>

መታረም ያለበት የአቶ ታዬ ቦጋለ ንግግር!  (አቻምየለህ ታምሩ)

መታረም ያለበት የአቶ ታዬ ቦጋለ ንግግር! 
አቻምየለህ ታምሩ
* አቶ ታዬ ቦጋለ የኔ አባባል ያለውን ንግግር ያደረገው በተለምዶ ሲቀርብ እንደምናየው እነ ዳግማዊ ምኒልክን ያልተማሩ፤ እነ መለስ ዜናዊን ደግሞ የተማሩ አድርጎ ከማሰብ ይመስለኛል ግን ይህ ፈጽሞ የተሳሳተ ነው…
አቶ ታዬ ቦጋለ ከሰሞኑ በመዲናችን በአዲስ አበባ አንድ መድረክ ላይ ተገኝቶ ጥሩ ንግግር አድርጓል። በንግግሩ አጠቃላይ ይዘት  እምብዛም ልዩነት የለኝም። ከንግግሩ ውስጥ «ያልተማሩ ምሁራን ያቆዩዋትን አገር የተማሩ ማይማን አያፈርሷትም»  በማለት ባቀረበው  አባባሉ  የተማረና ያልተማረ በሚል የገለጻቸው መሪዎች አቀራረብ ግን  ትክክል ነው ብዬ አላምንም። ያልተማረ ሰው ምሁር ይሆናል የሚለውም ትክክል አይደለም። ምሁርነት እንደዛር በሰው ላይ የሚሰፍር ነገር ነው ካልተባለ በስተቀር ያልተማረ ሰው ምሁር ሊሆን አይችም፤ የተማረም ማይም ሊሆን አይችልም።
ምሁርነት መማር የግድ የሚል የሀሳብ ሰው መሆን ማለት ነው። ይህ ደግሞ መዘጋጀትን ይጠይቃል። መዘጋጀት ማለት በአብዛኛው ማንበብ ማለት ነው። አንድ ሰው ምሁር ሆነ ማለት አነበበ፣ ሀሳብ አፍላቂ ሆነ ማለት አይደለም። አንድ ሰው አነበበ ማለት ለሀሳብ ማፍለቅ ሁኔታዎችን አመቻቸ ማለት ነው። ማንም ሰው ሀሳብ ይመጣለታል። ሕጻናትም ቢሆኑ ሀሳብ ይመጣላቸዋል። ሆኖም ግን የሀሳብን ጥሩነት ደረጃ በትክክልና በፍጥነት ለመገመት ከቀድሞው አንብቦ መዘጋጀት ያስፈልጋል።
ሀሳብ ማለት መንገድ ላይ የሚገኝ ወርቅ ማለት ነው። ወርቅን ካላወቅን ድንጋይ ብናገኝ ወርቅ ብናገኝ ልዩነት የላቸውም። ስለዚህ አንድ ሰው ሁል ጊዜ በውቀት የታነጸ የሀሳብ ባለቤት ወይም ምሁር ለመሆን ራሱን በንባብ ማዘጋጀት አለበት። አንድ ሰው ራሱን በንባብ ካላዘጋጀ ግን ሀሳብ እንኳ ቢመጣለት ተንኖ ይጠፋበታል እንጂ ጥቅሙን ሊያውቀውና ሊያደረጀው አይችልም። ወርቅ ብናገኝ ወርቅነቱን ካላወቅን በስተቀር ከድንጋይ ልንለየው እንደማንችል ሁሉ ሀሳብም ያለ ንባብ ጠቀሜታ የለውም። ያላነበበ ሰው አለምን የሚለውጥ ሀሳብ እንኳ ቢያፈልቅ የሀሳቡ አለም ለዋጭነት ሊታወቀው አይችልም። ስለዚህ የምናመነጨውን ሀሳብ ጠቀሜታ ለማወቅ በንባብ የበቃን መሆን አለብን! በንባብ የበቃ ሰው የሀሳብን ክብደት ማወቅ ይቻለዋል።
በመሆኑም ምሁር በንባብ የበቃ፣ የመረመረ፣ እንደ ባሕር ጥልቀት ያላቸው ቁምነገሮ ባለቤት የሆነና ተጨንቆ በማሰብ ሀሳብ የሚያፈልቅ ሰው ነው።
እንደመሰለኝ አቶ ታዬ ቦጋለ የኔ አባባል ያለውን ንግግር ያደረገው በተለምዶ ሲቀርብ እንደምናየው እነ ዳግማዊ ምኒልክን ያልተማሩ፤ እነ መለስ ዜናዊን ደግሞ የተማሩ አድርጎ ከማሰብ ይመስለኛል። ሆኖም ግን ይህ አስተሳሰብ የተሳሳተ ነው።
የኢትዮጵያ ነገሥታት አገር ለመምራት የሰለጠኑና በሥነ መንግሥት በእጅጉ የተማሩ ነበሩ። በነገሥታቱ ዘመን የነበሩት የኢትዮጵያ ቤተ መንግሥቶች የወደፊት የኢትዮጵያ መሪዎች የሚሆኑ ወጣቶች የአገር አስተዳደርና ሥነ መንግሥት የሚቀስሙባቸው ተቋማት ነበሩ። በሌላ አነጋገር የኢትዮጵያ ቤተ መንግሥቶች የወደፊት መሪ የሚሆኑ ወጣቶች የሚሰለጥንባቸው ተቋማት ነበሩ። ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ቤት መንግሥት ውስጥ ለአስር ዓመታት ያህል የኢትዮጵያን የአገር አስተዳድር ትምርትና ሥነ መንግሥት ሲማሩ ነበር። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ደግሞ የአገር አስተዳደር ትምህርትና ሥነ መንግሥት የተማሩት መጀመሪያ ባባታቸው በራስ መኮንን ቤት ከተቀጠሩላቸው የፈረንጅና ኢትዮጵያውያን መምሁራንና ኋላ ላይ ደግሞ ዳግማዊ ምኒልክ እግር ስር ተቀምጠው በብሔራዊው ቤተ መንግሥት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤትም ገብተው የውጭ ቋንቋና የኢትዮጵያን የመንግሥት ታሪክ ተምረዋል።
የኢትዮጵያ መሪዎች በልጅነታቸው በቤተ መንግሥት የአመራር ጥበብና የአገር አስተዳደር ትምህርት ሲማሩ የተቋሙ መርኅና የትምህርቱ ፍልስፍና «ኵሎ አመክሩ ወሠናይ አጽንዑ» ወይንም «ሁሉን መርምሩ መልካሙን ያዙ» የሚል ነበር። «ሁሉን መርምሩ መልካሙን ያዙ» የሚለው አስተሳሰብ የትምህርት ሳይንስ መሰረታዊ ባሕሪ ነው።
በሌላ አነጋገር የኢትዮጵያ ነገሥታት የትምህርት እውነተኛ ባሕሪ ወይንም «ሁሉን መርምሩ መልካሙን ያዙ» የሚለውን ፍልስፍና መመሪያቸው አድርገው በዘመኑ የመሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም በሆነው በቤተ መንግሥት የአገር አስተዳደር ትምህርትና ሥነ መንግሥት የተማሩ ስልጡኖች ናቸው።
በመሆኑም ትምህርትን ምዕራባዊ ቀለም ካልሰጠነው በስተቀር በኢትዮጵያ የመሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም በቤተ መግሥጥ ውስጥ ገብተው ለዓመታት ለመሪነት የሚያስፈልገውን የአገር አስተዳደር ትምህርትና ሥነ መንግሥት እየተማሩ ያደጉ የአገር የኢትዮጵያ ነገሥታት ያልተማሩ ልንላቸው አንችልም። ዐፄ ዮሐንስም ሆነ ዳግማዊ ምኒልክ እንዲሁም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በኢትዮጵያ የመሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ ገብተው መሪ ለመሆን የሚያስችላቸውን የአገር አስተዳደር ትምህርትና ሥነ መንግሥት ተምረው የጨረሱ ሰዎች ናቸው።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ነገሥታትና ራሶች አቶ ታዬ እንዳለው ያልተማሩ ምሁራን ሳይሆኑ መሪነት የሚጠይቀውን የአገር አስተዳደር ትምህርትና ሥነ መንግሥት ጠንቅቀው የተማሩና መሪ ለመሆን የተዘጋጁ ሊቃውንት ነበሩ።
በተቃራኒው አቶ ታዬ የተማሩ አድርጎ ያቀረባቸውን እነ መለስ ዜናዊን ያየን እንደሆነ የትምህርትን ባሕሪ ባፍጡሙ የደፉ፣ ጸረ ትምህርት አፍ ነጠቆችና መሪ ለመሆን ያልተዘጋጁ፤ የሥነ መንግሥት እሳቤ ያልነበራቸውና በእውቀት ላይ የሸፈቱ ሌጣዎች እንደነበሩ ማስተዋል እንጅላለን። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በሩ ላይ «ሁሉን መርምሩ መልካሙን ያዙ» የሚል አርማ አስቀርጸው የከፈተፉትን ዩኒቨርሲቲ ተማሩ የተባሉት እነ መለስ ዜናዊና መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ግን «ከኛ ውጭ ያለውን አትስሟቸው» በሚል የድንቁርና አስተሳሰብ ደምስሰው ወጣቱ «ሁሉን መርምሩ መልካሙን ያዙ» የሚለውን የትምህርት እውነተኛ ባሕሪ እንዳይከተል አድርገው ድንጋይ ማምረቻ አደረጉት።
እነ መለስ ዜናዊ እንኳን የተማሩ ሊሆኑ ተሰርተው ያላለቁ፣ የተማሩ ሰዎች ባገር እንዳይኖሩ ያደረጉ ደናቁርት ነበሩ። መለስ ዜናዊ እድሜ ዘመኑን የኖረው አንድ ነገር ካነበበና ስለአንድ ነገር ከሰማ ሌሊቱን ስለዚያ ስላነበበው ወይንም ስለሰማው ነገር ሲጽፍ በማደር በበነጋታው ወደ አገራዊ «ፖሊሲ» ሲቀይር፣ ያለጥናት ተከፍቶ ያለ ጥናት ተዘጋ እያለ ኢትዮጵያን የብክነት ማዕከል አድርጎ የኖረ ፍጡር ነው። ADLI፤ ውሀ ማቆር፤ BPR፤BSC፤ ማይክሮ ፋይናንስ፤ ውጤት ተኮር፤ ጥቃትንና አነስተኛ ተቋማት፤Develomental State፤ ወዘተ የሚባሉት አገራዊ ፖሊሲ የሆኑት ሁሉ ያለ ጥናት ሲከፈቱና ሲቋረጡ የኖሩ የአገር ፖሊሲን እንደ መስሪያ ቤት ማኑዋል በየቀኑ እየቀያየረ አገር ሲያባክን የኖረ ጮሌ ነው። መለስ ዜናዊ የትምህርትን መሰረታዊ ባሕሪ ባፍንጫው ደፍቶ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ከጋዜጣ በላይ ማንበብ የማይችሉ ካድሬዎች የበለጠ ጥሬ ሆነው ወደሚወጡበት የፖለቲካ ተቋማት የቀየረ ማይም ነው።
የኦሮሞ ብሔርተኞችም እንደዚያው ናቸው። የኦሮሞ ብሔርተኞች ስል ባመዛኙ የኦነግን ፕሮግራም የሚያቀነቅኑና ኦሮምያ የምትባል የተስፋ ምድር ፈጥረው እሷን አገር ለማድረግ በአንድም በሌላም መንገድ እየታገሉ የሚገኙትን ጎሳቸውን ያስቀደሙ ሁሉንም ብሔርተኛ ነን የሚሉ ከኦነግ እስከ ኦሕዴድ ያሉ ግለሰቦችን ያጠቃልላል። እነዚህ የኦሮሞ ብሔርተኞች ባለፉት 44 ዓመታት ጠባብ አላማቸውን በኢትዮጵያውያን መቃብር ላይ ለማስፈጸም የውሸት ትርክት ተስማምተው ፈጥረዋል፣ አሳትመዋል፣ተከታዮቻቸውን በጥላቻ አሳብደዋል።
ያሳበዱት ወጣት ደግሞ «ሁሉን መርምሩ መልካሙን ያዙ» በሚለው የትምህር እውነተኛ ባህሪ እየተመራ ግርድና ምርቱን እንዳያጣራ «ሌሎችን አትስሙ፣ ደብተራ የጻፈውን ታሪክ አታንብቡ፣ እውነቱ ይህ እኛ የምንነግራችሁ ነው» ብለው አደንቁረውታል።
እንደ ኦሮሞ ብሔርተኞች ባለፉት አርባ አራት ዓመታት ለሕጻን እንኳ የማይወራ የጅል ፈጠራ እየፈጠሩ በየሜዲያውና ባገኙት መድረክ ሁሉ እያስተጋቡ የኦሮሞ ወጣት ከነሱ ፈጠራ ውጭ ሌላው የሚጽፈውን እንዳያነብና እንዳመረምር አድርጎ የሚነግሩን ሁሉ እንደወረደ የሚቀበል ትውልድ እንዲፈጠር ያደረገ ቡድን ያለ አይመስለኝም። የኦሮሞ ብሔርተኞች ለሕጻን እንኳ የማይወራ የጅል ፈጠራ እየፈጠሩ በየሚዲያው የሚዘበዝቡትና በሚያወጡት ጥራዝ ሁሉ የደርቱት ጅል ስለሆኑ አይደለም። ሌላው መሳቂያ መሳለቂያ ቢያደርገንም ኦሮሞው ያምነናል የሚል እምነት ስላላቸው ነው። በሌላ አነጋገር የኦሮሞ ብሔርተኞች «ኦሮሞ ጅል ነው» ብለው ከልባቸው ያምናሉ።
የኦሮሞ ብሔርተኞች ከዛሬ መቶ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር አምስት ሚሊዮን በማይሞላበት ወቅት ምኒልክ አምስት ሚሊዮን ኦሮሞ ጨፈጨፈ የሚል እጅግ አስቂኝ የፈጠራ ታሪክ ሲያሰራጩ የኖሩት ለሌሎች ቢያስቅም ኦሮሞን ግን ያሳምናል ብለው ስለሚያምኑ ነው። ጊዜ ሰጥተው ትንሽ መጠበብና ከዚህ የተሻለ ተረት ተረት ፈልስፈው ኦሮሞ ዐማራን እንዲጠላ ማድረግና ማጫረስ ተስኗቸው ሳይሆን ኦሮሞን ለማሳመን ያን ያህል ውጣ ውረድ አያስፈልገውም ብለው በማሰባቸው ነው። በታሪክ ውስጥ ሐሰትን መፈልሰፍና ጥላቻን ማራባት የጎሳ ብሔርተኞች ተቀዳሚ ተግባር ነው። የኤርትራና የትግሬ ብሔርተኞች ሲፈለስፏቸው የቆዩ ተረቶች ታሪክን ለማያውቅ ሰው እውነት መስለው ሊታዩ የሚችሉ ነበሩ። እሳት የሚፋጅ መሆኑን የሚያውቅ የኦሮሞ ብሔርተኛ ተረት ተረት የቀልዶች ቀልድ መሆኑን ያውቃል። ሕዝባችን የሚሉት ይህን ያህል ማገናዘብ አይችልም ብለው የሚያስቡት እነዚህ ብሔርተኞች የሚፈጥሩት ለሕጻን እንኳ የማይወራ የጅል ፈጠራ ሕዝብን ለሚሉት ያላቸውን ግምት የሚያሳይ ነው።
የኦሮሞ ብሔርተኞችም ሆኑ ባጠቃላይ የኢትዮጵያ የጎሳ ብሔርተኞች አንድ በትክክል የተረዱት ነገር «ሁሉን መርምሩ መልካሙን ያዙ» የሚለውን የትምህርት እውነተኛ ባህሪ የቀሰመ፣ መረጃን በነጻነት የሚያገኝና የሚመረምር ሰው እንደፈለጉት እንደማይጠመዝዙት ገብቷቸዋል። የኦሮሞ ብሔርተኞች የኦሮሞን ወጣት «ሌሎችን አትስሙ፣ ደብተራ የጻፈውን ታሪክ አታንብቡ፣ እውነቱ ይህ እኛ የምንነግራችሁ ነው» እያሉ «ሁሉን መርምሩ መልካሙን ያዙ» ከሚለው የትምህርት እውነተኛ ባህሪ ያፋቱት አደንቁረው የነሱት ለሕጻን እንኳ የማይነገር የፈጠራ ታሪክ ሊሞሉት ስለፈለጉ ነው።
ባጭሩ አቶ ታዬ ካለው በተቃራኒ የተማሩቱ የኢትዮጵያ መሪዎች የትምህርት እውነተኛ ባሕሪ የሆነውን «ሁሉን መርምሩ መልካሙን ያዙ» የሚለውን እሳቤ መመሪያቸው አድርገው በኢትዮጵያ የመሪዎች ተቋም ውስጥ በመግባት መሪ ለመሆን የሚያበቃውን የአገር አስተዳደርና ሥነ መንግሥት ጠንቅቀው የተማሩትና የትምህርትን እውነተኛ ባሕሪ ተቋማዊ ያደረጉት እነ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንጂ የትምህርትን እውነተኛ ባሕሪ ባፍጡሙ ደፍተው፣ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ለሚሏቸው ለሕጻን እንኳ የማይነገር የፈጠራ ታሪክ እያመረቱ ሌሎችን አትስሙ የሚል ጨለማ ውስጥ እንዲጎለቱ ያድረጉት የድንቁርና የእውቀት ጾመኞቹ እነ መለስ ዜናዊ አይደሉም።
Filed in: Amharic