>

አማራ ዜጋ፣ ኦሮሞ ጎሣ (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም)

አማራ ዜጋ፣ ኦሮሞ ጎሣ

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም
መስከረም 2012

የኢትዮጵያ ችግር ምንጩ ብዙ ነው፤ አንዱን የተረሳና መሠረታዊ ምንጭ አእምሮው በጎሠኛነት ከመንሸዋረሩ በፊት መጀመሪያ አንሥቶት የነበረው ተኮላ ሀጎስ ነው፤ ተኮላ ከወያኔ የተለየበት ዋና ምክንያት የወያኔ ስብስብ የመሳፍንትና የመኳንንት ልጆች በመሆናቸው የዴሞክራሲ መሥራቾች ሊሆኑ አይችሉም በማለት ይመስላል፤ የነገሥታቱ፣ የመሳፍንቱና የመኳንንቱ ልጆች ተራማጆች ነን ቢሉም፣ የማርክስ ተከታዮች ኮሚዩኒስቶች ነን ቢሉም የአባቶቻቸውን ምርቃትም ይሁን እርግማን የተሸክሙ ናቸው፤ ይህንን ሸክም የሚያወርዱበት አእምሮም ሆነ የማሰብ ጊዜው አልነበራቸውም፤ በነገሥታቱ፣ በመሳፍንቱና በመኳንንቱ ዘመን ሕዝብ በጥሩ ቤት ውስጥ እንዳይኖር፣ ያመረተውን እንዳይበላና የጠመቀውን እንዳይጠጣ፣ የፈተለውን እንዳይለብስ፣ በትእዛዝ ደሀ ሆኖ ይኖር ነበር፤ የዘመናችን ነገሥታት፣ መሳፍንትና መኳንንት የሕዝብን ደሀነት በሕገ መንግሥት ጸደቀ፤ ‹‹መሬት የሕዝብና የመንግሥት›› ነው ተባለ፤ ሕዝብም የለ! መንግሥትም የለ! ስለዚህ መሬት የጉልበተኛ ባለሥልጣኖች ሆነ! በለሥልጣኖች የሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎችና የመሬት ባለቤቶች ሆኑ፤ የሚገበያዩትም በሚልዮን እየቆጠሩ ሆነ፤ እንደዱሮው ግብር የሚያበላ ባለመኖሩ ያልጾሙት ባለሥልጣኖች በሦስት መቶ ብር ዶሮ ሲፈስኩ ደሀዎቹ በሹሮ ይፈስካሉ፤ እግዚአብሔር ይህንን የማይመለከትና የማያስተካክል ይመስላቸዋል፡፡

ዱሮ ከሕዝቡ የዘረፉትን በዓመት አንዴና ሁለቴ ይደግሱና ለተወሰኑ በዓላት ግብር እያገቡ ደሀውን ያበሉት ነበር፤ በዚህ ግብር ላይ አይቶ የማያውቀውን ጮማ እየቆረጠና በአንነኮላ ጠላውንና ጠጁን እየጠጣ እገሌ ይሙት እያለ ሲምል ይኖራል፤

እኔ ያንተ አሽከር ያንተ ቡችላ፣
ኩፍ ኩፍ ይላል እንደጉሽ ጠላ!

እያለ ይፎክራል፤ እየፎከረ እርስበርሱ ይተላለቃል፤ ግን በኅብረቱ የአገሪቱን ነጻነት ጠብቆ ለእኛ ክብርንና ኩራትን አደረሰልን፤ ዛሬ ያጣነው ይህንን ውርስ ነው፡፡
በማይሆን መንገድ በማርክሳዊ-ሌኒናዊ ጎዳና መጥተን የጎሣ ተረተር ውስጥ ወድቀናል፤ የነገሥታቱ፣ የመሳፍንቱና የመኳንንቱ ሥርዓት በዓላማው ይለይ ይሆናል እንጂ በይዘት አንድ ናቸው፤ ሁለቱም አፋኞች፣ ሁለቱም ዘራፊዎች ናቸው፤ በነገሥታቱ፣ በመሳፍንቱና በመኳንንቱ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር በጣም ተንሽ ነበረ፤ በዚህም ምክንያት ችግር እንደዛሬው አስጨናቂ አልነበረም፤ ዛሬም ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር የተረጋገጠ ሆኖ አይደለም፤ ስለኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ስጽፍ ወደሀምሳ ዐመት ሆኖኛል፤ ዛሬ ደግሞ የጎሠኛነት ፉክክር ገብቶበት እውነት የራቀው ሆኗል፤ ሁለት ሚልዮን አማራ ጠፋ ተብሎ ያገኘው የለም፤ ስለዚህም በእርሻ ላይ የተመሠረተና የረጋ ኑሮ የሚኖሩት በከብት ርቢና በዘላንነት ከሚኖሩት ያነሰ ቁጥር አላቸው ይባላል፤ መረን መልቀቁ እዚህ ደርሷል፤
ለብዙ ምዕተ-ዓመታት ቋንቋ የፉክክር ምክንያት ሳይሆን ቆይቶ ነበር በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ጉሮሮዬ እስቲነቃ ሸረሬ በሎ ቶሌዳ እያልሁ የዘፈንሁት ዘፈኑም፣ ቋንቋውም የኔው የራሴ መስለውኝ ነበር፤ የኬኛ ቋንቋ ሳይመጣ! ዛሬ ዕድሜ ለሚስዮናውያን፣ ለተወናበደ የነጻነት ግንዛቤና በክህደት ላይ ለተመሠረተ የፈጠራ ታሪክ አማርኛና ኦሮምኛ ተናጋሪዎች የማይተዋወቁ ሆነዋል፤ ካለመተዋወቅም ይሻገራል፤ ወደጠላትነት ይጠጋል፤ ለመረዳት አስቸጋሪ ቢሆንም ኦሮምኛ ተናጋሪው በአማርኛ ተናጋሪው ውስጥ፣ አማርኛ ተናጋሪው በኦሮምኛ ተናጋሪው ውስጥ አለ፤ አንዱ ሌላውን አዝሎ እየኖረ ፉክክር! የአንዱ ደም በአንዱ ውስጥ አለ ቢባል ማንም አይከራከር፤ የቱ ያመዝናል? ደም ወይስ ቋንቋ? እሰከዚህ ድረስ ግራ ገብቶናል!

ለመሆኑ አብዲሳ አጋ በባዕድ አገርና በባዕድ ሰዎችና ባህል ውስጥ ሆኖ በአርበኝነት የተዋጋው ማን ሆኖ ምን ሆኖ ነው? ጄኔራል ጃገማ ኬሎስ? በነዚህ የሥልጣን ጥምና የእንጀራ አባቶቻቸው ሹክታ ባሰከራቸው ደንባሮች ምክንያት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነት የተሰውትን ኦሮሞዎች አንክዳቸውም፤ ልጆቻቸው ቢክዷቸውም ለእኛ አባቶቻችን መሆናቸውንና በለዕዳነታችንን አንክድም፤ የልጆቻቸው ክህደት ሌሎቻችን ያለንን ፍቅር ያጠነክርላቸዋል፤ ለኢትዮጵያ የሞቱት አሮሞዎች መንፈስና እውነተኛ ልጆቻቸው ተባብረው መሾጦዎቹን እንደሚያሸንፉ አልጠራጠርም፤ መሸጦ ወያኔዎችም ተሸንፈዋል፡፡

አማራ ነን ብለው የሚያጓሩት መሸጦችም ታሪክን የካዱና ለሀብትና ለሥልጣን ኢትየጵያን ለማመሰቃቀል የተነሡ ናቸው፤ ግፍንና ጭቆናን በሌላ ግፍና ጭቀና ለማስወገድ መጣር እስካሁን ድረስ ባለው ታሪካችን እንዳቃተን ያየነው ነው፤ ያንን ለመድገም መሞከር ድፍን ድንቁርና ነው፤ እሰካሁን ድረስ ያለው የኢትዮጵያ ታሪክ የግፍና የጭቆና ነው፤ በዚህ የግፍና የጭቆና ታሪክ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባያመልጥም አብዛኛው የኦሮሞ ባላገር ከሌላው የበለጠ ግፍና ብዝበዛ የደረሰበት መሆኑን መካድ አይቻልም፤ ግን ፖሊቲከኞች መረጃዎቻቸውን ለወሎም፣ ለትግራይም፣ ለጎጃምም ቢያዳርሱት የግፍና የጭቆና መሠረት ጎሣ ሳይሆን የተዛባ ሥርዓት መሆኑን ይረዱት ነበር፡፡

በአንዳንድ አውራጃዎችና ወረዳዎች እንዳጋጣሚ ሆኖ በሥልጣን ላይ የነበሩት ሰዎች የሚያስመሰግን ሥራ ሠርተዋል፤ በትግራይ ልዑል ራስ መንገሻ፣ በባሕር ዳር ፊታውራሪ ሀብተ ማርያም (ፊታውራሪነቱን እርግጠኛ አይደለሁም፤) በወላይታ ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት፣ በመርሐቤቴ ዶር፣ ኃይለ ጊዮርጊስና አቶ ገብረ ሕይወትና ሌሎችም የማላስታውሳቸው ይኖራሉ፤ እኔም በጊምቢ ውሀ አስገብቻለሁ፣ ሀኪም እንዲኖራቸው አድርጌአለሁ፡፡

ከላይ ከገለጽኋቸው ውጭ በየትም አውራጃ ሆነ ወረዳ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ሹማምንት ለሕዝቡና ለአገሩ የሚጠቅም ሥራ የሠሩ መኖራቸውን አላውቅም፤ የየአካባቢው ሰዎች ወሬኞቹንና ለነሱ እያሰቡ የሚሠሩላቸውን እየለዩ ማወቅ አለባቸው በጎሣና በሃይማኖት ሳቢያ መታለል አያስፈልግም፤ አንዱ አዲሰ ዘፋኝ ‹‹ታመናል›› እያለ ይዘፍናል፡፡

ከሁሉም በላይ ልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰውና ይቺን አገር ሲፈጥራትና ይህንን ሕዝብ ሲሠራው ከዳር እሰከዳር ጭቃ ወይም ድንጋይ አላደረገውም፤ መሬቱንም ይሁን ሰውን ሙሉ በሙሉ መሸጦ አላደረገውም፤እንደታየ ቦጋለ ያሉ የማይሸጡና የማይለወጡ የወላጆቻቸው ልጆች አሉ፤ ነበሩ፤ ይኖራሉም፡፡

Filed in: Amharic