣ ዱለታ፣ እና የአደባባይ ተቃውሞ ያስተናገደ የለም። ከ1960-66 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት የጎዳና ላይ ዐመፅ እና የተማሪዎች አድማ የዘውትር ክሥተት ነበሩ። የፀጥታ ተቋማቱ የወሰዷቸው ርምጃዎች ውጉዝ ከመ-አሪዮስነቱ ሳይዘነጋ፣ ከእርሳቸው በኋላ የመጡት መሪዎች በረባ-ባልረባው ከፈጸሟቸው የጅማላ ግድያዎች ጋር የሚነጻጸር አለመሆኑ የአደባባይ እውነታ ነው።
በዐፄው ዘመን ግዝፈት-ከነሡት የመፈንቅለ-መንግሥት ሤራዎች መኻል በ1943 ዓ.ም. በቢትወደድ ነጋሽ በዛብህ መሪነት የተሞከረው ተጠቃሽ ነው። በ‘ታኅሣሡ ግርግር’ እጁን ስለ መንከሩ የሚነገረው የአቶ ግርማሜ ንዋይ ወዳጅ አሜሪካዊው ሪቻርድ ግሪንፊልድ “Ethiopia A New Political History” በሚል ርእስ ባሳተመው መጽሐፍ የ1943ቱን የክሽፈት መንሥኤ ገልጾታል፦
“የአድመኞቹ ይቅር-የማይሰኝ ስሕተት የኦሮሞውን ታዋቂ ዐርበኛ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪን በደጋፊነት ለማሰለፍ መሞከራቸው ነው።”
በርግጥ፣ ግሪንፊልድ ‘ስሕተት’ የሚለው ደጃዝማቹ ጉዳዩን አስቀድመው ለቀ.ኃ.ሥ. በመንገር ዕቅዱን ያጨነገፉበትን ታማኝነት ነው። ከንጉሥ ተክለሃይማኖት በሚዛመዱት፣ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነትን ሥልጣን እስከ መጨበጥ በደረሱት፣ ለሴኔቱ በፕሬዚደንትነት የመሾም ዕድል ባገኙት ቢትወደድ ነጋሽ የተቀነባበረው አደገኛ ሙከራ አገር-ዐቀፍ ገጽታ እንደነበረውም ዘግቧል።
በውጪ አገር ሰዎች ጭምር “የኃይለሥላሴ አስተዳደር አውዳሚ ተግዳሮቶች ተደቅነውበታል” እስከሚል ድምዳሜ ከተለጠጠው የንጉሠ-ነገሥቱ ፈተና ያነሰ እንቅፋት የሚያወላክፈው፣ የብሔር መቀነት የጠለፈው፣ ተረኛነት የለከፈው… የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር፣ ጃንሆይ ያንን ሁሉ ጀግና የጦር አበጋዝ ከእነ ሰራዊቱ አንበርክከው አገር እና ሥልጣን ማስከበር ከቻሉበት ታሪክ ቢማር ተጠቃሚ ነው።
ንጉሠ-ነገሥቱ
***********
በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ልክ ታላላቅ የ‘ዲፕሎማቲክ’ ድል የተቀዳጀ፣ በዓለም-ዐቀፍ መድረክ የተከበረ፣ በኀያላኑ ተደማጭነትን ያተረፈ… መሪ ዛሬም ድረስ አለመነሣቱ የቁልቁለቱ ጉዞ መገለጫ ነው። ኤርትራ እና ኦጋዴንን ለመቀላቀል የተከፈለው ዋጋና የተገኘው ውጤት፣ ቢያንስ፣ ንጉሡን በሽንቁር ለመመልከት ያስችላል። የእንግሊዝን መሠሪነት ተጋፍጦ፣ የፈረንሳይን ሤራ አምክኖ፣ ‘ሁለቱ ሰይጣኖች’ን አፋጥጦ፣ የአሜሪካኖችን ብልጠት ተቋቁሞ፣ ጣሊያንን ከወራሪ ወደ አማካሪ ለውጦ… እንደ አገር መቆም የቻለ ከጃንሆይ በቀር ማን አለ? ያንን የመሰለ አስከፊ እና ዘግናኝ ዕልቂት በተስተናገደበት ጦርነት ማግስት የቤተሰባቸውን ሐኪሞች ጭምር ጣሊያናዊ በማድረግ ዝምድና ለመፍጠር ሞከረዋል። ጆን ስፔንሰር በአገሬው ዘንድ የተጠሉትን የእንግሊዝ ወታደራዊ ገዥዎችን ለማዳከም፣ በስውር በጣሊያኖች መጠቀማቸውን ጽፏል። ባለፉት ዐምስት ዐሥርታት በእንዲህ ዐይነቱ የረቀቀ ዲፕሎማሲያዊ ጥበብ የተካነ መሪ አላየሁም። (ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን እንዳንገመግም፣ አስቀድመው፣ ‘የእኔ ተሰጥኦ ልመና ነው፣’ ሲሉ የእምነት ቃል ሰጥተዋል።)
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቋቋምም ሆነ መቀመጫው አዲስ አበባ መድረጉ ያለ ኃይለሥላሴ የሚታሰብ አልነበረም። የፖል ሄንዝ፣ “የፓን አፍሪካን ፖለቲካ ከመምራቱ ወሳኝ ሚና አልተገቱም፣” ምስክርነትም ዋቢ ነው። ንጉሡ ዐሥር ሜትር ረዝመው የሚታዩት በሥልጣን ቆይታቸው፣ ለሕዝብ ያደረጓቸው ንግግሮች ላይ አንዳችም የስድብ እና የማዋረጃ ቃላት በመጠቀም ስሕተት አለመሥራታቸው ነው። ‘እንትናቸውን በሳንጃ ወጋናቸው’፣ ‘ወራዶች’፣ ‘የቀን ጅቦች’ን… በስላሽ ማስገባቱ ማነጻጸሪያውን ያጎላዋል። የግራ-ዘመም አስተምህሮን በመንተራስ ‘ያንኪ ጎ ሆም’ አንዱ የትግል ግብ ተደርጎ ከመወሰዱ በፊት፣ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ አሜሪካውያን የ’ሰላም ጓድ (Peace Corps)’ አበርክቶም እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም። ይህም በዲፕሎማሲዊ ውጤት ሥር የሚመዘገብ ነው።
የአክሱም ሐውልትን ጨምሮ፣ በዘረፋ የተወሰዱ ታላለቅ ቅርሶችን የማስመለስ ጥረት የተጀመረውም በይሁዳ አንበሳ ነው።
ዐፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ያጠፉበት ሽጉጥ በእንደራሴነት ዘመናቸው ማስመለሳቸውን ያተቱት በሪሁን ከበደ፣ “ሽጉጣቸውን ጠጥተው በወደቁ ጊዜ ከአንገታቸው የነበረውን የሰሎሞን ኒሻን ከነወርቅ ሀብሉ ከአንገታቸው አውልቆ የወሰደው ደብልዩ አርቡት ኖት የተባለ እንግሊዛዊ ሻምበል ነው። በተወሰደ በ80 ዓመት አፄ ኃይለሥላሴ ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር ተነጋግረው በ1940 ዓ.ም አስመለሱት። ተመልሶ መጥቶ በብሔራዊ ሙዜም አዳራሽ ውስጥ ክብር በአለው ቦታ ተቀምጦ ሲኖር ግንቦት 25 ቀን 1966 ዓ.ም እሁድ ተሰረቀ፣” ሲሉ መጽሐፋቸው ውስጥ አስፍረዋል። እኒህ ታሪክ ዘጋቢ (በወቅቱ የሕግ-መወሰኛው ምክር ቤት አባል) የለገሀሩ የይሁዳ አንበሳ ሐውልትን መጋቢት 27 ቀን፣ 1961 ዓ.ም. ወደ አገሩ ማምጣታቸውንም ሆነ በ1939ኙ የኢትዮ-ኢጣሊያ የፓሪስ ስምምነት የአክሱም ሐውልትን የመመለስ ግዴታ እንዲካተት ማድረጋቸውን ዘግበዋል።
‘የአፍሪካን የጋራ መከላከያ ድርጅት’ የመገንባቱን ሂደት በተመለከተም፣ በአዲስ አበባ ለተሰበሰቡት መሪዎች “ነጻነታችንን እየጠበቅን ከምዕራባውያንም፣ ከምስራቅም ተስማምተን መኖር ግዴታችን ነው፣” ስለ ማለታቸው “የአፄ ኃይለሥላሴ ታሪክ” ድርሳን ነግሮናል። “ተፈሪ መኮንን ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ” የተሰኘው መጽሐፍ ደግሞ ወደ ኋላ ተመልሶ እንዲህ ይላል፦
“የዓለም ነፃ መንግሥታቶች ማኀበር በዤኔቭ ከተማ መቋቋሙን ራስ ተፈሪ ሲሰሙ፣ ኢትዮጵያ አባል ሆና እንድትመዘገብ ፋታ የማይሰጥ ጥረታቸውን ጀመሩ።”
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በኀያላኑ አገራት መሪዎች የነበራቸውን ተደማጭነት የሚያስረግጠው ፖል ሄንዝ፣ እ.ኤ.አ. በ1971 ዓ.ም. አዲስ አበባ የገቡት የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚደንት አግንዉ ስለተላኩበት ጉዳይ፣ ለሽፋን ከተነገረው ውጪ፣ የኢምባሲው ጉምቱ ዲፕሎማቶች እንኳን አለማወቃቸውን ካስታወሰ በኋላ፣ እውነተኛው ጉዳይ፣ “አሜሪካን ለኮሚኒስታዊቷ ቻይና ዕውቅና ለመስጠት መዘጋጀቷን ለኃይለሥላሴ መናገር ነበር፣” በማለት ጽፏል። ዐፄው በዚያው ዐመት፣ በኦክቶበር ወር፣ ሹሞቻቸውን አስከተለው ወደ ቤጂንግ በማምራት ከሊቀ-መንበር ማኦ ዚዱንግ ጋር ተወያይተው የዲፕሎማቲክ ግንኙነት መሥርተዋል። ማኦ፣ ለኤርትራ ዓማፅያን ከሚሰጡት ርዳታ ከመታቀብ በዘለለ፣ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉ እና ከምስራቅ ወደ ምዕራብ የአገሪቱን መኻል ሰንጥቆ የሚልፍ የፍጥነት መንገድ እንደሚሠሩ ቃል መግባታቸውን “Layers of Time፡ A History of Ethiopia” ከትቦታል።
ግርማዊነታቸው
*************
የመጨረሻዎቹ ዕድለ-ቢስ ቀናት ተጭነውት ትኩርት የተነፈገው ኢኮኖሚያዊ አበርክቷቸው ነው። ዘመኑን የቀደመው የነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ መጽሐፍን በብራሃንና ሰላም ጋዜጣ በተከታታ እንዲታተም በማድረግ ንቃተ-ኅሊና ለመፍጠር ሞክረዋል። እንደ ሥርዐቱ ብያኔም የውጪ ካፒታል ወደ አገር ቤት ለማስገባት በዐያሌው ማስነዋል። ወቅቱን የመጠነ ውጤት ማየት ጀምረው እንደነበረም ይታወሳል። ከመጀመሪያው የአውሮፓ ጉብኝታቸው መልስ፦ “ኢትዮጵያ የተከበረ ጥንታዊ ታሪኳን እንደጠበቀች፣ ልጆቿን በዘመናዊ ትምህርት ካስተማረችና ጠንክራ ከሠራች፣ ዓለም ከሚጠቀምበት የሥልጣኔ ደረጃ ላይ ለመድረስ አትቸገርም።” (ተፈሪ መኮንን ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ) የሚለውን ለእውነታ የቀረበ የንጉሡን ንግግር አስታውሰን፣ የፖሊሲዎቹ ሁሉ መዳረሻ በቀን ሦስቴ መመገብ እና ልመናን ማጥፋት ላይ መከንተሩ በራሱ ብዙ ይነግረናል።
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የ’ዐምስት ዐመት የእድገት ፕላን’ በመቅረጽ በተከታታይ ለሦስት ጊዜ ያኽል መተግበራቸው ይታወቃል።
“በ1944 (እ.ኤ.አ) የአስር ዐመት ኢንዱስትሪያል ዕቅድ ተነድፎ ነበር” የሚለው ፖል ሄንዝ፣ የመጀመሪያው ዐምስት ዐመት ለመሠረት-ልማት ግንባታ ሲሆን፣ ቀጣዩ ለኢንዱስትሪው እንደነበረ አብራርቷል። የውጪ ባለሀበት በብዛት እንዲመጡ ያበረታቱ ነበር። ወዳጅ አገራት፣ ዓለም ባንክ እና የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ በርካታ ዓለም-ዐቀፍ ድርጅቶች  ለጥሪያቸው ምላሽ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የመንገዶች ባለሥልጣን፣ መብራት ኃይል፣ ቴሌኮምዩኒኬሽን፣ የማእከላዊ ስታቲስቲክስ ቢሮም በዚህ ወቅት መቋቋማቸው አይዘነጋም። ብሔራዊ ባንክም ሆነ ሌሎች የፋይናንስ ድርጅቶችም የዚያው ዘመን ጥንስሶች ናቸው። ‘ማርትሬዛ’ም ወደ ብር በዚሁ ጊዜ ነው የተቀየረው። ሰፋፊ ዕርሻዎች እና ዘመናዊ ፋክትሪዎችም ማቆጥቆጥ የጀመሩበት ታሪካዊው ዘመን ዛሬ ትዝታው ብቻ ቀርቷል። ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ “Reading on the Ethiopian Economy” በሚል ርእስ ባሳተሙት ጥራዝ፣ ከማኑፋክቸሪንግ አኳያ ሦስቱን ሥራዐቶች አነጻጸረዋል፣
“በቅድመ 1974 እና ድኅረ-1991 ዓ.ም. (እ.አ.አ.) ጥሩ እድገት ሲመዘገብ፣ ከ1974-91 ዓ.ም. ያለው ጊዜ ከዜሮ በታች የወረደ ነበር።”   ለዓለም ገበያ የሚቀርበው የቡና ምርት እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1950 ዓ.ም.  21 ሺሕ ቶን የነበረው፣ በ1963 ዓ.ም. 63 ሺሕ ቶን መድረስ ችሏል። የመኢሶን አባል የነበሩት ዶ/ር ደሳለኝ ራህማቶ “THE PEASANT AND THE STATE” በተሰኘው የምርምር መጽሐፋቸው “ከ1957-1961ዱ ቀዳሚው የዐምስት ዐመት የእድገት ፕላን ትልቅ ትኩረት የሰጠው የአገሪቱን መሠረተ-ልማት መገንባት ላይ ነበር፣” ቢሉም፣ መንግሥታዊ ፖሊሲ የዕርሻ እድገትን ለመደገፍ እና የአዝመራ ጥበብን ለማስተዋወቅ መሞከሩን አትተዋል። የመካናይዜሽን የዕርሻ ልማቶች ከአርሲ እስከ ሲቲቱ ሁመራ መስፋፋቱ በሰነዶች ላይ ሰፍሯል። እንዲያም ሆኖ፣ የንጉሡ ወደረኞች፣ በተለይ፣ ጠርዘኛ ብሔርተኞች ‘ሥርዐቱን ለአንድ ማኅበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሰጠ’ አድርገው ከመተቸት አልተገቱም። ደሳለኝ ራህማቶ፣ “በቀድሞው ሥርዐት (ንጉሣዊው) የተተገበሩት የተለያዩ የግብርና ፕሮግራሞች፣ ከክልላዊ አንጻር ከታዩ፣ ከሰሜኑ የበለጠ ደቡቡ ተጠቃሚ ነበር፣” ማለታቸውን ማስተወስ ተገቢ ነው።
ሃምሳ ዐመታት የኋሊት
—————————
የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሥርዐት ከላይ ከተጠቀሱት ወሳኝ አበርክቶዎቹ በተቃራኒው፣ ውግዘት እና ርግማን የሚያዘንብበትን ስሕተት መሥራቱ አጠራጣሪ አይደለም። ይሁንና፣ በድኅረ-ዘወድ የገነኑት አገዛዞች የባሱ ሆነው መውጣታቸው አዛውንቱን መሪ ለመናፈቅ አስገድዷል። የአገረ-መንግሥት ግንባታን ዳር-ለማድረስም ሆነ ዝመናን ለማንበር የሚያበቃ የነብር-ጭራ መያዙ ተሳክቶላቸው እንደነበር አይስተባበልም።
ጅማሮውን በሕገ-መንግሥት እና ፖሊሲዎች ማሻሻያ አስደግፎ መግራት እየተቻለ፣ በሥር-ነቀልተኛነት የተንኮታኮተበት ፍርደ-ገምድል ዛሬ ድረስ ተከፍሎ ያላተጨረሰ ዕዳ ሆኗል። ፋሽስት ኢጣሊያ የፈጃቸውን ምሁራን የተኩት ታላለቅ ሚኒስትሮችም በአብዮት ሰይፍ መታጨዳቸው ውድቀቱን የከፋ አድርጎታል።
ለውድመቱ የ’አዞዎቹ’ ኅቡዕ ቡድን፣ የሰሜን ወንበዴዎች እና ተነጣይ የኦሮሞ ልሂቃንን ጨምሮ፣ በተማሩ ማርክሲስቶች የተመሠረቱት መኢሶን እና ኢሕአፓ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። የሞከሩት ሥርዐታዊ ሽግግር ከዐፄው ‘ኃይለ-ሥላሴዎች’  ወደ ‘ኮሙኒስት ሥላሴዎች’ የመሆኑ ርቀት ደግሞ የሐቲቱን ባዕድነት ያስረግጣል። ሁነቱን የበለጠ ለመረዳት ትውልዱ ከድንጋሬ እንዲወጣ ታስቦ የተዘጋጀውን “ትውልድ አይደነገር እኛም እንናገር” መጽሐፍ በምስክርነት ይቅረብ፦  “በአብዮት አምጪነት የሚታወቀው፣ የሚወሰደው፣ የሚረገመው የኔ ትውልድ ጭምር ጥር ወር ላይ የየካቲቱ 1966 አብዮት ከተማችን ደጃፍ ፈረሱን ማሰሩን አላየንም። ከዚህ ወጣት ትውልድ መሃል የሃገሪቱን እጣ የወሰኑት ሳይቀሩ ጥር ውስጥ የማርክስን ኮምኒስት ማኒፌስቶ ሳይሆን የማሪዮ ፑዞን ጎድ ፋዘርን (The God Father) ነበር የሚያነቡት።
የአሜሪካ ማፍያ ታሪክ። በወቅቱ የአምስት ኪሎው ኢንጅነሪንግ ኮሌጅ ተማሪ ነበርኩ። ምግብ የምንበላው አራት ኪሎ ካምፓስ ነው። የጎድ ፋዘር መጽሃፍ ገና መታተሙ ነበር። አሜሪካ ሄዳ የነበረች የአማኑኤል ገብረየሱስ እህት፣ ታደለች ገብረየሱስ፣ አብሮ አደጌ አምጥታልኝ እያነበብኩ ነበር። ‘ስጨርሰው እሰጥሃለሁ’ ብዬ ቃል የገባሁት ለመለስ ዜናዊ (ያኔ ለገስ ዜናዊ) ነበር። እየጨቀጨቀ ቢያስቸግረኝ፣ አንድ ቀን በአራት ኪሎና አምስት ኪሎ መሃከል ስንገናኝ ‘ያነበብኩትን ውሰድ፤ ቀረውን ስጨርስ እሰጥሃለሁ’ በማለት መጽሃፉን ለሁለት ሰንጥቄ ሰጠሁት። ከተወሰነ ቀን በኋላም በጄ የቀረውን ክፍል አስረከብኩት።”  ወንድም አንዳርጋቸው እንደነገረን፣ በማፍያ ከተቀኙ መሪዎችም ሆነ ከደቀ-መዛሙርታቸው ሕግ-አክባሪነትን መጠበቅ ‘ንፋስን እንደ መከተል ያለ የከንቱ ከንቱ ከንቱ ነው’። (ወታደራዊ ጁንታውን ዘንግቼው አይደለም፤ ሚናው ዘውዱን ከመነቅነቅ ይልቅ፣ ወደ ‘አብዮት ቀባሪ’ነት አጋድሎብኝ ነው።)
ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የፖለቲካው አቅጣጫ ዐዲስ ነገር ከመፍጠር ይልቅ ንጉሡ የሠሩትን በማፍረስ መጠመዱ ገሃድ የወጣ ነው። በርግጥ፣ አሁንም ቀጥሏል። የታሪክ ጎርፍ ያመጣቸው ዘውጌ-ድርጅቶች ስሑት-ወሬዎችን ተመርኩዘው ‘ጥንት እንዲህ ነበርን’ ዐይነት ጩኸትን ወደ ጎን ብሎ፣ ንጉሠ-ነገሥቱ ያስገነቧቸውና በስማቸው ይጠሩ የነበሩ መንግሥታዊ ተቋማት ወደ ቀድሞ ስያሜአቸው ይመለሱ ዘንድ ግፊት ማድረግ የዜግነት ግዴታ እንደሆነ ለማስታወስ እወድዳለሁ። ሕዳሴ ይህ ነው።
በድጋሚ፣ ግርማዊነትዎ፣ እንኳን ተወለዱ!
ፍትህ መጽሔት  ቁጥር 37 ቅዳሜ ሐምሌ 13/2011
Filed in: Amharic