>

ያፈጠጠው ችግራችን፤ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ለምን? (ብርሀኑ አድማሱ)

ያፈጠጠው ችግራችን፤ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ለምን?
ብርሀኑ አድማሱ
 
ኦሮሚያ ውስጥ ላሉ አማኞቻቸው ለጥናት ካሰራጬት  የመጠየቅ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ “ከሃይማኖትህና ከጎሣህ ማንን ታስቀድማለህ? ለምን?” የሚል ጥያቄ ነበረበት፡፡ እንደርሳቸው ገለጻ ከሆነ እድሚያቸው ከ35 ዐመት በታች የሆኑት በሙሉ የመለሱት መልስ “ጎሣዬን አስቀድማለሁ” የሚል ነበር፡፡ ከ35 ዐመት በላይ ካሉት ግን ሃይማኖታቸውን ያስቀደሙም ነበሩበት!!!
“የሞት ማሠሪያ ክህደትን በሃይማኖት ድል እንድንነሣው ያደረግህልን ለሚያምኑብህ ቅን ልቡናን የፈጠርህ ከሰው ወገን አማልክት ይባሉ ዘንድ፤ በመንፈስ የጠላትን ሃይል ሁሉ እንረግጥ ዘንድ የሰጠኸን፤ የማይፈታውን እንፈታ ዘንድ ከአባትህ ፍቅርን አደረግህልን፤ በመካከላችን ሆነህ አስታረቅኸን፡፡ አቤቱ የሚለምኑህን ስማቸው፣ አቤቱ የምንለምንህ እኛ አንከሰስ፤ በመከሰስ ጊዜ በጠላታችን ላይ እንኑርበት እንጂ፡፡ከጠላታችን ማታለል እንጠበቅ ዘንድ ዘወትር እንድንጸልይ አድርገን፡፡ የዘለዓለም ንጉሥ ሆይ ስማ፡፡ ባልቴቲቱን አረጋጋ፤ አባት እናት የሞቱባቸውን ልጆች ተቀበል፡፡ የታለሉትን በቸርነትህ አንጻ፤ ሰነፎችንም አዋቂ አድርጋቸው፤ የጠፉትን መልስ፣ በግዞት ያሉትንም አድናቸው፤ ለሁላችን መጠጊያ ሁነን፡፡ አቤቱ አምላካችን ክቡር መንግሥት ያንተ ነውና፤ አሜን፡፡” /ከጸሎተ ኪዳን/
የክልል ቤተ ክህነት ለመጀመሪያ ጊዜ 
በአቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ፡፡ ፖለቲካዊ ተልዕኮ የተሰጣቸው የትግራይ ተወላጅ መነኮሳት በትግራይ ክልል ያሉ ጳጳሳት ለብቻቸው የራሳቸው ስብሰባ የሚያደርጉበት ጉባኤ እንዲኖራቸው ይገባል፡፡ በዚያውም የራሳቸው አስተዳደር ለብቻ ይኑራቸው ሲሉ ለቅዱስነታቸው ያቀርባሉ፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስም እኔ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ነኝ፣ እንደገና ሔጄ ክልል አልመራም ይላሉ፡፡ ግዴየለም እርስዎ ዋናውን ይዘው መቀሌ ላይ አንድ ሜትሮፖሊታን ጳጳስ ይሹሙሉንና በዚያ የትግራዩ ሲኖዶስ አካል የትግራይ ጳጳሳት ጉባኤ ይመራል ይሉና ወትውተው አጀንዳውን እንዲቀበሉ ያደርጋሉ፡፡ ከዚያም በአስተባባሪዎቹ በኩል ጥያቄው ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡ በወቅቱ የቋሚ ሲኖዶስ አባል ከነበሩት አንዱ አቡነ ገብርኤል ሜትሮፖሊታን ማለት የከተማ ጳጳስ ማለት ነው፡፡ መዓርጉም ሀገረ ስብከት ካለው ሊቀ ጳጳስ ያነሰ ነው፡፡ ሜትሮፖሊስ ከተማ ማለት ስለሆነ ሜትሮፖሊታንም የከተማ ጳጳስ ማለት ነው፡፡ በፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ ላይ ያለውን ሜትሮፖሊታኑንም ያክብሩት አይናቁት (በሥልጣን ያነሰ ነው ብለው) የሚለውን ጠቅሰው ይህ ሊሆን የማይችል ሞኝነት መሆኑን ያቀርባሉ፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ ሲጀመርም ፖለቲካዊ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ አንጂ ሃይማኖትንና ቀኖናን መሠረት ያደረገ አልነበረም፡፡ አቅራቢዎቹም የተሰጣቸውን አጀንዳ ለማስፈጸም ከመትጋት ባለፈ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንጻር ቆም ብለው ሊያዩት ወይ አልሞከሩም፤ ወይም በቂ እውቀት አልነበራቸውም ማለት ነው፡፡ ቅዱስነታቸው አቡነ ጳውሎስም ድሮውንም ያልወደዱትና ያልታያቸው ነገር ስለነበር አራክሰው እንዳይነሣ አድርገው በዚያው ይቀብሩታል፡፡ ይህን ታሪክ የነገሩኝ በወቅቱ ፍትሐ ነገሥቱን መሠረት አድርገው አቡነ ገብርኤል ያወያዩአቸው አንድ ወጣት የቤተ ክህነቱ ሊቅ ናቸው ፡፡
በርግጥ ይህ ነገር በትግራይ የተነሣው እንዲህ በመካከል ብቻ አልነበረም፡፡ ኢህአዴግ እንደገባም መቀሌ ላይ ካህናቱንና ሰንበት ተማሪዎችን ሰብስቦ ከዚያ ጥያቄ አድርጎ ሊያዋቅረው አስቦ እንደነበር በወቅቱ ከስብሰባው ከተሳተፉት ከአንዱ ሰምቻለሁ፡፡ ነገር ግን በክርስትናው የማያወላዳው የትግራይ ካህንና ሰንበት ተማሪ እዚያው ነገሩን አራግፎ ጥሎባቸው ይኖራል፡፡ ዶክተር አረጋዊ በርሔ በሦስተኛ ዲግሪ የማሟያ ጥናታቸው ላይ እንደሚሉት ደግሞ ቀደም ብሎ የታሰበበት የፖለቲካ አጀንዳ ነበር፡፡ የትግራይ ካህናትና ሰንበት ተማሪዎች ግን ከዚያው ከከተማቸው ሳይስወጡ አጀንዳውን ቀበሩባቸው፡፡ በኋላም አዲስ አበባ ላይ ተልእኮ በሚሰጧቸው መነኮሳትና ካህናት ቢያመጡትም አቡነ ጳውሎስ አላቀረብክም እንዳይባሉ ብቻ አጀንዳውን አቅርበው አሁንም እንዳያንሠራራ አድርገው ቀብረውት ሔዱ፡፡ ትግራይ ክርስትናውን ለፓርቲው ክልላዊ ሥልጣን ገባር ሊያደርገው አይችልምና፡፡ በርግጥ ሰሚ ባያገኙም ዛሬም ለማራገብ የሚሞክሩ ጥቂት የዋሐን እንዳሉ ታዝቢያለሁ፡፡
ይህ ከተዘጋ በኋላ ደግሞ ስልቱን ከእነርሱ የወሰዱ የኦሮሞ ልሂቃን አሁንም ቀስ አድርገው ወደ እኛው አገልጋዮች አስገቡት፡፡ ተንኮሉ ያልገባቸውና በዚያ ላለው ምእመን ቅንዓት ያላቸውም አሁንም ቀኖናውና ሃይማኖታዊ አካሔዱን ሳያጠኑ እንደማንኛውም የፖለቲካ ጥያቄ ይዘው ተነሡ፡፡ በዚህ ተቃውሞ ሲገጥማቸው ደግሞ ነገሩን ጥያቄውን ካለመረዳት ወይም ከሌላ መሰላቸው፡፡
ኦሮሚያ ውስጥ ባለችው ቤተ ክርስቲያን ችግር መኖሩ የማይታበል ነው፡፡ ብዙዎቻን ቅር ያሰኘንም ችግሩን ለመቀነስ ለምን ተጠየቀ የሚለው አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡ አንደኛ ልክ በሌሎቹ ክልሎች ችግሩ የሌለና ችግሩ ኦሮሚያ ውስጥ ለዚያውም ሆነ ተብሎ የተተወ እንዲመስል ተደርጎ በመቅረቡ ነው፡፡ ሁለተኛም ብዙ የዋሐንን ይዞ በጥቂት ተንኮለኞች ፖለቲካዊ ግብን ለማሳካት ይዞ መነሣቱ ነው፡፡ ሦስተኛ ደግሞ ችግሩን ሳይሆን መፍትሔ ይሆናል ተብሎ የታሰበውን የመብት ጥያቄ አድርጎ ማቅረቡ ነበር፡፡ ጥያቄ የሚየቀርብ አካል ጥያቄው ወይም ገጠመን ያለውን ችግር አቅርቦ ከረደመጠ በኋላ የመፍትሔ ጥናት ወይም አቅጣጫ አሳይ ካልተባለ በቀር መፍትሔ ራሱ አይሰጥም፣ የመብት ጥያቄማ ሊያደርገውም አይታሰብም፡፡
የሆነው ሆኖ ከኮሚቴው አባላት ብዙዎቹ እነርሱ የማያውቁት እንቅስቃሴ መሆኑን ሲረዱ ራሳቸውን ማግለላቸው እውነተኛነታቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ በተለይ ቀድሞ የወጣው መምህር ቀለመወርቅ ሚደቅሳ መውጣቱ ብቻ ሳይሆን ካለው የነገረ ቤተ ክርስቲያን ዕውቀቱ አንጻር ኦርቶዶክሳዊ ግንዛቤውን አሳይቶና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አክብሮ ማቆሙ ወደፊት በታሪክ ሁሉ ሲያስመሰግነው እንደሚኖር ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በርግጥም እንደ እርሱ ካለ ሰው የሚጠበቀውም ይኸው ነበር፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች ኦርቶዶክሳዊነታቸውን አሳይተው በሌሎች የሚደረገውን ተንኮሉንም ተረድተው ወደ ኋላ ካሉ እኛ ሁላችን ደግሞ ጥያቄያቸውን ኦርቶዶክሳዊ በሆነ መንገድ ማንሣትና በሥርዓታችን መሠረት መፍትሔ እንዲያገኝ መጣር ሃይማኖታዊ ግዴታችን ነው፡፡
በነገራችን ላይ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት አንኳን በአንድ ሲኖዶስ የመንፈሳዊ አስተዳደር አንደነት ያለን ቀርቶ በአስተዳደሩ አንድነት ከሌለን ነገር ግን ሃይማኖታዊ አንድነት ባለን በእነ ሕንድ፣ ግብጽ፣ አርመን፣ ሶርያና ኤርትራ ላይ ሁሉ እውነተኛ አስተያየቶችን የመስጠት መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም አለብን፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ እንዳለው የሲኖዶስም ውሳኔ ሃይማኖታዊ ሥርዓታዊ እስከሆነ ድረስ የትም የተወሰነው የሁሉም ነው፡፡ ምክንያቱም ሃይማኖት ብሔራዊ ተቋም ቢኖረውም በአስተዳደሩ ምክንያት ልክ እንደ ድርጅት ብሔራዊነት የሚያጥረው አሠራር ብቻ አይደለምና፡፡ ስለዚህ ፖለቲካዊ አጀንዳ ሊያደርጉት እንደሚፈልጉት አንዳንድ ያልገባቸው ሰዎች ኦሮሚያ ውስጥ ያለው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጉዳይ የኦሮሞዎች ብቻ አይደለም፡፡ ልክ እንደዚሁ ትግራይ ያለውም ሆነ አማራ፣ ደቡብም ይሁን አፋር ሶማሌ እዚያ ያሉ ሰዎች ጉዳይ ብቻ አድርጎ ማሰብ በራሱ ከዐሥራ ሁለቱ የኒቅያ ሃይማኖታዊ ዶክትሪኖች አንዱ የሆነውን የቤተ ክርስቲያንን አንድነት መካድ ነው፡፡
ኦሮሚያ ውስጥ ምን ሊደረግ ይችላል
የኦሮሚያ ቤተ ክህነት የሚለው የማይደረግ ብቻ ሳይሆን አስቂኝም ጭምር ነው፡፡ ከላይ በትግራዩ ሁኔታ ሀገረ ስብከት ያላቸውን ሊቃነ ጳጳሳት በሜትሮፖሊታን ማስተዳደር፣ መምራትና መሰብሰብ የሚቻል እንደመሰላቸው ዓይነት ያለ ያላዋቂ ጥያቄ ነው፡፡ ምንም ሊሸራረፉ ከማይችሉት የኦርቶዶክስ ቀኖናዊ ሥርዓቶች ውስጥ አንዱ በሊቀ ጳጳስ ላይ ከፓትርያርክና ከሲኖዶስ ውጭ በላዩ ላይ ሊሰየም የሚችል ምንም ዓይነት ቀኖናዊ ሥልጣን ያለው ሌላ አካል በምንም መንገድ ሊኖር አይችልም፡፡ በሥልጣነ ክህነት ደረጃ በኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ራሱ በእኩዮች መካከል ያለ ቀዳሚ አባት እንጂ እንደ ካቶሊክ ቀዳሚነት (Primacy) የለውም፡፡ ፓትርያርኩ እንኳ እንዲህ በሆነበት ሀገረ ስብከት ባላቸው ሊቃነ ጳጳሳት ላይ እንዲህ ያለ ከኦርተዶክሳዊነት ጋር የተጋጨ መዋቅር መፍትሔ አድርጎ ማቅረብ በምንም መንገድ ተገቢ ሊሆን አይችልም፡፡
ሌላው ቀርቶ በየሀገረ ስብከቱ ያሉት ሊቃነ ጳጳሳትን የሚያግዝ ተጨማሪ ረዳት ቢያስፈልግ በሥሩ ልክ እንደ ሜትሮፖሊታን ያሉ ጳጳሳት ያለሀገረ ስብከት ማለትም አጠቃላይ ጉዳዮች ላይ ረዳት የሚሆኑ ጳጳሳት (General Bishops) ይሾማሉ እንጂ በሀገረ ስብከት ሥር ሌላ ሀገረ ስብከት አይቋቋምም፤ አይደለም በበላዩ ላይ፡፡ የተቃወምነው ስለዚህም ጭምር መሆኑ ግንዘቤ መወሰድ አለበት፡፡ ከኮሚቴዎቹ አንዳንዶቹ በሚዲያ የተናገሩትን አስመልክቶ ለመመለስ አንድ መጽሐፍም ስለማይበቃው አልገባበትም፡፡ ምክንያቱም ምን አልባት ከቀናነት ሊሆን ቢችልም ብዙ ክህደት ያለበት ያለማወቅ ንግግር ስለሚበዛው እርሱን ማንሳት አስፈላጊ መስሎ አይሰማኝምና እርሱን ትቼ መፍትሔ ወደምለው ከማለፌ በፊት ኮሚቴዎቹም ሆኑ ሌሎቹ ከሚያነሷቸው ተጨማሪ አንድ ችግር ላስቀድም፡፡
ያፈጠጠው ኦሮሚያ ውስጥ ያለው የኦርቶዶክስ ችግር
ከሁለት ዐመት በፊት አሜሪካ ለአገልግሎት በሔድኩበት ወቅት በኦርቶዶክሳዊነቱ ርቱዕ የሆነ አንድ ኦሮሞ ወንድሜ አንድ የቪዲዮ ቁራጭ አሳይቶኝ ነበር፡፡ በዚያ ቪዲዮ የሚናገረው ሰው ኦሮሚያን ከኢትዮጵያ መገንጠል የሚፈልግ በውጭ ሀገር የሚኖር የእስልምና እምነት ተከታይ ኦሮሞ ነው፡፡ ኦሮሙኛውን ስለማልሰማ ትርጉሙን የነገረኝ ያ ወንድም ነበር፡፡ ያ ተነጋሪ የሚለው ኦሮሚያን ለመገንጠል ከእስላም የሚያስቸግር የለም፤ አስቸጋሪዎቹ ኦርቶዶክሶቹ ናቸው የሚልና በዚህ መሠረት ሰፊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መኖሩን የሚያሳይ ነገር ነበር፡፡ በተመሳሳይ ጉዳይ ለመመርመር ከአንድ ወንድሜ ጋር በእንግሊዝኛ የተጻፉ የመካነ ድሮችን በጉግል አስሰን ስንመለከት ያገኘነውም ፖለቲከኞቹ ኦርቶዶክስ ላይ እየሠሩት ያለው የፖለቲካ ሥራ ውጤታማ መሆኑንና የቤት ስራቸውን መጨረሳቸውን የሚያሳይ ነበር፡፡ በሰሞኑም የዚሁ የኦሮሚያ ፖለቲካ አቀንቃኞች ዋና ዋናዎቹ እነ አቶ በቀለ ገርባ፣ ግርማ ጉተማ እና ጃዋር መሐመድ የሚናገሩት ሁሉ ለዚሁ አስረጂ ነው፡፡ በተለይ ጃዋር ሰሞኑን ሰልፎቹን መነሻ አድርጎ በአፋን ኦሮሞ ጽፎት በአማርኛ ተተርጉሞ ያየሁት አጀንዳውን ገልብጦ ፖለቲካዊ ለማድረግ ያቀረበበት መንገድ ለተከታዮቹ በቂ ሊሆን ቢችልም አእምሮ ላለው ሁሉ ግን አሳዛኝ ተንኮል የተመላ ነው፡፡ በቀጥታ ሃይማኖታዊ ቢያደርገው ሊጠረጠር ስለሚችል የኦሮሚያን ፖለቲካዊ አንድነት ሃይማኖታዊ አንድነት በሚል ለማፍረስ እየጣሩ ነው ሲል ከስሷል፡፡ የእርሱ ጥረት የጎሣ አንድነት ከሃይማኖት አንድነት ይበልጣል ብሎ በሃይማኖት  አንድ የሆንነውን ለመለያየት ቆርጦ መነሣቱን ነግሮናል፡፡ በራሱ ሃይማኖት ይቻል ይሆናል፤ በክርስትና ግን ይህ ፍጹም ክህደት ነው፡፡
በኦሮሚያ ቤተ ክርስቲያናችን ለማዳከም የሚደረገው ፖለቲካዊ ሴራ ግን ይህ ብቻም አይደለም፡፡ አሁን ባለው የእነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት በሥልጣን ወደ ላይ ከፍ ያሉ ኦርቶዶክሳውያን ባለሥልጣናት ያለባቸው ጫናም ከፍተኛ እንደሆነ ይሰማል፡፡ አንዳንዶቹ  ኦርቶዶክሶች አሁን ከእነ ዐቢይና ለማ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ከበላይ ጓዶቻቸው ፓሰተሮች ይመደብላቸውና በፍጥነት ወደ ፕሮቴስታንት እንዲቀየሩ ይወተወታሉ፡፡ እሺ የማይሉ ከሆነ በዘዴ ወደታች ገፋ ይደረጋሉ፡፡ ይሉኝታው የያዛቸው ደግሞ ለይስሙላ ይሁን ለእውነት ባይታወቅም ተለውጠናል ብለው ነግረው ጫናው እንደቀነሰላቸው ይወራል፡፡ ይህ ለማጣራትና ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ቢሆንም እኔ የሰማሁት ወደታች የተገፋ ሰው ለጓደኛው ከነገረው ነው፡፡ በጠቅላይ ሚንስትራችን ቡራኬ የተሰጠውና  “መልካም ወጣት” በሚል ስም በእነ ፓስተር ዮናታን መሪነት የሚካሄደውና የጠቅላያችን ቡራኬ ዋስትና አድርገው የዞን መስተዳድሮች ሕግ ተላልፈው ለትምህርት ተቋማት ሳይቀር እየጻፉለት ያለው እንቅስቃሴ ደግሞ ይፋዊ ካልሆኑ ነገር ግን መንግሥት ስፖንሰር ከሚያደርጋቸው ኦርቶዶክስን የማዳከሚያ ፕሮጄክቶች ምንአልባትም አንደኛው ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ኦሮሚያ ውስጥ ኦሮቶዶክስ ያለችበት ያፈጠጠ ችግር በመሠረቱ ፖለቲካን ተገን አድርጎ ከተቻለ የማጥፋት ካለበለዚያም የማዳከም ጽኑ ፈተና መሆኑን መደበቅ አይቻልም ፡፡
እንዲህ ዐይነቱ በሥልጣን የመግፋትና የማስገደድ በደቡብ ኢትዮጵያም መኖሩን ገና የዛሬ ሃያ ዐመት ወላይታ ለአገልግሎት በሔድኩ ጊዜ በወቅቱ የዞኑ አስተዳዳሪ ከነበረውና የንጉሥ ጦና የልጅ ልጅ ከነበረው የአዲስ አበባ ዩኒበርስቲው ምሩቅ ሰምቼ ነበር፡፡ ያ ወንድም አሁን በሕይወት የለም፡፡ ስለአሟሟቱ የሰማሁት እውነት ከሆነም ከዚሁ የመገፋት ሒደት ጋር ግንኙነት ሳይኖረው አይቀርም፡፡
ጎሣየ ከሃይማኖቴ ይበልጣል
በኦሮሚያ ያለውን ሁኔታ የሚያከፋው ግን ሆነ ተብሎ የሚሠራው ሥራ ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ ከዐራት ወራት በፊት አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ የውጭ ሀገር ድርጅት በሀገሪቱ ያለውን ጎሳን መሠረት ያደረገ ቅጥ ያጣ ተቃርኖ ለማብረድ የሃይማኖት አስተማሪዎች ሚና ትልቅ ነው ብሎ በማመን ከሁሉም ሃይማኖቶች ጠርቶ አወያይቶ ነበር፡፡ በወቅቱ ከተጠሩት አንዱ ሆኜ ተገኝቼ ነበር፡፡ በውይይቱ መካከል ከወንጌላውያን የመጡ አንድ ተወካይ ያቀረቡትን ነገር አልረሳውም፡፡ እርሳቸው እንዳሉት ከሆነ ኦሮሚያ ውስጥ ላሉ አማኞቻቸው ለጥናት ካሰራጬት  የመጠየቅ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ “ከሃይማኖትህና ከጎሣህ ማንን ታስቀድማለህ? ለምን?” የሚል ጥያቄ ነበረበት፡፡ እንደርሳቸው ገለጻ ከሆነ እድሚያቸው ከ35 ዐመት በታች የሆኑት በሙሉ የመለሱት መልስ ጎሣዬን አስቀድማለሁ የሚል ነበር፡፡ ከ35 ዐመት በላይ ካሉት ግን ሃይማኖታቸውን ያስቀደሙም ነበሩበት፡፡ አስደናቂው ነገር ግን ለምን ለሚለው ጥያቄ የመለሱት መልስ ነበር፡፡ አሁንም እንደ እርሳቸው ገለጻ ከሆነ መላሾቹ ከሃማኖት ይልቅ ጎሣን እንዲመርጡ ያስቻላቸው መጽሐፍ ቅዱስ የጎሣ እንቅስቃሴን እንደማይቃወም እንዲያውም እነ ሙሴና ኢያሱ ረሳቸው የጎሳ መሪዎች መሆናቸውን የሚያሳይ በኦሮሙኛ ቋንቋ የተጻፈ መጽሐፍ ማንበባቸውን በመልሳቸው ላይ ማካተታቸው ነበር፡፡ ይህ የሚያሳየው  በክርስትና ያለውን ሃይማኖታዊ ዶክትሪን እዛው ክርስቲያን እንደሆኑ አስጥለው እነርሱ የሚፈልጉትን የፖለቲካ ትግል ለማሳካት ፖለቲከኞቹ ምን ያህል ርቀት እንደተጓዙ የሚጠቁም ይመስለኛል፡፡ የእነአቶ በቀለ ገርባ  ሰሞኑን በሚዲያ በሀገር ግንባታና መፍረስ ውስጥ ቤተ ክርስቲያንን ምን አገባት የሚለው የብስጭት ፉከራም ፕሮጄክቱ ሊከሽፍ ነው ከሚል ሥጋት የተወለደ ይመስላል፡፡
ይህ ሁሉ ባለበት ኦሮሚያ ውስጥ ያለችውን ቤተ ክርስቲያን ለማጠናከርና ክርስቲያኖች ከጊዜያዊ ፖለቲካዊ ውዥንብር ተርፈው ኦርቶዶክሳዊነታቸውን አጽንተው ጠንካራ ኦሮሞ ኦርቶዶክሶችን ለማየት ቤተ ክርስቲያን ምን ማድረግ ይጠበቅባታል የሚለውን ከአንድ ድንቅ ኦሮሞ ሊቅ ታሪክና ከደጆችሽ አይዘጉ ማኅበር አግልግሎት ልምድ ጋር በማቀናጀት እመለስበታለሁ፡፡ ሌሎቹን ባለፈው ጽሑፍ ላይ ያነሣኋቸውን ደግሞ ከእነዚህ ጽሑፎች በኋላ አስከትላለሁ፡፡ እናስተውል፣ እንመርምር፣ እንጸልይም፡፡ የእውነት አምላክ እግዚአብሔር ልጆቹን አጽናኝ አረጋጊ በሆነው መንፈስ ቅዱስ በእውነትና ለእውነት ብቻ ያጽናልን፤ አሜን፡፡
Filed in: Amharic