>
5:14 pm - Wednesday April 20, 4929

አንዳርጋቸውም ይናገር እኛም አንደናገር!!! (ታምሩ ሁሊሶ)

አንዳርጋቸውም ይናገር እኛም አንደናገር!!!
ታምሩ ሁሊሶ 
ለአቃቂሩ አቃቂር
የአንዳርጋቸው ጽጌ መጽሀፍ ብዙ አንጋግሯል። መጽሀፉ የተጻፈበት ጊዜና ይዘቱ ለበርካታ ዉይይቶች በር እንደከፈተ ይታመናል።  አንድ መጽሀፍ በዚህ ደረጃ ማነጋገሩ የአባት ሆኖ ሳለ ብዙው ሰው የሚነጋገርበት አውድ ግን ጤናማ አልነበረም። በርካታ ሰዎችና ሚዲያዎች መጽሃፉን ለውይይት ቢያመጡትም ከመጽሀፉ ላይ አሉ የሚሏቸውን ጉድለቶች ብቻ በመልቀም ሲያቃቅሩት ሰንብተዋል።
በሌላ በኩል በመጽሀፉን ጨርሶ እንዳላነበበው ወይም ደግሞ ጀምሮትም ከሆነ እንዳልጨረሰው የሚያስታውቅበት ብዙ ነው። እርግጥ መጽሀፍ ማንበብን “መዝናኛ” ብቻ አድርጎ የሚመለከትን ህብረተሰብ ይህን ዳጎስ ያለ መጽሀፍ ለምን አላነበብክም ብሎ ወቀሳም አይረባም። እርግጥ ነው ጥቂት የማይባለው፤ከመጽሀፉ ውስጥ የኔ የሚለው ጎራን የጠቀመ፣ሌላውን ደግሞ ያበሸቀ የመሰለውን ሃረግ እየሳበ፤ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጸሀፊውን ሊያሳጣ የሞከረም አለ።ከዚህ ንባባቸውን አናጥበው፤ ለትችት የተሽቀዳደሙት ግን ደግ አልሰሩም ብሎ ብቻ ብሎ ማለፍም አይበቃም። ለዚህ በአንድ ጎን እጅግ ያጋደለ አቃቂርም አቃቂር አስፈላጊ ሆኗል።
ለምሳሌ በርዕዮት ሬድዮ ላይ በቀረበው የመጽሀፍ ግምገማ ሳይሆን “ኑ አንዳርጋቸውን እናሳጣ” የሚል በመሰለ ፕሮግራም ላይ፤ የአማራ ዘውግን እወክላለሁ የሚሉት አቶ  አቻምየለህ ታምሩና የታሪክ ምሁሩ ዶ/ር መሰለ ተሬቻ በተከታታይ ቀርበው ነበር።
አቶ አቻምየለህ እንደተለመደው የበርካታ ነጭ ተጓዦችን ስምና ጽሁፍ እየጠቀሱ ቆይተው፤ብዙዎቹ አድማጮች የአንዳርጋቸውን መጽሀፍ አያነቡትም በሚል ትዕቢት ይመስላል፤ውይይቱ በተጀመረ 60ኛው ደቂቃ ላይ እንዲህ ሲሉ ጀመሩ። “አሁን ደግሞ ወደሚያናድድህ ጉዳይ ልሂድ” በማለት የአዘጋጁን የቴዎድሮስን ጭብጨባ ካገኙ በኋላ የመጽሀፉን ገጽ 300 እና 301 ጠቀሱ። በእነነዚህ ገጾች ላይ አንዳርጋቸው የተማሪውን የትግል እንቅስቃሴ እድገት ካሳየ በኋላ የዋለለኝ መኮንንን የብሄሮች ጥያቄ የሚል ጽሁፍ ያነሳል። የአገሪቱን ችግርም ግልጥልጥ አድርጎ ያሳየ ታሪካዊ ጽሁፍ መሆኑን ይገልጽና ዋለልኝ በዚህ ጽሁፉ ምክንያት በብሄር ፖለቲካ አራማጆች ዘንድ እንደ “ጽላት” ይታያል ይላል። አንዳርጋቸው ገጽ 301 ላይ ረዘም ባለ የግርጌ ማስታወሻው የጽሁፉን ይዘት ገልጾ፤እየዋለ እያደረ ሲሄድ ግን ከዋለልኝ ጋር ብዙ የማይስማማባቸው ነገሮች እንዳሉ ማየት መቻሉን ይገልጻል። ይህ በግልጽ ተጽፎ እያለ አቶ አቻምየለህና ቴዎድሮስ ጸጋዬ አንዳርጋቸውን አሁንም የዋለለኝ ሃሳብን የሚሰብክ፤ ጸረ-ኢትዮጵያ አድርገው ለማሳየት መከራቸውን ሲያዩ ተስተውለዋል ።
በቀጣዩ የርዕዮት “ኑ እናሳጣ” ዝግጅት ላይ የቀረቡት የታሪክ ምሁሩ ዶ/ር መሰለ ተሬቻ ነበሩ። ዶ/ር መሰለ የታሪክ ባለሙያ ሲሆኑ የሶስተኛ ዲግሪያቸውን ማሟያም ብዙም ባልተለመደ መልኩ የኢትዮጵያ የህክምና ታሪክ በማጥናት ነው የሰሩት ። በአንድ ወቅት በሸገር 102.1 ላይ የመአዛ ብሩ የቅዳሜ እንግዳ ሆነውም በህክምና ታሪክ ላይ በተለይም በላሊበላዎችና በሥጋ ደዌ ታሪክ ላይ ሸጋ የሆነ ጨዋታን አስኮምኩመውናል።
ዶ/ር መሰለ መጽሀፉ በወጣ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ መጽሀፉን በፌስ ቡክ ገጻቸው ተችተውት ነበር። ይህ ጽሁፋቸውም ሰፊ ተደራሽነት ነበረው። በዚህ ጽሁፍ ዶ/ር መሰለ ጥቃቅን የመሰሉ ነገር ግን ለእሳቸው ታሪካዊ ፋይዳቸው ትልቅ ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተው፤ አንዳርጋቸውን “ታሪክና የታሪክ ባለሙያዎችን ያዋረደ” ሲሉ ነበር መረር ባለ ትችታቸው የወቀሱት።  ይሁን እንጂ እሳቸውም ከርዕዮት ጋር በመጽሀፉ ላይ ባደረጉት ውይይት “መጽሀፉ እንዲያውም እንድንደናገር አድርጎናል፤አለፍ ሲልም ታሪካዊ ልብወለድ ነው።” በማለት አጣጥለውት ሲያበቁ እሳቸውን ከሚያክል ለሙያቸው ከሚቆረቆሩ የታሪክ ምሁር የማይጠበቅን ግድፈት ሰርተዋል። የቃለመጠይቁ 52ኛ ደቂቃ ላይ አንዳርጋቸው የተስፋዬ ደበሳይ ሾፌር እንደነበረ ያነሳውን ጉዳይ የጥያቄ ምልክት ውስጥ በማስገባት፤ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋም እንዲሁ የተስፋዬ ሾፌር እንደነበረና ሁለቱም ራሳቸውን ወደ ተስፋዬ በሾፌርነት ካለአግባብ ሊያስጠጉ እንደፈለጉ ተናግረዋል። አዘጋጁ ቴዎድሮስ ለወግ ያህል በመሃል ገብቶ ለማስተካከል ቢሞክርም፤ዶ/ር መሰለ፤ግን ማስተካከያውን ከመቀበል ይልቅ በእርግጠኝነት መንፈስ ዶ/ር ብርሃኑ የሟቹን የተስፋዬን ፎቶ ግድግዳ ላይ ተለጥፎ ካየ በኋላ ሽሽቶ እንዳመለጠ የዶ/ር ብርሃኑን የነጻነት ጎህ ሲቀድ መጽሀፍ ገጽ  አምስትን በመጥቀስ ተከራከሩ። ይሁን እንጂ የዶ/ር ብርሃኑን መጽሀፍ ገለጥ አድርጎ የሚመለከት ሰው ይህ የዶ/ር መሰለ ገለጻና ክስ ሃሰት መሆኑ ይረዳል። መጽሀፉ ላይ ዶ/ር ብርሃኑ በግልጽ የሚናገሩት የተስፋዬን ሞት ያወቁት አዲስ አበባን ለቀው ወደ ትግል ሜዳ ከሄዱ በኋላ ፎቶውን በተመለከበበት ወቅት ነበር። እንደ ዶ/ር መሰለ አይነት ለሙያው ቀናኢ ከሆነ ሰው፤ በተለይም አንዳርጋቸውን በትናንሽ የታሪክ፣የኩነት፣የቦታና የጊዜ ልዩነቶች ሊተች ከመጣ ምሁር ይህ የማይጠበቅ ስህተት ወይም ክስ ነበር። አቶ አንዳርጋቸውም የዶ/ር ብርሃኑ የረጅም ጊዜ ጓደኛ ሆነው ሳለ ይህ አይነቱን “በመንገድ የመተላለፍ” ነገርን በውሸት ወደ አደባባይ ሊያመጡት እንዴት ይችላሉ ብሎ መገመትም ብዙ የሚከብድ አልነበረም።
ከሶስት ሰዓት በላይ በፈጀ ሁለት ተከታታይ ቀናት በቀረበ ሰፊና አንድን ጸሃፊና መጽሀፉን ትኩረት በሰጠ ውይይት ላይ አንዲት መስመር አዎንታዊ ነገር አለመስማትም ትንሽ አስገራሚ ነበር።
የአንዳርጋቸው የታሪክ መጽሀፍ?
አንዳርጋቸው ምን ምን ጉዳዮች ላይ ትውልድ እንዳይደናገር እሱም እንዲናገር እንደፈለገ የመጽሀፉ በራፍ ላይ በጉልህ አሳውቆ ነው ወደ ውስጥ የዘለቀው። ሶስት ነገሮች። አዲስ አበባ ፣አንድ ቤተሰብ፣ እንዲሁም አብዮቱና ኢህአፓ ናቸው።
ይህ መጽሀፍ የኢትዮጵያ ወይም የአገር ታሪክ አይደለም።የኢህአፓ ታሪክም አይደለም። የአንድ ግለሰብና የቤተሰቡ ህይወት ታሪክ   ነው። መጽሀፉ ከ1870 አንስቶ ስለሚጀምር የሃገር ታሪክ ነው በሚል ታሪክ በማዛባት የሚወቅሱት ሰዎች ቢስተዋሉም ይህ ግን ስህተት ነው።
መጽሀፉ የአንድ ግለሰብና ቤተሰቡ የአገሪቱን ፖለቲካና ታሪክ የሚመለከቱበትና የሚመዝኑበት የግለሰብ እይታ ነው። ጸሃፊውም በመጽሀፉ መነሻ ላይ “እኔ ከግራ ፖለቲካ የኢህአፓ ሰልፈኛ ሆኜ የሰማሁትን፤ያየሁትን፤የተረዳሁ ያወቅኩትን ለትውልድ ለማካፈል ስነሳ እኔን ራሴን እንዲህ እንዳስብ ያደረገኝ የማንነት ቅመም ከየት እንደቀዳሁት ማሳወቅ ስላለብኝ የቤተሰቤን ታሪክ መተረክ አስፈልጎኛል”  ማለታቸውም ይህኑ ሃሳብ የሚያጠናክር ነው ።
የአንዳርጋቸውን መጽሀፍ ስናነብ ሶስት ነገሮችን ግምት ውስጥ አስገብተን ቢሆን የተሻለ ግብረ መልስና ጠቃሚ የሆነ ትችት ልናቀርብ እንችላለን።እነዚህም፦
የጸሀፊውን የታሪክ መጻህፍት ምን አይነት ቅርጽ ሊኖራቸው ይገባል የሚል እምነቱን፤ መጽሀፉን ሲጽፍ ጥብቅ እስረኛ የነበረ አንጋፋ ፖለቲከኛ መሆኑን እንዲሁም
የአንዳርጋቸውም መጽሀፍ ለታሪክ ግብዓት ሆኖ የሚያገለግል የግለሰብ ቢበዛ የአንድ ቤተሰብ እንጂ የሀገር ታሪክ እንዳልሆነ። ጥቂት እንሂድባቸው።
ታሪክ ወይስ ልብ-ወለድ?
አንዳርጋቸውን መነሻው ላይ በአግባቡ ካነበብነው ታሪክ በደረቅ መረጃ ላይ ብቻ ተመስርቶ መጻፍ እንደሌለበት እምነት እንደያዘ እንረዳለን። እንግሊዝ አገር እንደገባ በቴሌቪዥን አየሁት የሚለውን ክርክር መሰረት አድርጎ ለሱ የታሪክ መጽሀፍ ምን ማለት እንደሆነ ሊገልጽልንና፤የሚጽፈው መጻህፍም ምን ሊመስል እንደሚችል ፍንጭ ነገር ጣል የሚያደርግልን። ። የቴሌቭዥን ክርክሩ አንድ የአሜሪካንን የእርስ በእርስ ጦርነት ታሪክ ጻፍኩ በሚል ግለሰብና በሌሎች የታሪክ ባለሙያዎች መካከል ሲሆን፤ የመጽሀፉ ጸሀፊ “ታሪክ ነው የጻፍኩት “ ሲል ባለሙያዎቹ ደግሞ “ የለም ልቦለድ ነው የጻፍከው” በማለት ነው የሚሞግቱት። አንዳርጋቸው በዚህ ሙግት ላይ አቋም እንደያዘ በግልጽ ይታያል። አንዳርጋቸው ጸሃፊውን ወግኖ ቆሟል። ስለክርክሩ የያዘው ማስታውሻ አጠገቡ ሳይኖር ጸሃፊው አስያዘ የሚለውን ጭብጥ በጥሩ ቋንቋ በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ሲያስቀምጥ እናስተውላለን። ስለዚህ እንደአንዳርጋቸው ከሆነ፤ መነሻ የሚሆኑ መረጃዎች ከተገኙ ታሪክን ተጨማሪ የሆነ የጸሃፊ ግምትና አስተያየት እየሰጠን ብንጽፈው ችግር የለውም ባይ ነው። ይህን አመለካክቱን በዚህ መጽሀፉ በርካታ ቦታ ላይ አሳይቷል። ትንሽ ምሳሌዎች ጣል ጣል እናድርግ  ገጽ 317 ጎበዟና ሚጢጢዋ፤በኋላም የሳይናይድ መርዝ በልታ ህይወቷን ያጠፋቸው የዶ/ር ብርሃኑ እህት አስካለ ነጋ፤ ከንጉስ ኃይለስላሴ እጅ ሽልማቷን ስትቀበል፤ ንጉሱም ከሌሎች ተማሪዎች በተለየ ጊዜ ወስደው ሲያዋራት ከሩቅ ሆኖ የተመለከተው አንዳርጋቸው ምናልባት እንዲህ እያሏት ይሆናል በማለት ፈገግ የሚያስደርጉንን ምልልስ አቅርቧል።
ገጽ 145 እና 146 ላይ አያቱ አባቱን ይዘው ጣልያንንና ባንዳን ሽሸት ከሃረርጌ ወደ ሸዋ ያደረጉትን ጉዞ የገለጸበት መንገድ
ገጽ 566 አጎቱ ዘሪሁን ተስፋዬ ደበሳይን ለደርግ አሳሾች ጠቁሞ እራሱን ከመሳቱ በፊት እንዲህ ብሎ ይሆናል ያለበት መንገድ
በመሆኑም የአንዳርጋቸውን መጽሀፍ እንደ ጥሬ የታሪክ ማስረጃ ሳይሆን፤ በግለሰቡ አመለካክት የታሸና የጣፈጠ ብዙ መረጃ አድርገን መውሰድ አይኖርብንም።
ይሁንና አንዳርጋቸው ከዚህ አቋሙ አልፎ እንዲያውም እኛ አገር የተጻፉ የታሪክ መጻህፍት ከልቦለድ በምን ይለያሉ በማለት ሁሉንም የታሪክ ባለሙያ በአንድ ከረጢት ከቶ ለመውርወር መሞከር ተገቢ አልነበረም። እጅግ በጣም ጥቂት ቢሆኑም ሳይንሱ የሚፈልገውን የመረጃ አሰባሰብ፣አደርጃጀትና አቀራረብ ተከትለው የተጻፉ የታሪክ መጻህፍት የሉም ማለት ባልተገባ ነበር። እሱ በንዴት ያነሳቸው ልብ ወለድ ብሎ ያጣጣላቸው መጽሀፍት የታሪክ ምንጮች እንጂ የሃገር ታሪክ መጻህፍት ላይሆን ይችላሉ። እሱም የጻፈው መጽሀፍ የታሪክ ምንጭ እንጂ የሃገር ታሪክ መጽሀፍ እንዳልሆነ ሊረዳ በተገባው ነበር። በተለይ እንደኛ አይነቱ “አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ” በሆነ ማኅበረሰብና የሰማውን ሁሉ ሳያጣራ በመረጃነት ይዞ “ጡቴን ቆረጥከኝ ብልቴን ሰለብከኝ” እያለ አሁን ካለ ወንድሙ እህቱ ጋር ሊጣላ የሚፈልግ  ልሂቅ በተሸከመች አገር እንዲህ አይነቱ ነገር ጥንቃቄ ያሻው ነበር።
አንዳርጋቸው (ጸሃፊው) ማነው?
መጽሀፉን ዘልቀን ከማንበባችን በፊት ጸሃፊው ማነው የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ተለምዷዊና ተገቢ ነገር ነው። ይህንን ጥያቄ ብዙ ጊዜ አንባቢ በተለያየ መልክ ሊመልሰው ቢችልም፤ ጸሃፊው ሙሉ ለሙሉ አዲስ ከሆነ ግን፤ ከጸሃፊው ጋር ለመተዋወቅ መግቢያውን ማንበብ እንዳለብን መካሪው ብዙ ነው። ፈረንጆች Read the book Jacket first እንደሚሉት ነው እንግዲህ። አንድ ጸሃፊ ቢታወቅም ባይታወቅ ቅሉ፤ይህን የአንባቢ ፍላጎት ግምት ውስጥ በመክተት፤ “መግቢያ” ወይም አንዳርጋቸው ጽጌ በትክክል እንዳስቀመጠው “መግባቢያ” ንባብ ማስቀደም ሙያ ነው። በዚህ የ”መግባቢያ” ንባብ ወስጥ ጸሃፊው ማን እንደሆነ፤ምን እንደሚወድ፤ምን እንደሚጠላ፤ የፖለቲካ አቋሙ ወደየት እንደሚያጋድል፤ የት ላይ ቆሞ መጽሀፉን እንደጻፈው፤ህይወቱ በየትኛው ሃዲድ ላይ ተጉዛ ከመጽሀፉ ዘንድ እንዳደረሰችው ይገልጽበታል። አንዳርጋቸውም ይህን ለማድረግ ሞክሯል- በመግባቢያ ገጾቹ።
አንዳርጋቸው መግቢያው ላይ እንደገለጸው፤ጸጸተኛ ነው። ክክረምት ውሃ ጋር ተደባልቆ እንደወራጅ የፈሰሰ የጓደኞቹ ደም አሁንም ሰላም ይነሳዋል። እንዲህ በማለትም ስሜቱን ይገልጸዋል።
               “ሃዘንና ጸጸት አያስቀምጠኝም። የመቀመጫ እሾህ፤የጎን ውጋት ሆኖ ይወጋኛል። “ሞታቸው ምን አመጣ? ግርፋት ሰቆቃቸው ምን ፈየደ?ምን አርግዘው ምን አምጠው ምን ተወለደ? ለሚሉ ወሳኝ ጥያቄዎች ትርጉም ያለው መልስ አለመኖሩ የውጋቴን ስቃይ ያብሰዋል”
ራሱ አንዳርጋቸው እንዳለው መጽሀፉ የአንድ ግለሰብና የአንድ ቤተሰብ ከፊል ታሪክ (Autobiography) ነው። ይህ ከፊል ታሪክ ደግሞ እንዲሁ ገለጻን (description) ብቻ ሳይሆን ትንታኔም (Analysis) ይዟል። ጸሃፊው የሚታወቀው በፖለቲከኛነት በመሆኑ ምንም እንኳን የግልና የቤተሰቡን ታሪክ ብቻ ለመጻፍ ቢነሳም እያንዳንዷ በመጽሀፉ ላይ የሚጥላት ቃልና ገለጻ ብዙ ድምጽን (Multiple Voices) ይዛ መታየቷ የማይቀር ነገር ነው። ባለብዙ ድምጽ ስንልም የሚጽፈው ነገር ከሱ አልፎ የቤተሰቡ፤የጓደኞቹ፤የማህበረሰቡ ታሪክ ብቻ ተደርጎ ሳይሆን የሚወሰድለት በዚህ ዘመን ላይ ካለ ፖለቲካ የትኛው ጥግ ላይ ቆሟል በሚልም ጭምር ነው። ደግነቱ ራሱም የሚጽፈው ነገር የሱና የሱ ብቻ እንዳልሆነ ከመነሻው ገልጿል።
አንዳርጋቸው ጽጌ  በሌለበት “ይሙት በቃ” ተፈርዶበት ከሰንዓ የመን ተይዞ መጥቶ “አለም በቃኝ” የተወረወረ ሰው እንድነበር ይታወቃል። ብዙ ጊዜ እንደእሱ በጠላት እጅ የወደቀ የሞት ፍርደኛ ስለሞቱ በሰቀቀን ቀን ይቆጥራል እንጂ  “የምለው አለኝ ልጻፍ” ብሎ “ጠላቶቹን” አይጠይቅም። ግን ይሄ ሆኗል።የአንዳርጋቸው ተቺዎች የመጽሀፉ ይዘት ባያስደስታቸው እንኳን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በመንፈሰ ጠንካራነት ይህንን መጽሀፍ በማበርከቱ ይሁንታና ምስጋና ሊሰስቱ አይገባቸውም ነበር።
አንዳርጋቸው እንኳን የሞት ተራውን እየጠበቀ እንዳለ እስረኛ ሆኖ፤ለወትሮውም “እኔ ለራሴ ነው የምጽፈው ከሚሉ ትልቁን “የበሬ እበት ጣዮች” መሃል እንደማይመደብ ይናገራል።ሲቀጥልም “ትኩረቴ ልጽፈውና ወደህዝብ ሊደርስ ይችላል ብዬ ባመንኩት ዘመን ላይ ብቻ ሆኗል” ሲል ይገልጻል(ገጽ 30_31)። እዚህ ቦታ ላይ ነው አንዳርጋቸው የጻፈው ነገር የሰው እጅ ላይ እንዲደርስለት ምን ያህል ጉጉት እንደነበረው የምንረዳው። ይህ ሰው ነጻ ሰው አልነበረም። የጻፈው ነገር ካልተመቻቸው ፤ ፊቱ ላይ ቀዳደው ሊጥሉለትና እሱንም ወደ መሰቀያ ገመዱ የሚሸኙ ጠባቂዎች ስር ሆኖ ነው ይህን መጽሀፍ የጻፈው። ይህም በወቅቱ የነበሩ ጌቶቹን ማባበያ የሚሆኑ ነገሮችን በጽሁፉ ሳይወድ በግድ አአስገብቶ ይሆን የሚልን ጥያቄ ያጭራል። እንዲያ ከሆነስ ከወጣ በኋላ “አገኘሁት” በሚለው ነጻነት አንዳንድ በጫና ዉስጥ ሊጽፋቸው ይችላል ተብለው የሚታሰቡ፤ የመጽሀፉን ክፍሎች እንዴት ተመልሶ ሊያያቸው አልቻለም የሚል ጥያቄ ቢነሳ ተገቢነት አለው ።
አዲስ አበባና አንዳርጋቸው
አንዳርጋቸው አዲስ አበባን ተወልደው አድገውባት ከከተማዋ በጉልበተኞች ተገፍተው ለስደት ከበቁ የዚያ ዘመን ውጣቶች አንዱ ነው። ስለሆነም ስለአዲስ አበባ ሊጽፉ ከሚገባቸው ሰዎች እንደአንደኛው ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ። አዲስ አበባ የዛሬ ፖለቲከኞች ደርሰው “ ኬኛ” “የኛ” እንደሚሏት ሳይሆን፤ በደም ዋጋውን የከፈለ ትውልድ የኖረባት ከተማ ነች። ቢያንስ ሁለቱን ትልልቅ የደም ግብር ያወጣችባቸውን ጊዜያት ለመጥቀስ አንዱን በጣሊያን ወረራ ወቅት የካቲት 12 1929 ዓ/ም ሲሆን፤ ሌላውን ደግሞ በዘመነ ደርግ የቀይና ነጭ ሽብር ፍጅት ወቅት ነበር።
ድርጅቱን አንደ ሹፌር በማገልገሉ ሳይሆን አይቀርም በኢህአፓ ታሪኩ ላይ አንዳርጋቸው አዲስ አበባ ከተማን እንደ እጅ መዳፉ እንደሚያውቃት ያሳያል። ያልጠቀሰው፣ ያልሄደበት የከተማው አካባቢ አልነበረም (ገጽ 560_61)። በዚህም የኢህአፓን ታሪክ ድራማዊ በሆነ መንገድ ሲያስቀምጠው በተለይ ለአዲስ አበባ ልጅ፤ ክስተቱን በዓይነ ህሊናው ማየት ያስችለዋል። ለምሳሌ የዚህ ጸሃፊ የትውልድ አካባቢ የሆነውን “አደሬ ሰፈር” (ገጽ 560-561) አዲስ አበባ ውስጥ ካሉ ሰፈሮች ሁሉ የላቀ የኢህአፓ እንቅስቃሴ እንደነበረበትና የፍልስጥኤም ነጻ አውጪ ሰዎች እዚያ እንደከረሙ ሲገልጽ ፤ልጅ ሆኖ እናቱ ስለአደሬ ሰፈርና ኢህአፓ ስታወራለት የነበረውን ታሪክ እንዲያስታውስ አድርጎታል። እርግጥ ነው ድሮ ድሮ አዲስ አበባ ውስጥ መርካቶ መሃል ተቀምጦ፤ በጽዳቱ አለ የተባለ ሰፈር ቢኖር አደሬ ሰፈር ነበር። በውስጡ የነበሩ ወጣቶችም (ምናልባት የኢህሃፓ ትራፊዎች ስለሆኑ ይሆናል) ጥሩ አንባቢዎችና የነቁ ነበሩ።
ለብዙው የአንድነት ሃይልና የአማራ ልሂቅ አስቆጪ የነበረው አንዳርጋቸው እየደጋገመ አዲስ አበባን “የአያቶቼ የጥጃ ማሰሪያ” የማለቱ ጉዳይ ነው። በእውነቱ ይህ ለምን ያን ያህል አቧራ እንዳስነሳ ግልጽ አይደለም ። እንዲህ ማለቱንም አያቴ እያለ ከሚያነሳቸው አቶ ተሰማ ሮቢ ኦሮሞነት ጋር በማያያዝ ለ”ኬኛ” ፖለቲካ ተንበርካኪነቱን አሳይቷል የሚል ክስ ይመስላል በተደጋጋሚ የሚነሳበት።፤እርግጥ አንዳርጋቸው አያቱ ያስጠኑትን የኦሮሞ የዘር ሃረግ ዛሬ ላይ ሊነግረን መፈለጉ ፤ቀደም ብሎ በ1985 ዓ/ም “የአማራ ህዝብ ከየት ወደየት?” በተሰኘ መጽሀፉ አጽንኦት የሰጠበትን አማራነቱን፤ ኦሮሞነትም አለብኝ የሚል ማስተካከያ ይሆን እንዴ ያስብላል። ግና በመጽሀፉ ትኩረት ከሰጣቸው ሶስት ጉዳዮች አንዱ ቤተሰቡ ነውና ይህን የቤተሰቡን ሃረግ እስከቻለው ድረስ ባይሄድበት ደግሞ ታሪኩ ብዙ የተሟላ ሊሆን ስለማይችል እውነት አለውም ያስብላል። ለማንኛውም ጉቶ ቦሬን ወለደ፤ቦሬ ቡኒን ወለደ፤ ቡኒ ቱፋን ወለደ፤ ቱፋ ዶዮን ወለደ፤ዶዮ ሮቢን ወለደ፤ ሮቢ ተሰማን ወለደ፤ተሰማ የአንዳርጋቸው እናትን ወሮ አልታዬን ወለዱ። ለአንዲት ሴት ልጃቸው የመጀመሪያ ወንድ ልጅ እንደማንኛውም የድሮ አያት ብዙ ጉራ የቀላቀለበት ታሪክ ያጫውቱት ነበር ( ገጽ 65 እስከ 68)። ከዚህ ውስጥ አንዱ አዲስ አበባ የ”አያቶችህ የጥጃ ማሰሪያ” ነበረች የሚለውን አንዳርጋቸው አንጠልጥሎ ኖሯል። ይህች ሃረግ ካላት ስነጽሁፋዊ ውበትና፤ አንዳርጋቸው ታሪክ በዚህ መልኩ እየተዋዛ ሊነገር ይገባዋል የሚል እምነት መያዙን አንጂ፤ ለኔ ብዙ አቧራ የምታስነሳ ጉዳይ ሆና አላገኘኋትም። ከዚህ ይልቅ የአቶ ሮቢ ቅድመ አያት የሆኑት አቶ ቡኒ በምኒሊክ ተዘረፉ ብሎ ያነሳው ሃሳብን ፤ በግርጌ ማስታወሻ ጭምር ሊደግፍ ሞክሯልና ይህንን ስህተቱን በጨዋነት መሞገት ይቻላል ባይ ነኝ
የአያቱን ተረት (የአቶ ቡኒን 20 ሺህ ከብቶች ዘረፋ) ለመደገፍ የግርጌ ማስታወሻ ላይ አንዳርጋቸው ያመጣቸው ሁለት ማስረጃዎች፤ የወሬ ወሬ ሰማሁ የሚለውን አጼ ሃይለስላሴ ለግሪኮች በ1950ዎቹ የላኩትን የእርዳታ ከብቶች ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የፊታውራሪ ተክለሃዋሪያት ተክለማሪያምን “የህይወቴ ታሪክ” ነው። ሁለቱም ለከብት ዘረፋ ክስ ውሃ የሚያነሱ አስረጂዎች አይደሉም። ፊታውራሪ ተክለሃዋሪያት ከኦሮሞዎች ጋር ወደ አዳል ሲዘምቱና በአሸናፊነት ከአርብቶ አደሮች የማረኩትን የከብት ብዛት አንዳርጋቸው ሸዋ ላይ ከአንድ ግለሰብ (ቡኒ አርሶ አደርም ሊሆን ይችላል) “በምኒሊክ ተወሰደ” ከሚለው የከብት ብዛት ጋር ማነጻጸር ምክን ያት ፈልጎ ምኒልክን ላሳጣ ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? የአያቱን ተረት በሌላ ተረትና የማይመስል ቁጥር ሊተነትን መሞከሩ አንዳርጋቸውን ሃቀኛ የታሪክ ጠበቃ አያደርገውም። ምናልባት እስር ላይ እያለ ትከሻው ላይ ቆሞ ሲተነፍስበት የነበረውን ሃይል ማስደሰት ፈልጎ ካልሆነ በስተቀር።  ከዚያ ይልቅ ፊታውራሪ ተ/ሃዋሪያት በመጽሀፋቸው በአዳል ጦርነት የተሳተፉትና የአዳልን አንድ ጎሳ ከብቶች ሲዘርፉና ሲነዱ የነበሩት በብዛት አሮሞዎች መሆናቸውን እንደጠቀሱ አላስተዋለ ይሆናል። ከቤተሰብ “ፕሮፓጋንዳ” አልፍ ብሎ አንጀት ላይ ጠብ የሚል “ማስረጃ” ሳይጠቅስ እንዲሁ የአያቱን የምሬት ወግ እየደጋገመ ምኒልክን ለመክሰስ መሞከር እንደ አንዳርጋቸው ላለ የእድሜ ልክ ፖለቲከኛ “ትርጉሙ ምን ይሆን” ብሎ አለማሰቡ ትንሽ አስገራሚ ሊሆን ይችላል። የአያቱን ወግ “ፕሮፓጋንዳ” የሚለው እራሱ አንዳርጋቸው ነው (ገጽ 67)። ይህም ከአያቱ የሚሰማው ነገር ውሽት ቅልቅል እንደነበረ አንዳርጋቸው ራሱ ልቦናው ያውቀዋል ማለት ነው። ይህም ሆኖ አንዳርጋቸው የተጋነነውንና ውሸት ቅልቅል የሽማግሌ ተረቱን የተጋነነ ይመስላል እያለ በአንድ በኩል፤በሌላ በኩል ደግሞ እውነት እንደሆነ ሊያስረዳ በግርጌ ማስታወሻ መከራውን ይበላል።
ሊላው ከተማዋን አዲስ አበባ ከመባሏ በፊት ሸገር ወይም ደግሞ ፊንፊኔ እንደነበረች አስመስሎ ማቅረብንም አንዳርጋቸው ለምን እንደፈለገው አይገባም (ገጽ 71)። እንደሚታወቀው ፊንፊኔ አንዲት ምንጭን የምትወክል የቦታ ስም እንጂ ሌላ እንዳልሆነ መቼም አያጣውም። ልበ ቀና  የሆነ አንባቢ አንዳርጋቸው ይህን ሲጽፍ፦
አዲስ አበባ ዛሬ ላይ የዘውግ ፖለቲከኞች የሞት ሽረት  ቦታቸው አድርገው እንደሚመለክቷትና፤ ማንኛውንም ተረት የእነሱን ተረት ይደግፍ ከመስላቸው ፈጥነው ሊወስዱት እንደሚችሉ ያለመረዳት
አዲስ አበባ ከላይ እንደተጠቀሰችው የሞት የሽረት ቦታ መሆኗን አውቆ “ኬኛ” የሚያቀነቅኑ የኦሮሞን ልሂቃንን ለማባበል ያደረገው ሙከራ
የግራ ርዕዮተዓለም ላይ የተንጠለጠለችና እሱ የፊውዳል ተስፋፊነት የሚለውን የምኒሊክ እንቅስቃሴ የምትጠላ ነፍሱን ለማስታመም፤ በዚህም ከአሳሪዎቹ አዘኔታ ለማግኘት
በማለት ጉዳዩን ቀለል አድርጎ ሊገምትለት ይችል ይሆናል። ያም ሆኖ አንዳርጋቸውን ያሚያክል ትልቅ ፖለቲከኛ የዚህን ጉዳይ መዘዝ ሳያመዛዝን ወደ አደባባይ ማምጣት አልነበረበትም።
ከዚያ መለስ ከተማዋ የተሰራችበትን የጉልበት ምንጭ የባሪያ ፤ጥንታዊ የኢኮኖሚ ሞተሮቿም ሴተኛ አዳሪዎች፤ጠባቂዎቿም ጉልበተኛ ወታደሮች መሆናቸውን የገለጸበት መንገድ ፤ አንድ አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገ ጤናማ ሰው (rational person) ሊገልጸው የሚችለው ውሃ የሚያነሳ ግምት ነው (ገጽ 71 እስከ 82)።  ባሪያ በኢትዮጵያ የታሪክ አውድ ውስጥ ምንድነው የሚለው፤የነ ዶር መሰለ ክርክር ለግራ ፖለቲከኛው አንዳርጋቸው ጽጌ ብዙ የሚዋጥ አይደለም። አንዳርጋቸው ከዚህ ቀደም ያሳተመው “ነጻነትን የማያውቁ ነጻ አውጭዎች” የተባለ መጽሀፉ ላይ እንደሚታየውና የዕለት ከዕለት ኑሮውን የሚያውቁት እንደሚናገሩለት የድሃ ኑሮ የሚያስጨንቀው የመደብ ፖለቲከኛ ስለሆነ፤የድህነት አዘቅት ውስጥ የተነከረውን ሁሉ፤ ከባላባቱ “ቅንጦት” ጋር እያወዳደረ “የባሪያ” ኑሮን የሚገፋ አድርጎ ቢያቀርበው ብዙ አይፈረድበትም።
አንዳንድ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ “ባሪያ” ሳይሆን “አገልጋይ” የተባለ በምቾት የሚያዝ፤ ከቤተሰብ እኩል የሚቆጠር ፍጥረት እንደነበረ በመናገር አንዳርጋቸው መከራና ስቃይ የሚቀበል ባሪያ እንደነበር መጻፉን ይኮንናሉ ። እንደ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ አይነት ታላላቅ የታሪክ ባለሙያዎች ግን የጅማው አባጅፋር ባሪያን ለምች መድሃኒት መግዣ እንደሚዉል ሽርፍራፊ ሳንቲም ይጠቀሙበት እንደነበረ ሁሉ ጽፈዋል። ለዚህም የፕሮፌሰር ባህሩን History of Ethiopia ማየት ነው። በዚህ ደረጃ እንዳለ “ቁስ” የሚቆጠር ባሪያ የነበረበትን አገር “አገልጋይ” የሚባል “ቤተዘመድ” አይነት ነው ብሎ በቃላት መጫወትና አንዳርጋቸውን ማጣጣል ተገቢ አይመስልም ። በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የሚሸጥ የሚለወጥ “ባሪያ” የሚባል “ዕቃ” እንደነበረ መካድም መልካም አይደለም።
የአንዳርጋቸው አንድ ቤተሰብ
የአንዳርጋቸው አንድ ቤተሰብ የኢትዮጵያን ብዙ ቤተሰብ ሊወክል ይችላል። አንዳርጋቸው የዚህ አይነቱ ተራ ቤተሰብ ታሪክ ለምን ሳይታይ እንደዋዛ ያልፋል፤ይልቁኑ እንዲህ አይነቱ ቤተሰብ ታሪክ ሲኖረው ነው አገር ታሪክ የሚኖራት የሚል ሙግት አለው። የአንዳርጋቸው ቤተሰብ ታሪክ፤ ዘር ሳይቆጥር በመደቡ ብቻ ተመራርጦ የሚጋባ ህበረተሰብ እንደነበረን ፤ በርካታው ቤተሰብ በርካታ ግፍና መከራን እንዳለፈ፤ የእናቶቻችን መስዋዕትነት ( ልጆቿን አይኗ ስር ያረዱባት እናት ይህን ሁሉ አልፋ የጠፋ ልጇን የማግኘት ተስፋን)፤ ከሌሎች ተግባብቶ ተቻችሎ ማደርን፤ የጓደኝነት ፍቅርን፤ ባይወልዱትም የጎረቤትን ልጅ እንደራስ ልጅ የማየትን (ልጆች ለእስኪሪብቶ መግዣ ሳንቲም ሲፈልጉ ከጎረቤት ገብተው የተኛ ሰውን ቀስቅሰው ሳንቲም የሚጠይቁበት ደግ ጊዜ እንደነበረን)፤ የመሳሰሉና ብዙ ብዙ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የቤተሰብ ስዕሎችን በጣፋጭ ቋንቋና አስገራሚ ትውስታ ጽፎታል።
አንዳርጋቸው ስለቤተሰቡ ሲተርክ በኢትዮጵያውያን ያልተለመደን ግልጽነት ተላብሶ መሆኑ ሌላኛው የመጽሀፉ ውበት ነዉ። በጣም የሚወዳት እናቱን አልታዬ ተሰማን እንኳን መልኳ “ቆንጆ” እንዳልሆነች ብቻ ሳይሆን አባቱን “ምኗን አይተህ አገባሃት ለመሆኑ?” ብሎ እስከመጠየቅ መድረሱን እናያለን ። ይህም የአንዳርጋቸው ግልጽነት ድንገት ዛሬ የበቀለ ሳይሆን አብሮት የኖረ ባህሪው መሆኑን ያመላክተናል።
በአጠቃላይ አንዳንዶች እንደሚተቹት ሳይሆን በአብዮቱ ዋዜማ፤ በአብዮቱ ወቅት እንዲሁም ማግስት፤ አዲስ አበባ ውስጥ የነበረውን የመካከለኛ ቤተሰብን ኑሮ በዝርዝር ሊወክል የሚችል ግልጽነትና ጨዋነትን ያላጓደለ ትልቅ ስዕል የያዘ ትረካ ነው። አንዳርጋቸው የመጽሀፉ መግቢያ ላይ እንደገለጸው የመጽሀፉን ምዕራፎች እራሳቸውን የቻሉ እንዲሆኑ አድርጎ ስላስቀናጃቸው፤ አንባቢ ከክፍል ሶስት እስከ አምስት ያሉትን ክፍሎች በማንበብ ብቻ፤ የዚያን ወቅት የአዲስ አበባ ከተማን ቤተሰብ፤ ልጅነትና ጉልምስና፤ ጉርብትናና ዝምድና በአይነ ህሊናው ሊቃኝ ይችላል።
አንዳርጋቸው አብዮቱና ኢህአፓ – አይ ዘመን፤ አይ ስነልቦና
አንዳርጋቸው አብዮቱንና ኢህአፓን የተረክበት የመጨረሻዎቹ ሁለት ክፍሎች ብቻ (7 አና የመጽሀፉን ግማሽ ያክል ይዘዋል። ኢህአፓ ከአንዳርጋቸው ልብ ውስጥ የሚወጣ ፓርቲ እንዳልሆነና አሁንም በፍቅር እንደሚያስታውሰው ብዙ ቦታ ላይ እንረዳለን። በዚህ ሊፈረድበት ይገባል ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ኢህአፓና የዚያ ትውልድ አባላት ብቻ ናቸው ኢትዮጵያን ለዛሬ ያለችበት ሁናቴ ያበቋት የሚለው ድምዳሜ ብዙ አጨቃጫቂ የፖለቲካ ታሪክ ሊሆን የሚችልበት እድል ስለሚኖርና አንዳርጋቸው ከዚህ በተቃራኒ ሊቆም ስለሚችል። በጊዜ ጋሪ ወደኋላ መሄድ የሚቻል ቢሆንና እያንዳንዱ የዚያ ትውልድ አባላትን በጨቅላ እድሜያቸው ብናጠፋቸው የዛሬይቱን ኢትዮጵያ እናገኝ ነበር ወይስ አናገኝም የሚል ሙግት ፍልስፍናዊ ሊሆን ይችላል። ስለሆነም ለኢህአፓ ያለው ፍቅር አያስወቅሰውም።
አንዳርጋቸው ለኢህአፓ ፍቅር ይኑረው እንጂ ሌሎችንም ሲተች እስከዛሬ እንደነበረው እያብጠለጠለና እያጥላላ አልነበረም። ለምሳሌ የውታደሮችን በአብዮቱ ጣልቃ ገብነትና የንጉሳውያን ስርዓትን መጣልን እብዮትን እንደማኮላሸት ነው የምመለከትው ብሎ ሲያበቃ፤ ድምዳሜው ግን እንደሚጠይቅ በመግለጽ ወታደሮቹ “አብዮተኛ አልነበሩም” እንጂ “ጸረ-አብዮተኞች” እንዳልነበሩ ይገልጻል። ገጽ 384።    ኢህአፓ ለህዝባዊ መንግስት ምስረታ ሲጮህ ለስልጣን ጥማት ብለው ይህንን በመቃወም ለአገሪቱ ፖለቲካ ውድቀት መኢሶኖች የበለጠ አስተዋጻኦ አድርገዋል ብሎ ቢወቅስም፤ በወቅቱ የነበረ እብደትን ሁሉም የሚጋራው እንጂ የመኢሶን እዳ ብቻ ነው ብሎ አያምንም።
አንዳርጋቸው አስቦትም ሳያስበው፤የእነዋለልኝ የብሄር ትንተና ጠንካራ ኢትዮጵያዊነትን የያዙ ወጣቶችን መበከል እንደቻለ ይገልጻል። ለምሳሌ አቦማ ምትኩ የተባለው የኦሮሞ ብሩህ ወጣት በተፈሪ መኮነን የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ ዋንጫ ባገኘበት የእንግሊዘኛ ውድድር ንግግሩን የዘጋው Let’s make Ethiopia , today, the Japan of Africa በሚል የጋለ የአገር ፍቅር ስሜት ነበር (ገጽ 369)። ይሄው ወጣት ዩኒቨርሲቱ ከገባ በኋላ ከኢትዮጵያ ብሄረተኝነት እንደሸሸና ኋላም የኦነግ አባል ሆኖ ባሌ ውስጥ በኦሮሞ እስላማዊ ግንባር ይገደላል። አንዳርጋቸው የነ ዋለልኝ የተዛባ የብሄር ትንተና እንዲህ አይነቶቹን ባለ ብሩህ ጭንቅላቶች እንዴት እንደበከለ ከመግለጽ ይልቅ የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ለዚህ እንዳበቃው ይገልጻል። ገጽ 370። ይህም የአንዳርጋቸውን እነዋለልኝን በአደባባይ ማሳቀል ያለመፈለግ ያሳያል ቢባል ስህተት አይሆንም። በዚህና በሊሎች መሰል ጉዳዩ አንዳርጋቸው ወጥ የሆነ የፖለቲካ ይሁን የግምገማ አቋም መንገዳገድ እዚህም እዚያም ይስተዋልበታል። ከአዕምሮ ትውስታው እየቀዳ የራሱንና የቤተሰቡን ታሪክ በእስር ቤት ውስጥ ለሚጽፍ ሰው ይህ አይነቱ ስህተት የሚበዛም አይደለም።
አጠቃላይ መጽሀፉ ስለኢህአፓና አብዮቱ ያለውን ይዘትን ጨምቀን እናውጣ ካልን እና በቀናነት ከተመለከትነው አንዳርጋቸው የመጣበት መንገድ ከእስከዛሬዎቹ የዚያ ዘመን ሰዎች በተለየ ኑዛዜያዊ ( confessional ) ነው። ወደኋላ እየተመለሱ ንክሻ የሌለበት ጸጸት ነው።
በወቅቱ የነበሩ እሱን መሰል ጎረምሶች በጥራዝ ነጠቅነት ወስደው አይናቸው ላይ የጋረዱት ርዕዮተ ዓለም ምን ያህል ከሰው ተራ አውጥቶ፤ በግፍ ለተገደሉ ታናናሽ ወንድሞቻቸው እንባ ማውጣትና ማልቀስ የማይችሉ፤ ከዚያም ሲያልፍ በሃዘን የተቆራመዱ እናትና አባቶቻቸው ላይ የሚዘባበቱ እንደነበሩ በጸጸት ደመቅ አድርጎ እንዳይረሳም አስምሮበት ነው የጻፈው።
ታናሽ ወንድሙ አምሃ ሚያዝያ 21 1969ዓ.ም በደርግ ተገድሎ፤ እናቱ የሚያጽናናት ዘመድ አዝማድ በሌለበት፤ በጎረቤት ህጻናት ተከባ ስታለቅስ፤ ጥቂት ቆይቶም ወላጅ አባቱ የወንድሙን አስከሬን አፈላልጎ አግኝቶ አስከሬኑን ሊወስድ ከጨረሰ በኋላ አትወስድም ተብሎ ባዶ እጁን ተስፋ ቆርጦ ሲመጣና ግቢው በለቅሶ ሲናጋ አንድም ቀን ሲያለቅስ አይቶት የማያዉቀው አባቱም ድምጽ አዉጥቶ በሲቃ ሲያነባ እሱና የቀሩት ወንድሞቹ እንዲሁም ጃፒና ዘውዱ የሚላቸው ጓደኞቹ አንጀታቸውን አደንድነው “ታጋይ ይሞታል እንጂ ትግል አይሞትም” እያሉ እንባና ለቅሶን የሽንፈት ምልክት አድርገው ሲመለከቱ እንደነበር በመጽሀፉ ገጽ 574 ላይ “የወንድሞቻችንን ሞትና የአባቶቻችንን ሲቃ ከቁም ነገር ሳንቆጥረው ያን ዘመን እንደዋዛ አሳለፍነው። አይ ስነልቦና! አይ ዘመን!” በማለት የጸጸት ስሜቱን ያጋራናል  ።
 ከሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ጋር በተጋራት የፖሊስ ጣቢያ እስር ቤት ውስጥ እንዴት ድንቁርናውን እንደተረዳና፤ ታላላቆቹ እነጸጋዬ ስለአገራቸው እንባቸው ሲያፈሱ ወጣቶቹ “አብዮተኞች” እነ አንዳርጋቸው ምን ይሰማቸው እንደነበር ዛሬ ላይ በሃፍረት ነው የገለጸው። ለእስር ቤቱ አባላት የጻፈው ድራማ ከታየ በኋላ የገጠመውን በገጽ 630 ላይ ሲገልጽ
 “ስለጻፍኩት ድራማ ያለውን አስተያየት እንዲሰጠኝ በግሌ ጋሽ ጸጋዬን ጠይቄው ግማሽ ቀን ሙሉ ስለስነጽሁፍ ምንነት ማብራሪያ ሰጠኝ። በህይወቴ ሙሉ ይዤ የምዞረው ሃብቴ ሆኗል። “ድንቁርና የድፍረት ምንጭ” እንደሆነ ትምህርት ያገኘሁት ሎሬት ጸጋዬ የጻፍኩትን ድራማ እንከኖች በዝርዝር ካስረዳኝ በኋላ ነበር። ከዛ በፊት ራሴን ታላቅ ጸሃፊ አድርጌ ለመቁጠር የምትቀጥለውን ጨረቃ መውጣት እየጠበቅኩ ነበር”
በማለት ነበር። እዚያው ገጽ ላይ ደግሞ ሎሬት ጸጋዬ “ፕሪዝን ባንድ” የሚያሰማውን ግጥም ሲሰማ የነበረውን ስሜት እንዲህ ይገልጸዋል።
ምግብ ማጣት ብቻ መቼ ሞረሞረን
ቅን አስተዳደር ነው እጅጉን የራበን
ሁሉም የናት ልጅ ነዉ ማን አለ ባዳ ሰው
ላገሬ ብሎ ነዉ ሆዱ የሚላወሰው
ባንዱ ይህን ባለ ቁጥር፤ ከጋሸ ጸጋዬ አይን የሚፈልቀው እንባ ለጉድ ነው።
አንዲት ጠብታ እንባ በማውጣት “ ስቃዩ የጋራችን ነው” ብሎ ያጽናናው አንድም እስረኛ አልተገኘም። “ታጋይ ይሞታል እንጂ ትግል አይሞትም” እያልን እንባንና ለቅሶን የሽንፈት ምልክት አድርገን እንደተመለከትን፤የታላላቆቻቻንን ሲቃ ከቁም ነገር ሳንቆጥረው፤ ያን ዘመን እንደዋዛ አሳለፍነው። አይ ስነልቦና ! አይ ዘመን!!
በአጠቃላይ የአንዳርጋቸው የዚያ ዘመን ትውስታ ጽሁፍ ቂም ጠቅሎ የያዘ ወረቀት ሳይሆን፤የሚከፋበትንና እንደሚጠላው የሚያስታውቅበትን ስርዓት እንኳን በጎ ጎኖች ካሉት ከማንሳት የማይቆጠብ ነበር። ብዙ የዘውግ ፖለቲካን የሚያኝክ ምሁር ተብዬ ቀዳማዊ ኃይለስላሴን በመድልዎ ሲከሳቸው ይታያል። ምንም እንኳን እንደ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ያሉ ሃቀኛ አዛውንቶች “ተው ይህ ነገር ልክ አይደለም፤ንጉሱ ችሎታ እንጂ ዘር አይመለከቱም” እያሉ ቢጮሁም። አንዳርጋቸው በመጽሀፉ ብዙ ክፍል ለአጼዎቹ ስርሃት ጥላቻ እንዳለው ያስታውቃል። ይሁን እንጂ ስለ አጼ ሃይለስላሴ በገጽ 204 ላይ የሚከተለውን ጽፎ እናየዋለን።
“የአጼ ኅይለስላሴ ዘመናዊ የሲቪልና የሚሊታሪ ቢሮክራሲ በሸዋ ሰዎች ተሞልቶ መገኘቱ፣ተመሪዎች ሆነን እንደምናስበው፣ የአጼ ኅይለስላሴ መንግስት ዘረኛ በሆነ መንገድ ቢሮክራሲውን በሸዋ ሰዎች በተለይ በሸዋ አማሮች ለመሙላት በማሰቡ አልነበረም። ስርዓቱ ማስተማር የቻለው የሸዋን የደሃ ልጆች በመሆኑ ነበር
“አጼ ኃይለስላሴ፣የተማረ ሰው ካገኙ ስራ ለመስጠት ብቻ ሳይሆን፣ በተለይ በስልጣን ዘመናቸው የመጀመሪያ ዓመታት  የሚለውንም ለማድመጥ ዝግጁ ነበሩ። የታወቀውን፣ በጀርመን ሃገር ትምህርቱን ያጠናቀቀውን የትግራይ ምሁር፤የነጋድራስ ገ/ህይወት ባይከዳኝን ”መንግስትና የህዝብ አስተዳደር” የሚል ድንቅ መጽሀፍ አሳትመው ማንበብ ለሚችል ሁሉ ያሰራጩት አጼ ኃ/ስላሴ ናቸው”
ይህን እና መሰል የመጽሀፉ ትርክቶች አንዳርጋቸው ወደኋሊት ሲመለሰ የሚጠላውና የሚተቸው ነገር ብቻ ሳይሆን ከጥሩ ነገሩም ወስዶ ለማካፈል አልሳሳም።
አንዳርጋቸውና ስነጽሁፍ 
አንዳርጋቸው ይህን መጽሀፉን ሲጽፍ ታሪኩን ደረቅ እንዳይሆንበት ብቻ ሳይሆን ስለስነጽሁፍ ውበቱም እንደተጨነቀ ያሳብቅበታል። ለምሳሌ በክፍል 6 ስለቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ ሊተርክ ሲነሳ የመጀመሪያውን ምዕራፍ ያደረገው “ምዝገባና ኮልታፋዋ ልጅ “ የሚል ርዕስን ነው። ይህን አጭር ምዕራፍ ሙሉ ለሙሉ ለዚያች ኮልታፋ ልጅ ቢሰጥም ማን እንደሆነች ሳይነግረን ነው ምዕራፉ የሚያልቀው። በዚህም አንባቢ ልክ ልብወለድ የሚያነብ ያህል ይህች ልጅ ማን ትሆን እያለ ልቡ ተሰቀሎ ወደ መጽሀፉ እንዲዘልቅ ያደርገዋል። ይህች ኮልታፋነቷን ለመግለጽ ጓደኞቿ “ኮልት” እያሉ የሚጠሯት፤ባለብሩህ አዕምሮዋ ወጣት የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ታናሸ  “አስካለ ነጋ” ነበረች ። ኋላም የኢህአፓ አባል ሆና አራት ኪሎ አካባቢ ደርግ እጅ ላይ ላለመውደቅ የሳይናይድ መርዝ በልታ እራሷን እንዳጠፋች በሌላ ክፍል ውስጥ ስናነብ የአንዳርጋቸውን ለትረካው ስነጽሁፋዊ ዋጋ ምን ያህል ተጨንቆ እንደነበር ይገባናል። መጽሀፉ በዚህና መሰል በርካታ በፊልም መልክ ሊቀርቡ የሚችሉ ታሪኮችን የያዘ መሆኑ የጸሃፊውን እምቅ የሆነ የስነ ጽሁፍ ችሎታ የሚያሳይ ነው። ተጨማሪ የዚህ ዓይነቶቹን ስነጽሁፋዊ ውበትን የያዙ ትረካዎች ብዙ ቦታዎች ላይ እናገኘዋለን። ለምሳሌ “ብዙ ጊዜ ባልተደፈረው” ጸጥ ያለ የቀበና ጫካ ውስጥ የኖረችውን ውቧን የእናቱን አክስት ጥሩነሽ ብርሌን ሲገልጽ ለጉድ ነው። ደጃዝማች ፍቅረማሪያም ከጣሊያኖች ጋር ከወ/ሮ ብርሌ ግቢ ውስጥ ሆኖ ሲዋጋ፤ ወ/ሮ ብርሌን አንዳርጋቸው በሚከተለው መልኩ ነበር የገለጻት። ገጽ 167
“ከላይ የለበሰችው ሸሚዝ ነጭ ነው። የቀይ ጽጌረዳ ምስል ጣል ጣል ያለበት። ከታች ሱሪ ታጥቃ ነበር። ትከሻዋ ላይ ወፍራም ሻርፕ ጣል አድርጋለች ። ሱሪዋ ጉልበቷ ድረስ በሚደርሰው ረጅም ጥቁር የቆዳ ቦት ጫማ ውስጥ ገብቷል። ሸሚዟን ሱሪዋ ውስጥ አስገብታ በቀጭን ቀበቶ ወገቧ ላይ አስራዋለች። ከዝሆን ጥርስ በተሰራ የሲጋራ ማጨሻዋ ላይ የሰካችውን ሲጋራ ከንፈሯ ላይ አድርጋ ጢሱን ቡን እያደረገች ነበር ትእዛዝ የምትሰጠው”
ለስነ ጽሁፍ ውበት እንዲህ የሚጨነቀው አንዳርጋቸው ግን ለእንዲህ አይነቱ ወፈር ያለ መጽሀፍ  ለማቃቀር እንዲመች መጠቁም (Index) እንዲኖረው አለማድረጉ መጽሃፉን ወደገባያ ለማውጣት ችኮላ ወይም ጥሩ ገምጋሚ አጥቶ ነው ወይ ያስብላል።
 
ያ ትውልድ እንዴት ይጻፍ?
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በአንዳፍታ ወጋቸው እንደሚያወጉን “ግለ ታሪክ መጻፍ ምክንያቱ እወቁኝ ነው”። ግለ ታሪክ ደግሞ የሚጻፈው፤ ራስን ወደኋላ በመመለስ ኑባሬያዊ (በነበር) በመሆኑ ነገሮችን ከአዕምሮ ብልጭታ እያፈለቁ ሲጽፉ፤የሚዘለሉ ማስረጃዎች ወይም ደግሞ የሚቀነባበሩ (Reconstructed) አስረጂዎች ይኖራሉ። ፕ/ር ጌታቸውም ይህንኑ “ ላንዳፍታ ላውጋችሁ “ ባሉት ግለ ታሪካቸው ላይ ይጠቅሱታል።
ከላይ እንደተቀመጠው የአንዳርጋቸው መጽሀፍ እስካሁን በዚያ ትውልድ ከተጻፉ መጽሀፍቶች ሁሉ ሌላውን ሙሉ ለሙሉ የማይወቅስ የማይከስ፤ ለጥፋቱ ምክንያት ፍለጋ (Apologetic) የማይባክንና ሃላፊነትን የሚወስድ ሆኖ ሳለ ከብዙ አቅጥጫ ብዙ ትችትን አስተናግዷል። አንዳንዶች እንዲያውም ጸጸቱን በታላቅ ትህትና የጻፈውን ሰው ባልዋለበት እያዋሉ መውቀስ መክሰስ ለምን እንደፈለጉ ግራ እስኪገባ ድረስ የሚዲያ ዘመቻ አድርገውበታል።
እንደ አንዳርጋቸው አይነት የሞት አፋፍ ላይ ቆመው እውነትን ይቅር ባይነትን ከሚያውቁትና ከሚያስታውሱት ተነስተው በግልጽ እንዳይጽፉ የሚከላከል አለፍ ሲልም የሚያንጓጥጡ ሚዲያና ምሁራን ለዚህ ትውልዱ ከዚያ ትውልድ ምን እንዲጻፍለት እንደሚፈልጉ አብረው ቢነግሩን መልካም ነበር። ካለበለዚያ የቤተሳባቸውና የራሳቸውን የግል ህይወት ለበርካታ ችግር አጋልጠው በግልጽነትና በታማኝነት የሚጽፉ ሰዎችን እየኮረኮሙ ማስቀመጥ ጥቅሙ ምን ይሆን ያስብላል። እርግጥ ነው አንዳርጋቸው ብዙ “ኩርኩም” እየጠጣ ያደገ “ጠንካራ” ስብዕና ያለው ሰው ስለሆነ ይህ ምንም ላይመስለው ይችላል። የሌሎችን ቅስም ግን ይሰብራል።
ይህ ደግሞ ትውልድ እንደተደናገረ ይቅር የሚል ክፋት ብቻ ነው የሚሆነው። ስለዚህ እነአንዳርጋቸውም ይናገሩ፤እኛም አንደናገር።
Filed in: Amharic