>

አቶ ሙስጠፌ ኦማር ማናቸው? (ሙክታሮቪች ኡስማኖቭ) 

አቶ ሙስጠፌ ኦማር ማናቸው?
(ሙክታሮቪች ኡስማኖቭ)
አዲሱ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፋ  የተወለዱት በጀረር ዞን ባለችው አቡበሬ ወረዳ ነው። ከጅጅጋ 75 ኪሜ ከሶማሌላንዷ ቦረማ 17 ኪሜ ወረዳ በ1973 ነው [It must be in European Calendar]፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን በአውበሬ ፣ ቤተሰባቸው ወደ ደጋህቡር በመዘዋራቸው ምክንያት የመካከለኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው ደጋህቡር ተከታትለዋል። የማትሪክ ፈተናን በአስደናቂ አራት ነጥብ፣ ሁሉንም ትምህርት አይነቶች A በማምጣት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሀረር ከተማ መድሃኒያለም ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡
አዲስአባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ በማዕረግ ከተመረቁ በኋላ በተለያዩ መንግስታዊ መስሪያቤቶች አገልግለው በግላቸው ተጻጽፈው በፈታኝ ውድድር ባሸነፉት ስኮላርሽፕ እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ኢምፔርያል ኮሌጅ ኦፍ ለንደን በአግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ የማስተርስ ድግሪያቸውን ሰርተዋል። ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት ናቸው፡፡ ሙስጠፋ ኡመር ከአብዲኢሌ አስተዳደር ጋር ተጋጭተው በስደት የተለያዩ የውጪ ድርጅቶች ከመስራተቸው በፊት በሶማሊ ክልል በትምህርት ቢሮ ምክትል ሀላፊ፣ በአብዱልመጂድ የመምራን ማሰልጠኛን በዳሬክተርነት አገልግለዋል። የአብዲኢሌ ስርዓት የሚያስቡ፣ ብቃት ያላቸውን ሰዎች ሁሉ ስለማይፈልጉ ሀገራቸውን ማገልገል እየፈለጉ ከሀገር ሊሰደዱ ችለዋል፡፡ ሙስጠፌ ሀገራቸውን ማገልገል እየፈለጉ በግድ ተሰደዱ። ልባቸው ግን ከኢትዮጵያ እና ከሶማሌ ማህበረሰብ አንዴም ርቆ አያውቅም። የደሃ ህዝባቸው ሁኔታ ያንገበግባቸዋል።
ከሀገር ከወጡ በኋላ የተለያዩ አለማቀፍ መያዶችን አገልግለዋል፡፡ Save the children, WFP, UN, OCHA ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህ ስራቸውም ሶማሊያን፣ ኬንያን፣ ዚንባብዌንና አሜሪካን ሀገር በተለያዩ የሀላፊነት ቦታዎች በብቃት አገልግለዋል፡፡ ሙስጠፋ ኦሮምኛን እና አማርኛን አፍ ከፈቱበት ሶማሊኛ እኩል አቀላጥፈው ይናገራሉ፡፡ እንግሊዘኛን አረብኛንና ፈረንሳይኛን በተለያየ የችሎታ ደረጃ ቢችሉም በእንግሊዘኛ የሚጽፉት ጽሁፎቹን ላስተዋለ የቋንቋ ችሎታቸው ሳያደንቅ አያልፍም፡፡
አቶ ሙስጠፋ አብዲኢሌን ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ አምርረው በመቃወም፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ለሶማሌ ክልል ህዝብ በወያኔ አንባገነናዊ አመራር የሚደርስበትን ግፍ በማጋለጥ በንቃት ለብዙ አመታት ጽፈዋል፣ አጋልጠዋል፣ ሞግተዋል የመፍትሄ ሀሳቦችን ሰንዝረዋል፡፡ በዚህም እጅግ የሚያሳቅቅ የበቀል እርምጃ አብዲ በቤተሰባቸው ላይ አድርሶአል፡፡
ሙስጠፋ ያስከፈላቸው ዋጋ
አቶ ሙስጠፋ ኡመር የአብዲኢሌን የሰው—በላ ስርዓት አምርሮ በመቃወም፣ ለአለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት የመብት ጥሰቶችን ሲያጋልጥ፣ በዚያ መናገር ዋጋ በሚያስከፍልበት ዘመን ለነጻነትና ለፍትሃዊ ህዝባዊ ስርኣት ዋጋ ለመክፈል ቆርጦና ወስኖ ነበር፡፡  በዚህ ውሳኔውም ታናሽ ወንድሙን በአብዲሌ የግል ወታደሮች አጥቷል፡፡
በምህንድስና ሀገሩን እያለገለገለ ሳለ፣ በአብዲሌ ወታደሮች ተይዞ በአባቱ ፊት በጥይት ተመቶ እየከነፈ ከሚሄድ መኪና ላይ ተወርውሮ በአሳቃቂ ሁኔታ የተገደለ ነው፡፡ በወቅቱ አቶ ሙስጠፋ የአብዲኢሌን አስተዳደር እንዳይነቅፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት፣ እሺ ባለማለቱ የበቀል እርምጃ እንደሆነ ተነግሮታል፡፡
የበለጠ የሚያሳዝነው ደግሞ አባቱ የልጃቸውን መገደል በአይናቸው አይተው በመሪር ሀዘን ውስጥ ሆነው ጤናቸው ተቃውሶ ባለበት አብዲ አስሮ መድሃኒት ከልክሎ ያሰቃያቸው ነበር፡፡ “ልጅዎት በአዕምሮ ጤና ቀውስ ሳቢያ እራሱን አጥፍቶ ነው” ብለው ይመስክሩ እያለ በሀዘን ላይ ሀዘን በበሽታ ላይ በሽታ ደራርቦባቸው ቶርች ያደርጋቸው ነበር፡፡ ለሙስጠፋም ከድርጊቱ ካልተቆጠበ ቤተሰቡን እንደሚጨርስ፣ እህቶቹን እንደሚያስደፍር እና ኬንያ ናይሮቢ ያሉ ባለቤቱን እና ሁለት ልጆቹን እንደሚያስገድል አስጠንቅቆታል።
በህዝብ ወገንተኝነትና በቤተሰብ መስዋዕትነት በሁለት የተከፈለው ሙስጠፋ ምን ያህል አስጨናቂ ጊዜን እንዳሳለፈ መቼም ማሰብ ነው፡፡ በሚሰራበት የተባበሩት መንግስታት በኩል በኢትዮጵያ መንግስት ለቤተሰቦቹ የህግ ጥበቃ እንዲደረግለት፣ ኬንያም ለቤተሰቡ የህግ ጥበቃ እንድትሰጥለት በቲዊተርና በፌስቡክ በጣም ተማጸነ፡፡ ከአንባገነኑ የወያኔ ስርዓት ፍትህን እንደማይጠብቅ ተናግሮ ለቤተሰቦቹ የአለማቀፍ ማህበረሰብ እንዲረባረቡለት በከፍተኛ ደረጃ ተማጸነ፡፡
እጅግ አስጨናቂ ጊዜ ነበር ለሙስጠፋ ታናሽ ወንድምን በአስከፊ ሁኔታ ማጣት፡፡ ልብ ይሰብራል፣ አቅም ያሳጣል፣ እምነትን ይፈትናል፡፡ አብዲሌ ሙስጠፋ በሰራው ስራ ወንድሙን ነጠቀው፡፡ ይህ እንደ እግር እሳት የሚለበልብ እውነት ነው፡፡ ሙስጠፋ በቲዊተር ገጹ ስለወንድሙ መገደል፣ ስለ80 አመት የሞላቸው አባቱ መሰቃየት፣ ስለቤተሰቡ የበቀል ዛቻ ሁሉን ነገር ከገለጸ በኋላ ለሟች ታናሽ ወንድሙ ፋይሰል ኡመር ስሜት በሚነካ አነጋገር እንዲህ በማለት ጽሁፉን ይዘጋል:—
‹Allah yarham, brother. You know how much I love you. All I can do is to take care of your children and family, if they also survive this madness.›
አቶ ሙስጠፋ በሚሰጡአቸው ቃለምልልሶች ይህን የቤተሰቡ ታሪክ በፍጹም አያነሱም፡፡ የሚፈልጉት ስርአት በበቀልና በቂም ያለፈን ጉዳይ በማከክ ትናንትና ላይ የተቸነከረ ሳይሆን ትናንትን ተሻግረን ዛሬ ለነገ ትውልድ የምትበጅ ሀገርን ለመገንባት በመሆኑ ስለሀገራቸው ኢትዮጵያ እና ስለየሶማሌ ህዝብ ሁለንተናዊ ለውጥ ዘውትር ያስቡ ይጨነቁ ነበር፡፡ አቶ ሙስጠፋ ኡመር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በፌስቡክ በተለይም በትዊተር በትጋት ስለ የሶማሊ ህዝብ የአስተዳደር በደል ለአለማቀፉ ማህረሰብ በሰላ ብዕሩ ጽፏል፣ አንቅቷል፣ ህዝብ የሚገባውን ከሀገር ሀብት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ አተኩሮ ለሀገር አንድነት የሚበጀው ከብሄራዊ ማኣድ ሁሉ ህዝብ የድርሻውን ሲያገኝ ነው ለሁሉ የሚበጀው የሚል የጸና አመለካከቱን በስፋት አጋርቷል፡፡
አቶ ሙስጠፋ ዘውትር የሚያንገበግበው በዚህ 27 አመታት የሶማሊ ህዝብ በሀቀኛ፣ ብቃት ያላቸው በልጆቹ እራሱን ለማስተዳደር እድል ሳይሰጠው፣ በተዘዋዋሪ እጅ ጠምዛዥ አምባገነኖች እየተመራ፣ ነገርግን በመላ ኢትዮጵያውያን እራሱን መምራት እንደማይችል፣ በጀት አባካኝ፣ ግዴለሽ፣ ብቃት የለሽና ደንታቢስ ህዝብ ተደርጎ መሳሉ ነው፡፡ ሙስናው በዋነኝነት በአማካሪነት ስም እንደመዥገር የተጣበቁበት ጄነራሎችና የህወሃት አምባገነኖች ምህንድስና እና የበላይ አመራነት የሚሰራ ሆኖ ሳለ የብዙዎች አመለካከት የሶማሊ ህዝብ እና ሙስናን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ አድርጎ መቀበሉ ዘውትር ሙስጠፋን ያበሳጨዋል፡፡
ብቃት ያላቸው፣ ሀገራቸውን የሚወዱ፣ እጣፋንታቸውን ከኢትዮጵያውያን የጋራ እጣ ፈንታ ጋር ደምረው የሚመለከቱ፣ በሶማሊ ህዝብ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እና በሶማሊ ብሄራዊ ስሜት በተደላደለ ውሃልክነት እኩል የሚመለከቱ ሙህራን እንዴት በወያኔ አንባገነናዊ ስርዓት እንደሚገፉ አቶ ሙስጠፋ ስለሚያውቁ አሁን በዶክተር አብይ የታለመውን ለውጥ ለመቀላቀል አፍታም ማሰብ አላስፈለጋቸውም፡፡ አቶ ሙስጠፋ ኡመር ዘውትር የሚከራከሩበት አንድ ነጥብ የክልሉ ስያሜ ለምን የኢትዮጵያ ሶማሊ መባል እንዳስፈለገው ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ለመሆን የግድ ‹የኢትዮጵያ…› የሚል ቅጥያ አየስፈልገንም፣ ይህ እኛን መጠራጠርና ማግለል ካልሆነ በቀር ትግራይም የ”ኢትዮጵያ ትግራይ” አኟኩምና ኑዌሩም ፣ አፋሩም፣ ቦረናውም ‹የኢትዮጵያ…› በሚል ቅጥያ ሊጠሩ ይገባል የሚል የጸና አቋማቸውን ዘውትር ያንጸባርቃሉ፡፡
ልክ አሰፋ ጫቦ ‹ኢትዮጵያዊነቴ እና ጋሞነቴ ተጣልተውብኝ ላስታርቃቸው አንዴም ቁጭ ብዬ አላውቅም› እንዳሉት፣ አቶ ሙስጠፋም ኢትዮጵያዊነታችን እና ሶማሌነታችን አይጣላብንም፣ በዚህ በኩል ከኢትዮጵያ ወንድሞቻችን ጋር፣ በዚያ በኩል ደግሞ ከጎረቤት ሀገር ሶማሊ ወንድሞቻችን ጋር ሚዛን የጠበቀ ግኑኝነት መስርተን ምስራቅ አፍሪካን በማስተሳሰር ቀጠናውን በልማት ማስተሳሰር እንችላለን የሚል የጸና አቋማቸውን በተለያየ የሶሻል ሚድያ መድረኮች አንጸባርቀዋል፡፡
በሶሻል ሚድያ የአክቲቪዝም ጊዜያቸው እጅግ ጨዋና ስነምግባርን የተላበሰ፣ ሀሳብን ከግለሰብ እየለዩ በሰከነ መንገድ ሀሳብ እንደሚያንሸራሽሩ ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ ለምሳሌ ወደ ፕሬዝዳንት መምጣታቸውን ተከትሎ፣ የኬሌ ዩኒቨርሲቲው የህግ ሙሁር አዎል ቃሲም አሎ ስለሳቸው በትዊተር ገጹ የሚከተለውን ምስክርነት ሰጥቷል፡-
“I have known Mustefa Omer for nearly two years now and have had extensive conversations with him on the politics of Somali regional state, Ethiopia and the Horn of Africa. I can’t think of a more intelligent, decent, and perceptive candidate that can move the Somali region forward,”
በሶማሌ ማህበረሰብ ልሂቃን ለረጅም ጊዜ የጋራ መድረክ በሆነው Somali Online ላይ Abtigiis በሚል የብዕር ስም እጅግ ሞጋችና አጀንዳን አራቂ፣ ውይይት አሳማሪ እና መዓዛ ብሩ ፕሮፌሰር እንድሪያስን በ60ዎቹ የፖለቲካ ውይይትና ክርክር የነበራቸውን ሚና እንደገለጸቻቸው ‹የሀሳብ መደምዳሚያ አራት ነጥብ› ናቸው፡፡ አቶ መስጠፌ በህዝብ ለህዝብ ትስስር ከፍተኛ እምነት አላቸው። የወያኔን ሀሰተኛ ትርክት መስበርም አስፈላጊ በመሆኑ ስርኣትን ከህዝብ የለየ አቋማቸውን ሲገልፁ ከወራት በፊት ይህን ብለው ነበር
:—
“ወደ አማራ ክልል እንሄዳለን፣ ለበርካታ አመታት ስር የሰደደ አሉታዊ ስብከቶች ስለነበሩ፣ የመጀመሪያ ልዑካን ብድናችንን በቅርቡ ወደ አማራ ክልል ልከን የህዝብ ለህዝብ ትስስርን እናጠናክራለን” በቃላቸውም መሰረት ሄደው አሳክተዋል።
የአቶ ሙስጠፌ የፖለቲካ አቋም
አቶ ሙስጠፌ ለሶማሌ ማህበረሰብ አጥብቀው ይከራከራሉ። ሆኖም አሁን ያለው ዘርን መሰረት ያደረገ አስተዳደራዊ መዋቅር ለኢትዮጵያም ለሶማሌም፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታም እንደማይበጅ ወጥና ፅኑ አቋም አላቸው። የማንነት ጥያቄዎችን ለመመለስ በዘር ላይ መከፋፈል ሳይሆን በዜግነት ላይ፣ በእኩልነት ላይ ስርአትን በመመስረት ለሁላችን የምትሆን ኢትዮጵያን በመገንባት የማንነትን ብቻ ሳይሆን በርካታ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን መመለስ እንችላለን ብለው አጥበቀው ያምናሉ።
በምሳሌም ሲያስረዱ:—
“ማንነት ላይ ያተኮረ ፖለቲካ ዞሮ-ዞሮ ወደ ግጭት ነው የሚያመራው። ከማንነት ፖለቲካ ወደ ፖለቲካዊ እሳቤ ቶሎ ብንሸጋገር፤ በዜግነት ላይ ያተኮረ የመብት ጥያቄዎች የሚመለሱባት አገር ብንመሰርት ደስ ይለኛል…”” በማለት ለSBS ራዲዮ ከወራት በፊት በሰጡት ቃለምልልስ ገልፀዋል።  ድህነት፣ ጎሰኝነት እና መሃይምነት ለህግ የበላይነትና ለዴሞክራሲ ደንቃራ መሆናቸውን በማህበራዊ ድረገፅ የሚከተለውን ሀሳባቸውን ገልፀው ነበር።
23 July 2018 The three threats to rule of law are ethnicity, ignorance, and poverty. In Ethiopia, we suffer from an overdose of all three. In such contexts, the choice is between tyranny which enforces rule of law at human cost. Or democracy which must then overcome ethnicity, ignorance, and poverty if rule of law is to prevail without tyranny.
የተለያዩ ወገኖች በተለይ እሳቸውን የማያውቁ በሳቸው አቋም ሴራ እና አላስፈላጊ ግምት ውስጥ ይገባሉ። ከላይ የየተገለፀውን ማለታቸውን የማያውቁ፣ ባህርዳር ከቀናት በፊት ይህን የቆየ አቋማቸውን ዳግም ማንፀባረቃቸውን እንግዳ ሆኖባቸዋል። ይህ ከንባብና በልምድ ያካበቱትን እውቀት ተጠቅመው ለሀገር የሚጠቅም ያሉት አቋም በርካታ ጊዜ ከሶማሊ ፀሃፍት ጋር በማህበራዊ ሚዲያ ሲነታረኩበት የነበረ እንጂ ዛሬ ድንገት የመጣ አለመሆኑን እሳቸውን የሚያውቅ የሚመሰክረው ነው።
አቶ ሙስጠፌ ዳጎስ ያለ ጥቅምን በመተው ከተባበሩት መንግስታት ስራ ወደ ፖለቲካ ሲመጡ ለሀገር ለመጥቀም ነው። አንዳንድ የዳር ተመልካችና ሰነፍ አክቲቪስቶች የሳቸውን ስም ለማጥፋት ቢጥሩም ፣ በተግባር እየሰሩለት ያለው ህዝባቸው ግን ከጎናቸው ይቆማል። ኢትዮጵያውያንም ከጎናቸው ይቆማሉ።
Filed in: Amharic