>

ኦሮምኛን  የፌደራልና የአዲስ አበባ የስራ ቋንቋ የማደረግ እድሎችና ችግሮች!!! (አብርሃም ዓለሙ)

ኦሮምኛን  የፌደራልና የአዲስ አበባ የስራ ቋንቋ የማደረግ እድሎችና ችግሮች!!!
አብርሃም ዓለሙ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሀገራችንን የፖለቲካ አየር እያጨናንነቁ ካሉ ጥያቄዎች (ምናልባትም ከኦሮሞ ብሄርተኞች የ “አዲስ አበባ ባለቤትነት” (ፊንፊኔን ኬኛ)፣ እና የደቡብ (ሲዳማ፣ ወላይታ) የክልልነት ጥያቄ ቀጥሎ አናጋጋሪ የሆነ) አንዱ፣ “ኦሮሚኛ የፌደራልና አዲስ አበባ የመንግስት የስራ ቋንቋ ይሁን፤” የሚለው ነው፡፡ በርግጥ ጥያቄው በአለፍአገደም አንዳንዴ ጠንከር ብሎ፣ ሌላ ጊዜም እንደዋዛ ሲነሳ የኖረ ነው፡፡ ሰሞኑን ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር አዲሱን የትምህርት ፍኖተ-ካርታ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በርካታ የኦሮሞ ብሄርተኞች ፍኖተ-ካርታውን ላለመቀበል እንደ አንድ የመደራደሪያ ነጥብ ማስቆጠሪያ እያደረጉት ነው፡፡
ለመሆኑ አንድ ቋንቋ የአንድ ሀገር የስራ ቁንቋ ነው ወይም ይሁን ሲባል ምን ማለት ነው? ኦሮሚኛን (ሌሎችንም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች) በተጨማሪ የኢትዮጵያ ፌደራል ሀገረ-መንግስት የስራ ቋንቋ ማድረግስ ለኦሮሞና ለሌላውም የሀገሪቱ ህዝብ የሚያመጣው እድልና የሚያስከትላቸው ተግዳሮቶችስ ምንድን ናቸው? ይህን ለማድረግ በቅድሚያ ሊሟሉ የሚገባቸው ቅድመ-ሁኔታዎችስ ምን ምን ናቸው? በዚህ ረገድ ከሌሎች ሀገራት ልንማራቸው የሚገቡ ጉዳዮችስ ምንድን ናቸው? በዚህች አጭር ጽሁፍ እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችሉ የውይይት መነሻ ሃሶቦችን ለማንሳት ነው የምሞክረው፤ የጉዳዩን ሰፊና ጥልቅ ጥናትና ምክክር ፈላጊነት ለማሳየት ያህል፡፡
የአንድ ሀገር የስራ ቋንቋ (Official Language) ምንድን ነው? 
በአማርኛ “የመንግስት የስራ ቋንቋ፣” በእንግሊዝኛ “ኦፊሻል ላንጉዌጅ” (ስቴት ላንጉዌጅም ይባላል) የሚባለው፣ በአንድ ሀገረ-መንግስት ውስጥ በህግ ልዩ እውቅና የተሰጠው ቋንቋ ነው፡፡ የአንድ ሀገር የስራ ቋንቋ በሀገሪቱ  ህገ-መንግስት ወይም ሌላ ህጋዊ አስተዳደራዊ አካል እውቅና የተሰጠውና በሁሉም መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች ውስጥ አገልግሎት የሚሰጥበት(በትምህርት ቤቶች፣ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ ጣቢያ፣ ሆስፒታል፣ ወዘተ)፣ የመንግስትና የመንግስት ስራ ማከናወኛ (ፓርላማው የሚነጋገርበት፣ የመንግስት ህግጋት የሚደነገጉበትና የሚጻፉበት፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች መመሪያ የሚያወጡበት፣ የኮንትራት ስምምነት ውሎች የሚፈረሙበት፣ ወዘተ) ቋንቋ ነው።
የአንድ ሀገር ህዝብ በርካታ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች ሲኖሩት (ለምሳሌ፦ በኢትዮጵያ 89፣ በአሜሪካ 300፣ በናይጄሪያ 520፣ ካናዳ 145፣ ደቡብ አፍሪካ 35 ወይም ከዚያም በላይ)፣ የመንግስት የስራ ቋንቋ ግን ከግማሽ በላይ በሚሆኑት የዓለም ሀገራት ውስጥ በህግ የተወሰነ/ኑ አንድ ወይም ከአንድ በላይ ነው/ናቸው፡፡ ለምሳሌ ናይጄሪያ ውስጥ የሚነገሩ ከ520 በላይ ቋንቋዎች ሲኖሩ፣ የሀገሪቱ የስራ ቋንቋ ግን ሀገርኛ ያልሆነውና የቅኝ ገዢዎች ቋንቋ የሆነው እንግሊዝኛ ነው፤ በርግጥ ከ1951 እስከ 1967 ድረስ የስራ ቋንቋ የነበረው በሀገሪቱ ውስጥ በስፋት የሚነገረውና የሰሜናዊ ግዛቶች ቋንቋ የነበረው ሃውሳ ነው፡፡ ዩ ኤስ ኤ፣ ዩ ኬ (United Kingdom), አውስትራሊያ፣ ኒውዚላንድ የመሳሰሉት ሀገራት ደግሞ በሀግ የተወሰነ የስራ ቋንቋ (ኦፊሻል ቋንቋ) የላቸውም፡፡ እነዚህ ሀገራት በህግ የተደነገገ ኦፊሻል ቋንቋ የላቸውም ማለት፣ የሀገራቱ መንግስታት የሚጠቀሙባቸው የየራሳቸው መደበኛ የስራ ቋንቋ የለቸውም ማለት አይደለም፤ በህገ-መንግስታቸው እውቅና የተሰጠው አንድ የተወሰነ ቋንቋ የለም ለማለት ብቻ ነው፤ ለምሳሌ በአሜሪካ እንግሊዝኛ በተግባር (de facto) መደበኛና የጋራ ቋንቋ ነው፡፡ የነዚህ ሀገራት የቋንቋ አጠቃቀም ህብረ-ብሄራዊ ልሳነ-ብዝሀነት (official multilingualism) የሚባል ነው፡፡ ይኸውም ማንኛውም ግለሰብ በሚመርጠውና በሚችለው ቋንቋ መንግስታዊ ግልጋሎት የማግኘት መብት እንዳለውና በሀገሪቱ ውስጥ የሚነገሩ ሁሉም ቋንቋዎች እኩል መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡
አንድ ቋንቋ የስራ ቋንቋ ነው ማለት በሀገሪቱ ወስጥ ተቀዳሚው ቋንቋ ወይም በአብዛኛው ህዝብ የሚነገር ነው ማለትም ላይሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ እንግሊዝኛ የህንድና ፓኪስታን ኦፊሻል ቋንቋ ቢሆንም፣ በብዙሃኑ የሁለቱ ሃገራት ህዝቦች የሚነገር ግን አይደለም፡፡ ህንድ እንግሊዝኛን ጨምሮ 23 የስራ ቋንቋዎች ሲኖሯት፣ ሂንዲ ተቀዳሚ የስራ ቋንቋ መሆኑን ደንግጋለች፡፡ ደቡብ አፍሪካ 12 እኩል ስታተስ የተሰጣቸው የስራ ቋንቋዎች አሏት፤ ከነዚህ ውስጥ የደቡብ አፍሪካ እንግሊዝኛ (South African English) ተቀዳሚው ቋንቋ ነው (የፓርላማው መነጋገሪያ)፡፡ የመካከለኛው ደቡብ አሜሪካ ሀገር የሆነችው ቦሊቪያ ህገ-መንግስት ደግሞ ሁሉንም ሀገርኛ ቋንቋዎች ዘርዝሮ (ወደ 36 የሚደርሱ) የስራ ቋንቋ መሆናቸውን ይደነግጋል (ቁጥሩ በአሁኑ ጊዜ የጠፉ ቋንቋዎችንም ይጨምራል)፤ ከነዚህ መካከል ስፓኒሽ ተቀዳሚ ነው፡፡
ከአንድ በላይ ቋንቋዎችን በስራ ቋንቋነት በመጠቀም ረገድ በስፋት ተጠቃሽ ከሆኑት ሀገራት መካከል አንዷ ስዊዘርላንድ ናት፡፡ 8. 42 ሚሊዮን ጠቅላላ የህዝብ ብዛት (2017)፣ እና በዓለም ከፍተኛ የኤኮኖሚ እድገት (ከፍተኛ የጠቅላላ የኤኮኖሚ ምርት የነፍስ-ወከፍ ድርሻ፣ GDP Per Capita) አላቸው ከሚባሉት ሀገራት ተርታ የምትመደበው ስዊዘርላንድ፣ 4 ቋንቋዎችን የኮንፈደሬሺኑ ኦፊሻል ቋንቋዎች አድርጋ ትደነግጋለች (German, French, Italian, and Romansh፣ ከአራተኛው በስተቀር ሁሉም እኩል ስታተስ ያላቸው ናቸው)፤ 26ቱ የኮንፈደሬሽኑ አባላት (ካንቶን) የየራሳቸው የስራ ቋንቋ አላቸው፡፡
የስራ ቋንቋ ምርጫ ከላይ ለማመልከት እንደተሞከረው ከዓለማችን ጠቅላላ ሀገራት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አንድ ብቻ የስራ ቋንቋ ያላቸው ሲሆኑ፣ የተቀሩት ደግሞ ከአንድ በላይ ቋንቋዎችን በመንግስት የስራ ቋንቋነት መርጠው የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ ለመሆኑ የአንድን ሀገር የመንግስት የስራ ቋንቋ በመምረጥና መወሰን ሂደት ውስጥ ሊከናወኑ የሚገባቸው ተግባራት ምንድን ናቸው?
1/ ቋንቋ መረጣ 
አንድን ቋንቋ ወይም ከአንድ በላይ ቋንቋዎችን የአንድ ሀገረ-መንግስት የስራ ቋንቋ እንዲሆን መምረጥ የመጀመሪያው ተግባር ሲሆን፣ ይህም ፖለቲካዊ ሂደት ነው፡፡ ለስራ ቋንቋነት የሚመረጥ ቋንቋ የሀገሪቱን ህዝብ የሚያስማማና ብሄራዊ አንድነቱን ለማጠናከር የሚያስችል፣ ለኤኮኖምሚው መነቃቃት የሚረዳ መሆን አለበት፡፡ ይህ ካልሆነና ተገቢ ያልሆነ ቋንቋ መምረጥ የአንድን ሀገር ብሄራዊ አንድነት ከማጠናከር ይልቅ ወደ ማፍረስ/መበታተን ሊያመራ ይችላል፡፡
2/ቋንቋውን መደበኛ ማድረግ
አንድን ለሀገረ፟መንግስት ቋንቋነት የተመረጠ ቋንቋ ስራ ላይ ከማዋል አስቀድሞ በጽህፈት ሰርዓቱ፣ በሰዋሰው ህግጋቱ፣ በስነፍቺ ረገድና በሌሎችም ዘርፎች መደበኛ ቅርጽ እንዲኖረው (standardized) ማሳደግ ይገባል፡፡ የቋንቋውን መዛግብተ-ቃላት ከማዘጋጀት ጀምሮ፣ የሰዋሰውና ስነፍቺ ህግጋቱን በስፋት ማዘጋጀትና ማሰራጨት ያስፈልጋል፤ ውዥንብር ለማስወገድ፡፡
3/ ማስፋፋት
ይሄ የቋንቋውን ግልጋሎት ከመደበኛው የእለት-ተእለት መግባቢያነት ወደ ልዩ ልዩ ሙያዎች ቋንቋነት የማሳደግ ሂደትን ይመለከታል፤ የህክምና፣ የትምህርት፣ የቴክኒክ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቋንቋ እንዲሆን ማብቃት፣ ማዘመን ማለት ነው፡፡ አንድ ቋንቋ በከፍተኛ ደርጃ የረቀቁ ሃሳቦችንና ተግባራትን መግለጽ ሳይችል የስራ ቋንቋ መሆን አይችልም፡፡
4/ ቅቡልነት
አንድ ቋንቋ የአንድ ሀገረ-መንግስት የስራ ቋንቋ መሆን ይችል ዘንድ የማሳድግ፣ የማብቃት ጥረቶች ከተከናወኑ በኋላ ቀጣዩ ተግባር፣ ህዝቡ ቋንቋውን በስራ ቋንቋነት እንዲቀበለውና እንዲጠቀምበት ለማድረግ ለምክክርና ውይይት ማቅረብ፣ በመጨረሻም ለውሳኔ-ህዝብ (referendum) አቅርቦ ማስወሰን ነው፡፡ አንድን ቋንቋ እንዲገለገልበት የሚታሰበው ህዝብ ሳይፈቅደውና ሳይቀበለው በፖለቲካ ውሳኔ ሊጫንበት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ቋንቋውን በስራ ቋንቋነት መቀበል የሚያስገኘውን ማህበረ-ፖለቲካዊ ፋይዳዎች ለህዝቡ በማስተማር፣ በፈቃዱና በምርጫው (በድምጹ) እንዲወስን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
እዚህጋ አማርኛ የኢትዮጵያ የስራ ቋንቋ የሆነበት ሂደት ከላይ ከተገለጸው ሂደት ውጭ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ አማርኛ በታሪክ አጋጣሚ ከበርካታ ዓመታት በፊት፣ በፍቅርና በጉልበት ያደገ ቋንቋ ነው (አንድ አስተማሪዬ እንዳለው)፡፡ በመሆኑ ዛሬ ላይ ቆመን የደሞክራሲ ስርዓት በሚጠይቀው መርህና ህግ ልንዳኘው አንችልም፤ ህግ ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ ሊተገበር አይቻለውም፡፡
ኦሮሚኛን የስራ ቋንቋ የማድረግ ቅድመ-ሁኔታዎች
ከላይ የተዘረዘሩትን የአንድን ሀገረ-መንግስት የስራ ቋንቋ በመምረጥና መወሰን ሂደት ውስጥ ከግንዛቤ ሊገቡ የሚገቡ፣ ወይም ሊሟሉ የሚገባቸው ቅድመ-ሁኔታዎች አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል በተለይ በሀገራችን ኦሮሚኛንና ሌሎችንም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የስራ ቋንቋ ለማድረግ ከመወሰን በፊት የሚከተሉትን ዓበይት ቅድመ-ሁኔታዎች መሟላት ያስፈልጋል፡፡
1/ ህገ-መንግስቱን መቀየር
የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት፣ በአንቀጽ 5፣ ተራ ቁጥር 1-3 የሚከተሉትን ይደግጋል፤
1/ ማንቸውም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በእኩልነት የመንግስት እውቅና ይኖራቸዋል፡፡
2/ አማርኛ የፌዴራሉ መንግስት የስራ ቋንቋ ይሆናል፡፡
3/ የፌዴሬሽኑ አባሎች የየራሳቸውን የስራ ቋንቋ በህግ ይወስናሉ!
በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ 5፣ ተራ ቁጥር 2 እንደተደነገገው፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት የስራ ቋንቋ አማርኛ ነው፡፡ በመሆኑም የፊዴራላዊው መንግስት የስራ ማከናወኛ፣ የፓርላማው መምከሪያ፣ የህግጋት መደንገጊያና ከፌዴሬሽኑ አባል መንግስታት ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶች ሁሉ ማከናወኛ ብቻ ሳይሆን፣ በመላው ሀገሪቱ ውስጥ ዜጎች መንግስታዊ ግልጋሎቶችን ሊያገኙበት የሚገባ ቋንቋ ነው፡፡ ለምሳሌ፦ አንድ ኢትዮጵያዊ መቀሌ፣ አሶሳ፣ አዋሳ፣ ነቀምት ወይም ጂማ ውስጥ ጉዳዩን ለማስፈጸም መንግስታዊ መስሪያ ቤት ሄዶ፣ ጉዳዩን በአማርኛ (ወይም በሌላ በሚችለው ቋንቋ) አስረድቶ አገልግሎት የማግኘት ህገ መንግስትታዊ መብት አለው፡፡ በእርግጥ ይህ መብት ተግባራዊ እየሆነ ነው ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ አማርኛ በመላው ሀገራችን ውስጥ፣ በሁሉም ክልሎች ከየክልሉ የስራ ቋንቋ በተጓዳኝ የስራ ቋንቋ ሆኖ የማገልገሉ ተገቢነት ግን አጠያያቂ አይደለም፡፡
ስለዚህ ኦሮሚኛን (ሌሎችንም) ተጨማሪ የፌዴራል መንግስት የስራ ቋንቋ ለማድረግ የህገ መንግስቱን አንቀጽ 5 መቀየር/ማሻሻል ተቀዳሚው ተግባር ነው፡፡ ይህ ሲቀየር ደግሞ ሌሎችንም ድንጋጌዎች፣ በተለይም ኢትዮጵያን የዜጎቿ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩባት፣ ፍትህና እኩልነት የሰፈነባት፣ በዴሞክራሲ መርሆች የምትመራ ሀገር ለማድረግ እንቅፋት የሆኑትን ብሄር-ተኮር (ዘውጌ) ድንጋጌዎች ሁሉ መቀየር ይገባል፡፡ “እኛ የኢትዮጵያ ብሄ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች” የሚለው አገላለጽ፣ “እኛ የኢትዮጵያ ህዝብ” በሚለው አንድነትንና ዜግነትን መሰረት በሚያደርግ ህገ መንግስታዊ አገላለጽ መተካት አለበት፡፡
አማርኛ በታሪክ አጋጣሚ በመላው ኢትዮጵያ የሚነገር የጋራ ቋንቋ (lingua franca) ለመሆን የቻለ ነው፤ የንግድ፣ የትምህርት፣ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት፣ የባህል፣ ወዘተ። ቋንቋ፡፡ ይህን ቋንቋ መማርና መጠቀም መቻል ብዙ እድሎችን ይሰጣል፤ አለመቻል ደግሞ እድል ይዘጋ፡፡ አማርኛን መናገርና መጻፍ የሚችሉ ኢትዮጵያዊያን (የውጭ ሀገር ዜጎችም ጭምር)፦ የየትኛውም ብሄር አባል ወይም ቋንቋ ተናጋሪ ቢሆኑም፤ በሀገሪቱ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ከፍተኛ ደርጃ ላይ መድረስ መቻላቸውን መካድ አይቻልም፡፡ ይህን እውነታ ለመቀበል ዛሬ በሀገራችን ልዩ ልዩ “ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች” ስም የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞችን ይመለከቷል፡፡ ባንጻሩ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ሲካሄድ በቆየው ዘውጌ ፖለቲካ ምክንያት አማርኛን መማርና መናገር ባለመቻላቸው ብቻ የስራ እድል የጠበባቸውን የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ በእዚህ ረገድ ከሰሞኑ የተደረገው የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ (ፍኖተ ካርታ) እና አማርኛን (እንዲሁም ተማሪዎች የሚመርጡትን ሌላ የኢትዮጵያ ቋንቋ) በሁሉም ክልሎች ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እንዲሰጥ የተወሰነው ውሳኔ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ኦሮሚያን በመሳሰሉ ከፍተኛ የተማሪ ቁጥር ላላቸውና የአማርኛ ትምህርት ገደብ ተጥሎባቸው ለነበሩ ክልሎች፣ ይህን የፌዴራል የስራ ቋንቋ ማስተማርና የተማሪዎቹን ክሂሎት ማዳበር መቻል፣ የወጣቱን የስራ እድል በማስፋትና የስራ አጡን ቁጥር በመቀነስ ረገድ አዎንታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡
2/ የሀገሪቱን ኤኮኖሚ ከግንዛቤ ማስገባት 
የአንድ ሀገር ኤኮኖሚ፣ የቋንቋ አጠቃቀምና እድገት በእጅጉ የተቆራኙ ናቸው፤ አንደኛው ለሌላው እድገትና ውድቀት አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ፍሎሬን ኮልማስ የተባለው የማህበራዊ ስነልሳን ተመራማሪ፣ “Language and Economy” (1992) በሚል ርእስ ባሳተመው መጽሃፉ እንዳመለከተው፣ አንድን ቋንቋ መጠቀምና ማሳደግ ከፍተኛ ወጪና ኢንቨስትመንት ይጠይቃል፡፡ ይህም በምላሹ ለኤኮኖሚው የሚያስገኘው ተጨባጭ ትርፍ ሊኖረው ይገባል፤ ያለበለዚያ በሀገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ጫና ቀላል አይሆንም፡፡ በዚህም ምክንያት በኤኮኖሚ ያደጉና የበለጽጉ ሀገራት (እንደ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ስዊዘርላንድ) ካልሆኑት በቀር እንደ ኢትዮጵያ ላሉት ሀገራት ቋንቋዎቻቸውን እንደልባቸው ማሳደግና ማስፋፋት ቀላል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን የስራ ቋንቋ ከአንድ ወደ ሁለት ወይም ከዚም በላይ ለማሳደግ ከመወሰን በፊት የሀገሪቱ ኤኮኖሚ ውሳኔው የሚያስከትለውን ወጪ መሸከም መቻሉን፣ በምላሹም ለኤኮኖሚው እድገት የሚያበረክተው አንዳች አስተዋጽኦ ሊኖር እንደሚችል ማረጋገጥ ይገባል (Economics of Language)፡፡ እንግሊዝና አሜሪካ ለእንግሊዝኛ እድገትና መስፋፋት የሚያወጡትን ወጪና በምላሹም ቋንቋው ለሀገራቱ ብልጽግናና ሀያልነት የሚጫወተውን ሚና ያስታውሷል፡፡ በሀገራችን በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ የሚነገረው/ሩትና ለስራ ቋንቋነት የተሻለ አቅም ያለው/ላቸው የጋራ ቋንቋ/ዎች የትኛው/ኞቹ ነው/ናቸው ብሎ መጠየቅ ያሻል፡፡ የአንድ ሀገር የስራ ቋንቋዎች ሲበዙ፣ ቋንቋዎቹን ለማብቃትና ለማዘመን፣ ለማሳደግ፣ ለማስፋፋት፣ ለትርጉም፣ ለህትመት፣ ለስርጭት (በሬዲዮ፣ ቲቪ፣ ጋዜጣ፣ ኢንተርኔት) የሚያስፈልገውን ወጪ ከግምት ማስገባት የግድ ነው፡፡
3/ ኢትዮጵያዊነትንና የኢትዮጵያዊነትን የጋራ እሴቶች መቀበልና ማጠናከር፤
ወዳጄ ገለታው ዘለቀ፣ ሀገራችንን አሁን ከገባችበት ማህበረ-ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ለማውጣት “አዲስ ኪዳን መግባት ይኖርብናል”፤ የሚለው ሃሳብ አለው፡፡ ኢትዮጵያ የተሻለችና ለሁሉም ዜጎቿ የምትበቃ፣ የሁሉም ዜጎች ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነት፣ ታሪክ የሚከበርባት፣ ሉዓላዊነቷና ዘላቂ ህልውናዋ የሚረጋገጥባት፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትህና እኩልነት የሰፈነባት የበለጸገች ሀገር ትሆን ዘንድ፣ ኢትዮጵያዊነትንና የጋራ እሴቶቻችንን ከመቀበልና ማጠናከር ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በእምነት/ሃይማኖት፣ በመኖሪያ አካባቢ የምንለያይ ብንሆንም፣ የኢትዮጵያዊነታችን መሰረት የሆኑና እንደ አንድ ሀገር ህዝብ በሰላማዊ አብሮነት እንድንኖር የሚያደርጉን እጅግ በርካታ የጋራ እሴቶች እንዳሉን መካድ አይቻልም (ዛሬ ዛሬ አንዳንድ ጽንፈኛ ብሄረተኞች እንደሚሉት)፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን፣ አንዲት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገረ፣ የሰው ዘር፣ የአዝርእት፣ የሃይማኖት፣ የጥንታዊ ስልጣኔ፣ የእውቀት ምንጭ የሆነች ሀገር፣ የአውሮፓን ቅኚ ገዢ ሀይላት በጀግንነት የመከላከልና ድል ነስቶ የመመለስ አኩሪ ታሪክ/የነጻነት ተምሳሌት፣ የብዝሃ ባህል፣ የራሷ ፊደል/ጽህፈትና የዘመን/ጊዜ አቆጣጠር ስርዓት ባለቤት፣ … የሆነች የጋራ ሀገር ያለን ህዝብ ነን፡፡ በየጊዜው የምንፈጥራቸውና እስከዛሬም ያልተፋታናቸው ብዙ ችግሮች ቢኖሩብንም፣ እንደ አንድ ሀገር ህዝብ (ኢትዮጵያዊያን) የሰላማዊ አብሮነታችን መሰረት የሆኑ እነዚህን የመሳሰሉ የጋራ እሴቶች እንዳሉን ተቀብለንና አጠናክረን፣ ሀገራችንን ከተዘፈቀችበት ፈርጀ ብዙ ትብታብ ለማውጣት ተባብረን መስራት ግድ ይለናል፡፡ ይህን ለማድረግም ነገሮችን በቀናነት ለማየትና ነባር ቁርሾዎችን/ቅሬታዎችን በሰላማዊ መንገድ ፈትተን፣ ኢትዮጵያዊነታችንና አንድነታችንን ለማደስ፣ ለማጠናከር በአዲስ መንፈስ ቃል መግባት፣ ተግባራዊ እርምጃዎችንም መውሰድ ይገባናል፡፡ ከበጎውና መልካሙ የሀገራችን ገጽታ/ታሪክ ይልቅ፣ ክፉውን እየነቀስን፣ እየደጋገምን ማላዘን አይበጀንምና፡፡
በዚህ ረገድ ኦሮሚኛና ሌሎቹም የሀገራችን ቋንቋዎች ከጥንታዊ የስልጣኔ ቅርሶቻችን አንዱ በሆነውን የኢትዮጵያን ፊደል/የጽሁፍ ስርዓትና የቀን አቆጣጠር (ካለንደር) መጠቀማቸው ጉልህ ሀገራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ባለፉት ከ 20 በላይ ዓመታት የኦሮሞ ማህበረስብና ኦሮሚኛ በብሄረተኞች ፖለቲካዊ ውሳኔ የተጫነበትን የባእዳን፣ የቅኝ ገዢዎች የላቲን ፊደል (ቁቤ) አስወግዶ፣ ወደ ሀገራዊው የኩራት ምንጭ የኢትዮጵያ ፊደል እንዲመለስ ማድረግ ይገባል፡፡ ይህ እንዲሆን ተደጋጋሚ ጥያቄዎችና በርካታ ምሁራዊ ክርክሮች እንደነበሩ ይታወቃል፤ ለአብነት፣ የጌታቸው ሀይሌ፣ ባዬ ይማም፣ አበራ ሞላ፣ ፍቅሬ ቶለሳ ስራዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ባንጻሩ ኦሮሚኛ በኢትዮጵያ ፊደል ሊጻፍ እንደማይችል፣ ቢጻፍ እንኳን በቋንቋው የሚደረግን አንደበታዊ ተግባቦት በትክክል በጽሁፍ ለመወከል እንደማያስችል የሚከራከሩ ብዙ የኦሮሞ ብሄርተኛ ምሁራንም/ሊሂቃን አሉ፡፡ ከእነዚህ የኢትዮጵያ ፊደል/የጽሁፍ ስርዓት ኦሮሚኛን በመጻፍ ረገድ እንዳሉበት ከሚጠቀሱ “ችግሮች” መካከል የሚከተሉት በተደጋጋሚ ይጠቀሳሉ፤
• የኦሮሚኛን አንዳንድ ድምጸ ልሳናት የሚወክሉ ሆሄያት የሉትም፤ ለምሳሌ “ቂቤ” የሚለው የአማርኛ ቃል አቻ የኦሮሚኛ ፍቺ በኦሮሚኛ ለመጻፍ /“dha”/ የሚለውን ድምጽ የሚወክል ፊደል የለም (dhadhaa)፤
• በኦሮሚኛ የሚጠብቁና የሚረዝሙ ድምጸ ልሳናትን የሚወክሉ ምልክቶች የሉትም፤
• በኢትዮጵያ ፊደል ኦሮሚኛን ታይፕ ማድረግ ያስቸግራል፤ ውድም ነው፤
• የኢትዮጵያ ፊደላት ብዙ በመሆናቸው ለህጻናት ለማስተማር ያስቸግራል፡፡
ከላይ የተጠቀሱትና የመሳሰሉት “ችግሮች” ኦሮሚኛን በራሳችን የኢትዮጵያ ፊደል ከመጻፍ ይልቅ፣ በባእዳን ፊደል (ላቲን) ለመጻፍ ሰበብ እንጂ ዋና ምክንያት አይደሉም፡፡ በስፋት እንደሚታወቀው ዋናው ምክንያት፣ “ኢትዮጵያ ባለፉት 150 ዓመታት ኦሮሞን በቅኝ ግዛት ገዝታለች፤” ወይም “ኢትዮጵያዊነት በሀይል ተጭኖብናል፤” የሚለው በኦነግ የሚመራው የኦሮሞ ብሄርተኞች ፖለቲካዊ ትርክት ነው፡፡ ይኸውም የኦሮሞን ማህበረሰብና ባህል ከኢትዮጵያ የጋራ ታሪክና ስልጣኔ ለመነጠል የሚደረግ ሙከራ አንዱ አካል ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፊደል ኦሮሚኛንም ሆነ ሌሎችን የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ለመጻፍ ከባእዳኑ ላቲን ይልቅ ተመራጭ መሆኑን ለማረጋገጥ ብዙ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል፤
• በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ፊደል የኢትዮጵያዊያን ብሄራዊ ማንነትና ኩራት ምንጭ መሆኑን ልብ ይሏል (የአፍሪካ ብቸኛው ፊደልና አህጉራዊ የኩራት ምንጭም ጭምር)፤
• የኢትዮጵያ ፊደል ከ 120 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን፣ መላውን መጽሃፍ ቅዱስ (ብሉይና አዲስ ኪዳን) ወደ ኦሮሚኛ መተርጎምና ማሳተም ያስቻለ ፊደል ነው (ኦነሲሞስ ነሲብ 1893 እአአ፤ ኦነሲሞስ የክርስትና ስሙ ሲሆን፣ ወላጆቹ ያወጡለት ስም ሂካ ይባላል፤ “ተርጓሚ፣ ፈቺ” ማለት ነው፤ ስምን መላእክት ያወጡታል እንዲሉ)፤
• ኦነሲሞስ ነሲብና አስቴር ገኖ፣ በኢትዮጵያ የስነጽሁፍ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ ሊባል የሚችለውን የንባብ ማስተማሪያ መጽሃፍ በኦሮሚኛ፦ “ጀልቀበ ዱቢሳ” (የባብ መጀመሪያ) በሚል ርእስ ያሳተሙት በኢትዮጵያ ፊደል ነው (1894 እአአ)፤
• ኦነሲሞስ ነሲብ የሉተርን “ካቴኪስሞስ” ጨምሮ 6 ያህል መጻህፍትን ወደ ኦሮሚኛ ተርጉሞ አሳትሞበታል፤ በኢትዮጵያ ፊደል፤
• ኦነሲሞስና አስቴር ገኖ ዛሬ “የሚወክለው የኢትዮጵያ ፊደል የለውም፤” የሚሉትንና በላቲን “dha” የሚጻፈውን ድምጽ፣ ከኢትዮጵያ ፊደል “ደ” ን ወስደውና አሻሽለው “ዸ” በማድረግ ያለ ምንም ችግር ጽፈውበታል (ዸዻ፣ በዻሳ፣ ዻበሳ)፤ በ 1991 በላቲኑ እስከተተካበት ድረስ ሌሎችም በርካታ የኦሮሞ ጸሃፍት (ለምሳሌ ቄስ ደፋ ጀሞን ያስታውሷል) እና መላው የኦሮሞ ማህበረሰብ ሲጠቀሙበት ኖረዋል፡፡ የኢትዮጵያን ፊደል በላቲን የመተካቱ ውሳኔ በርካታ ኦሮሞዎችን ማንበብና መጻፍ ከመቻል ወደ አለመቻል የለወጠ እንደሆነም ያስታውሷል፡፡
• የላቲን ፊደል (ቁቤ) ኦሮሚኛን ለመጻፍ እኮኖሚያዊ አለመሆኑና ቀላል አለመሆኑንም ልብ ይሏል፤ አስረጅ፦
Lammaa Guuyyaa (13)– ለማ ጉያ (4)፤ dhadhaa (7)– ዸዻ (2)፤ Taaddasaa Birruu (15)– ታደሰ ብሩ (5)፤ ይህ ንጽጽር በረጃጅም መጻህፍት ረገድ ሲታሰብ እኮኖሚያዊ ልዩነቱንና አክሳሪነቱን አለመገንዘብ አይቻልም፡፡
• የላቲኑን ፊደል (ቁቤ) መደበኛ ለማድረግ (standardize) አስቸጋሪ መሆኑን በርካታ ጥናቶች ያሳያሉ (በቅርቡ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የቀረበን አንድ ጥናት ያስታውሷል)፤
• የላቲኑ ጽሁፍ ስርዓትና እንግሊዝኛ አንድ ፊደል የሚጠቀሙ ቢሆንም፣ በላቲን ፊደል ኦሮሚኛንና እንግሊዝኛን መጻፍና ማንበብ ተመሳሳይ አጠቃቀም ወይም የድምጽ ውክልና ያለው ባለመሆኑ፣ ተማሪዎችን ለማስተማር እጅግ ያስቸግራል፤ (/x/ በኦሮሚኛው ቁቤ /ጥ/ የሚለውን ድምጽ ይወክላል፤ “box/ቦክስ” በኦሮሚኛ ሲነበብ “ቦጥ” ተብሎ ሊነብብ ይችላል፡፡
• ከሁሉም በላይ ቋንቋዎቻችንን በራሳችን የኢትዮጵያ ፊደል መጻፍ ለጆቻችንን ማንበብና መጻፍ ለማስተማር ቀላል ያደርገዋል፤ ተደጋጋፊ በመሆናቸው፡፡ በሶስት የተለያዩ ፊደላትና የጽሁፍ ስርዓት (በላቲን/ቁቤ፣ እንግሊዝኛና በኢትዮጵያ) ማስተማር ልጆቹን ግራ ያጋባቸዋል፡፡ ልጆቻችን በኢትዮጵያዊነታቸውና በሀገራቸው ታሪክና ስልጣኔ የሚኮሩ፣ ሀገራቸውን ኢትዮጵያን የሚወዱ፣ ሉዓላዊነቷንና ዳርድንበራዊ ምልዓቷን የሚያስጠብቁ፣ የሚያሳድጉና የሀገር ፍቅር ስሜት በልባቸው ሰንቀው የሚያድጉ መልካም ዜጎች ይሆኑ ዘንድ፣ በሀገራቸው ፊደል መማራቸው፣ ማንበብና መጻፍ መቻላቸው ላቅ ያለ ሀገራዊና ስነልቦናዊ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
4/ ህዝባዊ ውይይትና ውሳኔ (Referendum) 
ኦሮሚኛንም ሆነ ሌሎችን የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መርጦና አብቅቶ ተጨማሪ የስራ ቋንቋ ለማድረግ፣ መላውን የኢትዮጵ ህዝብ ማወያየትና ውሳኔውን እንዲሰጥ ማድረግ ግዴታ ነው፡፡ ጉዳዩን በፖለቲካ ውሳኔ ህዝቡ ላይ ለመጫን መሞከር፣ የህዝቡን የስልጣን ባለቤትነት ከመጋፋቱም በላይ፣ የእርስበርስ ግጭት ሊያስከትል ይችላል፡፡ የብሄርተኞችና ፖለቲከኞች ህዝቡን “እኛ እናውቅልሃለን” ቀረርቶና ፉከራ፣ “እንቆምለታለን” ለሚሉት ማህበረሰብ አንዳችም ጠብ የሚል ፋይዳ እንዳላመጣለት በተግባር የታየ ነው፡፡
በጥቅሉ የአንድን ሀገረ መንግስት የስራ ቋንቋ/ዎች መምረጥና መወሰን እጅግ አወዛጋቢና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም ከላይ ለመጠቃቀስ የሞከርኳቸውን ነጥቦችና ሌሎችንም አስፈላጊ ጉዳዮች ማጤን፣ ሂደቱንም በእውቀትና በምክክር ማስኬድ ይገባል፡፡ በዚህ መሰረት ሂደቱን በብስለትና በሰከነ ሁኔታ በመምራት፣ ኦሮሚኛንም ሆነ ሌሎች በጥናት የሚመረጡ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ተጨማሪ የስራ ቋንቋ ማድረግ፣ የዜጎችንና ቋንቋዎቹን ተናጋሪ ማህበረሰባትን በሀገራቸው ማህበረ-ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት ውስጥ የባለቤትነት፣ እምነትና ሙሉ ተሳታፊነት (belonging, trust and inclusiveness) ስሜት እንዲፈጠር ይረዳል፡፡ ሊጤኑ የሚገባቸውን ጉዳዮች ሳያጤኑና ሳያገናዝቡ፣ መሟላት የሚገባቸውን ቅድመ ሁኒታዎች ሳያሟሉ በግብታዊነትና በብሄርተኝነት ስሜት ወደ ውሳኔ መሄድ፣ ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ ህልውና አፍራሽ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል ከወዲሁ መገንዘብ ግድ ይላል፡፡
Filed in: Amharic