>
10:43 am - Wednesday November 30, 2022

የባለ አደራ ምክር ቤት የፓርላማውን ውሳኔ ተከትሎ የተሰጠ አስቸኳይ የአቋም መግለጫ!!!

የባለ አደራ ምክር ቤት የፓርላማውን ውሳኔ ተከትሎ የተሰጠ አስቸኳይ የአቋም መግለጫ!!!

ነሐሴ 02 2011 ዓም
የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ሐምሌ 30 በአካሄደው ስብሰባ በወቅታዊ የሀገራችንና የመዲናችን ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል። የባለአደራ ምክር ቤቱ  ኢህአዴግና አጋር ድርጅቶቹ ሙሉ ለሙሉ በተቆጣጠሩት ፓርላማ፣ ሐምሌ 24  2011 ዓም ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ ያጸደቋቸውን አዋጆች በዝርዝር ተመልክቷል።
ከእነዚህም ውስጥ፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች ምክር ቤት እና የአካባቢ ምርጫ እንዲራዘም መወሰኑን ፤ እንዲሁም  “ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታቸውን ለሚለቁ የሚከፈል ካሳ ሁኔታን ለመወሰን” የተዘጋጀ አዋጅን ተመልክቷል።
 የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት “ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታዎችን ለሚለቁ የሚከፈል ካሳ ሁኔታን ለመወሰን” የወጣው አዋጅ አደገኛና የዜጎችን መብት ሙሉ በሙሉ የሚገፍ መሆኑን በዝርዝር ተመልክቷል። በተለይም፣ ከመሬታቸው የሚፈናቀሉ ዜጎች የካሳ ቅሬታ ቢኖራቸው፣ ቅሬታ ማቅረብ የሚችሉት መሬታቸውን አስቀድመው ለቅቀው መሆን እንደሚገባው በአዋጁ መደንገጉ ፍትሐዊነት የጎደለው እንደሆነ  ለወትሮው ታማኝና ታዛዥ በሆኑ የፖርላማው አባላት ሳይቀር መገለፁ፣  የህጉን አደገኛነት ማሳያ ሆኖ  አግኝተነዋል።
በመሆኑም፣ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ከላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ በመወያየት የሚከተሉትን ውሳኔዎች  አስተላልፏል:-
አንደኛ:– አሁን ያለው የአዲስ አበባ መስተዳድር ምክር ቤትም ሆነ አቶ ታከለ ኡማን ጨምሮ ያለው አስፈጻሚ አካል የስራ ዘመኑን ከጨረሰ ሁለት ዓመት የሞላው በመሆኑ፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ ውክልና እንደሌለው የሚታወቅ ነው። በመሆኑም፣ ይህ ህገወጥ ምክር ቤትና መስተዳድር በአስቸኳይ ተሰናብቶ በምትኩ የህዝቡን ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ “ገለልተኛ  የሙያተኞች አስተዳደር” እንዲቋቋም፣
ሁለተኛ:– በአዲስ አበባ ሕዝብ ተሳትፎ በከተማ ፣ ክፍለ/ከተማና በወረዳ ደረጃ የሚቋቋመው “ገለልተኛ የሙያተኞች አስተዳደር፣” በከተማዋ የፖሊሲና ስትራቴጂያዊ አመራር የሚሰጥ ሳይሆን፣ በመደበኛ ዘርፋዊና የማዘጋጃ ቤት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ብቻ በማተኮር በተጠያቂነትና የኃላፊነት ስርዓት እንዲዋቀር
 ሦስተኛ:- ፓርላማው ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታዎችን ለሚለቁ የሚከፈል ካሳ ለመወሰን አዘጋጅቶ ያጸደቀው አዋጅ በአዲስ አበባ በሕዝብ የተመረጠ ምክር ቤት እስኪመሰረትና ሕዝብ እስኪወያይበት ድረስ ተግባራዊ እንዳይሆን፤ በከተማዋ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ አስተዳደር እስኪኖር ድረስ ዜጎችን ከመሬታቸው ማፈናቀልም ሆነ ባዶ መሬቶች ላይ ማንኛውም ዓይነት አዲስ ግንባታና መሬት ምሪት  እንዳይካሄድ በአፅንኦት እናሳስባለን።
 የአዲስ አበባ ባለአደራ  ምክር ቤት
 አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30 2011
Filed in: Amharic