>
11:10 am - Wednesday December 7, 2022

አደጋዎች ያንጃበቡበት ለውጥ!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

አደጋዎች ያንጃበቡበት ለውጥ!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
ኢትዮጵያ ዛሬ የለውጥ መንገድ ላይ ነች። የለውጡ እንቅስቃሴ ብዙ ተስፋዎችን የሰነቀ ቢሆንም በብዙ አደጋዎችም የተከበበ ነው። ዋና ዋና ከሆኑት እና ለውጡን ሊገዳደሩ ወይም ፍጥነቱን ሊገቱ ወይም ሊያደናቅፉ እና አቅጣጫውንም ሊያስቱ ይችላሉ ብዮ የማስባቸውን ነጥቦች ለውይይት በሚያመች መልክ ለማስቀመጥ ልሞክር። ስጋቶቹ የእኔ ብቻ ከሆኑ እና መሬት ላይ ካለው እውነታ የራቁ ከሆነ እሰየው። እኔው ብቻዮን እሸበርባቸዋለሁ። ስጋቱ የብዙዎች ከሆነ በጋራ መፍትሔ ከወዲሁ መፈለግ ግድ ይላልና እንወያይባቸው። ለውጥ አደናቃፊ ሊሆኑ የሚችሉት አደጋዎች፤
– ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ኢትዮጵያዊነት እየተቀነቀነ ቢሆንም በዛው ልክ ጎሰኝነትም እንዲሁ እየተራገበ ይመስላል። ክልሎች አገር እየሆኑ ነው። እያንዳንዱ ክልል በራሱ መንገድ እየተመመ እና መሁራንም በጎሳ ተቧድነው በትልቋ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት ትልቅ መሆን እንደሚችሉ እየመከሩ ነው። ይህ አይነቱ ስሜት እየቆየ በክልሎች መካከል ፉክክርን ብቻ ሳይሆን የተጀመረውን መገፋፋት እያጠናከረ የሚሔድ ይመስለኛል። መገፋፋቱ ደግሞ ሌሎች አደጋዎችን ሊወልድ ይችላል።
– ከላይ ከተነሳው ችግር ጋር ተያይዞም የአክራሪ ብሔረተኞች መጠናከር እና በአንዳንድ አካባቢዎችም በትጥቅ ወደተደገፈ እንቅስቃሴ መገባቱ፤
– እየተካሔደ ያለው ለውጥ ወይም ሊመጣ የሚችለው ውጤት የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ጥቅሜን ይነካብኛል ወይም ከወዲሁ ጥቅሜን አሳጥቶኛል የሚሉ ኃይሎችም በሁሉም መንገድ ሂደቱን ለመቀልበስ ያላቸውን አቅም እየተጠቀሙ ይመስላል። ለዚህም በየክልሉ የሚታዩት ግጭቶች እና ውጥረት፣ የገንዘብ ሽሽት፣ የጦር መሳሪያዎች ዝውውር እና የዜጎች መፈናቀል ጥሩ ማሳያዎች ይመስሉኛል።
–  ከላይ የተጠቀሱትን አደጋዎች ለመቋቋምና ሊቀለብሱ የሚችሉ አገራዊ ተቋማት እጅግ የተዳከሙበት እና እነሱን የማጠናከሩም ሥራ ጊዜ እና ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ መሆኑ አደጋዎቹ እንዲስፋፉ እድል እየፈጠረ ይመስላል።
– ሌላው አደጋ የዶ/ር አብይ እራዕይ እና የሚመሩትን ድርጅት የኢህአዴግን ቅዠት እንዴት ማስታረቅ ይቻላል የሚለው ነው። የድርጅቱ አብዛኛው ፖሊሲዎች እና የፖለቲካ መስመር ዶ/ር አብይ በየመድረኩ ከሚገልጹልን ነገር ጋር አይገናኝም። ሕዝብ በተደመረበት መጠን ድርጅታቸው ተደምሯል ወይ የሚልው የብዙዎች ጥያቄ ነው።
ልክ የዛሬ ዓመት ይቸን ጫር አርገን ነበር ፤ ጽሁፉ ዛሬንም ጥሩ አድርጎ ይገልጻልና አካፈልኳችሁ!
Filed in: Amharic