>
5:14 pm - Monday April 20, 0595

“ኦዳ ቡልቱም” በሀረርጌ (Odaa Bultum in Hararghe (አፈንዲ ሙተቂ)

“ኦዳ ቡልቱም” በሀረርጌ (Odaa Bultum in Hararghe)
አፈንዲ ሙተቂ
አምስቱ ኦዳዎች
  በጥንት ዘመናት የኦሮሞ ህዝብ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ብሂል ነበረው። ይህም ዲሞክራሲያዊውን የገዳ ስርዓትን መሰረት ያደረገ እንደሆነ በልዩ ልዩ ምሁራን በተጠናቀሩ ጽሑፎች ተጠቅሷል። ሀገሩን የሚመራው መንግሥት የሚቋቋመውም “ጨፌ ገዳ” በተሰኘው ህዝባዊ ሸንጎ በሚመረጡት የመስተዳድር አባላት ነው። ይህ ሸንጎ ጉባኤውን የሚያካሄደው በየስምንት ዓመቱ ነው። ጉባኤው የሚካሄድበት ስፍራም በህግ የተወሰነ ነው። በዚህ ስፍራ ላይ መገኘት ካለባቸው ቋሚ ነገሮች መካከል የላቀ ስፍራ የሚሰጠው ደግሞ “ኦዳ” የተሰኘው ዛፍ ነው።
 “ኦዳ” በኦሮምኛ “የሾላ ዛፍ” ማለት ነው። የገዳ ሸንጎ ጉባኤውን የሚያካሄደው በዚህ ዛፍ ጥላ ስር ነው። “ኦዳ” ለጉባኤ ማካሄጃነት የተመረጠው በግርማ ሞገሱና በጥላው ስፋት ብቻ አይደለም። የኦሮሞ ሽማግሌዎች እንደሚናገሩት “ኦዳ”ን ከሌሎች ዛፎች ይበልጥ ተመራጭ ያደረገው ከክረምት እስከ በጋ ሳይደርቅ (ቅጠሉን ሳያራግፍ) መቆየት የሚችልና የህዝቡን ተስፋና የሀገሩን ልምላሜ የሚጠቁም ምልክት በመሆኑም ጭምር ነው። ታዲያ ሸንጎው በስምንት ዓመት አንዴ የሚሰበሰብ ቢሆንም “ኦዳ”ው ምን ጊዜም ቢሆን ተፈላጊ ነው። ምንጊዜም ቢሆን ዛፉ የኦሮሞ ህዝብ ልብና የአንድነት ምልክት ተደርጎ ነው የሚቆጠረው። ስለዚህ የህዝብ ጥበቃና እንክብካቤ ይደረግለታል። እረኞች ፍሬውን ከመብላት ውጪ ሌላ ጉዳት እንዲያደርሱበት አይፈቀድላቸውም። ዛፍ ቆራጮችም “ኦዳ”ን እንደሌላው ዛፍ መገንደስና የቤት መስሪያ ማድረግ አይችሉም።
*****
ከአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን በፊት በነበረው ጊዜ በሁሉም ክፍላተ ሀገር የሚኖረው የኦሮሞ ህዝብ በአንድ ማዕከል ስር ይተዳደር ነበር። ይህም ማዕከል በዛሬው የባሌ ክፍለ ሀገር፣ ደሎ አውራጃ ውስጥ ባለችው “መዳ ወላቡ” የተሰኘች ቀበሌ ይገኝ ነበር። እያደር የህዝቡ ብዛት ሲጨምርና በርካታ አስተዳደራዊ ችግሮች ሲፈጠሩ ከዋናው ማዕከል በተጨማሪ በየቀጣናው አንዳንድ የገዳ ማዕከል ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ። በዚህም መሰረት “ኦዳ ወላቡ” (ለደቡብ ኦሮሚያ የሚያገለግል)፣ “ኦዳ ሮባ” (ለደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ የሚያገለግል)፣ “ኦዳ ነቤ” (ለማዕከላዊና ሰሜን ኦሮሚያ የሚያገለግል)፣ “ኦዳ ቢሲል” (ለምዕራብ ኦሮሚያ የሚያገለግል) እና “ኦዳ ቡልቱም” (ለምስራቅ ኦሮሚያ የሚያገለግል) የተባሉ ማዕከላት ተመሰረቱ። “ኦዳ ወላቡ” ከደቡብ ቀጣና ማዕከልነቱ በተጨማሪ የህዝቡ ትውፊታዊ የአንድነተ ምልክት እንዲሆንም ተወሰነ። ህዝቡም በየዓመቱ በተመራጮቹ አማካኝነት የታማኝነት ቃሉን በወላቡ ለሚቀመጠውና “አባ ሙዳ” ለሚባለው መፈንሳዊ አባት እንዲገልጽ ታወጀ።
እንግዲህ የዚህ ወግ የትኩረት ነጥብ የሆነውና በምስራቅ ኦሮሚያ የሚገኘው የ“ኦዳ ቡልቱም” ህልውና የተበሰረው በዚህ መንገድ ነው። በዚህ የገዳ ማዕከል ሲካሄድ የነበረውን የገዳ ባህልና ልማድ የቻልኩትን ያህል አወጋችኋለሁ።
የኦዳ ቡልቱም ጉባኤ
የምስራቅ ኦሮሚያ የገዳ ማዕከል በሆነው የኦዳ ቡልቱም ትውፊት የሚተዳደሩት ሶስቱ የሀረርጌ ኦሮሞ ነገዶች (ኢቱ፣ አፍረን ቀሎ እና አኒያ) ናቸው። “ኦዳ ቡልቱም” የተሰኘው ማዕከል የሚገኘው በአሁኑ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ከበዴሳ ከተማ 20 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ነው። በዚህ የገዳ ማዕከል ከፍተኛ የስልጣን አካል የነበረው “ጨፌ ገዳ” የሚባለው የኦዳ ቡልቱም ሸንጎ ነው።
የኦዳ ቡልቱም ሸንጎ ጉባኤውን የሚያካሄድበት ቦታ “ሆረ ባዱ” ይባላል። ቃል በቃል “የአሬራ ሐይቅ” ማለት ነው። ስያሜው ለምን እንደወጣለት በትክክል ለማረጋገጥ ባልችልም “ጉባኤው በሚካሄድበት ጊዜ ለጉባኤተኞቹ የሚቀርበውን የማሽላ ቂጣና የአሬራ ግብዣ ለመዘከር ነው” የሚል መረጃ ደርሶኛል።
  በዚህ “ሆራ ባዱ” በተሰኘ ስፍራ ላይ አንድ አነስተኛ ሐይቅ አለ። ይህ ሐይቅ የከብቶች ውሃ ማጠጫ ወይም “ሆራ” ነው። ከሐይቁ ወዲህ እጅግ የለመለመ የጨፌ መስክ ይታያል። ከጨፌው ወዲህም ሰፊ መስክ አለ። በመስኩ ላይ ያለው ሳር አይታጨድም። ከብቶች ግን እየገቡ ይግጡታል። የመስኩም ሆነ የሀይቁ ይዞታ የጋራ በመሆኑ ማንኛውም ሰው ከብቱን ወደዚህ ስፍራ እያስገባ ማብላት ይችላል። ከሩቅ ወረዳዎችና አውራጃዎች እንኳ ከብቶቻቸውን እያመጡ በስፍራው የሚያግዱ ሰዎች አሉ። በተለይ በበጋ ወራት በርካታ ህዝብ ከብቶችን ለግጦሽ የሚያሰማራው ወደ “ሆራ ባዱ” ነው።
   የኦዳ ቡልቱም ጉባኤ በሆራ ባዱ የሚካሄደው በየስምንት ዓመቱ ነው። ሸንጎው የሚሰየምበት ቦታም እላይ ከተገለጸው ለምለም መስክ ፈንጠር ብሎ የሚገኝ ገላጣ ስፍራ ነው። በገላጣው ስፍራ መሀል ላይም በተጸውኦ ስሙ “ኦዳ ቡልቱም” የሚባለው የኦዳ ዛፍ አለ። “ኦዳ ቡልቱም” የሚለው ስያሜ ከምን እንደመነጨ የሚነገረው አፈ-ታሪክ ከቦታ ቦታ ይለያያል። አንዳንዶች “ቡልቱም የሚባል ሰው የመጀመሪያው አባ ገዳ ሆኖ ስለተመረጠ ነው” ይላሉ። በርካቶች እንደሚሉት ግን የህዝቡ መተዳደሪያና የወደፊት ብሩህ ተስፋ መንገድ ተደርጎ የሚቆጠረው የኦሮሞ ህዝብ ጥንታዊ ህገ-ደንብ የተደነገገበት ስፍራ መሆኑን ለማመልከት ሲባል ነው “ኦዳ ቡልቱም” (የማደሪያችን ኦዳ) የሚል መጠሪያ ያገኘው።
 የገዳ ጉባኤ በኦዳው ስር በሚካሄድበት ወቅት ጉባኤተኞቹ የሚቀመጡት ከጨፌው እየታጨደ በሚነጠፈው ቄጠማ ላይ ነው። እነዚህ ጉባኤተኞች ሌሊቱን የሚያሳልፉባቸው ስምንት ጎጆዎችም ከጨፌው ይሰራሉ። በየቀኑም ለምግባቸው የሚሆን በሬ ይታረድላቸዋል(ጉባኤው የሚካሄደው ለስምንት ቀናት ነው። ጎጆዎቹም ስምንት ናቸው። አንዳንድ ሰዎች ይህንን ቁጥር ከእድልና ከጥንቆላ ልማድ ጋር ያይዙታል። ይሁንና ስምንት ቁጥር ስምንቱን የገዳ ዓመታት ከመወከሉ ውጪ ከቁጥሩ ጋር የሚገናኝ አንዳች ድብቅ እምነት የለም)።
*****
      በኦዳ ቡልቱም የሚካሄደው ጉባኤ “ኮረ ገዳ” ወይንም “ያኢ ገዳ” ይባላል። ከላይ እንደገለጽኩትም ጉባኤውን የሚያካሄደው ሸንጎ “ጨፌ ገዳ” ተብሎ ይጠራል። የጉባኤው ተሳታፊዎች የሚመረጡት በጎሳና በንዑስ ጎሳ ደረጃ በሚቋቋመው መለስተኛ ሸንጎ አማካኝነት ነው። በነዚህ አነስተኛ ሸንጎዎች የሚመረጥ ሰው “ሉባ” ተብሎ ይጠራል። ለሉባ ምርጫ በእጩነት የሚቀርብ ሰው እድሜው በ40 እና በ48 ዓመታት መካከል ሊሆን ይገባል። በተጨማሪም የአካልም ሆነ የአዕምሮ ጉድለት የሌለበት፣ አስተዋይና በስነ-ምግባር የተመሰገነ ሰው መሆን አለበት።
ከያንዳንዱ ጎሳ “ሉባ” ሆኖ የተመረጠ ሰው ኦዳ ቡልቱም ከደረሰ በኋላ “አባ ጨፌ” ለሚባለው ጊዜያዊ የሸንጎ አስተባባሪ ያመለክታል። “አባ ጨፌ”ው ወደርሱ የሚመጡትን ሉባዎች ተቀብሎ ወደተመደበላቸው የመኝታና የመመገቢያ ቦታዎች ይመራቸዋል። ጉባኤው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስም መስተንግዶውን በበላይነት ይመራል። ለጉባኤው የሚወጣውን ወጪ ሁሉ በበላይነት ይቆጣጠራል። የአባ ጨፌ ትልቁ ስራ ግን የኦዳ ቡልቱምን “አባ ገዳ” ማስመረጥ ነው። ይህንንም የሚያደርገው ጉባኤው በሚጀመርበት ዕለት ነው። ይህ የምርጫ ስነ-ስርዓት የሚፈጸመው ከየጎሳው “ሉባ” ሆነው በጉባኤው የተገኙ ተሳታፊዎች “ጎሳችንን ይወክላል” ብለው በሚያቀርቧቸው እጩዎች መካከል በሚደረገው ፉክክር ነው። ጉባኤተኞቹ ከፍተኛ ድምጽ የሰጡት ሰው “አባ ገዳ” ሆኖ ይሰየማል።
“አባ ገዳ” ቃል በቃል “የገዳው አባት” ማለት ነው። በአውዳዊ ፍቺው “የዘመኑ አባት” እንደማለት ሊሆን ይችላል። በእርግጥም ከምርጫው ማግስት ጀምሮ ባሉት ስምንት ዓመታት (የአንድ ገዳ የስልጣን ዘመን) “አባ ገዳ” የህዝቡ አባት ተደርጎ ይቆጠራል። የመንግሥቱም ሆነ የጠቅላላው ሀገር ርዕሰ ብሔር በመሆን ያገለግላል። ህዝቡንም በልዩ ልዩ መድረኮች ላይ ይወክላል።
   ሌላው የ“አባ ገዳ” ትልቁ ስራ “ጨፌ ገዳ” የተባለው ሸንጎ የሚያካሄደውን የስምንት ቀናት ጉባኤ መምራት ነው። ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ይህ ጉባኤ በህብረተሰቡ ዘንድ እንደ ከፍተኛ የስልጣን አካል ይወሰዳል። በስምንቱ ዓመታት የተከናወኑ አበይት ድርጊቶች በዚህ ጉባኤ ይገመገማሉ። በዘመኑ ህዝቡን ሲያስተዳድሩ የነበሩ መሪዎችም በታላቅ ስነ-ስርዓት ይሸኛሉ። ወደፊት የሚተገበሩ እቅዶችም ይወጠናሉ። ህብረተሰቡ የሚተዳደርባቸውና “ሴራ” ተብለው የሚጠሩት ህጎችና ደንቦች ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ከሆነ ጉባኤው በሚያደርገው ውይይት እንዲሻሻሉ ይደረጋሉ። አስፈላጊ ሆነው የተገኙ ደንቦችና መመሪያዎችም እንደ አዲስ ይረቀቃሉ። በስተመጨረሻ ላይም ሸንጎው የወደፊቱን አስተዳዳሪዎች በመምረጥና የስልጣን ርክክብ በመፈጸም ጉባኤውን ያጠናቅቃል።
*****
  የ“ጨፌ ገዳ
” ሸንጎ በሚያደርገው የአስተዳዳሪዎች ምርጫ የሚመረጡት ስድስት ሰዎች ናቸው። እነዚህም ሰዎች ለስምንት ዓመታት ሀገሩንና ህዝቡን የሚያስተዳድሩ ናቸው። በመሆኑም የምርጫው መስፈርት የሉባ (የሸንጎ አባል) ከሚመረጥበት መመዘኛ ስርዓት ጠበቅ ይላል። በዚህ መሰረትም ለመስተዳድሩ መሪነት የሚመረጠው ሰው በጀግንነቱ የተመሰገነ፣ የንግግር ችሎታ ያለው፣ የህዝቡን ባህልና ወግ በደንብ የሚያውቅ፣ የህግ እውቀቱ የተመሰከረለት፣ በስነ ምግባሩና በሐቀኝነቱ የተመሰገነ፣ በአካሉም ሆነ በአእምሮው ጤነኛ የሆነ ወዘተ.. መሆን ይገባዋል።
እነዚህ ስድስት እጩዎች የሚጠቆሙበት አሰራር ከትውፊት አዋቂዎች የተነገረኝ በአንድ ወጥ ሁኔታ አይደለም። አንዳንዶች “የየጎሳው ተወካዮች አንዳንድ እጩ ይጠቁማሉ” ብለውኛል። ሌሎች ደግሞ “ያለፈው ዘመን አስተዳዳሪዎች ተተኪዎቻቸውን ይጠቁማሉ” የሚል መረጃ ሰጥተውኛል። እርግጠኛውን ነገር ወደፊት አጣርቼ ለመጻፍ እሞክራለሁ።
—–
ማስታወሻ፦ ይህ ወግ “ኡመተ ፈናን ኡመተ ቀሽቲ” በተሰኘው መጽሐፌ ውስጥ ተካትቶ ነበረ፡፡ በቅርቡ በጀመርኩት ፕሮጀክት ደግሞ የኦዳ ቡልቱም ትውፊት በደንብ ተጠንቶ ራሱን በቻለ መጽሐፍ በሰፊው ይቀርባል፡፡
Filed in: Amharic