>
5:13 pm - Saturday April 19, 1732

"የምንሊክ የአደራ ቃል!!!" (ያሬድ ጥበቡ)

“የምንሊክ የአደራ ቃል!!!”

ያሬድ ጥበቡ

ባለቅኔው ፀጋዬ ገብረመድህን በምናብ 100 አመት ወደኋላ ተመልሶ፣ አጤ ምንሊክ ለልጅ ልጃቸው ኢያሱ ያቃመሱት ምክር ተረክ ነው ።
የዙሪያ ክብ ፍልስፍና ላይ የሚያጠነጥን እሳቤ ። ዛሬ የፀጋዬን የአደራ ቃል ከመስማቴ በፊት የሃበሻን ዙሪያ ክብ ፍልስፍና የነገረኝ የትውልዳችን ታላቅ ምሁር ኤልያስ ወልደማርያም ነበር ። በ1968 ዓም አራት ኪሎ የሳይንስ ቤተመፃህፍት ወስዶ አንዲት የሳይንስ አመጣጥና እድገት ታሪክ የምታወሳ ትንሽ መፅሃፍ ተዋሰልኝና ከሰጠኝ በኋላ፣ ስለሃበሻ የዙሪያ ክብ ፍልስፍና አጫወተኝ።
ትዝ ይለኛል፣ ከፊቱ በማይጠፋው ፈገግታ ተሞልቶ “አይህ ጎጇችን ክብ፣ ምግብ ማብሰያ ድስቶቻችንና መመገቢያ መሶቦቻችን ክብ፣ ሰአሊዎቻችን የሚስሏቸው ፊቶችና ዐይኖች ከብ ሆነው ሳለ፣ ኢትዮጵያችንን ከድህነት ሊመነጥቃት ይችል የነበረ አንድ ክብ ነገር ግን መፈልሰፍ አልተቻለንም፣ ምን ይመስልሃል?” አለኝ።
እንደርሱ የሳይንስ ተማሪ ባለመሆኔ የቴክኖሎጂ መልስ መስጠት እንደምቸገር ገብቶት፣ ወዲያው “አየህ፣ ጎማን ፈልስፈን ቢሆን ስንት ተአምር መስራት እንችል እንደነበር ይታወቅሃል? ጎማን ፈልስፈን በነበረ ለጉድጓድ ውሀ ማውጫ ፑሊ እንሰራ ነበር፣ ከአውድማ ወደ ጎተራ ፣ ከጎተራ ወደ ገበያ እህል የሚጭን ጋሪ እንሰራ ነበር፣ ጋሪ ስንሰራ ሰፋፊ መንገዶች መቀየስ እንማር ነበር ወዘተ ወዘተ ። ሆኖም ከአብያተ ክርስትያኖቻችን ጀምሮ ዙሪያችንን በዙሪያ ክብ ተከብበን፣ ግን ህይወታችንን ለመለወጥ ትችል የነበረችውን አንዲት ጎማ ለመፈልሰፍ ባለመቻላችን ይሄው በድህነት አዙሪት ውስጥ እንሸከረከራለን። ለምን ብለን መጠየቅ አለብን።
አስር ሺህ ጊዜ የማርክስን ወይም አፈናሲቭን የፍልስፍና መፃህፍት እንደ ዳዊት ብንደግም ጠብ የሚል ነገር የለም፣ የህዝባችንን ልቦና መለወጥ አይቻለንም ። ህዝባችን የታሰረበትን የፍልስፍና ገመድ ማወቅ አለብን። እርሱን ደግሞ ለማወቅ የፍልስፍናው መሰረት የተፃፈበትን የግእዝ ቋንቋ መማር አለብን። ምርጫ የለንም። የዚህ አስገዳጅነት  ስለተሰማኝ የግእዝ ትምህርት መውሰድ ጀምሬአለሁ፣ ሁላችንም ልንማረው ይገባል” አለኝ። ጃውሳውን ታላቅ ሰውም የቀይ ሽብር አመፅ በላው፣ እኛም በድህነት እንደተቆራመድን ቀጥለናል። አቤት! ስንት ዕድል አመለጠን?
Filed in: Amharic