እምዬ ምኒልክ
ምስጋናው ግሸን
አፄ ምኒልክ በመጀመርያ ባስገነቡት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እየቀሩ ሲያስቸግሩ ለምን እንደሚቀሩ እየጠየቁ አጣሩ፡፡ የሚቀሩበትም ዋናው ምክንያት አስተማሪዎቹ በመማታታቸውና በመሳደባቸው መሆኑ ታወቀ፡፡ ይህን የተማሪዎቹን ሰበብ የሰሙት ምኒልክ የተማሪዎቹንም መብት ለማስጠበቅ ግብፃውያን አስተማሪዎቹን እንዲመክሩላቸው በኢትዮጵያ ተቀማጭ ለሆኑት ግብጻዊ ጳጳስ ደብዳቤ እንዲህ ጻፉላቸው፡፡
ይድረስ ከአቡነ ማቴዎስ
እነዚህ አስተማሪዎች የሚማሩትን ልጆች ሁሉ እየተማቱ ትምህርትም አልገባቸው አለ፡፡ ወጊዱ እያሉ ልጆች ከትምህርት ወጡ አሉ፡፡ ማስተማር ድንጋይ እንደ መውቀር ያህል ነው፡፡ ዓመት ሳያዩዋቸው ወጊዱ ብሎ መስደድ መቼ መልካም ነው፡፡ ደግሞስ የትምህርት ነገር ባገራቸው የምንሰማው 5 ዓመት 6 ዓመት ድረስ ነው አሉ፡፡ ይሄማ ቋንቋው ላገራችን ሰው እንግዳ ነው፡፡ እነሱስ የሰው ባህርይ እየቻሉ ማስተማር ነው እንጂ በትንሹ ነገር ሁሉ ለምን ይበሳጫሉ፡፡ ይህማ ሲሆን ጊዜ ምን የሚማር ሰው ይገኛል፡፡
እኛስ ብዙ ደሞዝ መስጠታችን ባገራችን ትምህርት እንዲገባ ብለን አይደለምን፡፡ ደግሞ እነዚህን ለትምህርት የገቡ ልጆች ሁሉ አስተማሪዎቹ አያውቋቸውም፡፡ ልጅ ዘውዴ ልጆቹንም፣ አባታቸውንም ያውቃልና እሱ ባልደረባ ሆኖ የእገሌ ልጅ ወሳለተ፣ የእገሌ ልጅ እንዲህ ሆነ እያለ ለእናንተም ለእኛም እያስታወቀን የወሳለተው ይቀጣል ብንል ባንድ ቦታ ሁለት ሹም አይሆንም ብለው ከለከሉ አሉ፡፡
አሁንም ይኸው ለማስተርጎም ብዮ አቶ ገብሬን አድርጊያለሁና ደግሞ ከሱ ጋር ጠብ እንዳያደርጉ ይምከሩዋቸው፡፡ ይህንን ወረቀት ግን ወደ እርስዎ መጻፌ እኔ ብነግራቸው ይደነግጣሉ ብዩ ነው፡፡ የኔን መስማት ሳያስተውቁ በፈሊጥ አድርገው እንዲነግሩዋቸው ይሁን፡፡
ታህሳስ 3 ቀን 1900 ዓ.ም
ምንጭ፡- አጤ ምኒልክ #ጳውሎስ ኞኞ
ያጤውን ደብዳቤ ይዘት ውስጠ መልዕክት መስመር በመስመር ብንፈትሸው ብዙ እንቁ ሀሳቦችን ይዟል፡፡ ለምሳሌ፡-
አንደኛ፡- “ማስተማር ድንጋይ እንደመውቀር ያህል ነው፡፡” የሚለው መማር (ማወቅ) የሚፈጠረው በድግግሞሽ መሆኑን፡፡ ትምህርት በድግግሞሽ የምናመጣው የባሕሪ ለውጥ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡
ሁለተኛ፡- “ቋንቋው ላገራችን ሰው እንግዳ ነው፡፡” ትምርትን የማስተላለፊያ መንገድ ምን ያህል ድርሻ እንዳለው ቀድመው ተገንዝበዋል፡፡ in modern concept “teaching methodology” በጣም ወሳኝ እንደሆነ፡፡
ሦስተኛ፡- “እነሱስ የሰው ባህርይ እየቻሉ ማስተማር ነው እንጂ” ይህች ዓረፍተ ነገር በዘመናዊው ሥርዓተ ትምህርት የተማሪን የኋላ ታሪክ (study the background to assure whether it is need based or not) ቀድሞ ማወቅ ለመማር ማስተማሩ ወሳኝ እንደሆነ የሚጡቁም ሀሳብ ነው፡፡
አራተኛ፡- “ይህማ ሲሆን ጊዜ ምን የሚማር ሰው ይገኛል፡፡” መምህሩ ከተማሪው ልቆ በስነ ምግባርም አርአያ ካልሆነ የምንጠብቀው ትምህርት የታለ ብለው የሚጠይቁ ይመስላል፡፡
አምስተኛ፡- “የኔን መስማት ሳያስተውቁ በፈሊጥ አድርገው እንዲነግሩዋቸው ይሁን፡፡” በዚህ ሀሳብ ላይ ቁልፍ የተግባቦት መርህ ተገልጧል፡፡ አንድ ሰው እንዲረዳልን የምንፈልገውን መልዕክት በጥሞና ሰምቶ እንዲወስደው ቅድሚያ ለማዳመጥ ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ ይጠይቃል ይኸንም ማላላት…ማዘጋጀት…መቀስቀስ (unfreezing) እንለዋለን፡፡ ከዛም መልዕክቱን የማስተላለፊያ ዘዴ መወሰን ነው፡፡ “በፈሊጥ” እንዳሉት
ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!
አፄ ምኒልክ ልደት ነሐሴ. 12