ዶ/ር መስከረም ለቺሳ
+ + +
እስከሚገባኝ ድረስ፡ የመስከረም አራቱ ሰልፍ ዋናው ክፍል አልቀረም! ቅዳሴ ቀርቷል እንዴ?!
በመርሓ ግብሩ መሠረት፡ የሰልፉ የመጀመሪያው ክፍል፡ ኹሉም ምዕመን፡ ነጭ ለብሶ ቤተክርስቲያን ተገኝቶ የሚያስቀድስበት ነው፤ ከዚያ በኋላ ነው ወደየአደባባዩ በዝማሬ የሚወጣው፤ አይደለም እንዴ?! እና ከቅዳሴ በላይ ሰልፍ ከየት ይምጣ? ኦርቶዶክሳውያን በደንብ አስቡ እንጂ?!
ዋናውን ደብዳቤ፡ “ይግባኝ ለክርስቶስ” ብለን ለእናትና ልጁ ካቀረብን በኋላ፡ የቀረው እኮ፡ ውጪ ወጥተን፡ ግልባጩን ለሌሎች የምንልክበት ኺደት ነው እንጂ፡ ሌላ ትልቅ ነገር አይደለም። መፍትሔ ሰጪው የአገሪቱ ንጉሥ፡ ራሱ ክርስቶስ ነው።
ባለ ግልባጮቹማ፡ በየራሳቸው ችግር ግራ ገብቷቸው መፍትሔ የሚፈልጉ ናቸው እንጂ፡ መፍትሔ ሰጪ አይደሉም። ሲጀምር፡ አብዛኞቹ ጆሯቸው አይሰማም፤ በከንቱ ያደክሙን ይኾናል እንጂ!
እኔ “ሰልፉ ቀረ” የምለው፡ የዚያን ቀን፡ ቅዳሴ በሌሊት ተገኝተን፡ የመረረ አቤቱታ ወደ እግዚአብሔር ሳናቀርብ የቀረን እንደኾነ ነው። ቅዳሴውን እስከመጨረሻው ተካፍለን ወደየሠፈራችን በዝማሬ “ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማነው?” ብለን መመለስ ነው።
በቃ! ኢያሪኮ ይደረመሳል! ገዳማውያን አባቶችም እኮ ከዚያ በላይ አልጠየቁንም ነበር! በጳጉሜ ሲዞር የነበረውን መልእክት አላነበባችሁትም?
የውጪው ሰልፍ፡ ለሚድያ ፍጆታ ያኽል ብቻ ነው። ቢኖር ጥሩ ነው፤ ባይኖርም፡ “ባቄላ ቀረ ምን ቀለለ” እንደሚባለው ነው።
እመኑ! ገና ቅዳሴው ሲጀምር እግዚአብሔር ሥራውን ይጀምራል። በዐድዋ ጦርነት ጊዜ ይዘን የኼድነው የጥቅስ ታፔላዎችን አይደለም። ወይም፡ “ቅኝ ግዛት ይቁም!”… “የጣልያን መንግሥት ከኢትዮጵያ ላይ እጁን ያንሳ”… ምናምን የሚሉ መፈክሮችን አልነበረም። ይዘን የኼድነው ታቦት ነው–ልንቀድስበት። ቅዳሴው ሲጀምር ጦርነቱ ተጀመረ፥ ቅዳሴው ሲያበቃ በድል ተጠናቀቀ! ይኸው ነው።
ይልቅ፡ ያን ቀን፡ ስለግል ሕይወታችን የምንጸልየውን ቀነስ አድርገን፡ ስለአገርና ስለቤተክርስቲያን መጸለዩ ላይ እንበርታ!
በታቦቱ ፊት ተንበርከኩና፡ ሰይፈ ሥላሴን፥ ሰይፈ መለኮትን፥ አርጋኖኑን፥ ዳዊቱን ምዘዙ! ሳይውል ሳያድር፡ የሳጥናኤል ልጆች፡ ከውስጥም ከውጪ፡ ሲተረማመሱ ታዩአቸዋላችሁ።