>
5:13 pm - Tuesday April 18, 4305

ፍርድ ቤቱ በአ.ብ.ን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና በባልደራሱ ጸሀፊ ላይ ተጨማሪ 28 ቀናት አዘዘ!!! (ታምሩ ጽጌ)

ፍርድ ቤቱ በአ.ብ.ን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና በባልደራሱ ጸሀፊ ላይ ተጨማሪ 28 ቀናት አዘዘ!!!

ታምሩ ጽጌ

* በዓቃቤ ሕጉና በሌሎች ተጠርጣዎች ላይ የተፈቀደው ዋስትና ታገደ

* ሁሉም ይግባኝ ጠይቀዋል

በሽብር ተግባር ወንጀል ተጠርጥረው ታስረው የሚገኙት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና የሥራ አስፈጻሚ አባል፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) ጸሐፊ ላይ ፖሊስ የጠየቀው የ28 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ፡፡

ነሐሴ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርቦ የነበረው የአብን ሕዝብ ግንኙነትና ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ ላይ፣ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ እንደቀረውና ተጨማሪ ጊዜ እንደሚፈልግ ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት አስረድቷል፡፡ ፖሊስ የቀረውን ማስረጃ በተመለከተ እንደገለጸው፣ ያልተያዙ ግብረ አበሮችን መያዝ ይቀረዋል፡፡ የምስክሮች ቃል መቀበልና ለአሻራ ምርመራ (ፎረንሲክ) የሰጣቸውን ሰነዶች መሰብሰብና ሌሎች የምርመራ ሥራዎች እንደሚቀሩት አስረድቷል፡፡

አቶ ክርስቲያን በጠበቃው አማካይነት ባቀረበው ክርክር እንደተናገረው፣ ከታሰረ ጀምሮ ፖሊስ ቃሉን አልተቀበለውም፡፡ ቃሉን እንዲቀበሉት ቢጠይቅም አልተቀበሉትም፡፡ ሰነድና የሚያዙ ተጨማሪ ሰዎችን በሚመለከት ከእሱ ጋር የሚያገናኛቸው ነገር ስለሌለ፣ የዋስትና መብቱ እንዲከበርለት ጠይቋል፡፡ ማን ምን እንደሠራና ፖሊስ በማን ላይ ምን እንደሠራ ለይቶ እንዲያቀርብም ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ፖሊስ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ የሠራውን ምርመራ ለይቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ የተጠየቀውን 28 ቀናት በመፍቀድ ለጳጉሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

መልዕክት ሲለዋወጥ እንደነበርና በሽብር ተግባር እንደተጠረጠረ በፖሊስ የተገለጸበት፣ የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) ተብሎ የሚጠራው ጸሐፊና ጋዜጠኛ አቶ ኤልያስ ገብሩ ላይ ፖሊስ ያቀረበው ተጨማሪ የ28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፍርድ ቤት ነሐሴ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ፈቅዷል፡፡ አቶ ኤልያስ ሐምሌ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት ቀርቦ ክርክር አድርጎ ነበር፡፡ በጠበቃው አቶ ተማም አባቡልጉ አማካይነት ባቀረበው መከራከሪያ፣ የተጠረጠረው በሽብር ተግባር ወንጀል በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን የማየት ሥልጣን የለውም ብሏል፡፡

ፖሊስ እንደተናገረው የተጠረጠረበት የወንጀል ድርጊት ወንጀል አይደለም፡፡ ፖሊስ ተጠርጣሪን ማሰር ያለበት የጥርጣሬ ድርጊት መኖሩን ማስረዳት ሲችልና ድርጊቱም ሲኖር ቢሆንም ሊያስረዳ ስላልቻለ፣ እስሩ ሕገወጥ በመሆኑ ከእስር ሊፈታ እንደሚገባ ተከራክሯል፡፡ ፖሊስ መልዕክት ሲለዋወጥ እንደነበረና ከመረጃና መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ማስረጃ እየጠበቀ በመሆኑ፣ መረጃው እስከሚደርሰው የጠየቀው 28 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪው እንዳስረዳው የፈጸመው ድርጊት ካለ መነገር ያለበት ለፍርድ ቤት በመሆኑ እንዲያብራራለትም በመጠየቅ ተከራክሮ ነበር፡፡

ከአቶ ኤልያስ ጋር በእስር ላይ የሚገኙት የብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ጽጌ ባለቤት ወ/ሮ ደስታ አስፋን ጨምሮ 14 ተጠርጣሪዎች ሲሆኑ፣ በአራት ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመሥረቱ ከመገለጹ በስተቀር በቀሪዎቹ ላይ ፍርድ ቤቱ የተጠየቀውን 28 ቀናት ፈቅዷል፡፡

በሌላ በኩል በባህር ዳርና አዲስ አበባ ከተማ ግድያ ከተፈጸመባቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በነበሩት የወንጀል ምርመራ ሠራተኛ በነበረው ዋና ሳጅን ሞገስ ደጀንና ዓቃቤ ሕግ የወግሰው በቀለ፣ በተጠረጠሩበት ወንጀል ላይ ማስረጃ ሊቀርብባቸው ስላልቻለ እያዳንዳቸው በ5,000 ብር ዋስ እንዲለቀቁ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተሰጠው ትዕዛዝ ታግዷል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረበው የይግባኝ አቤቱታ እንደገለጸው፣ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በርካታ ምርመራዎችን አድርጓል፡፡ የምስክሮችን ቃል መቀበል፣ የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰብ፣ የተከሳሽነት ቃል መቀበል፣ ለኢንሳ ለምርመራ የተሰጡ የተጠርጣሪዎች የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን መሰብሰብ፣ ያልተያዙ ግብረ አበሮችን መያዝና የቴክኒክ ማስረጃዎችን መሰብሰብ እንደሚቀረው በማስረዳት ተጨማሪ የጠየቀው 28 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት መከልከሉ አግባብ አለመሆኑን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም የተሰጠው የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ አግባብ ባለመሆኑ እንዲፈቀድለት አመልክቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም የዓቃቤ ሕግን ጥያቄ ተቀብሎ በሰጠው ውሳኔ፣ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመሻር የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የከፍተኛው ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ ሰሚ ችሎት የይግባኝ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ባቀረቡት አቤቱታ እንዳስረዱት፣ ፖሊስ ግለሰቦችን የሚያስረው ሊያስጠረጥር የሚችል ምክንያት ሲኖረው ነው፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ራሱ ፖሊስ ምክንያት እንደሌለው መግለጹን፣ ዓቃቤ ሕግ የወግሰው በቀለ የተጠረጠረው የባልደራስ አባል ነው ተብሎ መሆኑን፣ አይደለም አንጂ ቢሆን እንኳን ወንጀል እንዳልሆነ፣ ዋና ሳጅን ሞገስም ፖሊስ በመሆኑ ብቻ ሚስጥር አሳልፎ ሰጥቷል በሚል ጥርጣሬ ብቻ ማስረጃና መረጃ ሳይቀርብበት ማሰር በራሱ ወንጀል መሆኑን በይግባኛቸው አመልክተዋል፡፡

ከፍተኛው ፍርድ ቤት ለዓቃቤ ሕግ የፈቀደው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ ከሚቅደውና ፖሊስም በሥር ፍርድ ቤት ከጠየቀው ቀናት በላይ በመሆኑ፣ ተገቢነት እንደሌለውና ሕግን የጣሰ አሠራር መሆኑን  አስረድተዋል፡፡ አዋጁ ከ28 ቀናት ያላነሰ ቢልም፣ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ግን 28 የሥራ ቀናት ብሎ መፍቀዱ፣ እሑድና ቅዳሜ ሲደመር ከ35 ቀናት በላይ ስለሚሆን አዋጁን የጣሰና ፍርድ ቤቱንም ትዝብት ላይ የሚጥል በመሆኑ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡

Filed in: Amharic