>
5:16 pm - Monday May 23, 2214

በ ¨ኦሮሚያ ቤተ ክህነት¨የምትወረስ መንግሥት እግዚአብሔር የለችም!!! (ቀለመወርቅ ሚደቅሳ )

በ<ኦሮሚያ ቤተ ክህነት> የምትወረስ መንግሥት እግዚአብሔር የለችም!!!
ቀለመወርቅ ሚደቅሳ 
በኦሮሚያ “ቤተ ክህነት ምሥረታ” ላይ ስሳተፍ የነበርኩና በነአባ ገዳ ተሾመ አማካይነት ጥያቄያችንን ለቅ/ሲኖዶስ ካቀረብነው የስብስቡ አባል አንዱ የነበርኩ  ወንድማችሁ መምህር ቀለመወርቅ ሚደቅሳ ራሴን ከዚህ እና መሰል እንቅስቃሴዎች ማግለሌን አሳውቃልሁ። በሂደቱም የእኔ ያልኩትን እውነት ለምእመኑ እነሆ ብያለሁ
–‘፣፦፥
በዚህ አጀንዳ መጻፍ በስለት ላይ መራመድ ቢሆንም እንደገባንበት እንውጣ በሚል የቀረበ አስተያየት፡-
በኦሮሚያ ያለው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በተጨባጭ ካለው ችግር ጋር የተጣጣመ ባለመሆኑ አገልግሎቱን የሚያስተባብር ‹የኦሮሚያ ቤተ ክህነት› ጽ/ቤት የተሰኘ መዋቅር እንዲፈጠር ለብ/ወ/አቡነ ማትያስ የቀረበው በመጋቢት 2010 ዓ.ም ነበር፡፡ እርሳቸውም በሀሳቡ ደስተኛ መሆናቸው ገልጸው ከአባቶች ጋር መክሬበት አንድ ውሳኔ እናደርጋለን የሚል ምላሽ ሰጡ፡፡ በወቅቱ አንዳንድ ማኅበራትና ‹ወንድሞችና አባቶች› ጉዳዩ ለቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳ ሆኖ እንዳይቀርብ ዘመቻ ከፈቱበት፡፡ ተሳክቶላቸውም ሳይቀርብ ቀረ፡፡ በ2011ዱ የጥቅምት ሲኖዶስ ግን አጀንዳ ሆኖ ጥያቄ አቅራቢዎች ለብጹአን አባቶች ጉዳዩን የማስረዳት እድል አገኙ፡፡ ለዝርዝር ጥናት እንዲሁም ከመሪ ዕቅድ ጋር አብሮ መፍትሔ እንዲሰጠው ለአፈጻጸም ለብ/ዋና ሥራ አስኪያጁ ተመራ፡፡ በተለመደው ጉዳዮችን የማኮላሸት የቤተ ክህነቱ አካሄድ ጥያቄው አንድ ጋት ሳይራመድ ግንቦት ደረሰና ሥራ አስኪያጁም ተቀየሩ፣ ጎን ለጎን የጥያቄው ቃናና ጣዕምም ተለወጠ፡፡ ሌሎች ባለ ፍላጎቶችን ሳበ፡፡
የኦሮሚያ ቤተ ክህነት እንዲቋቋም የሚጠይቀውን እንቅስቃሴ ከሚመሩት ወንድሞችና አባቶች የተወሰኑት ‹የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ› በሚል ስያሜ ማኅተም አስቀርጸው ለመገናኛ ብዙኀን ዜና መግለጫ ለመስጠት መነሳታቸውን ተከትሎ ቋሚ ሲኖዶስ ለእንቅስቃሴው እውቅና እንዳልሰጠና መንግሥት እንዲገታው መግለጫ አውጥቷል፡፡ ይህ ‹የቋሚ ሲኖዶስ መግለጫ› ከቁብ ሳይቆጠር ‹የኦሮሚያ ቤተ ክንህት አደራጅ ኮሚቴ› ነሐሴ 26 መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም አስቸኳይ የምልዐተ ጉባኤ ስብሰባ በማድረግ ‹ጥያቄውን አግጃለሁ› ብሏል፡፡
‹የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ›፡-
#‹የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ› ከስያሜው ጀምሮ ስህተት ነው፡፡ ቀደም ሲል ለቅዱስ ሲኖዶስ የቀረበው ጥያቄ ቤተ ክህነቱ ይህንን መዋቅር ይዘርጋ የሚል እንጂ ራሳችን እናደራጀዋለን የሚል አልነበረም፡፡ ራስህን አደራጅ ብለህ ከሰየምክ ግን ለምን ወደ ቤተ ክህነት ትመጣለህ?
# መጋቢት 2010 ዓ.ም ለቅዱስ ፓትርያርኩ ቀርቦ ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ በተመራው የጥያቄ ሰነድና ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም በተሰጠው መግለጫ መካከል የይዘት ልዩነት አለ፡፡ ቀን ቆርጦ ምላሽ ካልተሰጠኝ የራሴን ውሳኔ አድርጋለሁ ማለትም ቀኖናዊ አይመስለኝም፡፡ በተባለው ቀነ ገደብ ምላሽ ባይገኝ ምን ሊደረግ ነው? በዚህ ምክንያት የሚነሳሳ ምእመን ቢኖር ቀነ ገደቡ ሲጠናቀቅ ምን ምላሽ ሊሰጠው ነው?
# ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር በነበረው ውይይት የይቅርታ ጉዳይ ሲነሳ የተሰጠው ምላሽ ስህተት ነው፡፡ በውይይቱ ፊት አውራሪ የነበሩት የሲኖዶሱ አባላት ይቅርታ ጠይቁ የሚለውን ሀሳብ ያቀረቡት ጥያቄውን ሙሉ ለሙሉ ለመግደል እንደሆነ ቢታወቅም በግትርነት ይቅርታ አልጠይቅም ከማለት ለተቀላቀሉት ሀሳቦችና ለአካሄድ ስህተቱ ይቅርታ መጠየቅ ይገባ ነበር፡፡ ከዚህ አልፎ ይቅርታ መጠየቅ ያለበት ሲኖዶሱ ነው የሚለው አቋም ኦሮቶዶክሳዊ አይደለም፡፡
# የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ከተገለጸ በኋላ ምልዐተ ጉባኤው ሳይሟላ፣ እነ አቡነ እገሌ ሳይገኙ፣ ወዘተ በማለት ውሳኔውን ላለመቀበል የተወሰደው አቋም ኦርቶዶክሳዊ አይደለም፡፡ ሲኖዶስ ሊሳሳት ይችላል፡፡ ስህተቱን የማረም ስልጣን ግን የራሱ የሲኖዶሱ እንጂ በራስ ሚዛን ውሳኔውን ላለመቀበል አቋም መውሰድ ትክክል አይደለም፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ፡- 
 ‹የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ› መግለጫ ልስጥ በማለት ለመገናኛ ብዙሃን ጥሪ ሲያቀርብ ጉዳዩን ቀኖናዊ እና አባታዊ በሆነ መንገድ ሊመለከተው ይገባ ነበር፡፡ ጥሪው እደተሰማ ጉዳዩ ቀደም ብሎ የሚታወቅ ስለነበረ ጥያቄ አቅራቢዎችን ጠርቶ ማናገር በስምምነት ካለቀ እሰየሁ፣ ካለሆነም አግባብነት ያለውን ቀኖናዊ ውሳኔ ማሳለፍ፡፡ ይህን መንገድ ስቶ መግለጫ መስጠቱ (የመግለጫው ይዘት በራሱ ችግር ያለበት ነው) ተቋሙን አሳንሶት ወደ ‹ኮሚቴው› ደረጃ ያወረደው ይመስለኛል፡፡
 # በ2010 ዓ.ም ቀርቦ የነበረውን ጥያቄ ከ‹የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ› መግለጫ ጋር ጨፍልቆ ለመግደል የተኬደበት መንገድም ትክክል አይደለም፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት 2011 ዓ.ም ባደረገው ምልዐተ ጉባኤ ቀደም ሲል የቀረበውን ጥያቄ አግባብነት አምኖበት ለብቻው ይመለስ ወይስ ከመሪ ዕቅድ ትግበራው ጋር አብሮ ሊመለስ ይገባል የሚለውን ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መምራቱ ይታወሳል፡፡ በዚህ አስቸኳይ ስብሰባ ወቅት ከ‹የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ› ጋር በተወያየበት ወቅት ቀደም ሲል የቀረበው ጥያቄ በአግባቡ እየታየ ለምን ወደዚህ ርምጃ ገባችሁ በማለት ጠይቋል፣ ለቀደመው ጥያቄ ፈጣን ምላሽ አለመሰጠቱም ስህተት መሆኑን አምኖበታል፡፡ በመጨረሻ ግን ‹ጥያቄውን አውግዘናል› የሚል መግለጫ ሰጥቷል፡፡ የቱን ጥያቄ ነው ያወገዘው? ‹የኮሚቴውን› ወይስ ራሱ አምኖበት ለጠቅላይ ቤተ ክህነት የመራውን?
# በአስቸኳይ ምልዐተ ጉባኤው መጨረሻ ቅዱስ ሲኖዶስ ‹ኮሚቴው› ጋር በስምምነት እንዳልተለያየ ሲታወቅ አንድ ነገር ጠብቄ ነበር፡፡ ቀኖናዊ ውሳኔ፡፡ በኮሚቴው መግለጫ ፊት ለፊት የነበሩት እና ምልዐተ ጉባኤው ጠርቶ ያናገራቸው ካህናትና መምህራን ናቸው፡፡ ስለዚህ አልታዘዝ ብለውኛል ካለ ክህነታቸውን መያዝ፣ ከአገልግሎት ማገድ የቅዱስ ሲኖዶስ ሙያ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያንን መብት ማስከበርም የቅዱስ ሲኖዶስ ኃላፊነት ቢሆንም ክስና ፍርድ ቤት ግን ሁለተኛ ጉዳይ መሆን ነበረበት፡፡
በአጠቃላይ ‹ኮሚቴው› እና ቅዱስ ሲኖዶስ በተጨባጭ በኦሮሚያ ያለውን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጠረጴዛ ላይ አድርገው በወያዩ ይግባቡ ነበር፡፡ ነገር ግን አንደኛው ወገን ‹ብዝሃነትን አስጠባቂ› ሌላኛው ደግሞ ‹ሀሳቡ ሀገር የከፋፈለውን ፌዴራሊዝም ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገባ ተከላካይ› ሆነው ስለተሟገቱ ሊግባቡ አልቻሉም፡፡ እንጂማ በ<ኦሮሚያ ቤተ ክህነት> በኩል ብቻ የምትወረስ ወይም በኦሮሚያ ቤተ ክህነት መቋቋም ምክንያት የምትከለከል መንግሥት እግዚአብሔር የለችም!!
ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አይሳሳትም የሚል ትምህርት የላትም፡፡ ነገር ግን የተሳሳተውን የማስተካከል ሥልጣን የቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ መሆኑን ታስተምራለች፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ማክበር ኦርቶዶክሳዊ አካሔድ ነው፡፡
Filed in: Amharic